>
3:55 am - Tuesday May 24, 2022

በወለጋ የሚታየው ችግር የተፈጠረው እንዴት ነው!!! (አፈንዲ ሙተቂ)

በወለጋ የሚታየው ችግር የተፈጠረው እንዴት ነው!!!

 አፈንዲ ሙተቂ
ዶ/ር ዐቢይ ለፓርላማ በሰጠው ማብራሪያ “የወለጋው ግጭት በኦሮሞና በአማራ መካከል ያለውን መካረር ወደ ጫፍ የሚያደርስ ነው” ሲል ሰማሁት፡፡ እነ ማን ናቸው በወለጋ እየተጋጩ ያሉት? ችግሩስ የተፈጠረው እንዴት ነው? እውነቱን ለማያውቁት እውነቱን እንደሚከተለው እናስረዳለን፡፡
የኦነግ ጦር ለረጅም ጊዜ በወለጋ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚያ የሚንቀሳቀሰው ጦር ታሪኩ የሚጀምረው በ1972 ኦነግ በወለጋ የምዕራብ እዙን በከፈተበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በአካባቢው የኦነግ ጦር አለ፡፡ ይህ ጦር እንደ ሁኔታው ሲበዛ እና ሲያንስ ነበር፡፡ የሚቆጣጠረው አካባቢም አንዳንዴ ይሰፋል፤ አንዳንዴ ያንሳል፡፡ ሆኖም የኦነግ ጦር ለአርባ ዓመታት ያህል ከአካባቢው ጠፍቶ አያውቅም፡፡ በተለይም ከ1981-1983 እንዲሁም ከ1985-1987 ባሉት ዘመናት ከበድ ያሉ ውጊያዎች በአካባቢው ተካሂደው ነበር፡፡ በዚያ ዘመን በአካባቢው ሲንቀሳቀስ የነበረውን የኦነግ ጦር ሲመሩ የነበሩት አሁን የኦነግ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኦቦ ዳውድ ኢብሳ እና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኦነግ የፖሊት ቢሮ የነበሩት አባ-ጫላ ለታ ነበሩ፡፡
በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ደግሞ የኢህአዴግ  መንግሥት በ2001 ለገሰ ወጊ የሚባለውን የኦነግ ጦር መሪ አድኖ ለመያዝ  በርካታ ቁጥር ያለው ሠራዊት በአካባቢው አዝምቶ እንደነበረ እናስታውሳለን (ኢቴቪ “የሳራ በረሃ ሚስጢር” በሚል ርእስ የሰራውን ዶክመንተሪ ያስታውሱ)፡፡
ከለገሰ ወጊ ሞት በኋላም የኦነግ ጦር ከአካባቢው ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ከ2002 አንስቶ እስከ አሁኗ ዕለት ድረስ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን የኦነግ ጦር የሚመራው ኩምሳ ድሪባ ወይንም “ጃል መሮ” ነው፡፡ ጃል መሮ ጦሩን እየመራ በአካባቢው መንቀሳቀስ ከጀመረ አስር ዓመት ያህል ሆኖታል፡፡
ከዚህ እንደምትረዱት የኦነግ ጦር በአካባቢው መንቀሳቀስ የጀመረው ትናንት አይደለም፡፡ ጦሩ ከጃል መሮ ጋር በድንገት የተፈጠረም አይደለም፡፡ የኦነግ ጦር በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ ኢሉባቦር፣ ምሥራቅ ሀረርጌ፣ ባሌ እና ቦረና ዞኖች በሚገኙት ጫካዎችና ቆላማ መሬቶች ውስጥ ለረጅም ጊዜ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡
—–
የኦነግ ጦር በሀገር ቤት በተንቀሳቀሰባቸው ረጅም ጊዜያት ሁሉ የግንባሩ ዋና ጽ/ቤት በውጪ የሚገኘው በውጪ ሀገራት ነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሃያ ዓመታት ውስጥ የግንባሩ ዋና ጽ/ቤት በሞቃዲሾ እና በካርቱም ይገኝ የነበረ ሲሆን ባለፉት ሃያ ዓመታት ደግሞ ጽ/ቤቱ አስመራ ነው የነበረው፡፡
ታዲያ አንድ ነገር ልብ በሉ፡፡ የኦነግ ጦር በኤርትራ ከጽ/ቤት ባሻገር የማሰልጠኛ ካምፕም ነበረው፡፡ ለሽምቅ ውጊያ የሰለጠኑ ብዙ ተዋጊዎችን ከኤርትራ ወደ ወለጋ አድርሶአል (ለገሰ ወጊ እና ጃል መሮም በኤርትራ ነበር የሰለጠኑት)፡፡
—-
የኦነግ መሪዎች አስመራ ሳሉ ወያኔ ወደቀ፡፡ አዲሱ መንግሥትም ኦነግ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ እንዲንቀሳቀስ ጥሪ አቀረቡለት፡፡ እነርሱም አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ፡፡ በዚህ መሠረት ኦነጎች በአስመራ ያሉትን ስታፎቻቸውን እና በስልጠና ላይ ያሉ ወታደሮቻቸውን በመያዝ ወደ ሀገር ቤት ገቡ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ያልተጠበቁ ነገሮች ተከሰቱ፡፡
የኦነግ አመራር ከአስመራ ወደ ሀገር ቤት ሲገባ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር  የመግባቢያ ሰነድ ብቻ ነው የተለዋወጠው እንጂ አሳሪ የሆነ ስምምነት አልተፈራረመም፡፡ ሁለቱ ወገኖች የቀሩ ጉዳዮችን በሀገር ቤት ከጨረስን በኋላ ፊርማውን በዚያው እንፈራረማለን የሚል ሃሳብ ነበራቸው፡፡ ኦነጎች ወደ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ለኦነግ የገባውን ቃል ክዶ በግንባሩ ላይ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጀመረ፡፡ “ሸኔ ጦርነት ፈላጊ ነው” ከሚለው ተራ ክስ ጀምሮ “ኦነግ አስራ ሰባት ባንክ ዘርፏል” እስከሚለው ግዙፍ የስም ማጥፋት ዘመቻ ድረስ የሄደ የማጠልሸት ተግባር በግንባሩ ላይ ተካሄደ፡፡
መንግሥት በአስመራ የገባውን ቃል ለማጠፍ የተገደደው የኦነግ መሪ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ አያና ወደ ሀገር ቤት በገቡበት ወቅት በህዝቡ በተደረገላቸው ደማቅ የሆነ አቀባበል በመደናገጡ ነው፡፡ ህዝቡ ኦቦ ዳውድን እንደዚያ ወጥቶ የተቀበለው ኦነግም ሆነ መሪው በኦሮሞ የትግል ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ ያላቸው በመሆናቸው ነው፡፡ የአዲሱ ዘመን የኢትዮጵያ መሪዎች ያንን የህዝብ ማዕበል ሲያዩ ግን “ኦነግ ምንም ሳይሰራ በምርጫው ሊያሸንፍ ነው” በማለት በከፍተኛ ፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ ነው የወደቁት፡፡ በኦነግ ላይ የሚሰሩትንም ሸርና ተንኮል የጀመሩት በዚያው ሌሊት ነበር፡፡ እስቲ በጥቂቱ  እናስታውሳቸው፡፡
ከአስመራ የመጣው የኦነግ ጦር መንግሥት ወዳዘጋጀለት ማሰልጠኛ ገብቶ ህገ-መንግሥቱንና ሌሎች የሀገሪቱን ህጎች ካጠና በኋላ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር ይቀላቀላል ተብሎ ነው የታሰበው፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት በዚህ የኦነግ ጦር ላይ አሳፋሪ ግፍ ነበር የፈጸመው፡፡ ከነ ጭራሹም “በጦሩ ውስጥ ትግርኛ የሚናገሩ ሰዎች ተገኝተዋል፤ የወያኔ ጦር ከኦነግ ጋር ተቀላቅሏል” በማለት ርካሽ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አካሄደበት (በኦነግ ውስጥ የተገኙት ትግርኛ ተናጋሪዎች ቋንቋውን የለመዱት በአስመራ ነው፤ ትግርኛ የኤርትራ ብሄራዊ ቋንቋ በመሆኑ እዚያ የኖረ ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ ቋንቋውን ሊለምደው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ቋንቋን መናገር በምን ሂሳብ “ወያኔ” እንደሚያስብል ብልጽግናዎች ብቻ ነው የሚያዉቁት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትግርኛን እየተናገሩ አይደል?)
በወለጋና በጉጂ ያለው የኦነግ ጦር እነዚህ መረጃዎች ሲደርሱት አዲሱ የአብይ መንግሥት ወያኔ በ1984 በኦነግ ላይ የሰራውን ድraማ ለመሥራት እንደተዘጋጀ ተረዳ፡፡ በመሆኑም ወደ ማሰልጠኛ ገብቶ ከመንግሥት የፖሊስ ሃይል ጋር እንደማይቀላቀል አስታወቀ፡፡ አቶ ዳውድ ኢብሳ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰውን ጦር ለማዘዝ እንደሚያስቸግራቸው ለሚዲያ ተናገሩ፡፡ ታዲያ ድራማ መሥራት ወጉ የሆነው የብልጽግና መንግስት የአቶ ዳውድን ቃል በመቆራረጥ “ሸኔ በመንግሥት ላይ ጦርነት አወጀ” በማለት ድራማ መሥራቱን ቀጠለ፡፡ እነ እስክንድር ነጋ በሚያዘጋጁት ፕሬሶችና ኢሳትን በመሳሰሉት ቀጣፊ ሚዲያዎች በኩልም በኦነግ ላይ ከባድ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አካሄደ፡፡
ነገሮች ተካርረው በዚህ ደረጃ ላይ ሳሉ የኦሮሞ አባገዳዎች በሁለቱ ሃይሎች መካከል እርቅ ለመፍጠር እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ እንቅስቃሴው ሰምሮም እርቅ የተፈጠረ መሰለ፡፡ አባገዳዎች የኦነግ ጦርን ተረክበው በአንድ ወር ውስጥ ወደ ካምፕ ለማስገባት የሚችሉ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡ ኦነግ ማስማቱን ገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በቅድሚያ ስምምነቱን ገለጸ፡፡ አባገዳዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሊያነጋግሩ ቤተ መንግሥት ድረስ ሲሄዱ ግን “ከየት መጣችሁ? ለምን መጣችሁ?” የሚላቸውን ሰው ጠፋ፡፡ በመጽሐፍ ምርቃትና በግጥም ምሽት ላይ እየተገኘ ሰውን surprise የሚያደርገው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አባገዳዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን አላነጋግር አለ፡፡ በዚህም በኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አሳፋሪ ነጥብ አስመዘገበ፡፡
ይህንን ሁሉ ከርቀት የሚከታተለው በጃል መሮ የሚመራው የኦነግ ጦር መንግሥት ወደ ካምፕ ካስገባው በኋላ እምሽክ አድርጎ ሊያስወግደው እንደተዘጋጀ ግልጽ ሆነለት፡፡ በዚህም የተነሳ በትጥቅ ትግሉ ለመቀጠል ወሰነ፡፡ በኦቦ ዳውድ የሚመራው የኦነግ የፖለቲካ አመራር ግን ከጦሩ በተለየ ሁኔታ በምርጫው እንደሚሳተፍ አስታወቀ፡፡ መንግሥት በቃሉ ታማኝ ከሆነ በጃል መሮ የሚመራውን ጦር ወደ ሰላም መድረክ ለማምጣት እንደሚጥርም ገለጸ፡፡ መንግሥት ግን ለተፈጠረው ፍጥጫ ፖለቲካዊ መፍትሔ ማፈላለጉን ትቶ በወታደራዊ ዘመቻው ቀጠለ፡፡ ነገር ግን በወታደራዊ ዘመቻውም በለስ ሳይቀናው ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከችግሩ ጋር እየተንገታገተ ነው፡፡ የኦነግን ጦር ማሸነፍ ሲያቅተው ደግሞ ከአንድ ወር ለሚበልጥ ጊዜ በሰላማዊው የወለጋ ህዝባችን ላይ የስልክና የኢንተርኔት ኔትወርክ ዘግቶ ህዝቡን አሳሩን እያሳየ ነው፡፡

ወገን!

ኦሮም የሆነከውና ኦሮሞም ያልሆንከው! 

ከላይ የጻፍኩት ሐሰት ያልተቀላቀለበት እውነት ነው፡፡ ወለጋን ሰንጎ የያዘው ችግር የተፈጠረው ከላይ በተገለጸው መንገድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ሁሉ ሐሰት ነው፡፡ በተለይም ኦሮሞና አማራ ነው የተጣሉት፣ ግጭቱ ሁለቱን ብሄሮች ያባላል” የሚለው ሁሉ ነጭ ውሸት ነው፡፡ በመሆኑም በሚዲያው በሚሰማው ቅጥፈት እንዳትሸወዱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
Filed in: Amharic