>
3:09 am - Saturday December 10, 2022

"ጥምቀት በሆሳዕና አይከበርም!!!"  ሀገረ ስብከቱ

“ጥምቀት በሆሳዕና አይከበርም!!!” 

ሀገረ ስብከቱ
አደባባይ ሚድያ
(አደባባይ ሚዲያ Jan.17/2020):- በUNESCO በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ታላቁ የጥምቀት በዓል በሆሳዕና ከተማ እንደማይከበር የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት መግለጫ ያትታል። «እስከዛሬዋ እለት ድረስ በክፍተኛ ትእግስት ሲጠባበቅ የነበረው የሆሳዕና ከተማ ህዝብ ዛሬ ቁርጡን አውቅዋል : ለጊዜውም ቢሆን አንገቱን ደፍቶ ወደቤቱ ገብቷል ነገ የሚፈጠረውን ግን አናውቅም» የጥምቀት ቦታ አስመላሽ ኮሚቴ አባላት።
ዛሬ ይፋ የተደረገው የሀዲያና ሥልጤ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት መግለጫ የከተማው ሕዝብ ለረዥም ዘመናት ያቀረበው በዓሉን የሚያከብርበት ሥፍራ ጥያቄ በከተማ አስተዳዳሩ ምላሽ ባለማግኘቱ እና ከዚያም አልፎ ከበዓሉ ጋር በተገናኘ “የፀጥታ ሥጋት” ያለው ችግር መከሰቱ በዓሉን ለመሰረዝ ምክንያት ሆኗል። በሆሳዕና ከተማ የሕዝበ ክርስቲያኑን ቅስም የሚሰብር ውሳኔ እንዲተላለፍ ምክንያቱ የከተማ አስተዳደሩ ነው ተብሏ። ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ በአንድ ሃይማኖት ተከታዮች የተሞላው የከተማ አስተዳደሩ በማንአለብኝነት የክልሉን ትእዛዝ ወደ ጎን በመተው ለጥምቀት በዓል ማክበሪያነት የተፈቀደው ቦታ እንዳይሰጥ አድርጓል።
«ከቀናት በፊት የክልሉ ምክር ቤት ለጥምቀት ማክበሪያ ቦታ 20 ሺህ ካሬ ሜትር ለቤተ ክርስቲያኗ እንዲሰጥ ቢወስንም እስከዛሬው ዕለት ድረስ የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት ውሳኔውን ባለመቀበሉ እና ባለ ማስፈፀሙ ከዚህ ቀደም በተለመደው መልክ ለማክበር ቢሞከር ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ሊከሰት ስለሚችል አለማክበሩን መርጠናል» ብሏል ሀገረ ስብከቱ።
አደባባይ ሚዲያ በተደጋጋሚ እንደዘገበው የሆሳዕና ከተማ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ ጥያቄ በክልሉ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ዞኑና ወደ ከተማው አስተዳደር ቢመራም ምንም ተጨባጭ ምላሽ ሳይገኝ ቀርቷል። ዘንድሮ ጥምቀት በዩኒስኮ መመዝገቡን ተከትሎ በመላው ኢትዮጵያ እና በውጭ ሀገርም ጭምር በተለየ መልኩ ለማክበር ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ጊዜ የሆሳዕና ከተማ ዘጠኝ አብያተ ክርስቲያናት ግን ይህን ደስታ በሩቁ እንድመለከቱ ብቻ ግድ ሁኖባቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ታዋቂ ለሆኑ የፕሮቴስታንት ሰባኪዎች የከተማ አስተዳደሩ ሰፋፊ ይዞታዎችን ማደሉን በማስረጃ አስደግፈን ማቅረባችን ይታወሳል። አደባባይ ሚዲያ የከተማው ሕዝበ ክርስቲያን በዓሉን በምን መልክ ለማሳለፍ እንዳሰበ የነዋሪዎቹን አስተያየት ይዘን እንቀርባለን።
Filed in: Amharic