>
5:56 pm - Monday May 16, 2022

አስታራቂም የለን... እኛው እንታረቅ! (አሰፋ ሃይሉ)

አስታራቂም የለን… እኛው እንታረቅ!

አሰፋ ሃይሉ
ቀደም ብሎ በጎንደር ክፍለሀገር ሥር እየተዳደረ የነበረውን  ወልቃይት/ሑመራ/ፀገዴ/ፀለምት ህወኀት “ምዕራባዊ ትግራይ” ብሎ በመሰየም አስተዳደሩንና የሥራ ቋንቋውን ቀይሮ በትግራይ ሥር ጠቅልሎ እያስተዳደረው ይገኛል። (በተመሣሣይ በህወኀት አስተዳደር ሥር የተካተተው የቀድሞው የወሎ ክፍለሀገር አካል የነበረው የራያ ጉዳይም አለ)።
ይህ የህወኀት ድርጊት ከፖለቲካ ኃይሎች አልፎ ላለፉት ዓመታት በሁለቱ አጎራባች ሕዝቦች መካከል ያልተገባ መቃቃርና መጠራጠር እንዲኖር ያደረገ – እና የአሸናፊና የተሸናፊ ስነልቦናዊ ተፅዕኖን በሕዝቦች ላይ የጫነ ከመሆኑም በላይ – አሁንም ሆነ ወደፊት በሁለቱ ተጎራባች ሕዝቦች መካከል ለሚፈጠሩ መካረሮችና ፍጥጫዎች ሁሉ ዋነኛ የጠብና መለያየት አቀጣጣይ ነዳጅ ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ – በማንኛውም ሰዓት የሚያመጣው መዘዝ በቀላሉ የማይታይ በጠርሙስ ውስጦ ተከርችሞበት የኖረ – በአማራና በትግሬ ሕዝብ መካከል የገባ – አደገኛ የጠብ ጂኒ ነው!!
ነገር ግን ይህ ጉዳይ በፍፁም በሠላም የማይፈታና አመቺ ጊዜ እየጠበቀ ያለ የሞትና የሽረት ጉዳይ ተደርጎ በብዙዎች የሚቀርበውን ያህል፣ ብዙ አዳማጭም ባይኖራቸው ጥቂት የማይባሉ ሁኔታውን ያስተዋሉ ዜጎች ደግሞ ጉዳዩ የሚመስለውን ያህል ብዙ ውስብስብነት ያለው ጉዳይ እንዳይደለ ሲናገሩ ይደመጣል። እነዚህ ጥቂት አስተዋዮች ለችግሩ እንደ መፍትሄ የሚያስቀምጡት (እና መተኪያም የማይገኝለት!) ቀላሉ መፍትሄ ከስሜት ሰከን ባለ መልኩ የሚደረግን የፊት ለፊት የሁለትዮሽ ውይይትንና ድርድርን ነው።
መሬቱም ሆነ በላዩ እየኖረ ያለው ሕዝብ በየትኛው ክልል ፓርቲ ሥር ሊተዳደር ይገባዋል? በህወኀት ወይስ በብአዴን (አዴፓ)? በምን መልኩ? ሀብት ንብረት ላፈሩ ግለሰቦች ምን ዓይነት ዋስትና አላቸው? የሁለቱ ክልሎች ሕዝብ ኢንተረስቶች በምን ዓይነት አሬንጅመንት ቢስተናገዱ ነው በተሻለ ሠላማዊ መንገድ ሊጠበቁ የሚችሉት? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ሁለቱ ፓርቲዎች (ህወሃትና አዴፓ) በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀራርበው በግልፅ ሊነጋገሩና በጉዳዩ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሀቅ ላይ የተመሠረተ ዘላቂ የጋራ ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይገባቸዋል።
ኢትዮጵያን የፈጠሩም፣ ኢትዮጵያን ያቆዩም፣ ኢትዮጵያን የሚያድኑም ሁለት የአንዲት ሀገር ወንድማማች ሕዝቦች –  በህወኀት የማንአለብኝነት ፖለቲካና በብአዴን የደፈጣ የቁርሾ ፖለቲካ – መለያየትና መደማማት የለባቸውም። ሀገር የሁሉም ዜጋ ነች። ልዩነቱ ማን የትኛውን የሀገር ክፍል ያስተዳድር? በሚለው ላይ ነው። ይሄን የሀገራችንን ክፍል ማን ፓርቲ ያስተዳደር የሚለውን ግን በሠላም እና በአርቆ አስተዋይነት ከወዲሁ መፍታት – እና ኢትዮጵያችንን በተባበረ ክንድ ከተደቀኑባት ጠላቶች በጋራ ተሠልፈው ማዳን – ወቅቱ የሚጠይቀው የትግል ጥሪ ነው።
እኛ የዛሬው ዘመን ሰዎች ይህንን የአብሮነትና የእርቅ የትብብር ጥሪ የሚቀበል ልብ አጥተን ቸል ብንል – በማይለቅ ቀለም በየታቦታቱ ማደሪያ ላይ የተቀረፀው የጋራ ታሪካችን ግን አብሮነታችንን በደማቁ እየመሠከረብን ይኖራል!! የኋላውን የማያይ፣ የፊቱን አያይም። ከሆነውና እየሆነ ካለው ይልቅ የሚሆነው ይበልጣልና መጪውን አስተውለን – እኛው ያጠፋነውን – እኛው እንመልሰው – እያልኩ እሰናበታለሁ!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!
ኢትዮጵያ በልጆቿ የተባበረ ክንድ ለዘለዓለም ፀንታ ትኑር!
@ ንዋይ ደበበ (“እኛው እንታረቅ”፣ 1977 ዓ.ም.)
“ልቤ እንደ መረበሽ አለ እንደ መናፈቅ
ከፊቴ ላይ ሳጣሽ ሁልጊዜ መጨነቅ
ሁሉን ነገር ትቼ ይቅርታ ልጠይቅ
አስታራቂም የለን እኛው እንታረቅ
እኛው እንታረቅ እኛው እንታረቅ
“ንፋስ አይግባብን ስንል እንዳልነበር
እንዲህ በቀላሉ ተኳርፈን እንዳንቀር
አትሁኝ ሆደ ባሻ አይብዛ ቅያሜሽ
የሆዴን ሳታውቂ ያፌን ተከትለሽ
ቅያሜ የሌለበት ሰላማዊ ኑሮ
አገር እንመስርት አናብዛ ቀጠሮ
“ፍቅሬ ሆይ ጥፋቴን አላስተባብልም
በድንገት መሳሳት አያጨካክንም
ግድ የለም ግድ የለም ግድ የለም
ፍቅር ፍቅር ያለ የማይሆነው የለም”
Filed in: Amharic