>
5:13 pm - Saturday April 18, 1254

ቱርክ እንዴት ሰለመች..? (ዲያቆን ጸገየ ኃይለሚካኤል)

ቱርክ እንዴት ሰለመች..?

 

 

ዲያቆን ጸገየ ኃይለሚካኤል
• ቱርክ የኦርቶዶክስ ሀገር
ይኽ ጽሑፍ የተጻፈው ቤተክርስቲያን ሲቃጠል ፣ የምዕመናን ቁጥር ሲቀንስ እየተመለከቱ እግዚአብሔር ያውቃል በማለት የሚኖሩ ሰዎችን አብነት አድርጎ ነው፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ማወቁን ያውቃል እንኳን የተደረገውና የተፈጸመውን ይቅርና በሰው ልቦና የታሰበውንና ገና ሊታሰብ ያለውን ጭምር ያውቃል ፡፡ ዳሩ ምን እናድርግ የሚለውን መወያየት ሲገባን እግዚአብሔር ያውቃል ብለን እጅና እግራችን አጣጥፈን ብንቀመጥ የቱርክ ዕጣ ፈንታ እኛም እንደሚደርሰን ልናውቅ ይገባል ፡፡ እስኪ ጥቂት ስለ ቱርክና ኢትዮጵያ እንመልከት ፡፡
• ቱርክ የኦርቶዶክስ ሀገር
በቤተክርስቲያናችን ታሪክ ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው ቦታዎችና ሀገራት መካከል የአሁኗ ቱርክ በቀድሞዋ አጠራርዋ ቁስጥንጥንያ በመባል ትጠራ የነበረችው አንዷ ናት ፡፡ የመጀመሪያዎቹ አማኞች ክርስቲያን ተብለው የተጠሩባት አንፆኪያ ፣ ከሮማዊያን ግፍና መከራን በመሸሽ ክርስቲያኖች የተጠለሉባት ቆጶዶቂያ፣ የቅዱስ ጳውሎስ የትውልድ ሀገር ተርሴስ ፣ አባታችን አብርሃም የኖረባት ካራን ፣ ይህችው ሀገር እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን የመሳሰሉ ቅዱሳንን ያፈራች ሀገር ናት ፡፡ የቅዱስ ፖሊካርፐስ የትውልድ ሀገር ኢዝሚር የምትገኘው በቱርክ ነው፡፡ እረ እንደው ምን አለፋችሁ ቆጥረን የማንጨርሳቸው ቅዱሳን አባቶች መገኛ ናት ፡፡ ሊቃውንት ስለ ቤተክርስቲያን ሕልውና የመከሩበት ሀገር የዛሬዋ ቱርክ ነች፡፡ መቼስ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን አስታውሶ ስብከቱን ማስታው ግድ ይላል ስብከቱን አስታውሶ ሰማዕያኑን እነማን ነበሩ ብሎ መጠየቅ የትላንት ሰዎች እነማን እንደነበሩ ለማስታወስ የሚረዳ ነው ፡፡ መንበረ ፕትርክናዋ ቁስጥንጥንያ የተሰኘላት … እንደነ ሐጊያ ሶፍያ የመሳሰሉ ድንቅና ምጡቅ የሰው ልጆች አዕምሮ የተጠበባቸው ቤተክርስቲያኖች ባለቤት የሆነች ሀገር ጭምር ነበረች፡፡
ትላንት በነበር ቀረ … ዘመነኞች ተነሱባት
•ቱርክ ተወረረች ተደመሰሰች የኦቶማን ተርክ መነሳት … በኤፌሶን በቁስጥንጥንያ በኢዝሚር በቆጶዶቅያ ፍሬ እያፈራ የነበረውን ክርስትና , በጦር ኃይል ደመሰሰው ፡፡ የኦቶማን ጦር በደረሰበት እግሩ በረገጠበት ቦታ ሁሉ ቤተክርስቲያንና ክርስቲያኖችን ይደመስስ ያቃጥል ያሳድድ ጀመረ፡፡ ለማፍረስና ለማቃጠል የከበዱትን ቤተክርስቲያኖችን በቁማቸው ወደ መስኪድነት ቀየራቸው መስቀላቸውን አውርዶ ጨረቃና ኮከብ አኖረበት ፡፡ የባዛንታይን ጥበብ ያረፈባቸውን ስዕሎች እየነደለ በምትካቸው ከቁርዓን የተወጣጡ ጥቅሶችን ለጠፈባቸው፡፡ Upon capture, Sultan MehmedII, ordered the Hagia Sophia to be converted into a mosque. The bells, altar, and sacrificial vessels were removed and many of the mosaics were plastered over ኤፌሶን በባለ ተረኞቹ ጦረኞች ስም መጠራት ጀመረች በኦቶማን የተነሳ …ቱርክ ተባለች፡፡ ቁስጥንጥንያ ኢስታምቡል ተባለች፡፡ ከክርስትናው ዓለም ወደ እስልምናው ዓለም 360 ዲግሪ ተሸከረከረች፡፡ ይባስ ብሎ ቱርክ በእስልምና አንጋሽነቷ ከሳውዲና ከኢራን ጋር የምትነታረክ ሀገር ሆና በዓለም አደባባይ ብቅ አለች፡፡
ዊኪፒዲያ ከተሰኘው የሀገሪቱን መረጃ ከያዘው ድኅረ ገጽ የምናነበውና በአሁን ሰዓት ያለው የሃይማኖት ምጣኔ ወይም ስብጥር ይሕን ይመስላል የሱኒ ሙስሊም 83.5 % ፣ የሺአ ሙስሊም 13.5 % ፣ ቁርዓናዊ ሙስሊም 1 % ፣ ክርስቲያኖች 0.2 % ፣ እንደነገሩ የሚኖሩ ስለ ሃይማኖት ግድ የሌላቸው 1 % ፣ ሌሎች ደግሞ አንድ ላይ ተደምረው 0.3 % …. የክርስቲያኑን ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ልብ በሉ https://en.wikipedia.org/wiki/Turkey#Religion
በእውነት ይህች ሀገር ትላንት እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሰበኩባት ያስተማሩባት ሀገር ናት ወይ ያስብላል
• የቱርክ ክርስቲያኖች ጭቆና
Middle East Quarterly በተሰኘው ድኅረ ገጽ ላይ Turkey Turns on its Christmas የሚል ጽሑፍ ያስነበበችን አና ክርስቲን ( Anna Christine Hoff) በቱርክ ክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ነጥብ በነጥብ አስቀምጣዋላች ፡፡ የተወሰኑትን እንመልከት https://www.eurasiareview.com/27072018-turkey-turns-on-its…/
1) እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም በክርስቲያኖች የዘመን መለወጫ ዕለት በአንድ መድረክ ላይ የቀረበው ድራማ እጅግ አስገራሚ ነበር ፡፡ በተለምዶ የገና አባት የምንለውን (Santa Claus) ግንባሩ ላይ ጥይት ተደቅኖበት ሃይማኖቱን እንዲቀይር ሲገደድ የሚያሳይ ነው ፡፡
2) Van በተሰኘችው የቱርክ ምሥራቃዊ ከተማ ውስጥ የተሰቀለው የማስታወቂያ ሰሌዳ እንዲህ ይላል Have You Ever seen a Christian celebrating edi al adha፣ why are we celebrating their festivals ፡፡ ይህ ዓይነቱን ድርጊት ጸሐፊዋ በመንግስት የተደገፈ (State sponsored conspiracy ) በማለት ትገልጸዋለች፡፡
3) የኢስታምቡል ቴክኒካል ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለክርስቲያኖች ያላቸው ንቀት ለመግለጽ የሚከተለውን መፈክር አንግበው ታይተዋል Don’t be tempted by Satan don’t celebrate new year በሰይጣን እንዳትፈተኑ አዲስ ዓመትን አታክብሩ የሚል ትርጓሜ አለው፡፡
4) ቤተክርስቲያን በቱርክ ለመስራት በጣም ከባድ ነው፡፡ ያም ሆኖ ከባዱን ፈተና ታልፎ ለመገንባት ፍቃድ ከተገኘ መንግስት ለቤተክርስቲያን ግንባታ በተለየ ሁኔታ ከፈቀደው ርዝመት በላይ መገንባት አይቻልም ፡፡
5) እንደ አና ዘገባ ከሆነ ክርስቲያኖች በቱርክ ተወዳድረው መንግስታዊ ሥራ ማግኘት አይችሉም ፡፡ (Christian have no access to state jobs)
በቱርክ የሚገኙት አጠቃላይ ቤተክርስቲያኖች ብዛት 236 ነው፡፡ ይኽ አሃዝ የካቶሊኮችን የፕሮቴስታንቶችን የኦርቶዶክሶችን ቤተክርስቲያን በአንድነት የሚያጠቃልል ነው፡፡ እናም ይህን የቤተክርስቲያን ቁጥር ለሀገሪቱ የቆዳ ስፋት(783,356 sq m2) ለማካፍለው ብንሞክር የምናገኘው መረጃ አስደንጋጭ ነው ፡፡ በስምንት መቶ ኪሎ ሜትር ውስጥ አንድ ቤተክርስቲያን ላይገኝ ይችላል ፡፡
የቱርክ ክርስቲያኖችን ጉዳይ በይደር እናቆየውና በወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንመለስ

ኢትዮጵያ በቱርክ ጎዳና

ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በተለየ ሁኔታ ቤተክርስቲያንን ማቃጠል እንደ ፋሽን እየታየ መጥቷል ፡፡ በተለይ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት በመለስ ያሉት ዓመታቶች ለቤተክርስቲያን ከባድ ዓመቶች የነበሩ ይመስለኛል ፡፡ የቤተክርስቲያን አፍራሾቹና ፣ ቃጠሎ አስነሺዎቹ ፣ በከተማ ከንቲባዎች አይዞሕ ባይነት የሚከወኑ መሆናቸው ድርጊቱን አንድ ነገር እንድንጠረጥር ያደርገናል State sponsored conspiracy፡፡ የግለሰቦች መኖሪያ ቤት እተሸጠ ወደ መስኪድነት ሲቀየር ዝም ያለ የከተማ ከንቲባ ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ ግን ወደ ኋላ አይልም ፡፡ በጥምቀት ቦታዎች / በታቦት ማደሪያዎች መስኪዶች እንዲሰራ የሚፈቅዱ ከንቲባዎች አካሄዳቸው ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቱርክ ጎዳና እንድትጓዝ ከማድረግ የዘለለ ራዕይ የላቸውም፡፡ ዛሬ ቤተክርስቲያን ስትቃጠል ዝም ያለ አመራር ነገ መኖሪያ ቤቱ እሱን በሚያስንቅ ዘረኛና አክራሪ ሲቃጠል ምን ሊመልስ እንደሚችል ማየት ነው፡፡ ልክ ቱርክና ሊሎች ሀገራት ወደ እስልምና የተቀየሩበትን አካሄድ በሀገራችንም እየተካሄደ ለመሆኑ ብዙ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፡፡
በትምህርት ሳይሆን በመውለድ መዋለድ መብዛት መባዛት ሀገሪቱን የሚመራው መንግስት የሚወስደው ኋላ ቀር እርምጃ … ከቤተክርስቲያን መቃጠል ይልቅ የፖለቲካው ፕሮፖጋንዳ የሚያሳስበው መሆኑ፡፡
በቅርቡ የኤርትራ መንግስት በኳታር ፣ በሱዳንና ፣ በቱርክ መንግስታት ላይ ያቀረበውን ክስ መንስዔውን ለመመርመር ብትሞክር ከላይ ከጠቀስነው አንድን ሀገር እስላማዊ የማድረግ ፕሮጀክት የፈጠረው ችግር መሆኑን ልብ ትላለኽ ፡፡ ብዙኀኑን የክርስትና እምነት ተከታይ እንደ ጥቂት እንዲቆጠር የማድረግ ሥልት በአንዳንድ ክልሎች መንግስታዊ መዋቅርን እስከ መቆጣጠር የደረሰ ነው ፡፡ እንዲኽ ላለው ፕሮጀክት ይሉኝታ የተጫነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተመቸው ይመስላል ፡፡
በክልሎች የኦርቶዶክሳዊያንን ስርጭት ምን እንደሚመስል እ.ኤ.አ በDecember 2008 ዓ.ም Summery and Statical Report Of the 2007 Population and Housing census በሚል ከታተመውን የህዝብና ቤት ቆጠራ ሪፖርት ላይ እንመልከት፡፡
ትግራይ ( 95.6 % ኦርቶዶክስ እና 4% ሙስሊም)
አፋር (3.9 % ኦርቶዶክስ እና 95.3 %ሙስሊም )
አምሐራ ( 82.5 %ኦርቶዶክስ እና 17.2%ሙስሊም )
ኦሮሚያ (30.5 % ኦርቶዶክስ እና 47.5 % ሙስሊም )
ሶማሌ(0.6 % ኦርቶዶክስ እና 98.4 % ሙስሊም )
ቤንሻንጉል(33 % ኦርቶዶክስ እና 45.4%ሙስሊም 13.5 %ፕሮቴስታንት)
ደቡብ (19.9% ኦርቶዶክስ እና 14.1% ሙስሊም 55.5 %ፕቶቴስታንት
ጋምቤላ (16 % ኦርቶዶክስ እና 4.9 %ሙስሊም 70.1 %ፕሮቴስታንት)
ሐረሪ(27.1 %ኦርቶዶክስ እና 69 %ሙስሊም)
አዲስ አበባ (74.7%ኦርቶዶክስ እና 16.2 % ሙስሊም 7.8% ፕሮቴስታንት)
ድሬደዋ(25.6 % ኦርቶዶክስ እና 70.9 %ሙስሊም) ፡፡
ከዚሕ በመነሳት ቀጣዩ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ይዞት የሚወጣው መረጃ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይስለኝም ፡፡ ምክንያቱን ኦርቶዶክስ በሚለው ስር ቅባት ፣ ጸጋ የሚሉ አማራጮች መኖራቸውን ስናስብ ምን ያህል ቤተክርስቲያኗን ለማዳከም ስራ የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ነው፡፡ የእነዚሕ አካላት ሥራ ብቻ ሳይሆን የኛም መተኛት ደግሞ ለምለም መስክ ሆኖላቸዋል፡፡
ዞሮ ዞሮ ሀገራችን ኢትዮጵያ በቱርክ ፣ በግብጽ ፣ በሶርያ እና በመሳሰሉት ሀገራት ጎዳና እየተጓዘች እንደሆነ እየተመለክትን ነው፡፡ እንዴት ብለን ይሄን ጊዜ የምንሻገረው የሚለው ጥያቄ እያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ሊያሳስበውና ሊጠይቀው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩን እንዴት መቅተፍ ይቻላል የሚለው ሃሳብ የሚተገበረው ወደ መፍትሔው ለመቅረብ በሚያደርገው ጥረት የሚወሰን ነው የሚሆነው ፡፡
እግዚአብሔር ያውቃል ብቻ ብለን በዝምታ እጅና እግራችንን አጣጥፈን ብንቀመጥ የሚመጣው ጥያቄ ልክ እንደ ግብጽ እንደ ሶርያ እንደ ቱርክ … ኢትዮጵያ እንዴት ሰለመች ይሆናል፡፡ ምን እናድርግ የሚለውን መነጋገር ከኦርቶዶክሳዊያን የሚጠበቅ ጉዳይ ነው ::
“አንተ የምትተኛ ንቃ” ኤፌ 5÷15
የቅዱሳን አምላክ በረድዔቱ አይለየን ፡፡
አሜን
Filed in: Amharic