>

ለኛስ የብሄር-ብሄረግዚት መፍትሄ ማን ያምጣልን...? (አሰፋ ሃይሉ)

ለኛስ የብሄር-ብሄረግዚት መፍትሄ ማን ያምጣልን…?

 

 

አሰፋ ሃይሉ
* .. “ለእኛስ የብሄር-ብሄረግዚት መፍትሄ ማን ያምጣልን? …እኛስ ኢትዮጵያውያን መቼ ይሆን ከገባንበት የ”ብሄር-ብሄረሰቦች” ቅርቃር ወጥተን፣ የብሄርን ጉዳይ ለባህል ሚ/ር ሰጥተን፣ ፖለቲካችንን፣ ሀገራችንን፣ ሕዝባችንን፣ ኢኮኖሚያችንን፣ ዕውቀታችንን፣ ትውልዳችንን፣ ሰው-ነትን የተራበ ሁለነገራችንን ነፃ የምናወጣው? መቼ? መቼ?!!! 
እኛ ስለ ብሄር ብሄረሰብ ስንነታረክ ዓለም ጥሎን ነጎደ። ኢትዮጵያዊነታችንን ይዘን ያመለጠን ዓለም ላይ ለመድረስ መሮጥ ሲኖርብን በኋላቀር ኃይሎች ተይዘናል። የብሄር ብሄረሰቦች ኋላቀር አገዛዝ ለኢትዮጵያውያን ያተረፈልን ነገር የውርደት ክብረወሰኖችን ብቻ ነው።
ጎሰኛው ኋላቀር የብሄር ብሄረሰቦች ፖለቲካል ኢኮኖሚያችን ያተረፈልን ነገር፦ በኢኮኖሚ የተንኮታኮተች፣ በልመና አንደኛ የወጣች፣ በድንቁርና ተወዳዳሪ ያልተገኘለት አረመኔ ትውልድ ያፈራች፣ ሙስና እንደጉድ የተንሰራፋባት፣ ሕግና ሥርዓት ያልተረጋገጠባት፣ የውርጋጦች መፈንጫ የሆነች ኢትዮጵያን ነው።
የጎሣ ሕገመንግሥቱ የተከለው ኋላቀር የጎሰኞች ሥርዓት የተጠጉትንና የተጠለልንበትን ዜጎች ሁሉ – ሀገራችንንና ሕዝባችንን ጭምር ይዞ – ወደ መድረሻ አልባ የውድቀትና የውርደት ጥልቅ እንጦረጦስ ስቦ የጨመረን እና እየጨመረን ያለ መውጫ ያልተገኘለት የውድቀት ቤርሙዳችን ነው። ከዚህ የውድቀት ቤርሙዳ በጊዜ ካልወጣን ከዘመናዊው ዓለም ተፋተንና ተረስተን መጥፋታችንም ሆነ መጠፋፋታችን የማይቀር የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው የሚሆነው።
መኪናን የፈለሰፈው ኦሮሞ የተባለ ብሄር አይደለም። አውሮፕላንን የፈጠረው ትግሬ የተባለ ጎሣ አይደለም። የነፃገበያ ህግጋትን የነደፈው አማራ የተባለ ነገድ አይደለም። ፖዘቲቭና ኔጌቲቭ ብሎ ኤሌክትሪክን የፈለሰፈው ሲዳማ የተባለ ዘውግ አይደለም። ዲ ኤን ኤን፣ እና አር ኤን ኤን ከሕይወታውያን ውስጥ ፈልጎ ያገኘው አፋር የተባለ ሳይንቲስት አይደለም። ኤክስሬይን የፈለሰፈችው ሀረሪ የተባለች መንደር አይደለችም። ስልክን የፈጠረው ሶማሌ የተባለ ብሄረሰብ አይደለም። ቡታጋዝን የፈለሰፈው ደንጣ ዱባሞ ክችንችላ የተባለ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አይደለም።
የዓለምን ግኝቶች ያገኙት፣ የዓለምን ኢኮኖሚ ያቆሙት፣ የብልፅግናዎች ሁሉ አርኪቴክቶች በዘርና በዘረኝነት ጉዳይ ላይ 24 ሰዓት ተጠምደው ሕዝባቸውን ሥራ ያስፈቱ ብሔር ብሔረሰቦች ወይም የብሔር ብሔረሰቦች የተወካዮች ምክርቤቶች አይደሉም።
የዓለምን ግኝቶችና ፈጠራዎች ሁሉ ያገኙት፣ ዓለምን ያዘመኑት፣ የሰውን ልጅ ህይወት ያቀለሉት፣ በኢኮኖሚ ያበለፀጉት፣ የስነጥበብ ሥልጣኔን ማማ ያስረገጡት… በሚያምኑበት ታላቅ ነገር ላይ ተሠማርተው የራሳቸውንና የወገናቸውን አኗኗር ወደ ተሻለ ሕይወት፣ ወደ ተሻለ ዓለም ለማሸጋገር ቆርጠው የተነሱ፣ ለዚያም ታላቅን መስዋዕት የከፈሉና ለመክፈል የተዘጋጁ – ከዘርና ከጎሳ በላይ የተሻገረ – ታላላቅ ራዕይን የሰነቁ ባለራዕይ፣ ባለተሰጥዖ፣ ባለዕውቀት፣ ባለችሎታ ሰዎች ናቸው።
እነዚያን ሰዎች ለመፍጠር የቻሉት ማን ናቸው? ትምህርት ቤቶችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የትምህርትና ምርምር ተቋሞችን፣ ለዜጎች ሁሉ የተመቹና የዜጎችን ሁሉ የአዕምሮና የጉልበት ኃይል በአንድ ላይ አስማምተው የሚያስተባብሩ ሃርመናይዝድ ሥርዓቶችን ለዜጎቻቸው የዘረጉ፣ ያቋቋሙና ወደነዚያ ለመድረስ የተጉ ሀገሮችና ኃላፊነት የሚሰማቸው የወደፊቱን የሕዝቦች ብልፅግና የሚመለከቱ ሕዝቦች መሪዎች ናቸው።
እኛ ሀገር እነዚያን ዓይነት ሰዎችን እየዋጠ የሚያመክን ብሔር ብሔረሰቦች የተባለ ዜጎችን አምካኝ ወጥመድ፣ እና የብሔር ብሔረሰቦች ሕገመንግሥት የተባለ የድንቁርና አስጠባቂ የሥልጣኔ ቤርሙዳ አለ። ይሄ በጎሣ የተለከፈ ሕገመንግሥትና “ፖለቲካ” ተብሎ ለመጠራትም የማይበቃ ጎሠኛ የፖለቲካ ሥርዓት እስካለ ድረስ ባለንበት መርገጣችን፣ እርስ በርስ መዋደቃችን፣ ደክመን መውደቃችን፣ ከዘመናዊው ዓለም ላንደርስበት ተፋተን መቅረታችን አይቀርልንም።
በዘመናዊው ዓለም የሚኖረው አብዛኛው ሀገር ያለማቋረጥ የዛሬ ዜጎቹንና የነገ ትውልዶቹን ለተሻለ ዓለም የሚያዘጋጅበትን የተሻለ የምርታማነትና የብልፅግና መንገድ በማፈላለግ ላይ ተጠምዷል። እኛ ደግሞ ብሔር ብሔረሰቦችን በማይክሮስኮፕ እያፈላለግን የዛሬ ዜጎቻችንንና የነገ ትውልዶቻችንን በቆፈርነው የብሔር ብሄረሰብ ቤርሙዳ ውስጥ አስገብተን ከዓለም በተቃራኒው በተዘረጋ የኋላቀርነት አቅጣጫ የምንቀረቅርበትን የጎሣ ወጥመዶች በማፈላለግና በመዘርጋት ላይ ተጠምደናል።
ከዚህ የሱሳይድ የኋልዮሽ ጉዟችን ካልወጣን፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወስነን ከእነዚህ ኋላቀር ጎሰኞችና ሥርዓታቸው በቻልነው አቅምና ፍጥነት ታግለን ለመገላገል ካልቻልን ውጤቱ ግልፅ ነው። ሁላችንም በሀገር ደረጃ በገባንበት የብሄር ብሄረሰቦች ቅርቃር ውስጥ እንደተከረቸመብን ወደማይቀረው ውድቀታችን – ከነትውልዳችን – ማዝገማችንን እንቀጥላለን። ጊዜው ታግሎ ከእስራት የመውጫ ጊዜ ነው። አሊያ ግን ጊዜው የሞት ሞት ነው።
እያልኩ የባጡን የቆጡን አሰብኩ። አሰብኩ። አሰብኩ። አሰብኩ። እና ምን አመጣሁ። ምንም። ሽበት ብቻ። ራስ ምታት ብቻ። የጨጓራ መላጥ ብቻ።
አሁን የBrexit ዜና ቲቪውን አጣቦታል። “ዩኬ ከአውሮፓ ኅብረት ወጣች”። ወጣች? ኦኬይ! ይቅናታ እንግዲህ… ሌላ ምን ይባላል??
በአዕምሮዬ… “ለእኛስ የብሄር-ብሄረግዚት መፍትሄ ማን ያምጣልን? …እኛስ ኢትዮጵያውያን መቼ ይሆን ከገባንበት የ”ብሄር-ብሄረሰቦች” ቅርቃር ወጥተን፣ የብሄርን ጉዳይ ለባህል ሚ/ር ሰጥተን፣ ፖለቲካችንን፣ ሀገራችንን፣ ሕዝባችንን፣ ኢኮኖሚያችንን፣ ዕውቀታችንን፣ ትውልዳችንን፣ ሰው-ነትን የተራበ ሁለነገራችንን ነፃ የምናወጣው? መቼ? መቼ?!!! እያልኩ እየመላለስኩ አሰብኩ።
ምኞቴ አይከለከልም። ተስፋዬ አይሟጠጥም። ትግሌ አይሞትም። አንድ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ – ሁላችንም በያለንበት – የቤር-ቤረሰብ ቤርሙዳችንን ሰብረን እንደሚያስብ ባለሙሉ ፀጋ ሰው ነፃ እንወጣለን። አንድ ቀን አይቀርም።
ድሮ በልጅነቴ የሰፈሬ ልጆች ተሰብስበን በልጅነት ቀጫጭን አንጀት የሚበላ ድምፃችን የምናቀነቅነው እንዲህ የሚል የህፃናት መዝሙር ነበር፦
“አሞራ በሠማይ፣ ጦጢት በዛፍ ላይ፥
አምላክ አትግደለኝ፣ ኮሌጅን ሳላይ…”
እውነትም ፈጣሪ ልመናችንን ሳይረሳ የሰፈሬን ልጆች ሁሉ ኮሌጅን አሳየን። አንድም አልቀረ። አሁንም – በዚያ ነገን በሚያውቀው የልጅነቴ አምላክ እመካለሁ። ኢትዮጵያውያን ከጎሣ ቀንበር ነፃ ወጥተን በነፃ አዕምሮ ለግላችን፣ ለቤተሰባችን፣ ለሀገራችን፣ ለትውልዳችን ብልፅግና የምንገሰግስበትን ያን ቀን በዕድሜዬ አየዋለሁ። ማለት ፈለግኩ። አልቻልኩም። አበቃሁ። “ተናነቀኝ እንባ። ተናነቀኝ።” (- ቴዎድሮስ ካሳሁን)
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ።
(እና ጠላቶቿን በፊታችን ያንበርክክ።😁)
የተሻለ ጊዜ ያምጣልን።
Filed in: Amharic