>

የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች አገዛዝ በተለዋወጠ ቁጥር አጋጣሚውን እየጠበቁ በአማራ ላይ የሚፈጽሙት ... [አቻምየለህ ታምሩ - ክፍል ፪]

የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች አገዛዝ በተለዋወጠ ቁጥር አጋጣሚውን እየጠበቁ በአማራ ላይ የሚፈጽሙት ግድያ፣ ዝርፊያና ማሳደድ!

[ክፍል ፪]
አቻምየለህ ታምሩ
በክፍል አንድ ወጋችን ራስ እምሩ የኦነጉ የአባ ቢያ አባት የጅማው አባ ጆቢር አማራ አንገቱ እንዲቆረጥ የሰላሳ ብር ጉርሻ  በአዋጅ ማሳወጃቸውን ተከትሎ ሽማግሌው፣ አሮጊቱ፣ ሴቱና ሕጻናቱ ሁሉ ነፍሴ አውጭኝ ብሎ ጫካ ውስጥ ተጠልሎ እንዳገኙትና ሕዝብ ከማስጨርስ ብለው ሳይዋጉ ለፋሽስት እጃቸውን እንደሰጡ፤ አሮጌ፣ ሽማግሌው፣ ሴቶችና ሕጻናት የበረከተበት ሕዝብ አብሯቸው ባይኖርና ያስከተሉት ደረቅ ጦር ብቻ ቢሆን ኖሮ ጦርነት ሳያደርጉ እጃቸውን እንደማይሰጡ በስሜን ግንባር ይዘውት በዘመቱት ሠራዊት ብቃታቸውን አውስተናል። እውነትም ከከበቧቸው ጠላቶች አኳያ ጦርነት እንኳ ቢከፈት ሲሆን ድል ያደርጉ አልያም «እጅዎን ስጡ» ተብለው የተጠየቁበት ሰዓት ወደ ማታ እንደመሆኑ መጠን የቻሉትን ያህል ሲከላከሉ አምሽተው ሲመሽ ጨለማውን ተገን አድርገው ያመልጡ ነበር እንጂ አይማረኩም ነበር። የሆነው ሆኖ ራስ እምሩ ለጠላት እጃቸው ለመስጠት የተገደዱት አባ ጆቢር በፈጸሙት አሰቃቂና አስነዋሪ ተግባር መድረሻ አጥተው የተጠጉትን የአማራ ሕጻናት፣ እናቶች፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች አላስጨርስም ብለው ነበር።
ባጭሩ አማራ በአባ ጆቢር አዋጅ እንደ ፋሲካ በግ በሰላሳ ብር አንገቱ የተቀላው አማራ ጅማን በድሎ ሳይሆን ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አባ ጅፋር የባርያ ንግዱን አቁመው የሰውን ልጅ  በተለይም የድሀውን ኦሮሞ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት እንዲያከብር በማድረጋቸው ነው። ይህንን እሳቸውም አልደበቁም! «ምኒልክ አባቴን  እንዲደኸይ ያደረገውን ሂሳብ አወራርጃለሁ» ብሏል። አባ ጆቢር «ምኒልክ አባቴን እንዲደኸይ ያደረገውን. . .» ማለታቸው  ዳግማዊ ምኒልክ አባ ጅፋር የባርያ ንግድ  እንዲያቆም  ስላደረጉት ገቢው የቀነሰበትን ነው።
ያንን ሁሉ ግፍ በአማራ ላይ የፈጸመው አባ ጆቢር ግን በኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ የኢትዮጵያ መንግሥት መልሶ ሲቋቋም ለፈጸሙት  የዘር ማጥፋት ተጠያቂ ሳይሆኑ እንኳን እስርና ለወንጀላቸው ተመጣጣኝ ቅጣት ሊያገኛቸው  ለፍርስ ሳይቀርቡ  ምህረት አግኝተው  የወር ደመወዝ እየተቆረጠላቸው ደልቷቸው ተዘባነው እንዲኖሩ ንጉሡ አደረጉ። የእሳቸው  የመንፈስ ልጆች ኦነጋውያንና  ኦነጉ ልጃቸው አባ ቢያ  ግን የተበዳዩን ቂም ቋጥረው
የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ ነበረ ተረቱ፣
ምነዋ ዘንድሮ ተወጊው ሲረሳ ወጊ አለመርሳቱ፤
ከዚያም አልፎ ተርፎ የተወጊው ጉዳይ የከበደው ነገር፣
በደሉን ረስቶ የወጋውን ጩቤ ልሶ ስሞ ማደር።
እንዳለው ገጣሚው አባጆቢር ሰላሳ ብር እየከፈሉ አንገታቸውን ባስቀሏቸው አማሮች ላይ ሰይፋቸውን መዝዘው የአገዛዝ ለውስጥ በተፈጠረ ቁጥር ሥርዓት አልበኛነት እየፈጠሩ በየጊዜው አማራውን ሲገድሉ፣ ሲዘርፉና ከቅየው ሲያሳድዱት እነሆ  እስከዛሬ ድረስ አሉ።
ደርግ የሚባለው ደሞዛቸውን ለማስጨመር የተሰበሰቡ ሻለቆችና የበታች መኮንኖች ስብስብ በአገዛዝ ወንበር እንደተሰየመ  በመሀል የተፈጠረውን ሥርዓት አልበኛነት እንደአጋጣሚ በመጠቀም ኦነጋውያኑ እነ አባጆቢርና ባሮ ቱምሳ የጀመሩት የአማራ ጭፍጨፋ ተጠናክሮ ቀጠለ። ደርግ የኦሮሞ ብሔርተኞችን ድርጅቶችን ይዞ በአገዛዝነት ከተሰየመ በኋላ ከአምስቱ የኢማሌድኅ  የኦሮሞ ብሔርተኛ ድርጅቶች መካከል ዋናዎቹ የሆኑት  መኢሶንና ኢጭአት በደርግ በኩል ሲያስፈጽሙት የነበሩት የአማራ ጭፍጨፋ በመንግሥትነት ተሰይመው ነበር። በመኢሶንና በኢጭአት ሽፋን ይንቀሳቀሱ የነበሩት ኦነጋውያን በመንግሥትነት ተሰይመው በባሌና በሐረርጌ ክፍለ ሐገሮች በሚኖረው የአማራ ገበሬ ላይ በጋራ ተንቀሳቅሰው ያካሄዱበት ጭፍጨፋ ሳይጠቀስ ሊታለፍ አይገባም።
መገርሳ በሪ በስም መኢሶንና በሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት በኩል የባሌ ክፍለ ሐገር ምክትል አስተዳዳሪ ነበር። መኢሶኑ መገርሳ በሪ የባሌ ክፍለ ሐገር ምክትል አስተዳዳሪ ተደርጎ የተመደበው የሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት አባል በነበረው በኢጭአቱ ባሮ ቱምሳ ግፊት መሆኑን ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ  እኛና አብዮቱ በሚል በጻፈው መጽሐፍ  ነግሮናል። ባሮ ቱምሳ የሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት አባል ሆኖ የኦነግን ፕሮግራም የሚያስፈጽሙ አባላትን ከኢማሌድኅ አባል ድርጅቶች በመመልመል በየክፍለ ሐገራቱ የሚገኙነት የሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤቶችን  በኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ  የደርግ ካድሬዎች መሙላት ከመቻሉም በላይ የአርሲን ጽሕፈት ቤት ሙሉ በሙሉ፣ የሐረርንና የባሌ ክፍለ ሐገራትን ደግሞ በከፊል  በአማራ ጠል የደርግ ካድሬዎች ለመቆጣጠር ችሎ ነበር። ይህን በሚመለከት ለበለጠ ማወቅ የሚፈልግ የፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ «እኛና አብዮቱ» በሚል ባዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ ስለ ኢማሌድኅ የጻፈውን ምዕራፍ ያንብብ።
በሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት የሚመደቡ የኦነግ ካድሬዎች በባሮ ቱምሳና በኃይሌ ፊዳ በቀላሉ እየተመለመሉ በክፍለ ሐገር አስተዳድሪነት፣ በክፍለ ሕዝብነትና በጸጥታ ኃላፊነት ይመደቡ የነበሩት የእጩዎቹ ሹመት በኢማሌድኅ ስብሰባ ላይ ለውውይት ሲቀርብ አብረው ድምጽ በመስጠት ነበር። በዚህ መልክ በመንግሥት መዋቅር ተጠምጥመው የተደራጁት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች አርሲ፣ ባሌና ሐረርጌ የተመደቡት የኢጭአትና የመኢሶን የክፍለ ሐገር አስተዳዳሪዎችና የአውራጃ ጸጥታ ኃይፊዎች ግንባር ፈጥረው በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የኦነግ ታጣቂዎች ጋር በመተባበር በየአካባቢዎቹ የነበሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ባላገሮች ላይ በተለይም ደግሞ አማሮችን «መጤ፣ ሰፋሪና ነፍጠኛ» የሚል መጠሪያ እየሰጡ በጠመንጃ ኃይል ከእርስት መሬታቸው ማፈናቀልን ዋናው ስራቸው አድርገው ያዙት። በካድሬነት የተሰማሩት በባሮ ቱምሳ የተመደቡ የሕዝብ ድርጅት አባላት ደግሞ ተከባብሮና በሰላም የኖረውን ሕዝብ እርስ በእርሲ እንዲቃቃርና እንዲጠፋፋ መቀንቀስን ዋነኛ ሥራቸው አድርገው ወሰዱት። ይህንን ዊክሊክስ ካሾለከውና እ.ኤ.አ. July 25 ቀን 1974 ዓ.ም. የአዲስ አበባው የአሜሪካ ኢምባሲ ወደ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከላከው ሚስጥራዊ መልዕክትና ኦነግ ራሱ እ.ኢ.አ. በ1970/71 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ይዋጉ ለነበሩት ከጻፈው ደብዳቤ ማየት ይቻላል።
በዚህ አክኋን በሕጋዊ መንገድ፣ በመንግሥት መዋቅር ተጠምጥመው የኦነግን ፕሮግራም ያስፈጽሙ የነበሩ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች የሆኑት አብዛኛዎቹ የኢማሌድኅ ድርጅቶች እየተፈናቀለ ሜዳ ላይ የሚወድቀው አማራ በሚያሰማው የየእለት ጩኸትና ዋይታ ሳቢያ አማራውን በግላጭ «መጤና ሰፋሪ» እያሉ መግደልና ማፈናቀል እንደማይችሉ ሲያውቁት ሌላ የትግል አማራጭ ለመውሰድ ተገደዱ። በካድሬነት፣ በክፍለ ሐገር፣ በአውራጃና በወረዳ አስተዳዳሪነት በሕዝብ ድርጅት በኩል ተመድበት ይሰሩ የነበሩ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች በአርሲ ክፍለ ሐገር የሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በነበረው ክንፈ ኢንዴሳ አስተባባሪነት ተሰባስበው ከባሮ ቱምሳና በኢጭአት ስም ይንቀሳቀሱ ከነበሩ ሌሎች የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ጋር በመክተት ቀደም ሲል በሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት በኩል እየታገዘ በሐረርጌ ክፍለ ሐገር የደፈጣ ውጊያ ያካሂድ ከነበረው ከጃራ ኃይል ጋር ተቀላቅለው የኦነግን የትጥቅ ትግል ጀመሩ።
በዚህ መልክ የቀጠመው ኢማሌድኅ የሚያራግፈውን አራግፎና ሕቡዕ የገባው ሕቡዕ ገብቶ ለሶስት ዓመታት ያህል ከቀጠለ በኋላ የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን ወይንም ኢሠፓአኮ ሆነ። ከአራት አመታት በኋላ ደግሞ ኢሠፓአኮ ወደ ፓርቲነት ተለውጦ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ ወይንም ኢሠፓ ተመሰረተ። የዚህ በስተመጨረሻ ላይ የተፈጠረው ኢሠፓ የተሰኘው ውህድና አንድ ወጥ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ የሆነው መንግሥቱም ኃይለ ማርያምም ኦሮሞ ነው። ከሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት እስከ ኢሠፓ ምሥረታና የደርግ ውድቀት ድረስ የተፈጠሩት ከደርግ ጋር ሥልጣን የተጋሩ ድርጅቶች ሊቀመናብርቶችና በመሪነት የተሰየሙ ግለሰቦች አንዳቸውም አማራ አይደሉም። ምስኪኑ አማራ ግን ፈርዶበት ከሕዝብ ድርጅት እስከ ኢሠፓ ምስረታ ድረስ አገዛዙን ከላይ እስከ ታች በመንግሥትነትና በካድሬነት የተሰየሙ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች እየዘወሩትና የየክፈለ ሐገሩንና የየአውራጃውን አስተዳደርም አማራውን «መጤና ሰፋሪ» እያሉ የሚገድሉት፣ የሚያፈናቅሉትና የሚያሳድዱት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች እንደልተቆጣጠሩት እውነቱን የሚነግርለት ድምጽ አጥቶ በተቃራኒው «ደርግ» እየተባለ ባልዋለበት ሲገዘገዝ እስከ ዛሬ ድረስ ኖረ፤ ተለቅሞ በማይሞላ ጉድጓድ ውስጥ ተጣለ፤ በዱልዱምም ታረደ!
ኦነግ በእድሜ ዘመኑ ከታጠቀ ኃይል ጋር ገጥሞ ተዋግቶ አያውቅም። የኦነግ ዋነኛ ተግባር መንግሥት የላላበትን አካባቢ እየፈለገ ያልታጠቁ አማሮችን፣ ሕጻናትና ሴቶችን ማረድ ነው። ኦነግ በደርግ ዘመን ካካሄደው የባሌ፣ የሐረርጌና የአርሲ የአማራ ጭፍጨፋ በመቀጠል በዚያው በደር ዘመን ዐማራን ለመጨፍጨፍ የመረጠው ደርግ ውስጥ ባሉ ሚስጥረኞቹ የመንግሥት አስተዳደር እንደሌለው የተነገረውን የአሶሳን አማራ ነበር።
በጥር ወር 1982 ዓ.ም. የሻቢያና የኦነግ ጥምር ጦሮች በኢትዮጵያ ምእራባዊ ክፍል አሶሳ አውራጃ ውስጥ በአማራ ላይ ያካሄዱት የወረራ፣ የዘረፋና የጭፍጨፋ ዘመቻ የተካሄደው ልክ እንደከዚህ በፊቶቹ ጭፍጨፋዎች በአካባቢው በመንግሥነት የተሰየመ አካል አለመኖሩን ተጠቅመው  ነው። ኦነግ በጥር ወር 1982 ዓ.ም. “ከነፍጠኛ ወራሪ ነጻ የማውጣት  ዘመቻ” በሚል በከፈተው ዘመቻ ወደ አሶሳ እንደገባ የወሰደው እርምጃ ሕዝቡን በጎሳና በቋንቋ በመከፋፈል አማራና የአማራ ደጋፊ ያላቸውን ለይቶ በአንድ ጎራ በማሰለፍ  ባቃጠል ነበር። በዘመቻው አብሮ የነበረው ሻዕብያ ትግርኛ ተናጋሪዎችን  ከሌሎቹ እንዲነጠሉና ወደ ትግራይ እንዲወሰዱ አድርጓል።
በተለምዶ ጎጃም ሰፈር ተብሎ ይጠራ በነበረው አካባቢ ይኖሩ ለነበሩ አማራና ጉራጌ ገበሬዎች አካባቢው የኦሮሞ ሀገር ስለሆነ ነጻ ለማውጣት መምጣታቸውን ለገበሬዎቹ አውጀው አውራጃውን በአምስት ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፉ። ገበሬዎቹ በበኩላቸው አውራጃው አገራቸው እንደሆነና  እድሜ ዘመኑን  የኖረበት፣ በግብርናና በአነስተኛ ንግድ ተሰማርቶ ሕይወቱን የሚገፋበት ርስቱ መሆኑን  በመናገር መሄጃ እንደሌላቸው ገለጹ። ከዚህ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ በእለተ ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 1982 ዓ.ም. ኦነግ በነፍጠኛ ወራሪነት የፈረጁትን አማራ ሁሉ የአማራ ሴቶች፣ አዛውንቶችንና ልጆችንም ሳይቀር ባስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ። ሕዝቡንም ስብሰባ በተጠራበት ቦታ እንደደረሰ ወደ ትምህርት ቤት ሕንጻ ተወስዶ በሁለት መማሪያ ክፍሎች ውስጥ ሁለት ቦታ ተከፍሎ እንዲገባ ተደረገ። በመማሪያ ክፍሎቹ ውስጥ ከታጎሩት አማሮች መካከል የኦነግን አዋጅ ሰምተው ቦታውን መሰደድ ያልቻሉ እርጉዝ ሴቶች፣ ጨቅላ አራሶችን ያዘሉ እናቶች፣ ሕጻናትና አዛውንት በብዛት ይገኙበት ነበር። ከዚህ ቀጥሎ የኦነግ አመራሮች የመማሪያ ክፍሎቹ እንዲዘጉ ትእዛዝ ሰጥተው ውስጥ ያለው አማራ ሁሉ በአረመኔያዊነት በፈንጂና በላውንቸር ተደብድቦ እንዲረሸን አደረጉ። ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ ክፍሎቹ በእሳት እንዲጋዩ ተደረገ። እሳቱንና ጥይቱን በተዓምር አልፈው ለማምለጥ የሞከሩ አማሮች ታድነው እየተያዙ ተረሸኑ። ከተጨፈጨፉት 600 አማሮች ውስጥ  ከዘጠና በመቶው በላይ አዛውንት ወንዶች፣ ሴቶች፣ ሕጻናትና ገና የተወለዱ አራስ ጨቅላዎች ይገኙበታል። ሌሎች ብዙ ቁጥር ያላቸው አማሮች ደግሞ ከፍተኛ የአካል መጉደል ደርሶባቸዋል።
በርግጥ የአሶሳውን የአማራ ጭፍጨፋ ኃላፊነት የወሰደ ኦነግ ብቻ አይደለም። የሻዕብያው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂም ለአሶሳው የአማራ ጭፍጨፋ ኃላፊነት እንደሚወስድ በሬድዮ ጣቢያው በከፍተኛ ጀብዱ ገልጿል። የሰፊው ኤርትራውያን መገናኛ ድምጽ [Voice of the Broad Masses of Eritrea] በተሰኘው ሬዲዮ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል፤
«Within the framework of our co-operation with the Oromo Liberation Front The situation created by the destruction of communication installations, State mines Surveying installations, witnesses a political and military development that cannot be underestimated.»
ይህ ወደ አማርኛ ሲተረጎም እንደሚከተለው ነው፤
«በአሶሳ ላይ የተወሰደው እርምጃ በኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባርና በኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር በጋራ የተከናወነ ነበር። ባካባቢው እንዲህ አይነት ኦፕሬሽን ስናካሂድ ይሄኛው የመጀመሪያችን አይደለም። ከኦነግና ከሌሎች የተለያዩ ኃይሎች ጋር ያለን ግንኙነትና ትብብር በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ ነው:: በዚህ በጋራ በፈጸምነው ጥቃት መሰረት አካባቢውን በኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ቁጥጥር ስር ለማድረግ ተችሏል»
በወቅቱ የኦነግ መሪ የነበረው ገላሳ ዲልቦም ተመሳሳይ መግለጫ ሰጥቷል። በነገራችን ላይ ገላሳ ዲልቦ ባለፈው አመት  በሱ የሚመራውን ኦነግ እየመራ «ሊደመር» ወደ አዲስ አበባ ገብቷል።  በአሶሳው የአማራ ጭፍጨፋ ወቅት የኦነግ መሪ የነበረው ገላሳ ዲልቦ ማተቡን ከመበጠሱ በፊት ወላጆቹ ያወጡለት ስም ዮሐንስ በንቲ ይባል ነበር። ዮሐንስ በንቲ በዘመነ ደርግ የልጅ ሚካኤል ካቢኔ ሳይፈርስ ደርግና በዙሪያው የተጠመጠሙ የግራ ድርጅቶች ያቋቋሙት ኅብረት የሆነው የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ፍሕፈት ቤት ጓድ  የነበረ ሲሆን ለሁለት አመት ተኩል ያህል አለቃው የነበሩት አሰፋ ጫቦ ናቸው። አሰፋ ጫቦ በደርግ አስር አመታት ያህል የመታሰራቸው ምክንያት ሲገልጹ ገላሳ ዲልቦና ሌሎች አስር ጓደኞቹ ኦነግ ሆነው ሳለ ሽፋን ሰጥተሀል ተብለው መሆኑን ነግረውናል።
ገላሳ በደርግ ውስጥ ለሁለት አመት ተኩል እንዳገለገለ ቀይ ሽብር ካበቃ በኋላ ጫካ በመውረድ ኦነግን ተቀላቀለ። ከተወሰነ ጊዜ የኦነግ ቆይታው በኋላ ኦነጋውያን በደም ጥራትና በመንደር ልጅነት ሲሻኮቱ ኦነግን በመለየት በደበላ ዲንሳ አማላጅነት ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር ታርቆ ወደ ደርግ እንደገና ገባ። ደርግን ለተወሰነ ጊዜ ካገለገለ በኋላ ለመስክ ስራ ተልኮ በዋለበት ሳይመለስ ቀረ።
የውሀ ሽታ ሆኖ ከቆየ በኋላ ጫካ ወርዶ ጸጉሩን አንጨፍሮ፣ ጺሙን አሳድጎ የሚሳይ የገላሳ ፎቶ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ሰላዮች እጅ በመግባቱ ገላሳ ዲልቦ ወደ ትፋቱ ወደ ኦነግ መመለሱ ታወቀ። ከተወሰኑ የጫካ አመታት ቆይታ በኋላ ያገለግለው የነበረው የደርግ አገዛዝ ተወግዶ ወያኔ ሻእብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ሲገባ ገላሳም የኦነግ መሪ ሆኖ ወያኔን ተከትሎ አዲስ አበባ ገባ። ገላሳና ድርጁቱ የወያኔ ቀኝ እጅ ሆነው ካገለገሉ በኋላ የሆነውን ሁሉ ብዙ ሰው ስለሚያውቀው ነጋሪ አያሻም። እነ ገላሳ ወያኔ ከአገር ካባረራቸው በኋላ በውጭ አገር ሆነው  27 ዓመታት ሲታገሉ የኖሩትና ዛሬም እየታገሉ ያሉት ከአገር ያባረራቸውን ወያኔን ሳይሆን በፈጠሩት ትርክት የሚጠሏቸውን ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን ነበር።
ገላሳ ዲልቦ ዛሬ ሶስተኛ መንግሥቱ የሆነውን የዐቢይ አሕመድን ኢትዮጵያ ሲረግጥ ወያኔ ከአገር ሲያባርራቸው በወጣበት ቦሌ ሲደርስ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ «ይሄ ትልቅ መስዋትነት ተከፍሎ የተገኘውን ድል እና ኦሮሞን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ብሔሮች ያኮራ ለውጥ ወደኋላ እንዲመለስ አንፈልግም» ሲል በአማርኛ ተናገሯል። ይህ እንግዲህ ሌላ ማተብ ፍለጋ መሆኑ ነው። ገላሳ በሽግግሩ መንግሥት ተብዮው ጉባኤ በአዳራሹ ውስጥ ለነበሩት ለነመለስ ዜናዊና ኢሳያስ አፈወርቂ ይናገር የነበረው በኦሮምኛ ሲሆን ንግግሩን ወደ እንግሊዝኛ ያስተረጉምና ለጉባኤው ያሰማ የነበረው  ደግሞ ምክትሉ የነበረው ሌንጮ ለታ ነበር። ዛሬ ግን ገለሳ ያኔ እንግሊዝኛ ያስተረጉምለት የነበረው ሌንጮ ለታ አጠገቡ ስለሌለና ሌንጮም እንግሊዝኛውን ትቶ በአማርኛ መናገር በመጀመሩ ያለአስተርጓሚ ያውም ልቅም ባለ የአራዳ አማርኛ ቅኔ አዘል መልዕክቱን ለታዳሚ ጋዜጠኞች አስተላልፏል።
ለሰላሳ በላይ አመታት ያህል አማርኛ ሳይናገሮ ኖር ሳይጠፋበት እንዲህ በቅኔ የዋጀ አማርኛ ተናጋሪ መሆኖ በወቅቱ በሌንጮ ለታ የእንግሊዝኛ አስተርጓሚነት ይናገር የነበረው አማርኛ ጥላቻ እንጂ አማርኛ ባለመቻሉ አለመሆኑን  ከላቀው የአማርኛ  ክህሎቱ መታዘብ ይቻላል።  የዛሬን አያድርገውና  ይህንን የሚያውቁት ዶክተር መረራ ጉዲናም  በጦብያ መጽሔት በጥር 1988 ዓ.ም. «በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖር በሌሎች ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ ወርዋሪ አይሆንም» በሚል ለኦነጋውያን በሰጡት አጸፋ ገላሳ ዲልቦን በሚመለከት «የሽግግር መንግሥቱ ሲመሰረት ከፊል አማራ የሆኑት እነ አብዩ ገለታ ወይንም ገላሳ ዲልቦ «አማርኛ አናውቅም» እያሉ በእግሊዝኛ የመናገር ድራማ ሲሰሩ የሚሰሩትን በትክክል የሚያውቁት እነ መለስ ዜናዊ ግን በመንዝ አማርኛ እየተናገሩ የኢሕአዴግን ሠራዊት በሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊትነት አስመዝግበው እነሌንጮን አስፈረሙ።» ሲሉ ጽፈው ነበር።
ባጭሩ ገላሳ ዲልቦ በየዘመኑ ወደ ሥልጣን በሚመጡ አገዛዞች ዙሪያ እየተጠመጠሙ ጠባብ ፍላጎታቸውን ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንጻር የማስፈጽም የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸው ኦነጋውያን መካከል ቀዳሚው ነው። ወያኔና ደርግን ተጠምጥሞ አጋጣሚውን ሁሉ በመጠቀም ጠባብ ፍላጎቱን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አስፈጽሟል። አሁን ግን በፊት አጋጣሚ የነበረው ሰፊ በር ሆኖለት ወደ አገር ቤት ገብቷል።
ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ኦነጋውያን ከኦሮሞ በፊት የአካባቢው ባለቤት የነበሩትን አማሮች ሰፋሪና መጤ በማለት ያን ያህል ጭፍጨፋ በአሶሳ አማሮች ላይ የፈጸሙት የማዕከላዊው መንግሥት መላላቱን ተጠቅመው ፍጹም የሆነውን የአማራ ጥላቻቸውንና የጭካኔ ጥማታቸውን ሊያረኩ እንጂ እንኳን ኦሮምያ የሚሉት አካባቢ ይቅርና አሶሳ ወለጋ ክፍለ አገርም ቢሆን ኦሮሞም የኦሮሞ መሬትም አልነበረም።  «ነፃ አውጭ» ነን ቢሉ እንኳን ነጻ ማውጣት ያለባቸው  ኦሮሞን እንጅ ዛሬ ቤኒሻንጉል የተደረገውን አልነበረም።
ኦነግ ከሻዕብያ ጋር ሆኖ ይህንን የአማራ ጭፍጨፋ በደርግ ዘመን ካካሄደ ከአንድ አመት ከአምስት ወር በኋላ ፋሽስት ወያኔን ተከትሎ አዲስ አበባ በመግባት የመንግሥት ተጋሪ ከሆነ በኋላ  የመንፈስ አባታቸው አባ ጆቢር በፋሽስት ዘመን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት በጠፋበት ዘመን ጀምረውት የነበረውን የአማራ ጭፍጨፋ አጠናክረው ቀጠሉበት። በ1984 ዓ.ም. አርባ ጉጉ ላይ ያህ ሁሉ  አማራ አይኑ  እያየ የፊጥኝ አስረው ወደ ገደል እየተወረወረ  እንዲገደል አደረጉት። እንዲሁም በአርሲ ብዙ  ሺህ አማሮች ተገድለው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለ እንዲሰደዱ ተደርገዋል። ብዙ የአማራ ልጃገረዶች  በኦነግ ወታደሮች ክብረ ንጽሕናቸው ተደፍሯል፤ የቤት እመቤት ባለቤቶች ባሎቻቸው  እየተገደሉ ሴቶቹ መጫዎቻ ሆነዋል። ወጣቶች እንደበግ ተዘቅዝቀው ተሰቅለው ሳይሞቱ  ከነሕይዎታቸው  ቆዳቸው ተገፏል ፤ ብዙ ቤተክርስቲያኖች ተቃጥለዋል፤ በቅዳሴ ላይ የነበሩ ካህናት ሳይቀሩ  አማራ የሆኑት ብቻ እየተመረጡ መቅደሱ ውስጥ ታርደዋል።
ሕገ እግዚያብሔርን  ጠብቀው ከዓለማዊ ነገር ርቀው በጾም በፀሎት ተወስነው በአሰቦች ገዳይ ይኖሩ የነበሩ 17 መነኮሳት የሰሩት ኃጢያት ሳይኖር አማራ በመሆናቸው ብቻ በኦነግ ነፍሰበላ ወታደሮች እጅ ተሰይፈዋል። እንዲሁም ወለጋ ውስጥ አንፊሎ ወረዳ በ1984 ዓ.ም.  627 አማሮች በኦነግ እጅ እንደተገደሉና ገዳዮችም እንዳልተያዙ መጋቢት 12 ቀን 199 ዓ.ም. ታትሞ የወጣው የአንድነት ጋዜጣ ያስረዳል።
ሌላው ኦነግ ከወያኔ ጋር የሽግግር መንግሥት ተብዮው አካል እንደሆነ ያደረገው ነገር ቢኖር ኦሮምያ በሚል በተፈጠረው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ልጆች በላቲን ፊደል በኦሮምኛ ቋንቋ ብቻ ካልሆነ አትማሩም ተብለው ከትምህርት ርቀው እንዲቀመጡ ማድረጉ ነው።
ይቀጥላል…
Filed in: Amharic