>

ጠ/ሚ/ር ቢኒያም ናትኒያሁ ከትውልደ ኢትዮጵያዊቷ "ጥቃት"አመለጡ...(ታምሩ ገዳ)

ጠ/ሚ/ር ቢኒያም ናትኒያሁ ከትውልደ ኢትዮጵያዊቷ “ጥቃት”አመለጡ…

 

(ታምሩ ገዳ)

የእስራኤሉ ጠ/ሚ/ር ቢኒያም ናትኒያሁ በምረጡኝ ዘመቻ ቅስቀሳ ላይ ሳሉ በአስተዳደራቸው ቅሬታ ከደረባት አንዲት ትውልደ ኢትዮጵያዊት ከተወረወረባቸው የፖም(Apple )ፍሬ መትረፋቸው ታወቀ።

የፊታችን መጋቢት/ማርች 2/2020 እኤአ በምድረ እስራኤል ለሶስተኛ ዙር ይካሄዳል ተብሎ የሚጣበቀው ምርጫን ለማሸነፍ ከትላንትና ወዲያ ወደ ቤታኒያ ከተማ ለቅስቀሳ ዘመቻ ያቀኑት ጠ/ሚ/ር ቢኒያም(ቢቢ) መምጣትን ሲጠባበቁ ከነበሩት መካከል አንዷ ከሆነችው ከብር ነሽ ዘሀበ ፖም የተወረወረባቸው ሲሆን ለጠ/ሚ/ሩ የተወረወረው ፖም (አፕልም )ኢላማውን ስቶ በሌላ ሰው ላይ ማረፉ ታውቋል። ድርጊቱን ፈጽማለች ተብላ የተጠረጠርችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ፣መምህርት ብር ነሽ ለጊዜው በፓሊስ ቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ ከተደረገባት በሁዋላ መለቀቋም ታውቋል። ሀኔታውን በመለከተ የእስራኤሉ ቴሌቭዥን 12 ጣቢያ ብርነሽን ከመኖሪያ ቤቷ በእብራይስጥ ቋንቋ አጭር ቃለመጠይቅ ያደረገላት ሲሆን ጋዜጠኛ ዳዊት ጅግኔ ቃላመጠይቁን በከፊል ተርጉሞታል።

ብርነሽ በጠ/ሚ/ር ቢኒያም ላይ ለምን የተቃውሞ ጥቃት ለመፈጸም እንደተነሳሳች ለቀረበላት ጥያቄ ስትመልስ” ከአቅም በላይ እንደክማልን ፣እንጣጣራለን፣ነገር ግን ኑሯችን ፈቀቅ አላልም።ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረጉን ደግሞ ከቀድሞው የጀርመኑ የናዚ ፓርቲ ከነበረው አዶልፍ ሂትለር የማይተናነሱት ጠ/ሚ/ር ቢቢ ናቸው”ስትል ውስጣዊ ብግነቷን ገልጻለች። ተቃውሞን ያልተቃወመው ፣ነገር ግን ንጽጽሩ ተገቢ ያለመሆኑን የገለጸው የቴሌቭዥን ጋዜጠኛው ቃለምልልሱን በአጭሩ ለመቋጨት ተገዷል። መምህርት ብርነሽም በአነገገሯ የተጸጸተች መሆኗን እና ከትምህርት ሚ/ር ኃላፊዎች ጋር ሰሞኑን ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን ጋዜጠኛ ዳዊት አክሎ ገልጿል።

የእኛ አገር የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ንግግር በሚያደርጉበት ስፍራዎች አንዳንድ ጊዜ ገጀራ፣ቆመጥ ዱላ ፣የእጅ ቦምብ እና ነፍጥ ተይዞ መውጣት እና ማስፈራራት ባይሆንም በምእራቡ አለም ታዋቂ ፖለቲከኞችን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ማሸማቀቅ እና አላማን ማሳካት የተለመደ ስልት ነው ለአብነት ያህል:-

“ከዳቦ በፊት ነጻነት ይቅደም…”:-

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እኤአ ግንቦት/ሜይ 2012 በተካሄደው የአለም የምግብ ፕሮግራም ሲንፖዚየም ላይ ተገኝተው ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት የቀድሞው ጠ/ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ በንግግራቸው መሐል ከቀድሞው የኢሳት ጋዜጠኛ አበበ ገላው”መለስ አምባ ገነን መሪ ናቸው ፣ከምግብ በፊት ነጻነታችን ይከበር፣ እስክንድር ነጋ ይፈታ “በማለት ድምጹን ከፍ አድርጎ ተቃውሞውን በማሰማቱ በሁኔታው ለጊዜውም ቢሆን ጠ/ሚ/ር መለስ መደናገጣቸው ባይካድም ጉዳዩ በአለማቀፋዊ መድረክ ከመነጋገሪያነት አልፎ የኢትዮጵያን የተቃውሞ ጎራውን ሞራል ማነቃቃቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ባለ አስር ቁጥሩ ጫማ…

የቀድሞው የአሜሪካው ፕ/ት ጆርጅ ቡሽ(ልጅየው) የ ስልጣን ዘመናቸው ሊገባደድ በተቃረበበት እኤአ ታህሳስ/ዲሴምበር 14,2008 የመጨረሻ የኢራቅ ጉብኝታቸው በሆነው ስነ ስርአት ባግዳድ ከተማ ውስጥ ለጋዜጠኞች መግለጫ በመስጠት ላይ ሳሉ መቀመጫውን ግብጽ ላደረገው አል ባግዳድ ቴሌቭዥን ጣቢያ ይሰራ የነበረው የሀያ ስምንት አመቱ ጋዜጠኛ ሙንታንዳር ኤል ዛይዲይ ተጫምቶት የነበረው ሁለቱን ጫማዎች ወደ ፕ/ት ቡሽ አከታትሎ በመወርወር “ይኼ ከኢራቃዊያን የሙት ቤተስቦች የተሰጦት የመሰናበቻ ስጦታ ነው” ሲል በአረቢኛ ቋንቋ ለፕ/ት ቡሽ እና ለአስተዳደራቸው ገልጿል።

ከጋዜጠኛው ጥንድ የጫማ ውርወራ ጎንበስ በማለት የተረፉት ቡሽም “ስለተከሰተው ሀኔታ የታዘብኩት ነገር ቢኖር የተወረወረብኝ ጫማ ቁጥሩ 42 (ሳይዝ 10)መሆኑን ብቻ ነው” በማለት ቀልድ ብጤ ጣል አድርገዋል።

በፕ/ት ቡሽ ላይ ጫማዎቹን የወረወረው ጋዜጠኛም ወዲያውኑ በጸጥታ ኃይሎች ቢታሰርም፣አንዳንድ ወገኖች “ድርጊቱ የአረቡ ማህበረሰብ የእንግዳ ተቀባይነትን ያንኳሰሰ ነው” በማለት ቢወቅሱትም በርካታዎች ግን ብሔራዊ ጀግናቸው አድርገው ከመቁጠር አልፎ ሴት ልጆቻቸውን እንዲያገባላቸው ጠይቀዋል፣ገንዘብ ሊሸልሙት ቃል ገብተዋል፣ በተወረወረው ጫማ አይነትም ትክሪት ከተማ ውስጥ የጫማ ሐውልት ተሰርቷል፣አንድ የጫማ አምራች እንዲሁ “የቡሽ ጫማ / The Bush Shoe/የተሰኘ ጫማ በጊዜው ለደንበኞቹ አቅርቧል።
(ታምሩ ገዳ)

Filed in: Amharic