>

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የአቋም መግለጫ አውጥቶ ተጠናቀቀ!!! (ሀራ ዘ ተዋህዶ)

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የአቋም መግለጫ አውጥቶ ተጠናቀቀ!!!

ሀራ ዘ ተዋህዶ
ቅዱስ ሲኖዶስ: የኹለቱን ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ግድያ፥ “ክፉ እና ጭካኔ የተመላበት ድርጊት ነው” በማለት አወገዘ! እነበላይ መኰንን፥ “ተባርኮ የተሰጠን ጽላት[ፈይሳ አዱኛ] አለ” በማለት ሲናገሩ የቆዩት፣ ማደናገርያ እንደኾነ ምልአተ ጉባኤው በማረጋገጡ ምእመናን እንዳይሳሳቱ አሳሰበ
***
• ከየካቲት 9 እስከ 11 ቀን ድረስ፣ ለሦስት ቀናት ሲያካሒድ የቆየውን የምልአተ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ፣ ባለሰባት ነጥቦች ውሳኔ እና የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቀቀ፤
• በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 በቀድሞው ቀበሌ 24/18/16፣ ጥር 24 ቀን ለ25 አጥቢያ 2012 ዓ.ም. በኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ላይ የተፈጸመውን የግፍ ግድያ፣ “ክፉ እና ጭካኔ የተመላበት ድርጊት ነው” ሲል አወገዘ!!!
• መንግሥት፣ እንዲህ ዓይነቱን ክፉ እና የጭከና ድርጊት በፈጸሙት ወንጀለኛ አካላት ላይ ጥብቅ ምርምራ በማድረግ ውጤቱን ለምእመናን በሚዲያ እንዲገልጽ ጠየቀ፤
• በቀድሞው ቀበሌ 24/18/16፣ በቅዱስ ገብርኤል እና በቅድስት አርሴማ ስም መቃኞ ቤተ ክርስቲያን የተሠራበት ቦታ፣ ቤተ ክርስቲያን ከአራት ዓመታት በላይ ከመንግሥት ጋራ እየተነጋገረችና እየተጻጻፈች የቆየችበት፣ በታቦታት እና በከበሩ ንዋያተ ቅድሳት የከበረ እንዲሁም፣ በግፍ የተገደሉት ወጣቶች ደም የፈሰሰበት በመኾኑ፣ ወደ ክብሩ ተመልሶ፣ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶበት ምእመናን በሰላም አምልኳቸውን እንዲፈጽሙበት መንግሥት መመሪያ እንዲሰጥበት ጠየቀ፡፡
• በቤተ ክርስቲያን ላይ የተሳሳተ መረጃ ለሕዝብ በማስተላለፍ እና ስሟን በማጥፋት አገራዊ ቀውስ ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ያሉት፣ የኦኤምኤን፣ የኦቢኤስ እና የኤልቴቪ ብሮድካስት ሚዲያዎች ሓላፊዎች፣ በብዙኀን መገናኛ እና የመረጃ ነፃነት ሕግ መሠረት በሕግ እንዲጠየቁ፣ በቀጣይም ከመሰል ድርጊታቸው እንዲታቀቡ እንዲያደርግ መንግሥትን ጠየቀ፡፡
• “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እናዳራጃለን” በሚል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴያቸው፣ ከዛሬ ጀምሮ በንሥሓ እስኪመለሱ ድረስ ሥልጣነ ክህነታቸው የተያዘባቸው እነበላይ መኰንን፣ “ተባርኮ የተሰጠን ጽላት አለ” እያሉ ሲናገሩ የቆዩት፣ ሐሰተኛ እና ምእመናንን ማደናገርያ እንደኾነ በምልአተ ጉባኤው መረጋገጡን ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
• “እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት እና ደንብ ጽላት እንዲሰጣቸው አልጠየቁም፤ ከቤተ ክርስቲያናችንም የሰጣቸው አካል እንደሌለ በምልአተ ጉባኤው ተረጋግጧል፤” በማለት፣ ምእመናን ተሳስተው ከሚያሳስቱ ግለሰቦች፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናቸውንና ሃይማኖታቸውን ከምንጊዜውም በላይ እንዲጠብቁ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በአስቸኳይ ስብሰባ መግለጫው አሳስቧል፡፡
Filed in: Amharic