>
5:13 pm - Tuesday April 19, 1594

የህዳሴውን ግድብ የሸጡ ጠ/ሚር! (ያሬድ ጥበቡ)

የህዳሴውን ግድብ የሸጡ ጠ/ሚር!

 

ያሬድ ጥበቡ
ይህ የህዳሴ ግድብ ስምምነት እንዲቆምና እንዲመክን የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፁን ማሰማት አለበት። “የለውጡ አመራር” ኢትዮጵያን ከቀውስ ወደተረጋጋ ሁኔታ የማሸጋገር ሃላፊነት እንጂ የተሰጠው፣ ውክልና ባልተሰጠው የአባይ ጉዳይ ላይ እንዲደራደር አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግድቡ ላይ መከተል የሚፈልጉትን ፖሊሲ ለህዝብ ምርጫ አቅርበው ድጋፍ ካገኙ ብቻ ነው መደራደር የሚችሉት።
የአባይ ጉዳይ ፓርቲዎች በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት ሊከራከሩበት የሚገባ ጉዳይ እንጂ፣ ዉክልና የሌለው የ”ለውጥ መንግስት” ባፈተተው የፈለገውን የሚወስንበት መሆን የለበትም። የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መንግስት በጉዳዩ ላይ የመደራደር ውክልና እንደሌለው የሚያሳዩ የተቃውሞ ሰልፎችና የህዝብ ውሳኔዎች በመላ ሃገሪቱ ሊካሄዱ ይገባል። መንግስትም እነዚህን የተቃውሞ ሰልፎችና የድርጅቶች የውሳኔ ስብሰባዎች ደግፎ መቆም ይኖርበታል።
መንግስት  ደግፎ መቆም ይኖርበታል ስልም፣ ከህዝቡ ጋር ሰልፍ ይውጣ ማለቴ ሳይሆን፣ ሰልፎቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቁ ተገቢውን ጥበቃ ካደረገ በኋላ፣ እነዚህን ሰልፎችና ተቃውሞዎች ከድርድሩ ለመውጣት ምክንያት አድርጎ ሊጠቀምባቸው ይገባል። ለሚፈራቸውና፣ ተው እየተባለ አልሰማ ብሎና ዋሽቶ በአደራዳሪነት ያስገባቸው አሜሪካና የአለም ባንክ ጋ ሄዶ “ህዝቡ ለመደራደር ውክልና የለህም እያለኝ ነው፣ ምርጫ አካሂደን ቋሚ መንግስት እስክንመሰርት መጠበቅ አለባችሁ” ብሎ ሰልፎቹንና ተቃውሞዎቹን ከገባበት አጣብቂኝ መውጫ ጭምብል አድርጎ መጠቀም ይኖርበታል።
ይህ እንዲሆን ሠራተኞች በየድርጅታቸው እየተሰበሰቡ “መንግስት በህዳሴው ግድብ ላይ ለመደራደር ውክልና ስለሌለው ከድርድሩ መውጣት አለበት” የሚሉ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ አለባቸው። የባንክ፣ የአየር መንገድ፣ የኢንሹራንስ፣ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የመንግስትና የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ወዘተ በየመሥሪያ ቤቶቻቸው እየተሰበሰቡ ያላቸውን ተቃውሞ በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ ማሰማት አለባቸው።
ከልጆቻቸው ጉሮሮ እየነጠቁ የወር ደሞዛቸውን በአመት በመክፈል የሰሩት ግድብ በመሆኑ፣ በተጭበረበረና ሃገራቸውን በዘለቄታው በሚጎዳ መንገድ የሚደረግ ድርድርን መቃወም ተፈጥሯዊ መብታቸው መሆኑን አምነው በኢትዮጵያዊ ኩራትና አልደፈርባይነት ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፎ መቆሚያ ጊዜው አሁን ነው።
Filed in: Amharic