“ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”
አሰፋ ሃይሉ
ከ1984 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ኦነግ እላዩ ላይ የሰፈረበት የፀረ-ኢትዮጵያውያን አቴቴ ዛሩ በተነሳበት ቁጥር ሰላማዊ የገጠር ነዋሪዎችንና ተማሪዎችን ከያሉበት ሰብስቦ ሲያስጨፍርባት የኖረች የተለመደች ስንኝ አለችው እንዲህ የምትል፡-
“ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”
(ኦሮሚያ የኛ ነች! መጤው (እንግዳው) ይውጣልን!)
ይቺ የኦነግ “እኔን ከሚመስል ውጪ ሌላን የሰው ዘር አልይ!” የምትል “ዜኖፎቢክ” መፈክር የሰነበተች ናት፡፡ ይቺ የኦነግ የቆየች ነጠላ ዜማ – ስትበር ኖራ ኖራ ልትሞት ስትል ራሷን ከሰማይ ወደ ምድር እሾሆች ከስክሳ ትሞታለች የተባለችውን የእሾህ ወፍ (የቶርን በርድን) ነገር ታስታውሰናለች፡፡ ቶርን በርድ በሕይወቷ አንዴ ነው ለሁሉም የሚሰማ ጮክ ያለ ጣፋጭ ዜማዋን የምታሰማው፡፡ ያም ዕድሜዋን ሙሉ በርራ በርራ ኖራ ከሠማይ ቁልቁል ወደመሬት ራሷን ከስክሳ በእሾህ ላይ ተሰክታ ልትሞት ስትል የምታሰማው ነጠላ ዜማዋ ነው፡፡
ለምን እንደሆነ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ቢሆንም – ዘወትር ጡንቻው የፈረጠመ በመሰለው ቁጥር – ጥጋቡን ፈፅሞ በራሱ መግራት የማይችለው ኦነግም – ይቺን “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!” የምትል የጣዕረ ሞት ሲንግል ማሰማት የጀመረው አሁን አይደለም፡፡ ገና ያኔ – በ1984 – የሞት መቃብሩ እየተማሰለት በነበረበት በፍፃሜው ዋዜማ ላይ ነበረ፡፡
ያቺ የኦነግ የስንብት ነጠላ ዜማ – “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!” – በአርባጉጉ ‹‹ነፍጠኞች ናችሁ›› እየተባሉ ያረዳቸውን ንፁሃን ኢትዮጵያውያን ወገኖች አካል በግፍ ሲተለትል ተሰምታለች፡፡ በበደኖ ነፍጠኛ አማሮች እያለ ቀን ያልወጣላቸውን ምስኪን ኢትዮጵያውያን ወገኖቹን በጭካኔ ከነህይወታቸው ወደ ገደል ሲወረውር ተደምጣለች፡፡ በጨለንቆ፣ በጋራሙለታ፣ በአወዳይ፣ በደደር፣ በኢጀጊና፣ በሚያዪ፣ በፈዲስ፣ በቀርሳ፣ በገለምሶ፣ በአሰበተፈሪ፣ በወተር፣ በሌሎችም ኦነግ በተንቀሳቀሰባቸው በርካታ አካባቢዎች ላይ አሰቃቂ የንፁሃን ጭፍጨፋዎችን እያጀበች በየሥፍራው የተስተጋባች የኦነግ የአጥፍቶ መጥፋት አዋጅ የተነገረባት የክፉ ንግርት ነጠላ ዘፈን ነበረች፡፡ ከእነዚያ በኦነግ ከታረዱና ከተተለተሉ ንፁሃን ኢትዮጵያውያን ለቅሶ ጋራ ተቀላቅላ በኢትዮጵያ ምድር የተሰማች የጥንብ አንሳዎች ማጀቢያ ዘፈን ነበረች — “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”፡፡
“ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”፡፡ ይቺ የኦነግ ነጠላ ዜማ ከተሰማች በኋላ – በመንግሥት መዋቅር ላይ በተሾሙም – በያንዳንዱ የወረዳ አስተዳደር መዋቅር ሥር ሆነው የመንግሥትን የጦር መሣሪያ በታጠቁም ኦነጋውያን ታጣቂዎች – በሁለቱም ጎራ ባሉ ሠልፈኞች ነው – በሺህዎች የሚቆጠሩ – በዘራችሁ ነፍጠኛ አማሮች ናችሁ የተባሉ – (እና የሚገርመው ገሚሶቹ አፍ ከፈቱበት ኦሮምኛ በቀር አማርኛ እንኳ መናገር የማይችሉ የነበሩ) – በሺህዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ኢትዮጵያውያን በጠራራ ፀሐይ ለእንግልት ተዳረጉ፡፡ ባደጉበት በኖሩበት ቀዬ ቀና ብለው ለመራመድ ተሸማቀቁ፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ያለማንም ገላጋይ ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ተደረጉ፡፡
ሼክስፒር ‹‹ዘ ዴድ አር ፎርቹኔት›› (‹‹የሞቱት ዕድለኞች ናቸው››) የሚል አባባል ነበረው – በ16ኛው ክፍለዘመን ላይ – በኢንግላንዱ ጨካኝ ንጉሥ በሄንሪ 8ኛ ዘመን የእንግሊዝ ክርስትያኖች ሁሉ በተገኙበት እየተጨፈጨፉ ቀሳውስቱና ጳጳሳቱ በየዛፉ ላይ እንዲሰቀሉ የተደረጉበትን የግፍ ጊዜ እያስታወሰ ሲፅፍ፡፡ የእኛንም የኦነግ ግፍ ሲያስቡት እንደዚያው ነው፡፡ የሞቱት እና ተፈናቅለው በጊዜ ከኦነጋውያኑ ሸሽተው የወጡት የታደሉ ነበሩ፡፡ ያልቻሉት፡፡ እና ፈጣሪያቸውንና ወገናቸውን አምነው አንገታቸውን ደፍተው ያቺኑ የኮሰመነች ኑሯቸውን መታገሉን የመረጡት የኦነግ የእብደት አቴቴ ዛር ክፉኛ ሰለባዎች ሆኑ፡፡ እርጉዞች በኦነጋውያን የግፍ ካራ ታረዱ፡፡ እመጫቶች ከነህፃኖቻቸው ጡታቸው እየተቆረጠ ከነነፍሳቸው ወደ ገደል ተወረወሩ፡፡ እንደ ፋሺስት ዘመን አማራ ነፍጠኛ የተባሉ ንፁሃን አቅመቢስ ኢትዮጵያውያን በጋራ የመቃብር ጉድጓዶች ተጣሉ፡፡
ለእነዚያ የኢትዮጵያ ልጆች ኦነጋዊው ግፍ በዚህ ብቻ ያበቃላቸው አልነበረም፡፡ ባሉበት በሠላም መኖር ተከልክለው – ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ ደግሞ አሁን ቄሮ እንደሚባሉት በመሠሉ የያኔው የኦነግ የያካባቢው ታጣቂዎች ቁጥጥር፣ ወከባ፣ አፈናና ግድያ ይፈፀምባቸው ነበር፡፡ ከሀገር ሀገር፣ ከከተማ ከተማ የሚመላለሱ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በየመንገዱ እንዲቆሙ እየተደረጉ – ነፍጠኞች እና ክርስቲያኖች (በአንገታቸው ክር የተገኘባቸው) ኑ ውረዱ እየተባሉ – በማተባቸው እየተለዩ፣ በኦሮምኛቸው እየተገመገሙ – የመንገድ ዳር የሜንጫና የክላሽ ቅፅበታዊ የሞት ፍርድ ተበየነባቸው፡፡
(🔯አንድ በሐረር ኮምቦልቻ ትኖር የነበረች የገዛ ዘመዴ – በሀረር አወዳይ ላይ – ኦነጋውያኑ የትራንስፖርት መኪናውን አስቁመው ተሳፋሪውን ሲያስወርዱ – የአወዳይ ጫት ነጋዴ የኦሮሞ ሴቶች ጎትተው ድሪያ (ብትን ቀሚስ) አልብሰዋት ከጎናቸው አስቀምጠው – ሌሎቹ ‹‹ነፍጠኛ ተጓዦች›› እዚያው በዚያው ሲገደሉ – እሷን ከሞት ልትተርፍ ቻለች – የሌሎቹን ነገር በእንባ ጎርፍ እየተጥለቀለቀች ሰቀቀኗን ልትናገር እስካሁን ይመጣብኛል!)
በወቅቱ ምሥራቅ ኢትዮጵያን ከግንቦት 20 በኋላ ጦርነት ገጥመው የተቆጣጠሩት የወያኔ/ሻዕቢያ ኃይሎች ራሱ ያ (መንግሥቱ ኃይለማርያምን ያበቀለ የኦጋዴን አንበሣ ሠራዊት እምብርት የነበረ) አካባቢ በትክክልም የነፍጠኛ መናኸሪያ ነው ብለው ከኦነጉ እኩል ሳይደመድሙ አልቀሩም፡፡ ይሄ ሁሉ የኦነግ ግፍ ሲፈፀም – ያ ሁሉ ሰብዓዊ እልቂትና እንግልት ሲደርስ – ወያኔዎች በሐረር እና በአዲሳባ ከኦነግ ጋር የጋራ ልዑክ አቋቁመው ከኦነግ መሪዎች ጋር ዕርቅ ለማውረድ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ይደራደሩ ነበር፡፡ እርቁ እስኪሰምር እነዚያ ሁሉ ንፁሃን ሰሚ ከፈጣሪያቸው በቀር የጣዕር ጩኸታቸውን የሚሰማቸው በሌለበት እንደ ራሔል ብቻቸውን እርሪ ብለው ጮኸው፣ የብቻቸውን ሞት ያጭዷት ነበር፡፡
ኦነግ የገጠር ሴቶችን ወደ ከተማ ገበያ እያግተለተለ የስንብት ዜማውን ያሰማል፡፡ “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”፡፡ መትረየስ በጀርባቸው የተሸከሙ የወያኔ ላንድ ክሩዘር መኪኖች መጥተው ዘፋኞቹን በሃሎ ሃሎ እየለፈፉ ይበትናሉ፡፡ አንዳንዴም በሃሎ ሃሎና በሃይሎጋ ሆ መበተን ያልቻሉትን በሚባላ ጥይት ይበትናሉ፡፡ “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”፡፡ የኦነግ ጨፋሪዎች ባዶ እግራወችን እየጨፈሩ ወደየመጡበት ቀዬ እየጨፈሩ አቧራቸውን እያቦነኑ ተመልሰው ይከተታሉ፡፡
የሚገርመው – ኋላ ላይ – ያ ሁሉ ግፍ – ብዙ ዕድሜ አላገኘም እንጂ – ተመልሶ በወያኔዎቹ (እና በትግሬ ንፁሃን) ላይም ዞሮባቸው ነበር፡፡ ‹‹ለፃድቃን የመጣ ለኃጥዓን ይተርፋል›› (‹‹ለኃጥዓን የመጣም ለፃድቃን ይተርፋል››) ሆነና ነገሩ – ኋላ ላይ – ወያኔና ጥቂት ወያኔን ሊረዱ በኢትዮጵያ ከነትጥቃቸው የቆዩ የሻዕቢያ ሠራዊቶች – ኦነግን – በኦሮምኛም፣ በትግርኛም፣ በአማርኛም ሳይሆን – አሳምረው በሚያውቁት ቋንቋ በጠብመንጃና በጠብመንጃ ብቻ አናግረውት – በመጨረሻ በምሥራቅ ሐረርጌ ኦነግ በተቆጣጠራቸው አውድማዎች ሁሉ ላይ – የማያዳግም ሽንፈት ሲያከናንቡት – ቀድሞ በየመንገዱ ተሽከርካሪ እያስቆመ ነፍጠኛን ያርድ የነበረው ኦነግ – ኋላ ላይ – በግንባራቸው ‹‹11 ቁጥር›› የተጫረባቸውን ንፁሃን የትግራይ ተወላጆችንም ‹‹ነፍጠኛ›› ብሎ ከሚጠራው ከአማራ ጋር በሞት ምድቡ ቀላቅሎ – እንደልማዱ ከመኪና እያስወረደ እነሱንም ማረድ ጀምሮ ነበር፡፡
ማንንም አረደ፣ ማንንም ተለተለ፣ ማንንም ገደለ – በመጨረሻ – ጠባብ ዘረኝነት ከአቴቴ የአረመኔነት ዛር ጋር በላዩ ሰፍሮበት የነበረው የወቅቱ የኦነግ የአመፃ ጋኔን – በልመናም፣ በድርድርም፣ ንፁኀን አማሮችን ለእርዱ እንደ ጭዳ በሬ አሳልፎ በመስጠትም – በዚህ ሁሉ አሻፈረኝ ብሎ ቆይቶ – “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!” የሚል የእርድ ዳንኪራውን ሲያቀልጥ ከርሞ – በመጨረሻ – በሚገባው የሞትና የጠብመንጃ ቋንቋ የናፈቀው ምሱ ሲሰጠው – በፎከረበትና ባቅራራበት ምድር – በፍጥነት – ግብዓተ መሬቱ ተፈፀመ፡፡ ያ በሠልፈኛና በጠብመንጃ ብዛት ታውሮ ጥጋቡንና ጭፍን ጥላቻውን መቋቋም ያልቻለው የያኔው ኦነግ – ስንቱን ምስኪን የኦሮሞ ወጣት በጥላቻና ዜኖፎቢያዊ ስብከቱ ነድቶ የወያኔ የጥይት ራት አደረገው፡፡ ስንቱን የኦሮሞ ወጣት አካል ጉዳተኛ አደረገው፡፡ የስንቱን ወኔ አሰልቦ ስንቱን ወያኔን እንደፈጣሪ የሚፈራ የወያኔ አጎብዳጅ ጥገኛ አደረገው፡፡
የሚገርመው ያኔ ለኦነጋዊው የአጥፍቶ መጥፋት ዘመቻ የከተተው በኦነጋውያኑ ስብከት እየተነዳ ሆሆሆሆ… ብሎ የወጣው ምስኪኑ የኦሮሞ ወጣት ብቻ አለመሆኑ ነበር፡፡ ከሠለጠኑበት ሙያቸው፣ ከሚተዳደሩበት የመንግሥትና የግል ሥራቸው ኮብልለው በኦነግ ጫካዎች የኦነግን የዘር ማጥራት ተልዕኮ ሊወጡ የተመሙ (ራሳቸውን የኦነግ ነፃ አውጪ ብለው የሰየሙ) በርካታ ባለ ዲግሪና ባለ ዲፕሎማ ኦነጋውያን ታጣቂዎች ሳይቀር ነበር በወያኔ ጥይት እየተቀነደቡ በየጫካው የወደቁት፡፡
ስንቶቹ የተማሩ ወገኖች – ስንት ነገር ለወገናቸውና ለሀገራቸው መሥራትና ማበርከት ሲችሉ – የኦነግን የጥላቻ አረር ተሸክመው – ከእረኝነት በሸፈቱ ያልተማሩ ግን የውጊያ ልምድን በተካኑ የወያኔ ታጋዮች ጥይት በየተሰለፉበት እየተመቱ – ስንቶቹ ሙትና ቁስለኛ ሆነው ቀሩ!! ከእነዚህ መካከል የወያኔ ምርኮኛ ሆነው – ከውሻ ባነሰ ክብርና አያያዝ በወያኔ ማጎሪያዎች ታጉረው – መጫወቻ ሆነው ለዓመታት ያለአስታዋሽ የሰነበቱም ነበሩ፡፡ (‹‹ስለት ድግሱን፣ ደባ ራሱን›› እንዲል ያገራችን ሰው – የራሳቸው ጭካኔ – በመጨረሻ – በጨካኝ እጅ ጥሏቸው አረፉት!)
ሀገርን ለመገንጠልና ወገንን ለማድማት መዋሉ ነው እንጂ – አንዳንዴ ያ ብዙዎቻችን የሚታክተን የታጋዮቹ ስንኝ ይመጣብኛል፡፡ ‹‹የማያልፈው የለም፣ ያ ሁሉ ታለፈ…›› የሚለው፡፡ ሰዎቹን ብትጠላቸውም፣ ዘፈኑን ብትጠላውም፣ ግን የሆነ አንጀትህን የሚበላ የለማኝ ዘፈን የሚመስል ዜማ እንዳለው ግን መካድ አትችልም፡፡ ብቻ ግን የማይታለፍ የለምና እውነትም ‹‹የማያልፈው የለም… ያ ሁሉ ታለፈ››፡፡ እንደዚያ በመሆኑም… የሆነው ሁሉ ሆኖ… ያ የ”ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!” ኦነጋዊ እርድና እልቂትም አለፈ፡፡ ሰብዓዊ ጠባሳውን ትቶ፡፡
የያኔው ዜመኛ ኦነግ – በ1984 ዓመተ ምህረት የሽግግር መንግሥቱን ረግጦ ከወጣ በኋላ እና 300 ሺኅ የታጠቀ ሠራዊት አለኝ እያለ ሲያናፋ ከርሞ – 10 ሺህ በማይሞሉ – እና በወቅቱ ምሥራቅ ኢትዮጵያን ከወታደራዊው መንግሥት ተረክበው በዕዝ ሰንሰለታቸው ሥር ባዋሉ – ገና የተኩስ ተነሳሽነታቸው ግለቱ ከውስጣቸው ባልጠፋ የወቅቱ የወያኔና ሻዕቢያ ጨበሬ ታጋዮች – በመረጠው የጠብመንጃ መንገድ ድባቅ ተመትቶ – የናፈቀውን አፈር ተቀላቅሎ ነበር፡፡
ቁርጡን ሲያውቀው – ምንም የማያውቁ ገበሬዎችን ከየመንደራቸው በሃሎ ሃሎ እየሰበሰበ “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!” እያለ ደም ባፈሰሰባት ምድር ተቀበረ፡፡ የቀሩትም እግሬ አውጭኝ ብለው ይቺን የኢትዮጵያ ምድር እየተራገሙ ካገር ሸሽተው ነበር፡፡ አንዳንዶቹ የኦነግ አመራሮች በሰው ዘር ማጠፋት ሁሉ ክስ ተመስርቶባቸው ስማቸው ለዓለማቀፉ የወንጀለኞች አዳኝ ለኢንተርፖል ተላልፎ በዓለም ደረጃ ሁሉ እየታሰሱ – በየሄዱበት አንገታቸውን እንደ እባብ ቀብረው መኖር ቀጠሉ፡፡
(በነገራችን ላይ ከእነዚህ የዘር አጥፊዎች መካከል ስለ አንደኛው የተፃፈ መፅሐፍ በቅርቡ እጄ ላይ ስላገኘሁ በአሜሪካ የእርሱን የችሎት ቃልና ክርክር (ትራያል) ሌላ ጊዜ – ጊዜ ወስጄ – በሰዓቱ ለአንባብያን እንደማካፍለው ተስፋ አደርጋለሁ!)
እንግዲህ ከያኔው የወያኔ ጥይትና ምርኮ ከተረፉት ከእነዚያው “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባዎች!” መካከል – አንዳንዶቹ ፖለቲካን እርስ በእርስ ሲገናኙ ለመዶለትና ጥላቻቸውንና ቁጭታቸውን በሻይ ቡና ላይ ለመወጣት ካልሆነ በቀር – የፖለቲካው ዓለም ‹‹አባ ዓለም ለምኔዎች!›› ሆነው ከወያኔ ሥርዓት ተገልለው ኖረዋል፡፡
ከእነዚህ እጅግ የሚልቁት ሌሎቹ ብዙዎቹ ኦነጋውያን ግን – ከኦነግ ግብዓተ መሬት እና ሽብርተኛ ተብሎ መፈረጅ በኋላ – በኦነግ ስም እየማሉ፣ እና የኦነግን ባንዲራ እያውለበለቡ ኦነግ ሆነው በህይወት መሰንበትም፣ በሰላም መንቀሳቀስም ስለማይችሉ – ኦነግነታቸውን ውስጣቸው ሸሽገው – እና እንደ ደረቀ ሰሊጥ ከላያቸው የነፃ አውጪነት ፖለቲካቸውን እርግፍ አድርገው አራግፈው – በሌላ በሌላ ስሞች እየተጠሩ – ከወያኔና ከሥርዓቱ ጋር ተዳብለውና ተመሳስለው – ባስ ሲል እየተሰደቡም፣ እየተኮረኮሙም – በወያኔይቷ ኢትዮጵያ – በጥገኝነት – በመንግሥት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥም፣ በሚሊቴሪ ውስጥም፣ በበፀጥታና ደህንነት መዋቅሩ ውስጥም፣ በሸፍጥና ድራማ በተሞላው የወያኔ የፖለቲካ አመራር ውስጥም – እስትንፋስ አግኝተው፣ ጭምብል ለብሰው – በሠላም ለመኖርና ራሳቸውን ለማቆየት በቁ፡፡
እነዚህኞቹ ባስ ሲልም መለስ ዜናዊ በአደባባይ ፊት ለፊቱ አስቀምጦ “እንደ ፈጣን ሎተሪ ብትፋቁ ሁላችሁም አንድ ሳይቀር ውስጣችሁ ኦነግ ነው!” እያላቸውም ከመሞት መሰንበት ብለው አንገታቸውን ደፍተው በአሜን አሜን ኖረው እንደምንም በፈጣሪም ይቅር ባይነት ለዚህ ለአሁኑ ዘመን (ዘመነ ቄሮ) ራሳቸውን ማቆየት የቻሉ ትዕግስተኞችም ናቸው – ብዙዎቹ ኦነጋውያን “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባዎች!”፡፡
አሁን፡፡ አሁን ላይ ደረስን እንደምንም፡፡ “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”፡፡ ይህች የቶርን በርድ እሾሃማ ወፎች የኦነጋውያን የስንብት ነጠላ ዜማ በኢትዮጵያችን ምድር ጮክ ብላ ከተሰማችም እነሆ 28 ዓመት ሊደፍናት ነው፡፡ ነገር ግን – ግብዓተ መሬቱ ተፈፀመ የተባለው ያ ሁሉ የእልቂት ነጋሪት – ዳግም አፈር ልሶ ተነስቶ አየነው በኢትዮጵያ ምድር፡፡ ያ የድሮው ኦነጋዊ ትርክት፡፡
ያ ማፈናቀል፣ ያ የድሮው እገታና አፈና፣ ያ የድሮው እርድና ትልተላ፣ ያ የድሮው ፉከራና ሽለላ፣ ያ የድሮው ያዙኝ ልቀቁኝ፣ ያ የድሮው “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!” አሁንም – ዘንድሮም – ስሙን፣ ቅርፁን፣ አድራሻውንና የጨፋሪዎቹን መታወቂያ ቀያይሮ – እነሆ በኢትዮጵያ ምድር – ዳግም ደግሞ እየተሰማ ነው፡፡ ያቺ “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”፣ ያቺ የቶርን በርዶች የስንብት ዜማ – አሁንም አድማሷ ጨምሮ – ከቄለም ወለጋ እስከ ዋሺንግተን ዲሲ፣ ከአወዳይ እስከ ጉጂ፣ ከባሌ እስከ ቦሌ ቡልቡላ – ጮክ ብላ እየተስተጋባች ነው፡፡ ጆሮ ላላቸው – ያለፈውን ለማይረሱ – አዕምሮ ላላቸው – ለወደፊቱ በሚጨነቁ ሁሉ ዘንድ – ያቺ የእልቂት ዜማ – ዳግመኛ ጮክ ብላ እየተሰማች፣ ጮክ ብላ እየተደመጠች ነው፡፡
በእኔ አመለካከት – የአሁኖቹ ኦነጋውያን “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!” ዜመኞች፣ ሠልፈኞች፣ መሪዎችና አጫፋሪዎች – የበፊቱ ሂደት ቅጣዮች ናቸው፡፡ ማፈናቀላቸውን፣ እርዳቸውን፣ ትልተላቸውን፣ ግድያቸውን፣ እገታቸውን፣ በተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፅሙትን ድርጊት፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ሠራዊት አለን እናሸንፋለን ብሎ ማናፋቱንም፣ “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”ውንም፣ የመንግሥትን የፀጥታና የአስተዳደር መዋቅሮች ከየወረዳው መበጣጠሱንም፣ ሕዝቡን መስበክና ማነሳሳቱንም፣ የጦርነት ምታ ነጋሪቱንም፣ ጠብ አጫሪነቱንም፣ ከኛ በላይ ላሳር ባይነቱንም፣ የኛ ጊዜ ነው ባይነቱንም ሁሉንም ኦነጋዊ ትዕይንት በዓይነት በዓይነቱ ደግመው እያሳዩን ነው፡፡
እንዲያውም በዚያ በድሮው ላይ ከ1984ቱ የከፋ ቂምና ቁርሾም ጨምረውበታል፡፡ የ1984 ዓመተ ምህረት እሾህ ወፎች ዜማ ወደ 2012 ዓመተ ምህረት ተሸጋግሮ ሲመጣ – በቂምና በበቀል፣ በዓይነቱና በብዛቱ ጨምሮ መጥቷል፡፡ እነዚያ ኦነጋውያን በታይፕራይተርና በፍሎፒ ዲስክ ዘመን የተነሱ የ16ኛው ክፍለዘመን ጎሳዊ ትርክትን የሚያቀነቅኑ የጥፋት ሠራዊቶች ነበሩ፡፡ የ2012ቶቹ ደግሞ በሶሻል ሚዲያ፣ በኢንተርኔት፣ በብሮድካስቲንግ ኔትወርኮች፣ በትላልቅ ጂቢ ሃርድ ዲስኮች በተጫኑ መረጃዎችና ስብከቶች ራሳቸውን ያጋጌጡ ናቸው፡፡ ግን እነዚያው የ16ኛው ክፍለዘመን ጎሣዊ ሥርዓት ናፋቂዎች ናቸው፡፡
ያ የ1984ቱ የመጠፋፋትና የይዋጣልን ዛሩ አሁንም ያው ነው፡፡ የሥፋት አድማሱንና ድፍረቱን ግን ጨምሯል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ሽግግር አድርጓል፡፡ ኦነግ እየዳኸች ከሐረርጌ ወደ አዳማ፣ ከወለጋ ወደ ፊንፊኔ ገብታለች፡፡ የአቴቴው አምላክ ዋቄ ፈታ እንኳ የአምልኮት አድማሱን አሰፍቶ – ከቢሾፍቱ ሐይቅ ቆሪጦች በአንድ ትልቅ እርምጃ ተራምዶ በፊንፊኔ ታከለ-ኡማ ሠራሽ ሃይቅ ላይ መንፈሱን እስፍፏል፡፡ ኦነጋውያኑ የጦር አበጋዞችም የያኔውን የወያኔና ሻዕቢያ ማሊያ ለብሰው በእነርሱ እግር ተተክተዋል፡፡ መከላከያና መጠቃቂያ፣ አጥቂና ተከላካይ ያልተለየበት ድብልቅልቅ ጎራ በዝቷል፡፡
በተረፈ… ሌላ ሌላው ያው ነው፡፡ መፈክሩም አልተለወጠም፡፡ ነጠላ ዜማውም ጭምር ቁርጥ ያንኑ የድሮውን ነው፡፡ “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”፡፡ ወደፊት የሚቀረው – ምናልባት – ኦነጋውያኑ የአመፃ ናፋቂዎች – በዳግም ትንሳዔያቸው የሚከናነቡት ዳግማዊ ግብዓተ መሬታቸው ብቻ ነው፡፡
“መከላከያ ሠራዊት አትሂዱብን!”
— ወያኔ
“መከላከያ ሠራዊት ውጡልን!”
— ቄሮ
“ማነው ሂያጅ፣ ማነው መጪ? ማነው አስገቢ? ማነው አስወጪ?”
(እዚያው በዚያው፣ ሳይሞቅ ፈላ!)
— እኛ
ከያኔው የባሰ ሀገራዊ ትርምስ ነው እየገጠመን ያለው ጓዶች! “ኦሮሚያ ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገለቀባ!”፡፡ እስቲ የከርሞ ሰው ይበለን! አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን – ከጉግማንጉጎች የክፋት ሥራ – ፈፅሞ ይጠብቃት!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!