>

ባልደራስ የምሥረታ ጉባኤውን ዛሬ በተሳካ ሁኔታ አካሒዷል!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ባልደራስ የምሥረታ ጉባኤውን ዛሬ በተሳካ ሁኔታ አካሒዷል!!!

 

 

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

 

 

ሊቀመንበርና የምርጫ ምልክት ወይም አርማም መርጦ አጽድቋል!!!

 

 

በበኩሌ አርማውን ወድጀዋለሁ፡፡ እስክንድር ሊቀመንበር መሆኑን ግን አልወደድኩትም፡፡ 

 

እስክንድር ጸባዩ በማይጠበቅ ደረጃ ግትር፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚልና በመነጋገር ለመተማመን ዕድል የማይሰጥ በመሆኑ ለዚህ ፓርቲ ሊቀመንበርነት ይመጥናል ብየ አላምንም!!! የምናስበው ለሀገርና ለሕዝብ ከሆነ ሊቀመንበሩ ደረጃውን በጠበቀ መስፈርት በአባላት ምርጫ መደረግ ነበረበት፡፡ መስፈርቱ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ብቃት፣ ችሎታ፣ ቁርጠኝነትና የትምህርት ዝግጅት መሆን ነበረበት!!!

ወደ ዐሥር የሚሆኑ ዶክተሮች ባልደራስን እንደተቀላቀሉ ሰምተናል፡፡ አንዱም ዶ/ር ደረጀ ነው፡፡ እስክንድር ከእነኝህ ሰዎች ጋር ተወዳድሮ እንዳልሆነ በሊቀመንበርነት የተሠየመው የደረሱኝ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ነገር ተበላሸ ማለት ይሄ ነው፡፡ “ድል ለዲሞክራሲ!” እያለ የሚፎክረው እስክንድር ከማንም ጋር ሳይወዳደር በሊቀመንበርነት መሠየሙን በጸጋና በደስታ መቀበሉ ትልቅ ምጸትና እስክንድርን ለትልቅ ትዝብት የሚዳርግ ስሕተት ነው!!! ፈጥኖ መታረምም ይኖርበታል!!!

ሌላው ደግሞ ባልደራስ ከሀገር አቀፍ ፓርቲ ጋር ጥምረት ወይም ቅንጅት እንደሚፈጥር ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡም እነ እስክንድር ጥምረቱን ወይም ቅንጅቱን ከእነማን ጋር እንደሚያደርጉት ለመስማት በጉጉት እየጠበቀ ነው፡፡ ሕዝቡ ድጋፉን ለባልደራስ ለመስጠትም ሆነ ለመንፈግ ከማን ጋር እንደሚጣመሩ ማወቅን በቅድመ ሁኔታ ይዞታል!!!

በበኩሌ ምንም እንኳ ነገሩ “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ!” ቢሆንም እነ እስክንድር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘውን የጎሳ ፖለቲካን የሚጠላውን silent majority የሆነውን ሕዝብ ተስፋ ማጨለምና እነሱም በሕዝብ መተፋት ካልፈለጉ ከእነ አብን፣ ኢዴፓ፣ ኢኃንና ከሌሎች ከብአዴን ወይም ከአገዛዙ ጋር ግንኙነት ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ጥምረቱን ወይም ቅንጅቱን ፈጽሞ ከማድረግ ይቆጠቡ!!!

እነ እስክንድር ባልደራስን ሀገር አቀፍ ፓርቲ አድርገው ስላልመሠረቱት ከሀገር አቀፍ ፓርቲ ጋር ጥምረት ወይም ቅንጅት መመሥረት ይኖርባቸዋልና ጥምረቱን ወይም ቅንጅቱን ከዚሁ ከመኢአድ ጋር ያድርጉ፡፡ መኢአድ ችግር የለበትም እያልኳቹህ አይደለም፡፡ ያለበትን ችግር የምታውቁት ነው፡፡ አማራጭ ስለሌለ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ከበጣም መጥፎ መጥፎን መምረጥ የግድ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ፓርቲውን ሀገር አቀፍ አድርገውት ቢሆን ለመጣመር ባልተገደዱ ነበር፡፡ መኢአድ ብቻ ሳይሆን ከደቡብ፣ ከሱማሌ፣ ከአፋር… አካባቢዎችም ሌሎች የሚታመኑ ተጣማሪዎችን መፈለግ ይኖርባቸዋል!!!

ነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ይደረጋል ተብሎ ባይጠበቅም ወይም ባይታመንም ነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ አለመደረጉን ማጋለጥ የሚቻለው ገብቶ በማየትና የሚሆነውን በማጋለጥ ነውና ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ባይሆንም በምርጫው መሳተፍ አስፈላጊ ነው!!!

መልካም ዕድል እንግዲል ባልደራሶች!!!

Filed in: Amharic