>
11:39 pm - Wednesday November 30, 2022

የኦሮሞ ፅንፈኞች ዘሃ ፖለቲካ እና አረመኔያዊ ገፅታው!!! (አሰፋ ሃይሉ)

የኦሮሞ ፅንፈኞች ዘሃ ፖለቲካ እና አረመኔያዊ ገፅታው!!!

አሰፋ ሃይሉ
 
(The Parasitic Revenge Politics of Today’s Oromo Extremists)
ዘሃ ድር ነው፡፡ እንደ ሸረሪት ድር እጅግ ቅጥን፣ ስልምልም ያለ ክር ነው፡፡ ራሱን ችሎ መቆም አይችልም፡፡ ጥንካሬ የለውም፡፡ ስለዚህ እንደ ፓራሳይት ሌሎች ጠንካራ ቅስቶችን ፈልጎ በእነሱ ላይ ያደራል፡፡ እና ለህልውና አስፈላጊ የሆነውን ንጥረ ነገር ያገኛል፡፡ በሌላ አነጋገር ዘሃን እንደ ፓራሳይት ተክልም (parasitic plants) መውሰድ እንችላለን፡፡ እነዚህ ፓራሲቲክ ተክሎች በራሳቸው ምግባቸውን አብስለው ቀጥ ብለው ቆመው መኖር አይችሉም፡፡ እንደ ሐረግ በሌላ ተክል ግንድ ላይ ሥራቸውን ሰክተው፣ በዛፉ ተከልለው በመጠነኛ ቅጠሎቻቸው ዛፉ የሠራውን ምግብ በፀሐይ እያሞቁ እየበሉ ይኖራሉ፡፡
ባጠቃላይ ዘሃ የቀነጨረ ሐረግ ነው፡፡ ግን በሌላው ህልውና ሥር ራሱን በጥገኝነት አጣብቆ በሌሎች ላይ ተንጠላጥሎ ይኖራል፡፡ የዛሬን የኦሮሞ ፅንፈኞች ፖለቲካ ያስተዋለ ሁሉ ይህን ዘሃዊ ባህርይ ነው የሚያስተውለው፡፡ ራሱን ችሎ የማይቆመውን፣ በሌሎች ግዙፋን ላይ ተንጠላጥሎ የበቀል ረሃቡን የሚያስታግሰውን፣ አረመኔያዊ የዘሃ ፖለቲካቸውን፡፡ ለምን እንዲህ ልል ቻልኩ? ብዙ ምክንያቶች አሉኝ፡፡ የሩቆቹን ትቼ አንዳንድ የቅርብ ምሳሌዎችን እያነሳሁ ላስረዳ፡፡
‹‹ኦሮማራ›› የሚል ቅፅል ባተረፈው ምስጢራዊ የኦህዴድና የብአዴን ህቡዕ እንቅስቃሴ እና ከቁጥጥር ባፈተለከ ከፍተኛ ሕዝባዊ አመጽ ግፊት ህወኀት ከቤተመንግሥት ከመባረሯ ዋዜማ ጀምሮ – የኦሮሞ ፅንፈኞች በአንድ የጋራ የትግል ጥላ ሥር ያሰባሰባቸውን አዲስ የተበድለናል፣ ተረግጠናል፣ ተጨቁነናል የፖለቲካ አጀንዳቸውን ያገኙት የኦሮሚያ ክልል ከሶማሊ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው ቁጥራቸው የበዛ ወረዳዎች ላይ ከተቀሰቀሱና በኦሮሞ እና በሶማሊ ክልል ኃይሎች ጭምር ከታገዙት የእርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ ነበር፡፡
የኦሮሞው አክራሪ ኃይል በራሱ ሜጋሎማኒክ ቅዠት (ለራሱ በሚሰጠው ከእውነታው እጅግ የተጋነነ ግምት) የተነሣ – በቁጥሩ ከሶማሊዎች የሚልቀውን ሕዝባችንንና ልዩ ኃይላችንን አሠማርተን በከፍተኛ ሁኔታ የኦሮሞ ፅንፈኞችን አላላውስ ያለውንና ላቅ ያለ የማናለብኝነት ተግባር ይፈፅምባቸው የነበረውን፣ በአብዲ ኢሌ የሚመራውን የሶማሊ ልዩ ኃይል እንደመስሰዋለን ብለው ተንፈራግጠው ነበረ፡፡ ያ የኦሮሞ ልዩ ኃይሎችን አሰልፈው በተለያዩ የሶማሊ አዋሳኝ አካባቢዎች የፈጠሩት በመሣሪያ የታገዘ ግጭት የተጠናቀቀው በሶማሊ ልዩ ኃይሎች የበላይነት ብቻ ሳይሆን – ከበፊቱ የከፋ መጠነ ሰፊ ሕዝብ የማፈናቀልና የኦሮሞ ፖሊሶችንና ልዩ ኃይሎችን በየገቡበት እያሳደዱ በመምታት ሆነ፡፡
እውነተኛ አቅማቸውንና ከሶማሊዎቹ በኩል ሊመጣባቸው ያለውን የባሰ መቅሰፍት የተረዱት የኦሮሞ ፅንፈኞቹ የቀራቸው አማራጭ ከተለያዩ የሶማሊ ድንበር አካባቢዎች የተፈናቀሉ፣ የታሠሩ፣ የተገደሉ፣ የተገረፉ፣… የኦሮሞ ነዋሪዎችን ቁጥር እስከ ሚሊዮኖች ቁጥር በማብዛት ለዓለማቀፍ ተቋማትና ለመላው ኦሮሚያ ነዋሪዎች እሪታቸውን ማሰማት ነበር፡፡ ይሄም በወቅቱ እስላምና ክርስትያን፣ ዋቄፈታና አዳል ሆኖ ማዶ ለማዶ ተለያይቶ በሚኖረው የወለጋ እና የባሌ ኦሮሞ፣ የሸዋ እና የሐረር ኦሮሞ፣ የአርሲና የጅማ ኦሮሞ… መካከል የጋራ የተጠቂነትና የትብብር አጀንዳ ፈጥሮላቸው – ጥቃታቸውን የህወሃት የእጃዙር ጥቃት ነው ብለው በማሳበብ – በመቀጣጠል ላይ የነበረውን ሕዝባዊ አመፅ ይበልጥ አፋፍመው ለማቀጣጠል ረድቷቸዋል (ለጋራ የትግል አጀንዳነት ተጠቅመውበታል)፡፡
/ከብዙ የዓለማቀፍ ልዑካን አሰስመንት ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻለው መሬት ላይ የነበረው እውነታ ግን የኦሮሞውን ኃይል ያሳድድ እና ሰላማዊ ነዋሪዎችን ያፈናቅል የነበረው የህወኀት ወይም ሌላ ከሶማሊያ የመጣ አሸባሪ ኃይል ሳይሆን አስር ሺህ የማይሞሉ የአብዲ ኢሌ የሶማሊ ክልል ልዩ ኃይሎችና አደራጅተው ያስታጠቋቸው ጥቂት ፅንፈኛ ወጣቶች ነበሩ፡፡/
ዘወትር ታላቅነቱን ሲሰብክና ፅንፈኞችን እየፈለፈለ የኖረው የኦሮሞ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች የሚያስተዳድሩት የኦሮሚያ ክልል በህወኀት እጃዙር አገዛዝ ሥር ወድቋል እያለ ለሚከስሰው ለፌዴራሉ መንግሥት ያቀረበው የድረሱልኝ ጥሪ ያስገኘለት ነገር ቢኖር የየክልሉ ርዕሰ መስተዳድሮች ሄዳችሁ እርቀሠላም ፈፅሙ የሚል – እና እነ ለማ መገርሳ እየተናነቃቸው ሄደው የፈፀሙት – የለበጣ የእርቀሠላም ቀልድ ነበር፡፡
ይህን የአብዲ ኢሌን ውሱን ታጣቂ ኃይል መቋቋም ያቃተው የኦሮሞ ፅንፈኞች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ፅንፈኛ ብሔረተኛ ኃይል – የህወኀትን ከቤተመንግሥት መባረር ተከትሎ ምን አደረገ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ያ ራሱን ችሎ ሕዝቡን ከጎረቤት ጥቃት መከላከል የተሣነው የኦሮሞ ፅንፈኞች ኃይል በአብዲ ኢሌና ልዩ ኃይሉ ላይ ከፍ ያለ በቀልን ለመፈፀም  በእጅጉ እንደተራበ ግልፅ ነበር፡፡ ሆኖም ያንን በቀል ራሱን ችሎ ለመፈፀም በምድር ላይ ያለው እውነታ አይፈቅድለትም፡፡
ስለዚህ የኦሮሞው ኃይል ያደረገው ነገር ያንን የዘሃ ፖለቲካውን ቁማር ተጫውቶ – የፌዴራሉን መንግሥት የፖለቲካ አመራር ‹‹ኦሮ-ማራ›› በሚል አሰላለፍ በበላይነት ከተቆጣጠረ በኋላ – ያንን የኦሮሞውን ፅንፈኛ ኃይል ሲለበልብ የኖረ የበቀል አለንጋ – በኢትዮጵያ መንግሥት መከላከያ ሠራዊት ስም እና ሽፋን – ሰበብ ፈልጎ – አብዲ ኢሌ የሶማሊ ልዩ ኃይሉን አሰማርቶ – ሶማሊ ክልልን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል አዋጅ ሊያስነግር ስብሰባ ጠርቷል – በሚል ተልካሻ ሰበብ – የኦሮሞ ፅንፈኞች ባላቸው ኃይል ሁሉ ተንፈራግጠው ለማንበርከክ ያቃታቸውን የሶማሊ ክልል ኃይል – በእነርሱ የበላይነት የሚመራ የኢትዮጵያን ሕዝብ የመከላከያ ኃይል በማሠለፍ በአብዲ ኢሌ ላይ በቀላቸውን ለመወጣት አዘመቱበት፡፡
የፌዴራሉንና የሚሊቴሪውን የበላይ ሥልጣኖች የተቆጣጠረው የኦሮሞ ፅንፈኛ ኃይል ለበቀል ያለው ጉጉትና ተነሳሽነት (revenge appetite) የሚገርመው – ሌላ ቀርቶ በጎረቤት ሀገራት ሠላም አስከባሪ ኃይል ሆኖ ተሰማርቶ የነበረን የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል ሁሉ ሣይቀር – ከሠላም ማስከበር ግዳጁ ላይ አስነስቶ – በአብዲ ኢሌ ጦር ላይ ከሌላ አቅጣጫ እንዲዘምትበት እስከማድረግ መድረሱ ነው፡፡
ይህ በድህረ-ህወኀት የኢትዮጵያን መንግሥት ወታደራዊና ፖለቲካዊ መዋቅር በበላይነት የተቆጣጠረው አዲሱ የኦሮሞ ፅንፈኞች ቡድን የግል አክራሪ ኦሮሞአዊ አጀንዳውን ለማስፈፀም በራሱ ያቃተውን እርምጃ – በሀገሪቱ መደበኛ ሠራዊት፣ በሀገሪቱ ወጪ፣ በሀገሪቱ ህዝብ ኪሳራ፣ በሀገሪቱ የህግና ሥልጣን መዋቅር ተጠቅሞ ለመፈፀም ያለምንም ማወላወል ያሳየውን ከፍ ያለ አረመኔያዊ የበቀለኝነት ባህርይ ሳስተውል – ቮን ኪርችሄይመር የተባለውና በሂትለር ዘመን የነበረ የፖለቲካና የፍትህ ተንታኝ – ሂትለር ተቀናቃኝ የሀገሪቱን ኃይሎች ለማስወገድ የራሄውን መንግሥት ህጎችና ሥልጣኖች፣ መደበኛና ልዩ ሠራዊቶች እንዴት ባለ የማያወላውል ጭካኔ ጥቅም ላይ እንዳዋላቸው ከመነሻው በመገንዘብ – ያቀረባቸው በርካታ ሥርነቀል ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ እነርሱን አሁንም መልሼ እንድጠይቅ ያስታውሰኛል፡-
‹‹ከመንግሥት ባለሥልጣናት የተሰጠ ትዕዛዝ ህጋዊ ትዕዛዝ ሆኖ የሚቀጥለው እስከ ምን ጥግ ድረስ ነው? የበላይ ወታደራዊ ትዕዛዝ የሚተገበረው በጭፍን እና በጭፍን ብቻ ነውን? በፍትሃዊ ትዕዛዝ እና በኢ-ፍትሃዊ ትዕዛዛት መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት ማድረግ አይቻልምን? የመንግሥት እርምጃ መንግሥታዊነቱ የሚያበቃው ምን ደረጃ ላይ ሲደረስ ነው?›› ወዘተ የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት የናዚ ሒትለርን አካሄድ የሞገተበት “The Morality of Law & the Use of Legal Instruments for Political Ends” በሚል ርዕስ የጻፈው – የመንግሥትን ሥልጣንና ኃይል ለተወሰነ ቡድን ጥቅምና ለበቀል ጥማት ማስፈፀሚያ የማዋል ፍትሃዊነቱ የሚያበቃው የት ላይ ነው? የመንግሥት መንግሥትነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባው የትኛውን ሚዛን ሲስት ነው? በሚል ቮን ኪርችሄይመር ያቀረባቸውን የሰሉ ሙግቶች የሚያስታውስ ነው፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ መደበኛ መከላከያ ኃይል በገለልተኝነት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ ተገቢውን ሀገራዊ ውሳኔ መስጠትና የተፈጠረውን ግጭትና ሰብዓዊ ቀውሶች ማረጋጋት ሲኖርበት – የኦሮሞን ፅንፈኞች ራሳቸው ያላቅማቸው በለኮሱት ጠብ መድረሻ አሳጥቶ ያርበደበደውን (እና በእርግጥ ብዙ ንፁሃን ኦሮሞዎችንም ለከፋ መፈናቀል የዳረገውን) የሶማሊውን አብዲ ኢሌ ከነልዩ ኃይሉ ዘመተበት፡፡ እና የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይል ብቻውን መቋቋም የማይችለው አብዲ ኢሌ በመጨረሻ እጁን ሰጠ፡፡ ልዩ ኃይሉም የህወኀትን ሥልጣነ መንበር ለተረከበው አዲሱ የኦሮሞ ፅንፈኛ ኃይል ታዛዥና ታማኝ የሆኑ መኮንኖች እየተመደቡለት እንደ እፉኝት መንታዎች በየበረሃው እንዲበታተን ተደረገ፡፡
ከአብዲ ኢሌና ከሶማሊ ልዩ ኃይል ምርኮ በኋላ ምሁር ናቸው ተብሎ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ተደርገው የነበሩት ፕ/ር ነገሬ ሌንጮ በፌስቡክ ገጻቸው በእንግሊዝኛ የለቀቁት ስሜት የተሞላበት የደስታ መግለጫ መልዕክት የኦሮሞ ፅንፈኞች ቀደምት ተሰላፊ መሆናቸውን ያስመሰከረ ነበር፡- ‹‹ለመላው ኦሮሞዎች እና ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ! ዛሬ የሰሜን ደገኞችና የአፄው ሥርዓት ርዝራዦች የከፈቱብንን የእጃዙር ጦርነት ድል አድርገን በቁጥጥራችን ሥር አውለናቸዋል!››
የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣንና ሠራዊቶት፣ ከነነባር መዋቅሮቹ በቁጥጥራቸው ሥር ያስገቡት አዲሶቼ የኦሮሞ ዘሃ ፖለቲከኞች እየተጫወቱ ያሉት የጊዜያችን ቁማር ይህ ነው፡፡ ራሳቸውን ችለው ለመቆምና በራሳቸው ተቀናቃኛቸውን ለመገዳደር ዘሃ ቁመናቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ ራሳቸውን ሰማይ ሰቅለው እንዲመለከቱ ያበቃቸው ለራሳቸው ያላቸው የተጋነነ ግምት (ሜጋሎሜኒያ) እና በምድር ላይ ያለው ዘሃው አቋማቸው እስካልታረቁ ድረስ – የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ መጠበቂያና መከላከያ የሆኑት የፌዴራሉ መንግሥት ተቋማትና ሥልጣናት ሁሉ ተጠቃልለው የዚህ የኦሮሞ ፅንፈኛ ኃይል መጠበቂያ፣ ጠባብ ዘረኛ ፍላጎቱን ማስፈፀሚያ፣ ታሪካዊ ጠላቶቼ ናቸው ያላቸውን ማጥቂያ፣ እና ፅንፈኛ ኃይሉ ከግር እስከራሱ የተነከረበትን የቆየ ቂም በቀል ማስፈፀሚያ ሆነው እንደሚቀሩ ግልፅ ነው፡፡፡
ይህ የአብዲ ኢሌ ምሳሌ የኦሮሞ ፅንፈኛውን ዘሃ ፖለቲካ እና አረመኔያዊ ውጤቶቹን ለማመላከት ያቀረብኩት የመጀመሪያ ትንታኔዬ ነው፡፡ የአብዲ ኢሌ አጀማመርና አጨራረስ አንዱ ተጠቃሽ ምሳሌ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከያዝኳቸው ሰባት አበይት ምሳሌዎች ውስጥ የተቀሩትን ስድስቱን በተከታይ ፅሁፎች አለፍ እያልኩ ለማቅረብ ቃል እገባለሁ፡፡ በመጨረሻም መፍትሄው ምንድነው? በሚለው ላይ የማቀርበው ሃሳብ ይኖራል፡፡ እስከዚያው ሁላችንን ቸር ያቆየን፡፡ መልካም ጊዜ፡፡
አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
Filed in: Amharic