>

በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ግጭት ውጥረት ፈጥሯል!!! (አለማየሁ አንበሴ)

በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ግጭት ውጥረት ፈጥሯል!!!

አለማየሁ አንበሴ
በምዕራብ ኦሮሚያ በታጣቂ ቡድኖችና በመከላከያ ሰራዊት መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ አንድ የረድኤት ሰራተኛ መገደሉን፤ ሁለቱ መቁሰላቸውንና ስድስት ያህሉ መታሰራቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ትናንት አስታውቋል፡፡
በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ ባልታወቁ ታጣቂ ቡድኖችና በመከላከያ ሀይል መካከል ከባድ ጦርትና ግጭት እየተካሄደ መሆኑን የገለፀው ተቋሙ፤ በአካባቢው ያለው ሁኔታም የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ የማያስችል ሆኗል ብሏል፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የአካባቢው ምንጮች በበኩላቸው፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡንና አብዛኛው የመንግሥት መስሪያ ቤትም እስከ ትናንት ድረስ ዝግ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው በታጠቁ ሀይሎችና በመከላከያ ሰራዊት መካከልም ግጭቶች መኖራቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ባወጣው ሪፖርት እንደጠቆመው፤ በአካባቢው በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ግጭት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፤ ጎሳን መሰረት ያደረጉ የእርስ በእርስ ግጭቶችና ውጥረት ምዕራብ ደቡብ ኦሮሚያን አለመረጋጋት ውስጥ ከከተታት ሰነባብቷል ብሏል፡፡
ከሰሞኑ ከተገደለው የረድኤት ሰራተኛ በተጨማሪ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም በጋምቤላ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት ሰራተኞች እንደተገደሉና የአሟሟታቸው መንስኤም እስካሁን ድረስም ግልጽ አለመሆኑን ተቋሙ አመልክቷል፡፡
ከምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ በተጨማሪ በአማራ ክልል ቅማንት አካባቢ፣ በደቡብ ጌዲዮ ዞን፣ በቤኒሻንጉልና በሶማሌ ክልሎችም የተለያየ መልክ ያላቸው ብሄር ተኮር ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የረድኤት ተግባራትን አስቸጋሪ እንዳደረጉበት የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል፡፡
ከዚሁ ችግር ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በታጣቂዎች መታገታቸው የተገለፀ ሲሆን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህም ይህንን አረጋግጠዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞኖች በሙሉ ከባለፈው አርብ ታህሳስ 24ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ የተቋረጠ ሲሆን አካባቢውም በኮማንድ ፖስት ስር መተዳደር ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል ተብሏል::
በምዕራብ ኦሮሚያ አጋጥሟል ስለተባለው ግጭት መንግስት እስከ ትናንት ድረስ ይፋ መግለጫና ማብራሪያ ያልሰጠ ሲሆን ግጭት እየተካሄደ ነው የሚለውን መረጃ ተከትሎም በሃሮማያ፣ ቡሌ ሆራ፣ ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲዎች “በምዕራብ ወለጋ ላይ የሚፈፀመው ጥቃት ይቁም” በሚል ተማሪዎች መቃወማቸውን ምንጮች ገልፀዋል:: በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን “አዲስ ስታንዳርድ” ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በበኩሉ፤ ‹‹ትዕግስት ድንበር ሊኖረው ይገባል፤ ዝምታ ይብቃ›› በሚል ርዕስ ትናንት በአፋን ኦሮሞ ባሰራጨው መግለጫው፤ መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያና ደቡብ ኦሮሚያ ባለው ሁኔታ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥና የሚፈፀሙ ወታደራዊ ጥቃቶች እንዲቆሙ ጠይቋል፡፡
የቦረና ዞን፣ ጉጂ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ቄሊም ወለጋ፣ ኢሉ አባቦራና ቡኖ በደሌ በአሁኑ ወቅት በኮማንድ ፖስት ስር የሚተዳደሩ አካባቢዎች መሆናቸውን የጠቀሰው የኦነግ መግለጫ፤ አካባቢዎቹ በመደበኛ ሥርዓት እንዲተዳደሩ ጠይቋል፡፡
በአካባቢዎቹም የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ቀናቶች መቆጠራቸውንና ማህበረሰቡ በአፈና ሥርዓት ስር መውደቁንም ኦነግ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
በአካባቢው ያለውን ቀውስ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላት እንዲከታተሉትም ኦነግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
Filed in: Amharic