>
9:59 am - Wednesday December 7, 2022

ንጉሠ ነገሥት አጼ ቴዎድሮስ እና ማርቲን ሉተር ኪንግ Jr.! (አሰፋ ሃይሉ)

ንጉሠ ነገሥት አጼ ቴዎድሮስ እና ማርቲን ሉተር ኪንግ Jr.!

አሳፍ ሀይሉ
በንግሥት ቪክቶሪያ ወደ ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ የተላከውና የቴዎድሮስ መልካም ወዳጅ ለመሆን የበቃው (ነገር ግን ኋላ ላይ መልካም ወዳጅነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ምቾቱም ሳይጓደልበት፣ የቴዎድሮስን አውሮፓውያን የቁም እስረኞች የተቀላቀለው) የብሪታንያው ልዩ ልዑክ ሆርሙዝድ ራሳም ከአፄ ቴዎድሮስ ህልፈተ ህይወት አንድ ዓመት በኋላ ‹‹ወደ አቢሲኒያ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ የተደረገው የብሪታንያ ዘመቻ ዝክር›› በሚል ርዕስ ባሳተመው የታሪክ ማስታወሻ – የእንግሊዞች ጦር አፄ ቴዎድሮስ ወደ መሸጉበት የመቅደላ አፋፍ እየተጠጋ በመጣ ጊዜ – ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ ራሳምን አስጠርተው የነገሩትን ቃል በቃል አስፍሮት ነበር፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ቴዎድሮስ ለራሳም ካሉት ውስጥ እንዲህ የሚል ይገኝበት ነበር፡-
“‘ነገ እዚህች አምባ ላይ ወይ እኔ ወይ ደግሞ ያንተ ወገኖች መውደቃችን የማይቀር ነገር ነው፣ እኔ ያ አያሳስበኝም፣  በዚህች ዕለት እንደቀድሞዬ ኢትዮጵያ ሁሉ በእጄ ሆና ብንገናኝ ነበር የምመኘው፣ ምን ይደረግ ብለህ ነው?
ሀገሩ ሁሉ አመፀኛ ሆኖ ከዳኝ፣ አሁን በእጄ የቀረኝ
7ሺህ ወታደርና ይቺ የአለት ተራራ ብቻ ነች፡፡ ህይወቴ ብታልፍም ይህን እንደምታስተውል እርግጠኛ ነኝ፣ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት – እንክብካቤዬን ሳላጓድል በክብር ይዤያችኋለሁ፣ ከዚህም በኋላ ምንም እንደማይደርስባችሁ ቃሌን እሰጥሃለሁ፣ ለእናንተም ሆነ ለንግሥታችሁ በልቤ ጥላቻ ያላሳደርኩ መሆኔን ሳታውቀው አትቀርም፣ … እ… የናንተ ሰዎች እዚህ አምባ ላይ መጥተው ሲያዩኝ፣ እና ጥቁር መሆኔን ሲመለከቱ እንደማይጠሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ መቼም፣ አምላክ ሲፈጥረን ለሁላችን የሰው ልጆች የሰጠን አንድ ዓይነት ጭንቅላትና አንድ ዓይነት
ልብ ነውና…’ ብለው በመልካም መስተንግዶ አሰናብተውኝ፣
ታች ማዶ በሳላምጌ ወደ ተከሉት የጦር ካምፓቸው ወረዱ፡፡…”
(“…‘I hope, Mr. Rassam,’ Theodore added, ‘that when your people arrive they will not despise me because I am black; God has given us all the same faculties and heart.’ With this the interview closed and Theodore descended again to his camp at Salamgie.” — Hormuzd Rassam, Narrative of the British Mission to Theodore, King of Kings of Abyssinia (Murray, 1869); quoted in Alan Moorehead, The Blue Nile, pp 251, 1962.)
የእኚህን የሀበሻ ንጉስ ስለ ሰው ልጅ እኩልነት የነበራቸውን ያልተዛባ አስተሳሰብ ስመለከት በጣም ገረመኝ፡፡ በአጋጣሚ ሆኖ ዛሬ የታላቁ የአሜሪካኖች የፀረ-ዘረኝነት ትግል አራማጅ የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር የልደት ቀንም ነው:: ማርቲን ሉተር ጃንዋሪ 15 ተወለደ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ደግሞ ጥር 6፡፡ የሰው ልጅ በተግባሩ እንጂ ጥቁር ነጭ ተብሎ በዘሩና በቀለሙ እየተለየ ማንነቱ እንዳይዳኝ አጥብቆ ህልሙን የተናገረበት በጣም የምወደው የማርቲን ሉተር ትንቢት የመሰለ ንግግር አለ፡፡ ነገር ግን ማርቲን ሉተር በ1964 የሚናገረው ከእርሱ 100 ዓመት በፊት አፄ ቴዎድሮስ ለሆርሙዝ ራሳም የነገሩትን እና በክብር የሞቱለትን የነፃነት መርህ ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲህ ነበር ያለው፡-
“ሕልም አለኝ፡፡ አንድ ቀን አራቱ ልጆቼ እንዳሁኑ
በቆዳቸው ቀለም፣ በዘር ሃረጋቸው፣ ወይ በፀጉራቸው
ሳይሆን፣ በውስጣቸው በያዙት፣ እና አውጥተው
በሚያንፀባርቁት የባህርይ ታላቅነት ወይም ወራድነት
ብቻ ማንነታቸው የሚመዘንበት አንድ የነፃነት ቀን
እንደሚመጣ ሕልም አለኝ፡፡”
(“…I have a dream that my four little children will one day live in a nation where they will not be judged by the color of their skin but by the content of their character.”)
ማርቲን ሉተር ለብዙዎቻችን አርዓያ ሰብዕ የመሆኑን ያህል – ብዙዎቻችን ያለንን የማናውቅ ሆነን እንጂ – ከእርሱ በፊት የእርሱን የነፃነት መርህ በነፍሳቸው ተወራርደው ከፍ አድርገው በመቅደላ አደባባይ ያውለበለቡት ኩሩ ኢትዮጵያዊ ጀግና ንጉሥ ደግሞ እንዳሉን ስናስብ – ደስታችን ወደር የለውም! ይህች የሀበሻ ምድር፣ እና እኒህ የሀበሻ ነገሥቶቻችን – ለዚህች ላበቀለቻቸው ቅድስት ምድር፣ እና ለሚመላለሱበት የምድራቸው የተቀደሰ ነፃነት፣ እና የነፃነት አየር ምን ያህል ክፉኛ በፍቅር የወደቁ መሆናቸውን ሳስብ – ባለሁበት ሥፍራ – ከእነዚህ ታላቅ የሰው ልጅ የነፃነት ሃዋርያዎች የተመዘዝኩ ታላቅ ኢትዮጵያዊ በመሆኔ – በኢትዮጵያዊነቴ – ከፍ ያለ ክብርና ግርማ ሞገስ በላዬ ሲተንን ይሰማኛል፡፡ ክብር ለኢትዮጵያችን ይሁን!
በነገራችን ላይ የአለን ሙርሄድ መፅሐፍ ስለዚህ ከዘመኑ ቀድሞ ስለተወለደ አርቆ አስተዋይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ ብዙ የሚናገረው አለው፡፡ በሀገራችን በመልዕክተኝነት መጥቶ በእስረኝነት ያሳለፈው የንጉሡ ወዳጅ ራሳም እንኳ ከምሬቱና ከእገታው ባሻገር ለአፄ ቴዎድሮስ የነበረው ልዩ አክብሮት ሰማይ ጠቀስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
እኚህን ትውልዳቸው ያልተረዳቸውን፣ ዘመን ያከበራቸውን፣ ታላቅ የሰው ልጆች እኩልነት ሰባኪ፣ እና ታላቅ የኢትዮጵያ መሐንዲስ፣ ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊን፣ በዛሬዋ ዕለት እንኳን ተወለዱልን ንጉሣችን ብዬ በአክብሮት 201ኛውን የውልደታቸውን ዝክር በክብር አሰብኩ፡፡ ለታላቁ የአሜሪካ የፀረ-ዘረኝነት ትግል መሪ፣ ለምናከብረው ወንድማችን፣ ለዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየርም – የልደት ቀኑ መታሰቢያ ዝክር ይሆንልን ዘንድ በማሰብ ዝክሬን አበቃሁ!
ክብር ለኢትዮጵያ! ክብር ታላላቅ ሕልሞችን ለሰነቁ ታላላቅ ነገሥቶቻችን!
ክብር ለነፃነታችን! ክብር ለሺኅ ዘመናት በነፃነት ላስጓዘን ኢትዮጵያዊ ለአንድነታችን ይሁን!!
የበዛ ክብር ሁሉን ለፈጠረ አምላካችን ይሁንለት!
መልካም ጊዜ!
Filed in: Amharic