የፖለቲካ መርሐግብርን ማስተዋወቅ ወይስ ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ተልእኮ ?!?
ማኅበረ ቅዱሳን
* የከፋውና አደገኛው ሴራ ቤተ ክርስቲያንን በዘር የመከፋፈል ተልእኮ!!!
ትውልድን ለማነፅ፣ አገርን በሥነ ብዕልም ሆነ በዕውቀት ለማበልጸግ፣ ሰላምን እና ፍቅርን ለማስፈን የፖለቲካ መርሐ ግብር አውጥቶ ለ አገሩ ዜጋ እና ለደጋፊዎቹ ለማስተዋወቅ የሚነሣ የፖለቲካ ፓርቲ አስቀድሞ ራሱን መሠረታዊ ለሆኑ መርሖች ተገዥ ማድረግ ይጠበቅበታል። ለራሱ ማግኘት የሚፈልገውን ሥልጣንም ሆነ ማንኛውም ሰብአዊ መብት ነገር በአሳብ ተወዳድሮ በማሸነፍ እንጂ የሌሎችን መብት ረግጦ እና አማራጭ አሳጥቶ ለማሟላት በሞከር እንደሌለበት መረዳትይኖርበታል። የሌሎችን መብት ረግጦ የራሱን አሳብ ብቻ እንዲቀበሉት የሚያስገድደው በምርጫ እወዳደራለሁ ብሎ ሜዳ የገባ ፓርቲ ሳይሆን ሁሉን በኃይል እና በጉልበት ጸጥ ለጥ አድርጎ መግዛት የለመደ አምባገነን ብቻ ነው። ራሱ ጥፋት እየፈጸመ ሌሎችን አጥፍተዋል ብሎ መተቸት፣ ራሱ ታሪክ እያዛባ ሌሎችን አዛብተዋል ብሎ መክሰስ፣ ራሱ ያልተጻፈ እያነበበ ሌሎችን ማብጠልጠል በእምነት በሥነምግባራዊ ሕግጋትም ተቀባይነት የለውም፤ አገራችን በምትመራበት ሕግም ተጠያቂ ያደርጋል።
ነፃ ውድድር
እንዲህ አይነቱ አሳብ ተቀባይነት የማያገኝበት ምክንያት ለሕዝብ አስተዳደር(ዲሞክራሲ) ተገዥ ነኝ ብሎ ራሱን ገበያ ያወጣ በመሆኑ በጀመረው መንገድ ዳር መድረስ እንጂ የተለየ አሳብ እና እምነት ያላቸውን ሁሉ በግዴታ፣ በማስፈራራት እና በዛቻ ከውድድር ሜዳ እንዲጠፉ ማድረግ የሥልጡንነት መገለጫ ሳይሆን በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እና በሌሎችም እንደምናየው የአምባገነኖች እና የጭፍን አክራሪዎች ተግባር በመሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ግፍን እና በደልን እቃወማለሁ በማለት እየማለ እና እየተገዘተ የሌሎችን መብት መግፈፍ የዲሞክራሲ ፅንሰ አሳብ ስለማይፈቅድ ነው።ለሕዝብ አስተዳደር መርሕ የሚገዛ መሆኑን በተግባር ካልገለጠው ሌሎችን የመበደል እና የማጥፋት መንገድን የመረጠ መሆኑን ስለሚያመለክት ነው። የሕዝብ አስተዳደርን ባሕርይ የተረዱ የተማሩ ሰዎች ስብስብ እንዳለው ስለሚታሰብ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ዓለም ከደረሰችበት የሥነ ሀብት፣ የአስተዳደር፣ የቴክኖሎጂ፣ በሰላም አብሮ የመኖር መርሕ ይገነዘባል ተብሎ በሚታሰብበት በዚህ ዘመን ላይመርጠኝይችላል ብሎ የሚጠረጥረውንሕዝብ ማሳቀቅ እና ማሳደድ ተቀባይነት ስለማይኖረው ነው።
አገር የመምራት ኃላፊነት
በምርጫ ተወዳድሬ በማሸነፍ አገር እመራለሁ ብሎ ኃላፊነት ለመውሰድ የሚዘጋጅ የፖለቲካ ቡድን ከሌሎች የሚሻልበትን የፖለቲካ መርሐ ግብር በማውጣት በአሳብ ልቆ ለመገኘት እንጂ በመጀመሪያው ዙር ከጨዋታ ውጭ የሚሆንበትን የመከፋፈል እና አንዱን አቅርቦ ሌላውን የማግለልተግባር ከፈጸመ ስሕተቱን የፈጸመው እና የሕዝብ አስተዳደርን መርሕ ያፈረሰው ራሱ በመሆኑ ለውድቀቱ ሌሎችን ተጠያቂ ሊያደርግ አይችልም።
ሁሉን አውቃለሁ ማለት፣ ታሪክን ለራስ ዓላማ እንዲመች አድርጎ ካለቦታው በመጥቀስ አዛብቶ እና አጣሞ መተርጎም ያስተቻል እንጂ አያስመሰግንም። እንዲህ አይነት ተግባር መፈጸምም የሰበሰቡትን አካል አያውቅም ብሎ ማታለል ወይም መናቅ ነው። ተበደልኩ እያለ ሲጮኽ የኖረ አካል ለውድድር ሜዳ ስለገባ ብቻ ያሸነፈ መስሎት ከአምባ ገነኖች የከፋ አገር የሚያፈርስ ተግባር ከፈጸመ አሸናፊ የሚሆነው በዚህኛው የመሮጫ ሜዳ ሳይሆን በሌላ መንገድ ነው። እንዲህ ያሰበ አካል የመሮጫ ሜዳውን እና አሰላለፉን ማስተካከል ይኖርበታል እንጂ ሲመቸኝ በማንኪያ ሳይመቸኝ በእጄ አይነት አካሔድ አሁን ለተሰለፈበት ሜዳ አይሠራም። ይህም ለፖለቲከኞች ይጠፋቸዋል ብለን ሳይሆን የአዋቂ አጥፊ እየሆኑ ትውልድን የሚጎዳ ተግባር እየፈጸሙ በመሆኑ ነው። መድረክ ተገኘ ተብሎም ከሚሲዮናውያን እና ከግብረ አበሮቻቸው ሲጋቱት የኖሩትን የሐሰት ትርክት በየዋሑ ሕዝብ ላይ እውነት አስመስሎ ማስተጋባት ነውርም ወንጀልም ነው። እንዲህ ማድረግ አንድም በሕግ ያስጠይቃል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሞራል ዝቅጠትንም ያስከትላል።
የምሁራን ሚና
ዜጎች በዚህ ዓለም በውጣ ውረድ ሲኖሩ ለሚበጃቸውም ሆነ እንወርሰዋለን ለሚሉት ዘለዓለማዊ መንግሥት አብነት ወስደው የሚማሩት ከሃይማኖት ተቋማት እና ከሃይማኖት መምህራን ብቻ ሳይሆን ከምሁራንም ጭምር መሆኑ መታወቅ አለበት። ምሑራን፣ አስተዋይ ሰዎች እና የአገር ሽማግሌዋች አገር ጸንታ የምትቆምበትየማንነት ዐምድ እና ትውፊታዊ ዕውቀት ማኀደሮች ናቸው። ትውልድ ያንፃሉ በማለት አገራችን ያስተማረቻቸው ምሁራን የጥፋት መልእክተኛ ፣ ያስታርቃሉ የተባሉ ሽማግሌች ለብጥብጥ ምክንያት ከሆኑ እና ከመከራ እንዲታደጓቸው የተጠለሉባቸውን ለገዳዮች አሳልፈው ከሰጡ “ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡ፣ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ” የተባለው የአበው ብሂል በተግባር መፈሙ ነው። “ቅዳሴ ቢያልቅበት፣ ቀረርቶ ሞላበት” ተብሎ የተነገረው የሚፈጸው አንድን ጉዳይ ካለ ቦታው አምጥተው ሲደነጉሩት ነው። ንግግር ለማድረግ ሕዝብ ፊት የሚቀርብ ሰው አሳማኝ የሆነ አሳብ ይዞ መቅረብ አለመቅረቡን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ሊናገረው ያሰበው በአድማጩ ሕዝብ ባህል ቅቡልነት ያለው መሆን አለመሆኑንም መመርመር ይኖርበታል።
ሰሞኑን ኦፌኮ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በገብረ ጉራቻ እና በፍቼ ሰላሌ ለደጋፊዎቹ ራሱን የሚያስተዋውቅበት ንግግር ማድረጉ የሚታወቅ ነው። ንግግር ማድረጉ በራሱ ስሕተትም፣ ነውርም ባይሆንም ስሕተት እና ነውር የሚያደርገው የሚነገረው ጉዳይ ነው። እንዲህ ላለው ነገር “ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፉ የገባው ሳይሆን ካፉ የወጣው ነው” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ ተነግሮበታል። የተናገሩት ጉዳይ ይሰብራል፤ይጠግናልም፤ያድናል ይገድላልም።ለሚናገሩት ጥንቃቄ ማድረግ ነገ አገር ለመምራት ብቃት አለኝ ከሚል የተማረ አካል የሚጠበቅ ምግባር ነው። በመንግሥተ ሕዝብ ተወዳድሮ ለማሸነፍ የተሰለፈ አካልም መወዳደር አለብኝ ብሎ የሚነሣው አጠገቡ ካለው ደካማ ወይም ዕድሉን ሳይጠቀምበት ካለፈው አካል ጋር ሳይሆን ሕያው ሆኖ ሌሎች አርአያነቱን ለመከተል ከሚቀኑበት አካል ጋር መሆን ይኖርበታል።
ኦፌኮ በየመድረኩ ያደረገው ንግግር የፖለቲካ መርሐግብሩን ከማስተዋወቅ ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን አዎንታዊ አስተዋጽዖ ከማጠልሸት እና ክርስቲያኖችን በገዛ አገራቸው የስደተኝነት ስሜት እንዲያድርባቸው ከማድረግ ላይ ያተኮረ ነበር። ኦፌኮ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ ባደረገው የመተዋወቂያ ንግግር ወቅት አንደኛው ተናጋሪ በሐረር ስታዲየም የፖለቲካ ጥበብ የገባቸው የእምነት አባቶች አሉአችሁ፣ ለኦሮሞ ኦርቶዶክሶች አባት ቀሲስ በላይ አለላችሁ ለሙስሊሙ ደግሞ አገሌ” ብለዋል። ኦፌኮ ለተባለው የፖለቲካ ፓርቲ መቅረብ ያለበት የመጀመሪያው ጥያቄ የተናገሩት ጉዳይ ከፖለቲካ መርሐ ግብራቸው ጋር ምን ግንኙነት አለውየሚል ነው። ሐዋርያዊ እና ቀኖናዊ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ከቀኖና ውጭ የሆነ ተግባር እንዲፈጽሙ ሥልጣን የሰጣቸው ማን ነው? ይህ ንግግር ድፍረትም፣ ወንጀልም መሆኑን እንዲያውቁልን እንፈልጋለን።
ቤተ ክርስቲያንን በዘር የመከፋፈል ተልእኮ
ሐዋርያዊት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በዘር ለመከፋፈል የፈለጉት በራሳቸው የማይተማመኑ በመሆኑ ሕዝብን ለመከፋፈል እና የተወሰነም ቢሆን ደጋፊ ለማግኘት ይጠቅመናል ብለው ነው።እንዲህ አይነቱ ተግባር ራሳቸው ሲሠሩበት የኖሩት የፖለቲከኞች ቁማር እንጂ የቤተ ክርስቲያን ባሕርይዋ አለመሆኑን ተናጋሪው ሊረዱት ይገባል። የኦሮሞ ቤተ ክህነት እያለ ራሱን በራሱ በመሾም የሚንቀሳቀሰው አካል ከጀርባው ፖለቲካ እየዘወረው መሆኑን በግልጽ መናገር ብቻ ሳይሆን ማን እያንቀሳቀሰው እንደሆነ ጭምር ነግረውናል።
ኦፌኮ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ ለኦሮምኛ ቋንቋተናጋሪ ክርስቲያኖች እንደማይገደው ከተናጋሪዎቹ ንግግር መረዳት ይቻላል። ምክንያቱም ፓርቲው የሚፈልገው የክርስቲያኑን መብት ለማስከበር ሳይሆን ለክርስቲያኖች ፓርቲው የመረጠላቸውን እና ለምእመናን ሳይሆን ለራሱ የሚመቸውን ቤተ ክርስቲያን የመሰለ ድርጅት ሊፈጥርላቸው እየሠራ መሆኑን ያሳያል። መብቱን ለማስከበር ቆሜለታለሁ የሚሉትን ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክርስቲያን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቀኖና መሠረት ሐዋርያዊ ትውፊቱን እንደጠበቀ በየትም ቦታ እየኖረ አምልኮቱን በመፈጸም የመንግሥተ እግዚአብሔር ውራሽ የመሆን መብቱን እየተጋፉ እና እኔ አውቅልሃለሁ እያሉት መሆኑ መታወቅ አለበት።
ኦሮምኛ ቋንቋውን መናገር የሚችል ሰው ሁሉ ሀብት እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ከመሬት ተነሥተው በቦታ በመወሰን ክርስቲያኖችን ሰው ከመሆን ዝቅ የሚያደርግ፣ የቤተክርስቲያንን የክርስቶስ አካልነት እና የምእመናን አንድነት የሚያሳጣ ኢሰብአዊ ንግግር ነው፡፡ የቋንቋው ተናጋዎች ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠንን አባት ሳይሆን ፖለቲከኞች የሚመርጡልን ይሻለናል አላሉም። እንደዚያ ቢሉ እንኳ አሁን ክልሉን እየመራ ያለው ኦዲፒ በመሆኑ መናገር የነበረበት እሱ ነበር። በስውር የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የመከፋፈል አጀንዳ ይዘው አብረው እንደሚሠሩ ካልነገሩን በስተቀር።
ለክልሉ የሃይማኖት አባት ተብለው በኦፌኮ የተሰየሙት ሰውም የኦዲፒ አባል እና የክልሉ ዕንባ ጠባቂ ኃላፊ በመሆናቸው ቤተክርስቲያን የጣለችብዎትን ኃላፊነት እየተወጡ ባለመሆኑ ወደ ድርጅትዎ ይጠቃለሉ ስለተባሉ በቤተ ክህነት መሥራት አልችል ብለው ያጡትን አባትነት ከፖለቲከኞች አገኘዋለሁ ማለታቸው የሚያስገርም ነው። ከፓርቲው አባት ነዎት ቢባሉም በግድ ካልተጫነበት በስተቀር ሕዝበ ክርስቲያኑ ሊቀበላቸው እንደማይፈልግ መታወቅ አለበት።
ክርስቲያኖችን ከሐዋርያዊ ትፊት መነጠል
ከሐዋርያዊ ትውፊት የተነጠለች የግለሰቦች ስብስብ ካልመሠረቱ በስተቀር እገሌ ይውጣ እገሌ ደግሞ ይግባ የምትል ቤተ ክርስቲያን የለችም ። ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ሲባል አርባ እና አምሳ ዓመታት ሙሉ የዘር ፖለቲካ እያቀነቀኑ ኦሮምኛ የምንናገረውን ከሌላው ክርስቲያን ወገናችን ለመነጠል መድከም ክርስቲያኖችን በዘረኝነት በሽታ አጠውልጎ ከእውነተኛው የወይን ግንድ ከክርስቶስ ቅርንጫፍነት ለይቶ ለማድረቅ የሚደረግ ድካም ይሆናል፡፡ የክርስቲያኖች መመሪያ ዮሐ. ፩፣፲፪-፲፫ “፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ እና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም” የሚለው የማይሻረው የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ከወንድ እና ከሴት ፈቃድ በመወለዳችን በተፈጥሮ ልደት ያገኘነውን ብሔራችንን ከእምነታችን ከማኅፀነ ዮርዳኖስ፣ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከሥላሴ የተገኘንባትን ዘለዓለማዊ ሕይወት ካገኘንባጽ ቤጸ ክርስቲን ሊለዩን በመሆኑ ዓላማቸውን ልንረዳ ይገባልም፡፡ ቋንቋም ክርስትናም ከእግዚአብሔር የተሰጡን እንጂ በፖለቲከኞች አመራጭ ሆነው የሚቀርቡልን አይደሉም፡፡
የኦፌኮ አመራሮች እየፈጸሙ ያሉት ተግባር የኦሮሞ ቤተ ክህነት በማለት ቤተ ክርስቲያንን ለማደከም እና ምእመናንን ለመለያየት በስውር እየሠሩ ያሉት ፖለቲከኞች መሆናቸውን በገሀድ ስለነገሩን እናመሰግናቸዋለን፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጠላት ለይቶ ማወቅ ለክርስቲያኖች በአንድነት ቆሞ ለመከላከል ያስችላልና። “የአቦን ብቅል የበላ ያስለፈልፈዋል” እንዲሉ ፖለቲከኞች በድፍረት እናንተ ብትፈልጉ ባትፈልጉም፣ ብትቀበሉ ባትቀበሉም፣ ሐዋርያዊ ትውፊት ቢሆን ባይሆን ምን አገባችሁ። እኛ እንመርጥላችኋለን እያሉን በመሆኑ በዚህ የፓርቲው ራሱን የማስተዋወቂያ ንግግር ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም አመቺ ጊዜ ሲጠብቁ የኖሩ የሌሎች እምነት ተከታዮችም ደብቀውት የኖሩትን ዓላማ ለማሳካት ያግዘናል መስሏቸው የኦሮሞ ቤተክህነት መቋቋምን እንደግፋለን ማለታቸው ለድኅነታችን አስበው ሳይሆን ለፖለቲካ ግባቸው እንዲያግዛቸው ነው፡፡
ክርስትናን ገፍቶ እስልምናን ማቀፍ
ደግመን የምንጠይቀው እስልምናን ከአገራችን ክርስትናን አዳክሞ እና የክርስትናን አሻራ አጥፍቶ አዲስ የታሪክ አሻራ ለመመሠረት የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ከቤተ ክርስቲያን ላይ እጃቸውን እንዲያነሡ እና ከቀበሌ እስከ ዞን ከተሞች በባለሥልጣናት ጭምር ግፍ እየተፈጸመባቸውየሚገኙ ክርስቲያኖችን መከራ መንግሥት መፍትሔ ካልሰጠ የከፋ ችግር እንደሚፈጠር ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ክርስቲያኖች ደማቸውን አፍስሰው ጠብቀው ባቆዩዋት አገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንዲታዩ ከሚያደርግ አሠራር፣ በነፃነት እንዳይኖሩ የቅኝ ገዥዎችን ቀንበር የሚያሸክም፣ በማንኛውም የአገራቸው ክፍል ኖረው ሀብት የማፍራት፣ የመምረጥ፣ የመመረጥ መብታቸውን የከሚጋፋ እና ለፍተው ያፈሩትን ለቀማኛ እያስረከቡ እንዲወጡ የሚያደርግ እንዲህ አይነትንግግር እንዳይደገም ብቻ ሳይሆን በሕግም እንዲጠየቅ መንግሥትን እንጠይቃለን። የምርጫ ጊዜውን ያልጠበቀ እንዲህ አይነት ከሕዝብ አስተዳደር ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ቅስቀሳ የሚያደርጉትን የፖለቲካ ድርጅቶች ለሌሎችም አስተማሪ የሆነ ርምት እንዲሰጥልን እናሳስባለን።
ኦፌኮ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ መረን የለቀቀ ቅስቀሳ እና ዛቻ አልበቃ ብሎበየአካባቢው የክልሉ ፖሊስ ጭምር ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክርስቲያኖች በዓለ ጥምቀትን በትውፌታቸው መሠረት ለማክበር አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ እንዳይሰቅሉ የኦሮሞ ቤተ ክህነት ከልክሏል በማለት ሲፈጽመው የሰነበተውን አድሏዊ ድርጊት አጣርቶ ለሕግ እንዲያቀርብልን እንጠይቃለን።
የኦሮሚ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ውጭ ራሱን “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት” ብሎ የሠየመው አካል የሚያደራጃቸውን ወጣቶች በሕግ ያሰማራ እስኪመሰል ድረስ በኦርቶዶክሳውያን ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆሞ ይመለከት እንደነበር የየአካባቢው ክርስቲያኖች መናገራቸው እና በመላው ኦሮምያ ክልል ክርስቲያኖች ባንዲራ ይዘው እንዳይወጡ መደረጉ መንግሥት ማነው ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በ2012 ዓ.ም ክርስቲያኖች የጥምቀት በዓልን በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በአቦምሳ፣ በሆሣዕና፣ በምዕራብ ሸዋ ኢሉ ገላን ወረዳ ኢጃጂ ከተማ በማክበር ላይ ሳሉ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሲፈጸምባቸው የሰነበተውን እና አሁንም ክርስቲያኖች እየተመረጡ መታሰራቸው የቀጠለ በመሆኑ መንግሥት የሰጣቸውን ሥልጣል ክርስቲያኖችን ለማሰቃየት የሚያውሉትን አካላት ሥርዓት እንዲያስዝልን መንግሥትን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ነው።
ሲፈጸም የሰነበተውን ግፍ አይተን ክልሉ በማንነው እየተመራ ያለው ብለን እንድንጠይቅ ስላደረገን እንዲህ አይነቱ የተዛባ አመራር እንዲስተካከል እና ጥፋተኞችም በቶሎ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን። በገብረ ጉራቻም ሆነ በፍቼ ኦፌኮ በተባለው የፖለቲካ ፓርቲ ኣመራሮች እና ቀኝ እጅ ባደረጓቸው ራሳቸውን የኦሮምያ ቤተ ክህነት ኃላፊ በማለጽ የሾሙ ግለሰቦች የተነገረው ሐረር ከተነገረው የከፋ እንጂ የተሻለ አለመሆኑን አስረጅ በማቅበር እንመልከተው። መታወቅ ያለበት ይህ የፖለቲካ ፓርቲ ቅስቀሳ ባደረገባቸው አካባቢዎች ሁሉ በክርስቲያኖች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተጠናክሮ መቀጠሉ ነው።
የቤተ ክርስቲያንን አስተዋጽዖ የማጠልሸት ተልእኮ
“እንደ ኦሮምያ ቤተ ክህነት …በሌላው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝታ በጃዋር ሥነ ሥርዓት ላይ የምትቀር ቤተ ክርስቲያን አንፈልግም። በእምነት የምትነጣጥለን ቤተ ክርስቲያን አንፈልግም። ኦሮሞን በጎሳ የምትነጣጥል ቤተ ክርስቲያን አንፈልግም” (ትርጉም ዮሐንስ መኮንን)። ቤተ ክርስቲያንን ካለ ስሟ ስም፣ ካለግብሯ ግብር የሚሰጠው እንዲህ አይነቱ ንግግር ጤነኛ አእምሮ ካለው ሰው የሚቀርብ አይደለም። ንግግሩ ሚዛናዊነት የጎደለው ነው። ተናጋሪው የዲቁና መዓርግ ሰጥታ አገልግል ያለችውን ቤተ ክርስቲያን እንዲህ በማለት ያለስሟ ስም ሰጥቷታል። ለወግ ለመዓርግ ያበቃችውን ቤተ ክርስቲያን ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 90 የሚደርሱ ክርስቲያኖች ባስጨረሰ ጸረ ክርስቲያን ለውጧታል።
ቤተ ክርስቲያን እንድትገኝ እና ለጥፋቱ ይሁንታ እንድትሰጥ የምትጠየቀውም እያቃጠላት ላለው አካል ነው። በዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖችን ሲያሰቃይ ለነበረው ለአርያኖስ ትጸልይ እንደነበረው እንትጸልይለት ከሆነ ይህን ማንም ነግሯት ሳይሆን መሥራቿ አስተማሯት የምትፈጽመውመንፈሳዊ ተግባር ነው። ሕዝብን ለማበጣበጥ በሚጠራው ስብሰባ ግን አትገኝም። ለሚፈጽመው እኩይ ተግባርም ይሁንታ አትሰጥም። የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑትን ብቻ ሳይሆን ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክርስቲያኖችን በራሳቸው ክልል እንዳይኖሩ ሲያደርግ ለክርስቲያኖች መብት መነፈግ ያልገደደው ሰው እንዲያውም ለአጥፊው ጠበቃ ሆኖ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘጋጀው ጉባኤ ላይ ትገኝ ይላል። ክርስቲያኖች የራሳቸውን ቋንቋ በሚናገሩ ወገኖቻቸው ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ለፍተው ያፈሩት ሲወድም፣ በብዙ መቶ የሚቈጠሩ ክርስቲያኖች አካላቸው ጎድሎ ከቤታቸው ሲውሉ፣ ለሌላ ይተርፉ የነበሩት የሰው እጅ አይተው ማደር ሲጀምሩ ያልተናገረ ሰው ልጆቿን ላስጨረሰባት ግለሰብ በስብሰባው ተገኝታ ቡራኬ መስጠት እንዳለባት ቤተ ክርስቲያንን ያሳስባል። እንዲህ ብሎ መናገር መታመም ካልሆነ ሌላ ስም ሊወጣለት እንደማይችልም መታወቅ አለበት።
ቤተክርስቲያንን የሚጠሉ አካላት ለፈጸሙባት ጥቃት እስከ አሁን ፍትሕ ለተነፈገው ዕውቅና ለመስጠት በሚመስል መልኩ ያደረገው ንግግር በሰቀቀን ለከረሙ ክርስቲያኖች ተጨማሪ ሰቀቀን የሚፈጥር ነው። ቤተ ክርስቲያን የምትጸልየውም እንዲህ ላሉ ሰዎች ልቡና እንዲሰጣቸው ጭምር ነው። ልጆቿን እያስገደለ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከሚያቃጥል ጸረ- ኦርቶዶክስ ዘንድ ምን ልታደርግ ልትሔድለት እንደፈለገ የሚያውቀው ተናጋሪው ብቻ ነው።
መስቀል ማሳለምን በተመለከተ የተናገረውም የቤተ ክርስቲያንን ባሕርይ የሚገልጥ አይደለም።ንግግሩም አለማወቅን የሚያሳይ ካልሆነ በስተቀር ሊቅነትን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተምሮ ማደግን እና ለክርስቲያኖች ማሰብን አያሳይም። ተናጋሪው ስለቤተ ክርስቲያን ባሕርይ አያውቅም እንዳይባል እስከ ዲቁና የተማረ ነው። እንዲህ አይነቱ ንግግር ማገናዘብ የማይችለውን ወጣት በስሜታዊነት በመንዳት ጥቃት እንዲፈጽም ለማነሣሣት በዓላማ የተነገረ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ፓርቲው በክርስቲያኖች ላይ እየፈጸመ ባለው እኩይ ተግባር ምክንያት በገዳማት እና በአድባራት፣ በክርስቲያኖች ላይ ለሚደርስ ጥቃት ተጠያቂ እንደሚሆን ሊያውቀው ይገባል፡፡
መስቀል ማሳለም እና አለማሳለም የዘር እና የቋንቋ ጉዳይ ሳይሆን በቅዱስ መስቀሉ አዳኝነት፣ በክርስቶስ ቤዛነት የማመን የአለማመን ጉዳይ በመሆኑ እገሌን አሳልማ እገሌን ተወችው በማለት የተናገረውን ከየት እንዳገኘው እና ምን ሊጠቅመው እንደተናገረው የሚያውቀው ተናጋሪው ብቻ ነው። ቤተ ክርስቲያን ሰዎች እንዳይከፋቸው ብላ ከየቋንቋ ተናጋሪው በመስቀሉ አዳኝነት የማያምኑትን እንዲሳለሙ አታደርግም። እንዲህ ለማድረግ ባሕርይዋ አይፈቅድላትም። ሰው የማያምንበትን መስቀልን የሚሳለም ከሆነም አደርባይነት ካልሆነ በስተቀር ድኅነት አያገኝበትም። ከየቋንቋ ተናጋሪው እየተወከለ ለሥልጣን እንደሚበቃው የዘመናችን ፖለቲካ ሰማያዊውን እና ዘለዓለማዊውን ጉዳይ ለተራ ነገር ማዋል ራስን ያስተች ካልሆነ በስተቀር አያስመሰግንም። የስብሰባው ታዳሚዎች ንግግሩ እውነት መስሏቸው ለጊዜው ቢቀበሉት እንኳ ውሎ አድሮ እውነቱ መገለጡ ስለማይቀር ትርፉ ትዝብት ነው።
ሌላው ስሕተት ደግሞ ተናጋሪው ራሱን የኦሮምያ ቤተ ክህነት ተወካይ አድርጎ ማቅረቡ ነው። በቤተ ክርስቲያን እንዲህ አይነት መዋቅር አለመኖሩን ምእመናን ሊረዱት ይገባል። ተናጋሪው እንደሚለው ፖለቲከኞች ክርስቲያኖችን የሚከፋፍል መዋቅር ቢፈጥሩ እንኳ ከሐዋርያዊ ትውፊት ያፈነገጠ መሆኑን መረዳት ይጠበቅባቸዋል። ለቅዱስ ሲኖዶስ ግብዣ ይሁንታ የነፈገ አካል ለቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ሊሆን አይችልም። ተናጋሪው የፖለቲከኞች ጠበቃ እንጂ የሃይማኖት ተወካይ ሆኖ እንዳልቀረበ መረዳት ይገባል። ከሁሉ በፊት ራሱ ሕጋዊ መሆን ይጠበቅበታል። ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ሰጥታ ሳትፈቅድ በራሱ ተነሣሽነት ለማቋቋም የፖለቲከኞችን ይሁንታ እና ድጋፍ የሚፈልግ ሰው ሕጋዊ ዕውቅና ያለው አስመስሎ እና ራሱንም ተወካይ አድርጎ ማቅረቡ የዋሐንን ለማደናገር የተጠቀመበት ስልት ነው።
ቤተ ክርስቲያንን ከፋፋይ አድርጎ ማቅረብ
ቤተ ክርስቲያንን በእምነት እንደምትነጣጥል አድርጎ ባደባባይ መናገርም ተጨማሪ ስሕተት ነው። ቤተ ክርስቲያን ማንን ከማን እንደ ከፋፈለች በግልጽ ሳያሳይ ራሱ የመከፋፈል ተግባር እየፈጸመ ከፋፋይ ናት ይላል።ንግግሩ እውነት ከሆነ ማስረጃ ማቅረብ ይገባው ነበር። ማስረጃውን አቅርቦ ምሑራዊ ውይይት አድርጎ መርታት እንጂ የማያውቅን ማኅበረሰብ ማደናገር ተገቢ አይደለም። ምክንያት ፈጥሮ ለመከፋፈል ካልሆነ በስተቀር ቤተ ክርስቲያን እንዲህ አይነት የመከፋፈል ተግባር አትፈጽምም። እነዚህ አካላት አይታወቅብንም ብለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን፣ ቅድስት ድልግል ማርያምን እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያትን ከኢትዮጵያ ብሔሮች የአንዱ ቋንቋ ተናጋሪ አስመስለው ለማቅረብ ይቃጣቸዋል።
“የቱለማ መሬት የሰሜን ሰዎች መሬት ነው። የአማራ መሬት ነው ብለው የሚፎክሩ ብዙዎች ናቸው።የቱለማ ኦሮሞ ኦርቶዶክስ ስለሆነ ኦሮሞነቱን ለውጧል። ከዚህ በኋላ ከወንድሞቹ ከእስልምና እና ከፕሮቴስታንት ሰዎች ጋር በአንድነት አይኖርም” የሚሉ ሰዎች ብዙዎች ና ቸው።…መሬቱ የመገርሣ በዳሳ ነው። የአቡነ ጴጥሮስ መሬት ነው። ይህ መሬት የአቡነ አኖሬዎስ መሬት ነው።ይህ መሬት የአቡነ ፊሊጶስ መሬት ነው” ይላል። ይህ ንግግር ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ከ1000 ዓመታት በላይ በሰላም አብረው መኖራቸውን ከማያውቅ ሰው ቢነገር ባላስደነቀ። የሁለቱን ሃይማኖት ተከታዮች አብሮ መኖር የሚክድ ነው። ተናጋሪው ስማቸውን የተጠራቸው ሰዎች ክርስቲያን በመሆናቸው መሬታቸው ለአማራ አልተሰጠም። ኦሮሞ ለምን ክርስቲያን ሆነ ብሎ ቆጭቶት ካልሆነ በስተቀር። ኦሮሞዎች መሬታቸውን ለመንፈሳዊ አገልግሎት መጠቀማው የሚያስቆጨው ሰይጣንን ብቻ ነው፡፡
ክርስቲያኖች የራሳቸውን መሬት የአምልኮ መፈጸሚያ እንዲሆን ማዋላቸው ባሕር ተሻግሮ መጥቶ ባዐድ የሰፈረበት ማስመሰል የአስተሳሰብ መዘባት ነው፡፡ ተናጋሪው የሳተው ወይም ሆን ብሎ የሚያምታታው የዛሬ 28 ዓመት አማራ እና ኦሮሞ ተብሎ ዘውግ ወጥቶለት ተለያይቶ እንዲኖር መደረጉን ነው። ጉዳዩ ከሺህ ዓመታት በፊት ተፈጽሞ በቋንቋ ተለያይተው የኖሩ አስመስለው ማቅረባቸው ያስገርማል። ይህ ቅስቀሳ የፕሮቴስታንት ጀማሪ የሆነው ሉተር ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለመገንጠል ሲፈልግ ያደረገውን ንግግር የሚያስታውስ ነው።
ሉተር የወሰደው መፍትሔ ጥፋትን በበለጠ ጥፋት ለማስተካከል መሞክር ቢሆንም መቀመጫዋ ቫቲካን ሮም የሆነው ካቶሊክ የመላው አውሮፓን ገንዘብ በመሰብሰብ ለራሷ ታደርግ ስለነበር ለአገሩ ቢያስብ አያስነቅፈውም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን በጎ አድራጊዎች ፈቅደው ከሚሰጧት መሬት ውጭ የማንንም መሬትም ሆነ ገንዘብ አልወሰደችም። ይህ ንግግር ቤተ ክህነታችን ከተቋቋመ ከአምሳ ዓመታት እንዳልበለጠው የዘነጋ ነው።
አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ታደርግ የነበረውም ዘለዓለማዊ መንግሥትን እንዲወርሱ እንጂ ያላቸውን ለመውሰድ አልነበረም። በማስረጃ ማሳየት የሚገባው ቤተ ክርስቲያን የማንን መሬት እንደወሰደች ነው። ፖለቲከኞች ዛሬ ሕዝብ በዝቶ መሬት መወደዱን ትናንትንም በዛሬ ዓይን አይተው መናገራቸው የሚያስገርም ነው። እንኳን የዛሬ አምሳ እና መቶ ዓመት ከሃያ ዓመት በፊት አዲስ አበባ መሬት ወስዶ ቤት መሥራት ቀላል እንደ ነበረ ይዘነጉታል። ቤተክርስቲያን ከማንም መሬት ወስዳ እንደማታውቅ፣ ክርስቲያኖች የራሳቸውን መሬት ለራሳቸው እምነት መጠቀማቸው እውነት ነው። መሬት ከወሰደች የወሰደችውን ምን አደረገችው? የትስ አደረሰችው? ብሎ መጠየቅ ይገባል። ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ንግግር ለማድረግ በሚነሡበት ጊዜ ሊታመን የሚችል ፍሬ ነገር ይዘው መቅረብ አለባቸው። አፍ እንዳመጣ አይወራም። የቤተ ክርስቲያን አገልጋይነኝ የሚል ሰው ከሆነ ደግሞ እንዳይተችም፣ ሰዎች እንዳይሰነካከሉበትም መጠንቀቅ ይኖርበታል።
አቡነ አኖሬዎስ፣ አቡነ ፊልጶስም እና አቡነ ጴጥሮስ የተጋደሉት ፍትሕ በመዛባቱ እንጂ ለጊዜያዊ እና ኃላፊ ለሆነ መሬት አልነበረም። እነዚህ ቅዱሳን አባቶች በገዳም ተወስነው በተጋድሎ የኖሩ ናቸው፡፡ ተናጋሪው ስማቸውን የጠቀሷቸው አባቶች በአካለ ሥጋ ቢኖሩ ኖሮ መሬት ወሰዳችሁ ብሎ ከገዳም ባሰደዳቸው ነበር። የቤተ ክርስቲያንን ስም የሚያጠፉት ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት አልቻላቸው ብለው የቀሩ የአውሮፓ የወንጌል መልእክተኞች ናቸው። ዓላማቸውን አስታጥቀው የላኳቸውን ፖለቲከኞቻችን እውነት አስመስለው በየመድረኩ ሲናገሩት ኖረዋል። በቅርብ የተጀመረው ለየት የሚያደርገው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ለክህነት ታጭቶ በነበረ ሰው መነገሩ ብቻ ነው።
የሚሲዮናውያንን ስልት ለመተግበር ዕንቅልፍ ማጣት
ሚሲዮናውያን ፊት ለፊት መጥተው ተሸንፈው ሲመለሱ በኮሌጆቻቸው ያስተማሯቸው የእኛው ወገኖች የጥፋት መምህሮቻቸው ኢትዮጵያን ለማንኳሰስ እና ሕዝቧን ለመለያየት መግቢያ ይሆነናል ብለው የጻፉትን ስም ማጽፋት በምርምር የተረጋገጠ እውነት አስመስለው የዋሐንን ሲያሳስቱበት ኖረዋል። ይህ ትርክታቸው ሐሰት መሆኑ በምርምር ጭምር ቢረጋገጥም እነሱ እና የእነሱ ጉዳይ አስፈጻሚች ካፈርኩ አይመልሰኝ ብለው የሐሰት አፈታሪካቸውን መልሰው መላልሰው ይናገሩታል። ፍቼም ሆነ ገብረ ጉራቻ የተነገረው የዚያ ቀጣይ ወይም ተረፈ ታሪክ መሆኑን መረዳትም ይገባል።
የቀረበው ንግግር“ሚሲዮናውያን መግባባትን እና ሰላምን ለማምጣት ከመሥራት ይልቅ አንዱን ከአንዱ እያማቱ፣ አንዱን በሌላው ላይ እያነሣሱ መቃቃርን እና መለያየትን ማፋፋማቸው ይህንንም ለማከናወን የኢትዮጵያን ማእከላዊ መንግሥት እና ማእከላዊ ቤተ ክርስቲያን ስም በማጥፋት ለማዳከም፣ ኢትዮጵያን፣ ታሪኳን እና ሃይማኖቷን ማዋረድ እንደ ትልቅ ተልእኮ አድርገው መጠቀማቸው እና የመጡበት መሠረታዊ ዓላማ እንደ ሆነ መቍጠር ደረጃ ላይ ደርሰዋል።…የ19ኛው ምዕተ ዓመት ሚሲዮናውያን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊ የሆኑ ድርጅቶች መሪዎችን ለማንበርከክ፣ ለማዳከም እና ለመለወጥ ፖለቲካን እና መሣሪያዎችን (ጠመንጃ) እንደተጠቀሙ ሁሉ ምን አልባት የሃያኛው ምዕተ ዓመት ሚሲዮናውያን ደግሞ ለጤና እና ለትምህርት በሚሰጥ የእርዳታ ብር በመጠቀም ወደ ፈለጉት አቅጣጫ ሕዝቡን ለማስጎብደድ የተከተሉት ዘዴ አለመሆኑ እንዴት ሊታወቅ ችላል?”(ስቴቨን ሩቢንሰን በአክሊሉ ሀብቴ ገጽ 102 ውስጥ የተጠቀሰ) የሚለውን ያስታውሰናል። ይህ አሳብ ሚሲዮናዊው ስቴቨን ሩቢንሰን በሠሩት ጥፋት ተጸጽተው ከጻፉት መጽሐፍ የተወሰደ ነው።
የጦር ነጋሪት ጉሰማ
“እናንተ እኮ የታሪክ ባለቤቶች ናቸሁ። ደብረ ሊባኖስ የእናንተ ነው። … በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደብረ ሊባኖስን የመሠረቱት አባ ሊባኖስ ናቸው። ከዚያም አስቀድሞ ጎሐ ጽዮን ላይ በአብርሃ እና አጽብሃ ዘመን የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጎሐጽዮን ተራራ ላይ ተተክላለች። ግቡ (ወደ ቤተክርስቲያን) ። ስበሩ እና ግቡ። ከእጃቸው ተቀበሏቸው። እጃችሁን አስገቡ” የሚለው ንግግር የጦርነት ጉሰማ መሆኑን መረዳት ይገባል። ኦሮሞ የታሪክ ባለቤት መሆኑን እንደ አዲስ በመንገር ምን ጥቅም እንደሚያገኝበት የሚያውቀው ተናጋሪው ነው። ኦሮሞ የታሪክ ባለቤት ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሠሪም መሆኑን መዘንጋት እና ራስን መናቅ ነው።
ሌላው እና አስገራሚ የሆነው ንግግር ኦሮሞ እንደ ንዑሰ ክርስቲያን ከውጭ ቆሞ፣ ከምሥጢር ተከልክሎ፣ ከክህነት ተገልሎ፣ ከአስተዳደር ርቆ የኖረ አስመስሎ መናገሩ ነው። ግቡ ሲልም ከውስጥ የነበሩትን አስወጥተው መሆን እንዳለበት አስረግጦ ተናግሯል። ንግግሩ የሚፈለገው “ቤተ ክህነት” ምን አይነት እንደሆነ በግልፅ እየጠቆመን ነው። ክርስቲያኖች አባታችን ተክለ ሃይማኖት ከመሠረቱልን ገዳም እንዳንደርስ እየከለከለን ነው። ሐዋርያዊት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በቋንቋ እና በዘር በመከፋፈል አትድረሱብን፣ አንደርስባችሁም እንድንባባል ከሚፈልግ አካል የሚቀርብ ንግግር ነው።
በሕንድ የተፈጸመውን ኢትዮጵያ ውስጥ መድገም
በደብረ ሊባኖስ ገዳም ምን ያህል ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ መነኮሳት እንዳሉ የማይታወቅ ይመስል ግቡ ይላቸዋል። ለንግሥ፣ ለሱባኤ እና ለመሰል ሃይማኖታዊ በዓላት ለሚገኙ ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሎ መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው። ሊቋቋም የተፈለገው “ቤተ ክህነት” በፖለቲከኞች ወርድ እና ቁመት ልክ የተሰፋ መሆኑን የሚያስገነዝብ ንግግር ነው። ደብረ ሊባኖስ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ባይሆኑም በቅድስናቸው በምንመካባቸው አባ ሊባኖስ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሠረተ ገዳም ነው። በልዩ ልዩ ምክንያት ጠፍ ሆኖ ቆይቶ እንደገና በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አድርገው በጥንቱ ቦታ ላይ መሠረቱት። የጥንቱን ታሪክ ለማስታወስ ስሙ ደብረ ሊባኖስ ተባለ እንጂ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ አዲስ አልተመሠረተም።
አገራችንን ለማዳከም ፈልገው አልሳካላቸው ያሉ ሚሲዮናውያን ራሳቸውን አስመስለው በቀረጿቸው ጉዳይ አስፈጻሚዎቻቸው ከሚሲዮናውያን በላይ ጥፋት ሲፈጸሙ ኖረዋል። ፖለቲ ከኞችም እጅግ ዘግይቶ የገባውን ሃይማኖታቸውን የእኛ እና የእነሱ ባይሉም ኦርቶዶክስ ያንተ ሳይሆን የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ነው ይሉታል። እነሱ የኦሮሞን መሬት ብቻ ሳይሆን ቋንቋውን እና ባህሉን እያጠፉ ባህሉን እንደያዘ ኦርቶዶክስ እንዲሆን ስታደርገው የኖረችውን ኦርቶዶክስን ሲተቹ አያፍሩም። ለሁለት ሺህ ዘመናት ይዞት የኖረው ክርስትና የእሱ ካልሆነ ከግራኝ አህመድ ወረራ በኋላ በቦታው የገባው እስልምና እና አምሳ ዓመት ያልሞላው ፕሮቴስታንት የኦሮሞ ሃይማኖት የሚሆነው በምን እሳቤ እንደሆነ መናገር አይችሉም፡፡
በአንዲት ሉዓላዊት አገር ውስጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተወዳድሮ ሥልጣን መያዝ የሚፈልግ ፖለቲከኛ ሊመራው የሚፈልፈውን ሕዝብ መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ዕሴት ማክበር ሲገባው በማያውቀው ሃይማኖታችን ገብቶ ከመፈትፈት መታቀብ ይኖርበታል፡፡ መረን በለቀቀ እና ግብረ ገብነት በጎደለው ንግግር ቤተ ክርስቲያንን ማጥቃት ካልቆመ አብሮ ለመኖር ብለን አጥፈን ያስቀመጥነውን የታሪክ መዝገብ በመክፈት የማያዳግም መልስ በመስጠት ሐሰት የሆነውን ለማጋለጥ እንገደዳለን፡፡ ጥፋታቸውን እና የማን ዓላማ አስፈጻሚ መሆናቸውን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ ማሳወቅ እንችላለን። የሚሻላቸው ቤተ ክርስቲያንን ለቀቅ አድርገው የጀመሩትን የፖለቲካ መርሐግብር ጠበቅ አድርገው መያዝ ነው። ጊዜ ሰጠን ብሎ ሁሉን ልዋጠው ማለት ሁሉን እንደሚያስተፋ ከታሪክ የተማሩ ስለሚመስለን ይህን ለእነሱ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆንብናል። ቤተ ክርስቲያንን ለመገዳደር መሞከር ሳውል የደረሰውን አለማወቅ ነው። ከቤተ ክርስቲያን ጋር መሰላለፍ ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ እንዳሉት ከቆመ ብረት ጋር መላተም ነው። ተመክረው አልሰማ ካሉ እንዳይነሱ ሆነው ሲንኮታኮቱ ሁሉን ያውቁታል።
ሌላው የሚያስገርመው ንግግር “ግቡና ተቀበሏቸው” የሚለው ነው። እንዲህ ተብሎ የተነገራቸው ክርስቲያኖች ናቸው ወይስ ፕሮቴስታንት ወይስ ዋቄፈና ግልጽ አይደለም። ማን ነው ገብቶ ከማን የሚቀበለው? የፈልጉት ፕሮቴስታንት ገብቶ እንዲቀበለን እና አስረክበን እንድንወጣ ከሆነ ሲያምራቸው ይቀራል እንጂ አናደርገውም። አስወጥታችሁ ግቡ የሚል “ክርስቲያን” የምትከፋፍለንን ቤተ ክርስቲያን አንፈልግም ብሎ የመናገር ሞራላዊ ብቃት የለውም። እየከፋፈለ ያለ ማን እንደሆነም አድማጭ ተመልካች ይረዳዋል ብለን እናምናለን።
ፖለቲከኞችን ጥግ አድርጎ ቤተ ክርስቲያንን ለመውጋት መሞከር
ተናጋሪው ከፖለቲከኞች ተጠግቶ ቤተ ክርስቲያንን እየወጋ እንደሆነ መታወቅ አለበት። አሁን በደንብ ግልፅ እየሆነልን የመጣውም የኦሮሞ ቤተ ክህነት የሚባለው በፖለቲከኞች እየተዘወረ መሆኑን ነው።እየተፈጸመ ያለውን ግፍ የአገራችን መንግሥት እንዲያስቆምልንም እንፈልጋለን። የጥፋቱ ተባባሪ ሆኖ ወይም አላየሁም አልሰማሁም ብሎ ቤተ ክርስቲያን እንድትዳከምለት እየሠራ ከሆነም ክርስቲያኖች ድርጊቱን ለዓለም ማኅበረሰብ ከማሳወቅ በተጨማሪ እንዲህ አይነቱ የተንሸዋረረ አስተሳሰብ እስከሚስተካከል ጸንተን መታገል እንደሚኖርብን ማስገንገብ እንወዳለን።
ከተሳካላቸው ይማራል እንጂ የወደቀን አብነት አድርጌ ዓላማዬን ከዳር አደርሳለሁ ብሎ ማሰቡም ያስገርማል። የታሰበውን መከፋፈል ለአባቶቻችን በማሳወቅ የታሰበው ጥፋት መክኖ እንዲቀር ማድረግ ይኖርብናል። ቤተ ክርስቲያን በዮዲት፣ በኦቶማን ቱርክ ጂሃድ በተመራው አህመድ ግራኝ እንዲሁም በዘመነ መሳፍንት ሥልጣን ማግኘት ያሰከራቸው የስም ክርስቲያኖች ከአሁኑ የከፋ ችግር ገጥሟት ያውቃል። እግዚአብሔር አብሯት ስለነበረ አሁንም ስለአለ የታገሏት እንዳይነሡ ሆነው ወደቁ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን አልጎዷትም።
ይህን የምንለው ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተመሠረተች በመሆኗ እና እስከ ዓለም ፍጻሜ እንደማታልፍ አምላካችን በማይታበል ቃሉ ስለነገረን ነው። ከቤተ ክርስቲያናችን ዋቄ ፈናም፣ ፕሮቴስታንትም፣ ሙስሊምም እንደማያስወጣን መታወቅ ይኖርበታል። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየኝ ማን ነው? በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረው መመሪያችን መሆኑን ሊረዱት ይገባል። በሃይማኖት ጉዳይ ገብተው ለሚፈተፍቱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም አደብ ግዙ፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ለቀቅ አድርጋችሁ ፖለቲካችሁን ብቻ ያዙ እንላለን። ከ1960ዎቹ መጀመሪያ አንሥቶ ዓላማችሁ መክኖ የቀረው ከቤተ ክርስቲን ጋር የማይሆን መሰላለፍ ውስጥ ስለገባችሁ መሆኑን ተረድታችሁ ቤተ ክርስቲያንን ለቀቅ ፖለቲካችሁን ጠበቅ አድርጉ መልእክታችን ነው።