>

የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 201ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ (ልዑል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል)

የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 201ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ

ልዑል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል

የዳጃች ካሳ የጦር መሳሪያ ሥራ በጣቁሳ!!!

 
‹‹ዘመነ መሳፍንት›› የተባለውን የየየግዛት ባላባቶች ዘመን በማስቆም ኢትዮጵያን በአንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ስር ለማስተዳደር የሞከሩት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የተወለዱት ከዛሬ 201 ዓመታት በፊት (ጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም) ነበር፡፡
– – –
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የልጅነት ስማቸው ‹‹ካሣ›› ይባል ነበር፡፡ አባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደጊዮርጊስ፤ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ አትጠገብ ወንድበወሰን ይባላሉ፡፡ ልጅ ካሣ አባታቸው በሕፃንነታቸው ስለሞቱ ወደ አጎታቸው ደጃዝማች ክንፉ ዘንድ በመሄድ አድገዋል፡፡ ለትምህርት በተላኩባቸው ቦታዎችም የአስተዳደር ስራንና የሀገራቸውን የወቅቱን ፈተናዎች ተገንዝበዋል፡፡
– – –
የግዛት ባላባቶች በቡድን ተከፋፍለው ለስልጣን ደም እየተፋሰሱ የነበረበት ወቅቱ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ካሣን እረፍት ስለነሳቸው ኢትዮጵያን በአንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ስር ስለማስተዳደር ማሰብ ጀመሩ፡፡ አስበውም አልቀሩም፡፡ በየጊዜው የተጠመደባቸውን ሴራ በብልሃትና በጀግንነት እያለፉ የግዛት ባላባቶች በጦርነት ድል አድርገው የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ.ም በደረስጌ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ‹‹ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ዘውድ ደፉ (ነገሱ)፡፡
– – –
ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን በመገንባት ለመምራት ሙከራ አድርገዋል፡፡ የወቅቱ የኢትዮጵያ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ስሪትና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ከንጉሰ ነገሥቱ ባህርያት ጋር ተደምረው ዓላማቸውን ዳር ሳያደርሱ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም በአንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ስር የምትተዳደርና የዘመነች ኢትዮጵያን ለመገንባት የከፈሉት መስዋዕትነት ስማቸው ትናንት፣ ዛሬና ነገም በኢትዮጵያና በመላው ዓለም እንዳይረሳ ያደርጋቸዋል፡፡ 

የዳጃች ካሳ የጦር መሳሪያ ሥራ በጣቁሳ!!!

 
ደጃች ካሳን ራስ አሊ ግባ ብለው ይልኩባቸዋል፡፡ ዳጃችም የቀደመ እርቅ ነበራቸውና አልገባም እርቅ አለኝ ይላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ራስ አሊ ደጃች በለውንና ብሩ አሊጋዝን ከበርካታ ወታደር ጋር ለውጊያ ወደ ጣቁሳ ሳውድባ ይልኳቸዋል፡፡ ደጃች ካሳ በዚህ ቦታ ላይ የተለየ የጦር መሳሪያ ቀድመው ሰርተው ጠበቋቸው፡፡
“ከእንጨት መድፍ አስፈለፈልፍለው በላይ በላዩ ላይ ደግሞ ብረት ጠመጠሙበት፡፡ የብረት አረር አድርገው ለጉመው ደግመው ባሩድ በሸክላ በሸክላ አድርገው ምድሩን ቆፍረው ያ የሚወጋቸው ጦር ከሚሰፍርበት ውስጥ ቀብረው በረጃጅም ቀርከሀ ባሩድና ቀረ ጠንቅ ውስጥ ለውስጥ ከምሽጋቸው ድረስ አመጡት ለመተኮስ እንዲመች፡፡”
በእርግጥ ከጦርቱ በፊት አንድ የደጃች ካሳ ወታደር ከጦርነቱ በፊት ተማርኮ ስለነበር እና ስለዚህ ጥበብ በመናገሩ ለውጊያ አልዋለም፡፡
እንደው እራሱ መይሳው የሠራውን በልደቱ ሰበብ ለማንሳት ነው።

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ

 
(ምስሉን የሳሉት ዕውቁ ሰዓሊ፣እሸቱ ጥሩነህ ናቸው፡፡ እንደ ስዩም ወልደ ምስክርነት በመጀመሪያ  የተሳለውም ሞስኮ ላይ ነው፡፡ እሸቱ ጥሩነህ፣ሰባት ዓመት ገደማ በሞስኮ ለከፍተኛ ትምህርት ቆይተው ለመመረቂያ ያዘጋጁት ነው፡፡ ርእሱም  “መይሳው ካሳ” ነው፡፡ በዚያ የተሠራው 2 ሜትር ከ40 ሴንቲ ሜትር በ3 ሜትር ሆኖ ነው፡፡ ግዙፍ ስእል ነው፡፡ )
Filed in: Amharic