>
4:31 pm - Tuesday May 17, 2022

መንግስታዊ ስላቅ የተሞላው ልጅ ጨዋታ!!! (ኩኩ መለኮቴ... ኩኩ..!!) ይሉት አይነት!!! (አሰፋ ሃይሉ)

መንግስታዊ ስላቅ የተሞላው ልጅ ጨዋታ!!!

(ኩኩ መለኮቴ… ኩኩ..!!) ይሉት አይነት!!!

አሰፋ ሃይሉ
አሁን አሁንማ ጠቅላዩ ያስቀኝ ጀምሯል። ሲበዛ የህፃን የመሠለ “እኔ የለሁበትም፣ እሷ ነች፣ እሱ ነው፣…” ስነልቦናውን በአደባባይ እያወጣው። በሀገሪቱ ላሉ ሰዎች፣ ንብረቶችና ለሚፈጠሩ ሁኔታዎች ሁሉ በበላይነት ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለበት የሀገር መሪ ሳይሆን ልክ “ገፋኸኝ፣ ገፋሽኝ” እየተባባለ በመንገድ ዳር እንደሚጨቃጨቅ ግለሰብ ነው አክት የሚያደርገው። እንዴ?!
ባለፈው በተለያዩ ያገሪቱ ክፍሎች ቤተ ክርስትያኖች ሲቃጠሉና ካህናት ሲጨፈጨፉ የአዲስ አበባው የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪ ተብዬዎቹ ጠቅላዩን “የመንግሥቱ አለቃ እርስዎ ነዎትና ኃላፊነቱን ይውሰዱ” ብለው አስተዛዝነው ቢጠይቁት – የጠቅላዩ መልስ አስቂኝ ነበረ፦
“እኔ በየቤተክርስትያኖቹ ሄጄ እሳት አልለኮስኩም፣ እንደ እናንተ እዚሁ ቢሮዬ ተቀምጬ ነው ዜናውን የሰማሁት፣ እና እኔ ሄጄ ባላቃጠልኩት ነገር እንዴት ኃላፊነቱን ውሰድ ትሉኛላችሁ?” የሚል ነበረ መልሱ።
ባለፈው የአማራ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች ለፖለቲካ ዓላማ ሲባል ከወለጋ ደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ነን በሚሉ አሸባሪዎች ሲታገቱ ደግሞ ለጠቅላዩ ተመሳሳይ ጥያቄ ቀረበላቸው፦
“ወላጅ ልጆቹን ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚልከው ለደህንነታቸው መንግሥትን አምኖ ነው፣ እነዚህ ተማሪዎች ለደህንነታቸው ጥበቃ ስላላገኙ ከዩኒቨርሲቲው ለቀው ለመውጣት ተገደዱ፣ በአውቶቡስ እየወጡ ደግሞ በታጠቁ ሰዎች ታገቱ፣ ይሄ መንግሥት ዜጎቹንና ዩኒቨርሲቲዎቹን የመጠበቅ ኃላፊነቱን ስላልተወጣ በልጆቻችን ላይ የደረሰ ድርጊት ነውና፣ እርስዎ እንደ መንግሥት አለቃ ኃላፊነቱን ይውሰዱ” የሚል ጥያቄ።
የጠቅላዩ መልስ በሳቅ ያፈርሳል (አሊያ ግን በሀዘን ልብ ይሰብራል)፣ የጠቅላዩ ምላሽ ይህ ነበር፦
“እኔኮ ብዙ ሥራ፣ ብዙ ኃላፊነት ያለብኝ ሰው ነኝ፣ በየመንደሩ እየዞርኩ ሰዎችን ከጠለፋ የማስጥል የሰፈር ሚሊሺያ አይደለሁም፣ እና እንዴት ኃላፊነቱን ውሰድ ትሉኛላችሁ?”
ሰሞኑን ደግሞ አንዲት ማንበብ የተሳናት የ100 ፐርሰንቱ ፓርላማ አባል ጠቅላዩን እየጠየቀችው ነው፣ ወደ ትግራይ (አክሱም መሠለኝ) ለኢንቬስትመንት የመጣ የቻይና ባለሀብት ሆነ ተብሎ ከመጓጓዣ አውሮፕላኑ ሳይወርድ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ተደርጓል በሚል። እና ጠቅላዩን ትጠይቃለች እንዲህ የሚመስል ጥያቄ፦
“እርስዎ በሚመሩት መንግሥት ተቋሞችና ባለሥልጣንዎችዎ ስለተፈፀመው ስለዚህ ድርጊት ምላሽዎ ምንድነው? (በእርስዎ ኃላፊነት ሥር ለተፈፀሙ ድርጊቶች ተጠያቂነዎን አምነው ይቀበላሉ ወይ? ለወደፊቱስ ተመሣሣይ ድርጊት ላለመፈጸሙ ምን ዋስትና አለን?)” የመሠለ ጥያቄ አቀረበች።
ጥያቄው ከማንም ይምጣ – ፋክቶቹ እውነት ከሆኑ – ለተገቢው የመንግሥት የበላይ ሹም የቀረበ ተገቢ ጥያቄ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። የጠቅላዩ መልስ ግን ምን የሚል ነበረ? አስገራሚም አስቂኝም፦
“እኔ በአካል ሄጄ ጉምሩክን ወይም ሌላ መሥሪያ ቤትን አልቆጣጠርም፣ የሚያዝበት ባለሥልጣን እንጂ እኔ አልጠየቅበትም፣ ማናቸውንም ባለሥልጣን ጠርታችሁ ማብራሪያ መጠየቅ ስለምትችሉ፣ ያን አደረገ የተባለውን ባለሥልጣን እዚህ ፓርላማ ጠርታችሁ መጠየቅ ነው!” (የሚል እኔን ለቀቅ፣ ሰውዬሽን ጠበቅ!” ዓይነት ምላሽ!!)
እንዴ!!?? ይሄ “እኔ የለሁበትም” የሚሉት የጠቅላዩ የህፃን ልጅ ፈሊጥ እንዴት እንዴት ነው ግን ከሀገር መሪ አፍ እንዲህ ሳትም ሳያደርገው በቀላሉ የሚንበለበለው??? በእውነት አስቂኝ ነው። ሀገር ኃላፊነትን በሚሸሹ ልምጥምጦችና ቃላባዮች እጅ ስትወድቅ ግን አያስቅም። ግራ ያጋባል። ያስደነግጣል።
ባለፈው ሰሞን ጠቅላዩ በሊቀመንበርነት የሚመራው ኦህዴድ የተባለ ፓርቲ “በህገመንግሥቱ አንደራደርም፣ አንቀፅ 39 ለኦዲፒ የህልውና ጉዳይ ነው!” ብሎ የፓርቲውን አቋም ሲገልፅ አንድ ጋዜጠኛ ይጠይቀዋል ጠቅላዩን በሊቀመንበርነት ስለሚመራው ፓርቲ ወቅታዊ አቋም እንዲያስረዳው። የጠቅላዩ መልስ ምንድን ነበር? እንዲህ የሚል፦
“እኔ በስብሰባው ላይ አልነበርኩም፣ ስለጉዳዩም በግሌ የደረሰኝ ነገር የለም፣ ምናልባት እነ ለማን (እነ ለማ መገርሳን) ብትጠይቅ ስለጉዳዩ ሊነግሩህ ይችላሉ!” (እንዴ?! ኧረ በተሰቀለው!? ዋት ኧ ሼም!! የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነህ፣ በድርጅቱ ሰነዶች ላይ እየፈረምክ፣ ማኅተም እያሳረፍክ፣ እየወከልክ፣ እየመራህ – ይሄን የሚያህልን ሀገራዊ አጀንዳ ተወያይቶ፣ አፅድቆ፣ ለሕዝብ ይፋ ሲያደርግ… “እኔ የለሁበትም፣ እነ እገሌን ጠይቃቸው!” እንዴት ይባላል??! 🙂
በነገራችን ላይ ይኼው ህፃኑ ጠቅላይ እኮ ነው ባለፈው በለገጣፎ፣ በሱሉልታ፣ በሰንዳፋ፣ በሰበታ፣ እና በሌሎችም በአዲስ አበባ አፍንጫ ሥር ባሉ አካባቢዎች የኦህዴድ ባለሥልጣናት ዘር እየለዩ ዜጎችን ሲያፈናቅሉና የመኖሪያ ቤት በላያቸው ላይ ሲያፈርሱ፦ “እኔ ከተማን አላስተዳድርም፣ የማውቀው ነገር የለም፣ ሥልጣኔም አይደለም፣ በከተማ ጉዳይም ጣልቃ መግባት አልችልም!” ያለው ፍጥጥ ብሎ። (የእውነቴንኮ ነው… ግን የዚህ ሰውዬ ኩኩ መለኮቴዎች የጤና ናቸው ግን??!!)
ብቻ በቃ የጠቅላዩ “ኩኩ መለኮቴ”ዎች ማለቂያ የላቸውም። ኩኩ – ይሄ በሰው ማላከክና ከደሙ ንፁህ ነኝ – እኔን አያገባኝም ኩኩ መለኮቴው – አመል ሆኖበታል መሠለኝ። ወይ አመል፣ ወይ ድርቅና፣ ወይ ጨዋነት፣ ወይ ልጅነት፣ አሊያም ጅልነት ካልሆነ እንግዲህ ሌላ ምን ይሆናል?? በበኩሌ የጤና አይመስለኝም።
ሁሌ የሆነ ቁሻሻ የነካካትን ነገር (እንትን እንትኗን ሁሉ) በሰው መላከክ ነው። እኔ ምን ላድርግ? ነው። እኔ እሳት ይዤ አልለኮስኩም ነው። እኔ አልገደልኩም። እኔ አላረድኩም። እኔ አላፈናቀልኩም። እኔ አላገትኩም። ኩኩ ብቻ። እንደ ጮርቃ ህፃን። እንደ ሀገር መሪ ኃላፊነትን መውሰድና አልቲሜት ተጠያቂነትን መቀበል የምትባል ነገር በውስን መዝገበ ቃላቱ ውስጥ የለችም። አያውቃትም። አልለመደበትም።
ይገርማል ግን እንዲህ ዓይነቱ የኩኩ መለኮቴ የህፃን ልጅ ጨዋታ በሀገር መሪ በአደባባይ ሲጨወት (“ሲጨወት” የሚል ቃል አለ ይሆን ለመሆኑ?!! ምናባቴ ልሁን? ቢቸግር እኮ ነው!!)
ስላለፈው ሥርዓት ሲኮንንና ሲያሸሙር ራሱ በአቋም፣ በብሄርና በጎሣ እየተለዩ የኮምፒዩተር ሰላዮችና ጆሮ ጠቢዎች የሚመለመሉበትን የወያኔ/ኢህአዴግን በስይጥይናው የተሻሻለ የደህንነት መሥሪያ ቤት (ኢንሳን) የመለመለ፣ ያዋቀረና የመራ የወያኔ ክፉ ጆሮ ጠቢ እንደነበረ ራሱ እኮ ትዝም አይለውም። ረስቶታል። ወይም እንደልማዱ “ኩኩ መለኮቴ” ብሎ በሆነ አካል አላክኮታል። በጌች (ማለቴ በጌታቸው አሰፋ!!)
/እንዲህ ዓይነት ሎንግ ሜምሪውን ያጣ ሰው – እውነትም የታደለ ደስተኛ ሰው መሆን አለበት! – እንደ ህፃናት ! (ኧረ በዚህ አያያዙ ኪዱ የምድሩን መንግሥት ብቻ ሳይሆን… መንግሥተ ሠማይንም መውረሱ አይቀርም?!! ኧረ ያርግለት!! ደሞ በሠማዩ ምን አግብቶኝ? ምን ጥልቅ?!)/
“ጥሬ ጨዋዎች” በምትለው የደበበ ሰይፉ ቆየት ያለች ልብ-አርስ ግጥም ተለየሁ። መታሰቢያነቷ ለሀገሬ ኩኩ መለኮቴዎች በሙሉ ይሁንልኝ!! ፈጣሪ የሚበጀውን ያምጣልን። መልካም ጊዜ።

ጥሬ ጨዋዎች

መስለውኝ ነበረ ፣
የበቁ የነቁ
ያወቁ የረቀቁ
የሰው ፍጡሮች ፣
ለካ እነሱ ናቸው ፣
ጥሬ ጨው..ጥሬ ጨው
ጥሬ ጨዋዎች ፣
መፈጨት-መሰለቅ-መደለዝ-መወቀጥ-
መታሸት-መቀየጥ
ገና እሚቀራቸው ፣
“እኔ የለሁበትም!”
ዘወትር ቋንቋቸው ።
( ደበበ ሰይፉ)
Filed in: Amharic