>
5:13 pm - Tuesday April 20, 5390

የአማራ ተማሪዎች አጋች ታጋች ድራማ!!!  ( ቴዎድሮስ ኃይለማርያም)

የአማራ ተማሪዎች አጋች ታጋች ድራማ!!!

ቴዎድሮስ ኃይለማርያም

ከመጪው ምርጫ ጋር ይገናኝ ይሆን? የአማራን ሕዝብ ጎትቶ ጦርነት ውስጥ ለማስገባት!? ውጤቱስ …

የተማሪዎቹ እገታ ብዙ ጉዳዮችን ያስመዝዛል። የሞጣ መስጊዶች ቃጠሎ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ጫጫታው የተቀናጀና ሴራ ያዘለ እንደነበር በማስረጃ ተጋልጡዋል። አንዳንድ የዋሆች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጃዋርን ተከብቤያለሁ ተከትሎ ዜጎች በእምነት እና በሀይማኖታቸው ሳቢያ በአል ቄሮ ተጋድመው ጭምር ሲታረዱ ድምጻቸውን አጠፉ ተብሎ ስለተወቀሱ አሁን በሞጣው እና በወልዲያው ጉዳይ ሲፈጥኑ መውቀስ አይገባም አሉ። ከድሬዳዋ ሁለት ተማሪ ከፎቅ ሲጣል፣አዋሳ ላይ በጩቤ ተወግቶ ሲገደል እና አሁን ደግሞ ከወር ተኩል በላይ 27 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተቀነባበረ ሴራ ታግተው ትንፍሽ የለም። ይሄኔ ቀድሞ የተኙት ሁሉ መንቃት ጀምረዋል።
ድራማው ያስጓዘን ጠመዝማዛ መንገድ!
 
ህዳር 20 /21 ?— 17 አማራ ተማሪዎች (14ቱ ልጃገረዶች) ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የሚደርስባቸውን የዘር ጥቃት ሸሽተው ወደቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በጉዞ ላይ እንዳሉ እዚያው ደምቢዶሎ ውስጥ ባልታወቁ ቡድኖች ታገቱ።
ህዳር 24 ቀን — አንዲት ተማሪ ለወሬ ነጋሪ አምልጣ ከሶስት ቀን ስቃይ በኋላ ወደቤተሰቦቿ ተመለሰች። የሌሎች ተማሪዎች ቤተሰቦችም ጉዳዩን ሰምተው በያቅጣጫው ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ። ታህሣሥ 10 ቀን የታጋቾችና የቤተሰቦቻቸው  የስልክ ግንኙነት ቆመ።
ከአንድ ወር በላይ  የፌዴራል መንግሥትና የሚመለከታቸው ሚኒስትር መ/ቤቶች  ፣ አማራ ክልል  ፣ ኦሮሚያ ክልል  ፣ እንዲሁም  ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ጭምር ስለጉዳዩ የምናውቀው የለም ሲሉ እገታውን ካዱ።
የአጋችና ታጋች ድራማው ከአንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ እንደ አስራት ፣ ቪኦኤና ቢቢሲ የመሳሰሉ መገናኛ ብዙሃን ውጭ አስታዋሽ አጥቶ የተዳፈነ መሰለ። ማህበራዊ ሚዲያውም ከተባራሪ ወሬ በቀር ተቀዛቅዞ ከረመ።
    የቀጣፊ አለቆች አስተዛዛቢ ምላሽ!
ታህሣሥ 27 ቀን— የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት  አቶ ተመስገን ጥሩነህ 4 ተማሪዎች ስለመታገታቸው መረጃ አለኝ አሉ። መንግሥታቸውና ድርጅታቸው ብአዴን የሞት ሞቱን ይህቺን ጣል አድርጎ ተመልሶ ወደሳጥኑ ገብቶ ተኛ።
ጥር 2 ቀን—  የጠ/ሚሩ  አፈቀላጤ አቶ ንጉሱ ከ27 ተማሪዎች 21 ተለቅቀዋል የሚል አነጋጋሪ የምስራች ይዘው በብሄራዊ ቲቪ ብቅ አሉ። ከዚያ ወዲህ እስከዛሬ በሸሸት ወይም ራስ አግት ላይ ይገኛሉ።
ጥር 3 ቀን—  ከቀናት በፊት ሲያላግጡ የነበሩት የኦሮሚያ ክልል የፀጥታና ደህንነት ም/ሃላፊ  ኮለኔል አበበ ገረሱ የንጉሱን የምስራች በማረጋገጥ   ከመከላከያ ሰራዊት  ጋር በጋራ ጥረት  የተጠቀሱት ተማሪዎች ተለቅቀዋል። ከአካላዊና መንፈሳዊ ጉዳት እንዲያገግሙ በመንግስት እጅ ናቸው አሉ።
     አጋቹ ማነው?
ጥር 4 ቀን— አፋኝ የተባለው የኦነግ—ሸኔ መሪ  ጃልመሮ በቢቢሲ ሬዲዮ ቀርቦ እኔ በአጋች ታጋች ድራማው የለሁበትም። የዚህ ባለቤትና በዚህ ሰበብ ጦርነት ያወጀብኝ የአብይ መንግሥት ነው አለ።
ጥር 6 ቀን— ሌላ ቄሮ ነኝ የሚል ቡድን  የአማራ ተማሪዎችን   አግቻለሁ  ሲል በባለቤትነት  በኢሳት ቲቪ   ቀረበ። ተማሪዎቹን ያገትኩት በአማራ ክልል ለታሰሩት  ኦሮሞ ተማሪዎች መደራደረሪያ ነው አለ። የወሬ ነጋሪዋ ተማሪና የወላጆች ትርክት ከዚህ ጋር የሚቀራረብ ይመስላል።
ይህ ቄሮ የመንግሥት ነው ወይስ የጃዋር ነው?  በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም ፍንጮች በሚያስደነግጥ ሁኔታ  ወደ መንግሥት የአጋችነት ሚና  እያመሩ ነው።
     ከሃዲው ማነው?
ጥር 7 ቀን— የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ሃላፊ  ጄነራል መሃመድ ተሰማ በአማራ ቲቪ ቀርበው  መከላከያ  ስለጉዳዩ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በመናገር እንደገና ጉዳዩን ጥሬ አደረጉት።
በዚያው እለት — የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ጄላን አብዲ   ስለተማሪዎቹ መፈታት የማውቀው ነገር የለም አሉ። ሂዱና ተለቅቀዋል ብሎ የተናገረውን ሰው ጠይቁት የሚል የንቀት ምላሽ   አከሉ። የኦሮሚያው ኮለኔል አበበ ገረሱም እኔም አላውቅም  ብለው እንደገና ሸመጠጡ።
ንጉሱ እስካሁን የአማራም የኦሮሞም አልተነፈሱም። ግለሰቡ  የሴራ  ደቀመዝሙርም   selloutም ሊሆኑ ይችላሉ።  ደደብ ግን አይደሉም። ስለዚህ  ጊዜው ሲደርስ በውድም በግድም የሚሉትን እንሰማ ይሆናል።
      ባለቤት አልባ ጉዳይ 
የአማራ ተማሪዎች እገታና ስቃይ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ጉዳይ ነው የሚል ካለ ነፈዝ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚባል ቢኖር ኖሮ ልጆቻችንን መልሱ የሚለው ጩኸት ለአማራ ህዝብ ባልተተወ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ካለ  ሚናው ምንድነው? በአማራ  ነፍስ የፖለቲካ ጨዋታ የሚያምራቸው ጠ/ሚ አብይ አህመድና ሰው መሳይ ሚኒስትሮቻቸው እስካሁን ዝምታን መምረጥ አዋጭ ሆኖላቸዋል። አሁን ትርፋቸውን ለመዛቅ እየተዘጋጁ ይመስላሉ።
የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት እነ ኦቦ ሽመልስ ያ ለአማራ የሚከፈት ቦርቃቃ  አፋቸው እንደተከረቸመ ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለእገታው የተጠየቁ ሃላፊዎችም ምን ያህል ህሊና ቢስ ቀጣፊዎች ፣ ለአማራ ህዝብ የማይሞት   ጥላቻ ያላቸው እንደሆኑም  አሳይተውበታል። ከትዝብት በላይ ነው!
በሌላ በኩል አንዴ አናውቅም ፣ ሌላ ጊዜ ተፈትተዋል  ፣ መልሶ  አናውቅም የሚል አሳፋሪ የንቀትና የአረመኔዎች ድራማ ሲተወን የአማራ ክልል መንግሥትና ገዥው ብአዴን— አዴፓ እንደ ጠላት ዳር ቆሞ እየሳቀ ይገኛል። ለጊዜው  ጥርስህ ይርገፍ እንጂ ሌላ ምን ይባላል?
     ዘመቻ ዋለልኝ ካልአዊ
ከላይ የተዘረዘሩትንና ሌሎችንም  ነጠብጣቦች ስናገጣጥም ምን  ይታየናል? በበኩሌ የአማራ ህዝብን ተንኩሶ የማስቆጣት ወጥመድ ከፌዴራል እስከ ክልሎች የተዘረጋ ይመስለኛል። በተለይ አመፁ ከጥምቀት በዓል አከባበር  ጋር እንዲጣመርና የጎላ  ሰብአዊ  እልቂትና ቁሳዊ ጉዳት እንዲያስከትል መፈለጉ  ይታየኛል።
ይህ ከሆነ ጉዳቱን በመላው ዓለም  በማራገብ በጥፋተኝነት የሚወነጀለው  የአማራ ክልል በወታደራዊ ክንድ ስር ይውላል። ያኔ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ያሉት ጠ/ሚ አብይ የጦር ልብሳቸውን ለብሰው በአዋጊነት ይሰየማሉ። የኦሮሞና የትግሬ የቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ መቂናጦች በቅንጅት መዘወር ይጀምራሉ።
በቆረጣ ዘመቻ የአማራ የፖለቲካ ቡድኖች ተደርበው ይመታሉ። በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖረውም አማራ በወከባና ማስፈራሪያ አፉን እንዲዘጋ ይደረጋል። መጪው ምርጫ ከአማራ ህዝብና ከአማራዊ የፖለቲካ ኃይሎች እጅ ውጭ ይሆናል።
ስሌቱ ከተሳካ ሁለት የኦሮሞ ኃይሎችና ወያኔን ትርፋማ ያደርጋል። የአብይ ኦዲፒና የአራጁ ጃዋር ኦፌኮ አዲስ አበባን “በምርጫም በጡጫም” በኦሮሞ እጅ ያስገባሉ። ቀሪውን  ኢትዮጵያንና ኦሮምያን በዘመድ ጉባኤ ይካፈላሉ።   የአዳክሞና ከፋፍሎ መግዛት ስልት አባት ትህነግ  ትግራይን ካረጋገጠችና   አማራውን እንደገና በማይወጣበት ቅርቃር ከከተተች ሌላውን ጊዜ ይፈታዋል።
       መክት እንዳባቶችህ!
የአማራ ህዝብ  የተደገሰለትን የጥፋት ዘመቻ  በቆራጥነትና አስተዋይነት  ሊመክት የግድ ነው። ነገር ግን በራሱ ስልትና ጊዜ መሆን አለበት። ጠላቶቹ እንዳሰቡት በበአል ግርግርና ባልተደራጀ ሁኔታ መነሳት  suicidal  ይሆናል።
ስለዚህም የታገስነውን ታግሰናልና ከተራና ጥምቀትን በጥንቃቄ እንዲከናወኑ በተደራጀ መልኩ የየአካባቢያችንን ፀጥታ በማስከበር ላይ እንረባረብ።  በተማሪዎቻችን እገታ ጉዳይ የሚለወጥ ነገር ካለ እናዳምጥ።
እስከዚያው  ድረስ ለከፍተኛ  አለማቀፍና ሀገር አቀፍ የተቃውሞ ሰልፎች እየተዘጋጀን እንጠብቅ። በዋነኝነት
    – መላው የአማራ ህዝብ ፣
    – የአማራ (ክልል) የኃይማኖት አባቶች ፣ ተቋማትና ማህበራት ፣
    – የአማራ የሀገር ሽማግሎችና ታዋቂ ግለሰቦች ፣
    – የአማራ የፖለቲካ ድርጅቶች ፣
    – የአማራ ምሁራንና የሞያ ማህበራት ፣
    – የአማራ የወጣቶች ፣ የሴቶችና የተማሪዎች ማህበራት ፣
    – የአማራ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ፣
    – በህዝባችሁ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ለሚያንገበግባችሁ ዜጎች  በሙሉ!!
በጉዳዩ ላይ ምከሩ ዝከሩ።  ተቃውሞዎቹን ሰላማዊና ስርአታዊ በሆነ መንገድ ከማስተባበርና ከመምራት ውጭ ፣ በመንግስትና በአለማቀፉ ማህበረሰብ ላይ ጫና ለማሳደር አቅዱ።  የአማራ ህዝብም ለፈርጀ ብዙ እምቢተኝነት ይዘጋጅ።
Filed in: Amharic