>
5:13 pm - Saturday April 19, 7890

አማራውን እያጠፋ ያለው ራሱ አማራው ነው! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

አማራውን እያጠፋ ያለው ራሱ አማራው ነው!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

እንደመግቢያ – “ሰድበህ ለሰዳቢ አትስጠን” የምትሉኝን ‹አማሮች› ምንም ልረዳችሁ አልችልም – ከማዘን በስተቀር፡፡ አማራ እጅግ ሰፊ ሕዝብ ሆኖ ሲያበቃ ለዚህ የተዋራጅነት ደረጃ ያበቃው ከውስጡ የፈለቁ የገዛ ሆዳምና ማይም ልጆቹና በዚህ ግዙፍ ማኅበረሰብ ዘንድ የነበሩና ያሉ ሃይማኖታዊ ልምዶች እንዲሁም ሥረ መሠረታቸው ድህነት ሊሆን የሚችል የምቀኝነትና የመጠራጠር፣ የቂም በቀለኝነትና የመሠሪነት ጎጂ ልማዶች ናቸው፡፡ እነዚህን መካድ ለለውጥ በር ባለመክፈት በነበሩበት መንቦራጨቅን መውደድ ነው፡፡ እውነትን ተናግሮ እመሸበት ማደር ብዙም አያከስርም፡፡ በገዛ አካባቢው ሠርቶ የሚያልፍለት አማራ ካለ የሎተሪ ያህል ነው፡፡ እናም ይህን ሕዝብ ቀይደው የያዙትን እሾሆች ለመንቀል ትግሉ መጀመር ያለበት ከውጭ ሣይሆን ከቤት ነው፡፡ ማስመሰልና ባለፈ ታሪክ ብቻ መኩራራትም ይቅር፡፡ ኩራት እራት አይሆንም፡፡ ታሪክም ዳቦ አይገዛም፡፡አዜብ ጎላ፣ ገነት ዘውዴ፣ ሙሉጌታ አሥራት፣ ብርሃኑ ዳምጤ (አባ መላ)፣ ክፍሌ ወዳጆ፣ ሰሎሞን ተካልኝ… አማሮች ነበሩ፡፡ የሚያለቅሱት ግን በቅንድባሙ መሪ ፍቅር ወድቀው ነው፡፡ 

በወያኔ ዘመን – በጣም በቅርቡ – ከትምህርት ጋር ለሚገናኝ የመስክ ሥራ በአማራው ክልል እዘዋወር ነበር፡፡ያኔ የታዘብኩት ነገር አማራነትን ያስጠላል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በተለይም መለዮ ለባሾች ትምህርት እንዲማሩ አይፈቀድላቸውም፡፡ ሲማሩ ቢገኙ ይቀጣሉ ወይም የሥራ ቦታ ዝውውር ይደረግባቸዋል፡፡ በርቀት ትምህርት በድብቅ የሚማሩ ፖሊሶች እንደ እስላም ሴት ከእግር ጥፍር እስከራስ ፀጉር በሂጃብ ተሸፋፍነው ፈተና ሲወስዱ ታዝቤያለሁ፡፡ ዋናዎቹ ባለሥልጣናት ግን በፈለጉት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የርቀት ትምህርት ማዕከላት እንደሚማሩና በድግሪ እንደሚንበሸበሹ ተረድቻለሁ – በፎርጅድ ዲግሪ ጭምር፡፡ ይህ የሚያሳየን ምቀኝነት በአማራው አካባቢ ተወልዶና አድጎ ለወግ ለማዕረግም ደርሶ ወደ ሌሎች ክልሎች ኢክስፖርት የተደረገ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ጠባያችን ደግሞ አይደለም ከሦስት ሚሊዮን ሕዝብ የወጣው ወያኔ ከ20 ሽህ ገደማ ሕዝብ የሚወጣው አርጎቤም በሉት ሙርሲ እንደብረት ቀጥቅጦ እንደሰም አቅልጦ ይገዛናል፡፡ በነገራችን ላይ በዚያን ወቅት ትግሬና ኦሮሞ ፖሊስም ሆነ ሌላ ሠራተኛ ተደብቆ ሳይሆን በግዳጅ ነበር እንዲማር የሚደረገው፡፡ አማራን ለማደደብና ለማደህየት በውጤቱም እንደከብት ለመንዳትና እንደመጋጃ ለመጫን የተሄደው ርቀትና የተሠራው ሸፍጥ ይዘገንናል፡፡ አማራውም በኢትዮጵያዊነት ካባ ተጀቡኖ ዕልቂቱን ይጠባበቅ ይዟል፡፡ አማራው ሁለት ምርጫ አለው –  የተጠቀሱትን የገዛ ችግሮቹን ቀርፎ በአማራነቱ በመታገል ራሱን ከተደገሰለት ዕልቂት ማዳን ወይም በኢትዮጵያዊነቱ ሌሎችንም አስተባብሮ ከታሪካዊ የሀገራችን የእጅ አዙር ጠላቶቹ ጋር በመታገል የታላቋን ኢትዮጵያ ትንሣኤ ማብሰር፡፡…

ከፍ ሲል በተጠቀሰው መልክ ደንቁሮ የቀረ ዜጋ ከመሬት ተነስቶ “አፄ ቴዎድሮስ ተብሎ የተተነበየው ለኔ ነው” ቢል ማንም ሊፈርደበት አይገባም፡፡ ብአዴን የምን ስብስብ እንደሆነ በግልጽ እያየን ነው፡፡ ሰው የለውም ፡፡ እውነተኛው ልጅ እየተጣለ የእንግዴ ልጁ እያደገ ሀገራችን ለይቶላት የከብቶች በረት ሆነች፡፡ ትምህርት ከጠፋ ሆድ ይነግሣል፡፡ አእምሮ ከጫጫ ጉልበት ይገናል፡፡ ተናግሮ ማሳመን ዕርም ከሆነ ኃይል ህግ ይሆናል፡፡ “Mighty is Right.” ብሏልና የቀደመው ፈረንሣዊ ንጉሥ ናፖሊዮን (አንደኛው)፡፡

በዶክተር አቢይ የሰባተኛ ንጉሥነት (ለእውነት የቀረበ) እማዊ ትንቢት ተደንቀን ሳናበቃ አሁን ደግሞ አንድ የብል(ፅ)ግና ፓርቲ የአማራው አካባቢ ሹም ቴዎድሮስ የተባለው ንጉሥ እርሱ እንደሆነ ቅንጣት ሳያፍር መናገሩን ሰማን፡፡ ወዴት እየሄድን እንደሆነ ለማወቅ ቸገረኝ፡፡ ሀገር ሲያረጅ ጃርት ማፍራቱ በግልጽ እየታየኝ ዙሪያው ገደል ሆነብኝና መሄጃ አጣሁ፡፡ እውነት እንኳን ቢሆን ምናለበት ዝም ቢልና ሣቃችንን ባያስጨርሰን? ወይ ብአዴን! እዚያ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹን ካድሬዎችና ባለሥልጣናት ፕሮፋይልና የስብዕና ልኬት ብናጠና ብዙ ጉድ መዘርገፉ አይቀርም፡፡ ኤቢሲዲንና ሀሁን ከመለየት አንጻር ያለውን ገመና ትተን ሌላ ሌላውን ነውራቸውን ብናስተውል በድንጋጤ ገደል እንገባለን፡፡ በነገራችን ላይ ብልጽግና ፓርቲ የአለቆቹን ዓርማ ማክበሩን በአግራሞት እየተከታተልን ነው፡፡ ኢትዮጵያን ስለመጠየፉ የሚወራውን ግን ብዙም አልገዛውም፡፡ እርግጥ ነው – ኢትዮጵያ የፍየል ሥጋ የሆነችባቸው ሰዎች የሚሰባሰቡበት ፓርቲ ኢትዮጵያን በበጎ የሚያወሳ ነገር ሁሉ ስለሚያንዘፈዝፋቸው በዚያ ፓርቲ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሸት ነገር እንዲወገድ ቢደረግ ሰዎችን ለማስደሰት ታስቦ መሆኑ አይካድም፡፡ ለነገሩ ካዋጣቸው ይግፉበት፡፡ ግን የሚያዋጣቸው አይመስለኝም፡፡

እንደመውጫ – በወያኔ ግፍና በደል የደረሰባችሁ ወገኖቻችን በተሠራባችሁ ነውር ምክንያት አንገታችሁን አትድፉ፡፡ ወዳችሁ ባልገባችሁበትና ፈቅዳችሁ ባልሆናችሁት ማንነትና ነውር እየተሸማቀቃችሁ ከመኖር ወያኔን እያጋለጣችሁ በአዲስ መንፈስ ታገሉ፡፡ አንገታችሁን መድፋት ይቅር፡፡ ነውሩ በነሱ እንጂ በናንተ አይደለምና፡፡

ጆሮ ያላችሁ የመንግሥት ባለሥልጣናት ካላችሁ በአዲሱ ቀረጥ ሳቢያ አገርና ሕዝብ እየተተረማመሱ ነውና ጉዳዩን እንደገና ተመልከቱት፡፡ ማንን እያስተዳድራችሁ እንደሆነ ዕወቁ፡፡ለአንድ መቶኛ ሀብታም ስትሉ 99 መቶኛውን ድሃ ሕዝብ አትፍረዱበት፤ በኑሮ ውድነት ጨንገር አትቅጡት፡፡ ሌላውን ነገ ስንገናኝ፡፡

Filed in: Amharic