>
7:42 am - Sunday November 27, 2022

መለስ ዜናዊና የአፍሪካ ኅብረት ምን አገናኛቸው?  (አቻምየለህ ታምሩ)

መለስ ዜናዊና የአፍሪካ ኅብረት ምን አገናኛቸው? 

 

 

 

አቻምየለህ ታምሩ
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመሰረቱት የአፍሪካ ማኅበር ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሰራው አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የአገልግሎት ማዕከል [Africa Union Service Center] በወያኔው አምበል በመለስ ዜናዊ ስም ተሰየመ አሉ። ይገርማል! ሰሜን ሮዴዥያና ደቡብ ሮዴዥያ አንድ ሆነው ዚምባብዌ እንድትመሰረት ያገዙ የአፍሪካ አባቶች በጸነሱት  ተቋም ውስጥ፤ ታንጋኒካና ዛንዚባር ታንዛንያ እንዲሆኑ የረዱ የአፍሪካ መሪዎች ባቋቋሙት ድርጅት ቅጥር ፤ የባያፍራ ጦርነት እንዲያበቃና ናይጀሪያ አንድነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል ያደረጉ የአፍሪካ አባቶቹ ባጎለመሱት ድርጅት ግቢ  ውስጥ በነ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ተጋድሎ አንድነቷ የተረጋገጠዋ ኢትዮጵያ ለሁለት ተከፍላ ወያኔና ኦነግ  የሚገዘግዟት ኢትዮጵያና ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመትራት ኤርትራ እንዲፈጠሩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአለም ሁሉ አስቀድሞ ደብዳቤ የጻፈው አሳፋሪ ግለሰብ የአንድነት ምልክት ተደርጎ  በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ግቢ ውስጥ በስሙ መታሰቢያ ሲሰየምለት እንደማየት ምን አሳፋሪ ነገር አለ።
የመለስ ዜናዊ ስም ሲነሳ ከፊታችን ድቅን የሚለው መበታተን፣ ማጋጨት፣ ኢትዮጵያን አፍርሶ በጎሳ አጥር የሚተራመሱ የመንደር ሪፑብሊኮች የመመስረት ራዕዩ፣ ዘራፊነቱ፣ ዘረኛነቱ፣ ጨጓራው እስኪቃጠል ድረስ አማራን መጥላቱ፣ ከትግራይም አንሶ ከተወለደበት ቅዬው ከዓድዋ አስፍቶ አለማሰቡ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የመለስ ህያው መገለጫዎችና አሻራዎቹ  ትላልቅ አስተሳሰብ ከሆኑት ከኅብረትና አንድነት ጋር የሚያገናኛቸው አንዳች ነገር የለም። መለስ ዜናዊ ዜናዊ ኢትዮጵያ ሰማንያ አገሮች እድትሆን የጎሳ አጥር አበጅቶ መበታተንን ሕጋዊ በማድረግ  በማናቸውም ጊዜ የምትፈርስ የጎሳዎች ኅብረት መስርቶ እሱ እስከገዛት ድረስ  የጎሳዎች እስር ቤትና የአፓርታይድ ቤተ ሙከራ  እንድትሆን በማደራጀት በኢትዮጵያውያን ላይ የሲኦልን በር የከፈተ ሰይጣናዊ ግለሰብ ነው።
አንድነት በሚሰበክበት የአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ መለስ ዜናዊ  መታሰቢያ ተሰየመለት  መባሉን ማንዴላ ባጸደ ገነት ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? የአፍሪካ ኅብረት እንዲፈጠር በተደረገው ከፍተኛ ዝግጅት ውስጥ ዋና ተዋናይ የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ታላቁ አቶ ከተማ ይፍሩስ መለስ ዜናዊ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ግቢ ውስጥ መታሰቢያ እንደቆመለት ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? ማንዴላ የመለስ ዜናዊዋን ኢትዮጵያን ሳይረግጥ የሞተው  በመለስ ዜናዊ የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ማየት አልፈልግም ብሎ ነበር።
ለመለስ ዜናዊ በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ መታሰቢያ መሰየም  ማለት ኒዮርክ በሚገኘው ብሔራዊ የመስከረም 11 የመታሰቢያ እና ቤተ መዘክር ግቢ ውስጥ የቢላደንን ሐውልት እንደማቆም ማለት ነው። ስለእውነት መለስ ዜናዊና አንድነት ምን አገናኛቸው? መለስ ዜናዊኮ አይደለም የአፍሪካ መሪ ሊሆን ይቅርና የኢትዮጵያ  መራሔ መንግሥት ሆኖ ተሰይሞ በአገዛዝ ዘይቤው ከትግራይ ክልል ከአድዋ ወረዳ ገዢነት አልፎ ማሰብ ሳይችል  የኖረ የተቸነከረ ግለሰብኮ ነው።
እንደ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሰጠና በአገር ክህደት የፈጸመ  ከንቱ ግለሰብ የለም። ኢትዮጵያዊው አክሊሉ ሀብተወልድ ዓለምን አሸንፈው ያስመለሷትን ኤርትራን ለዘመዶቹ አሳልፎ የሰጠ የዓድዋው ጉድ  መለስ ዜናዊ ነው። ፋሽስት ጥሊያን ሳይቀር ዓሰብ የኢትዮጵያ የባሕር በር መሆኑን እየመሰከረ «ዓሰብ የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛት ነው» ብሎ የኢትዮጵያን  ታሪካዊ የባሕር በር አሳልፎ የሰጠና ኢትዮጵያን ያለ ባሕር በር ያስቀረው ጉደኛው መለስ ዜናዊ ነው።
የክዋሜ ኑክሩማህ ልጆች ሳይቀር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ እንዲቆም ሲታገሉ ነውረኛው መለስ ዜናዊ ግን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በግንባር ቀደምትነት ከመሰረቱት ድርጅት ታሪካቸው እንዲፋቅ ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም። አንድ ጊዜ ቶጎ ሎሜ ላይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመሰረቱት የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ባደረገው ንግግር፤  በ1984 ዓ.ም. መቀሌ በሕዝብ ፊት ቀርቦ «እንኳን ከእናንተ ከወርቅ ሕዝብ ተፈጠርኩ፤ እንኳን ከሌላ አልተፈጠርሁ» እያሉ መናገርን እንደ ትልቅነትና ተራማጅነት ቆጥሮት የነክዋሜ ኑክሩማህና የነጆሞ ኬንያታ ልጆች ይታዘቡኛል ሳይል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን «አድኀሪ» ወይንም Reactionary ሲል ተሳለቀ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ለአፍሪካ ኅብረት አንድ ሰው ይጠራ ቢባል እንደ ክዋሜ ኑክሩማህ ማንም የለም አለ። ኑክሩማህ ራሱኮ ይህን ቢሰማ የአፍሪካ ኅብረት ምልክትነት ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደሚገባ መመስከሩ ምንም ጥርጥር የለውምኮ። ይህን ስለማድረጉ ደግሞ የኅብረቱን መመስረት ተከትሎ ስለኢትዮጵያንና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሚና ኑክሩማህ ራሱ የሰጠው ምስክርነት በቂ ማስረጃ ነው።
ለነገሩ መለስ ዜናዊም ቢሆን በጥላቻ ታውሮ የኑክሩማህ ሐውልት እንዲቆም ሽንጡን ገትሮ የተከራከረው እውነቱ ጠፍቶት ሳይሆን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይቆምላቸው ነበር። ለነገሩ እንኳን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት ይቁም ተብሎ አጽማቸው እንኳን መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚባል ጨካኝ አውሬ በግፍ ከቀበረበት የቀበሮ ጉድጓድ ተቆፍሮ ወጥቶ እንደነገ በክብር ሊያርፍ እንደዛሬ ማታ « ከኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የወጣ መግለጫ» በሚል ርዕስ መለስ ዜናዊ በሚቆጣጠው አንድ ለናቱ ቴሌቭዥን ባስነበበው የኃጢዓት ክስና የክፋት ፕሮፓጋንዳ በግፍ ተገድለው ለ17 ዓመታት ያልህ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የቀበሮ ጉድጓድ ተቀብሮ የኖረው የንጉሠ ነገሥቱ አጽም ላይ እስኪበቃው ድረስ ክብራቸውን ካጎደፈ በኋላ የሚያዋርድ የኃጢዓት ክስ ማውረዱ ቁስሉ  ከህሊናችን መቼ ጠፋና። እነ ማንዴላ ሳይቀር ብሔራዊ ቀብር ይካሄድላቸው ዘንድ ጠይቀው በክብር እንዲያርፉ ያልፈቀደው መለስ ዜናዊ ብቻ ነበር።
የመለስ ዜናዊ መታሰቢያ መሰየም  ካለበት ሊየም የሚገባው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመሰረቱትና አንድነትና ኅብረት በሚሰበክበት የአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ አይደለም። ከመለስ ዜናዊ ጋር ኢትዮጵያን ለመውጋትና በጎሳ አጥር የሚተራመሱ  የአካባቢ አገራትን  ለመመስረት ጫካ የገቡት እነ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ ሻዕብያ፣ ጀብሐ፣ መኢሶን፣ ወዘተ በወያኔ አጋፋሪነት ተሰባስበው ኅብረት ይመስርቱና ቢፈልጉ ደደቢት በረሀ፣ አሊያም አሲምባ ተራራ፣ ቢያሻቸው ሞቃዲሾ ዚያድ ባሬ ቤተ መንግሥት ወይንም ናቅፋ ተራራ ላይ በእጁ መዶሻና አካፋ፤ በትክሻው ደግሞ ቀይ ባንዲራውን አስይዘው ቢፈልጉ ሐውልት ያቁሙለት፤ አልያም «አንቀጽ 39 የአገልግሎት ማዕከል»  ብለው መታሰቢያ ይሰይሙለት። ለመለስ ዜናዊ የሚመጥነው ይህ ብቻ ነወ።  ለምን ቢባል የመለስ ዜናዊ ራዕይ  የሚገጥመው የርዕዮተ አለም አጋሮችይ እነ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ ሻዕብያ፥ ጀብሃና መኢሶን ይዘውት ከተነሱት ድንቅርና ጋር እንጅ ትላልቆቹ የአፍሪካ አሳቢዎች ራዕያቸውን እውን ለማድረግ ከመሰረቱት አፍሪካ አንድነት ድርጅት ወይም ከአፍሪካ ኅብረት መንፈስ ጋር አይደለምና ነው!
Filed in: Amharic