>

በእኛ ዘንድ የአሸናፊዎች ታሪክ ተከድኗል! በሌሎች ዘንድ የተሸናፊዎች ኃውልት ቆሟል!!! (አሰፋ ሃይሉ)

በእኛ ዘንድ የአሸናፊዎች ታሪክ ተከድኗል!

በሌሎች ዘንድ የተሸናፊዎች ኃውልት ቆሟል!!!

 
አሰፋ ሃይሉ
 
 
‹‹ይህች ዓለም የሠላም መድረክ ሆናለች፣ በጦር የተጋደሉ ጀግኖች ተዋናዮቿ ከመድረክ ወርደዋል፣ ቃለመነባንባችንን የምናሰማው ከዳተኛ ተዋናዮቿ ነን፣ በመድረክ የቀሩት ጀግኖች ዝም ያሉት ዛፎች ብቻ ናቸው!››
               (— ስሙ ያልታወቀ የጥንት ፈላስፋ)
መጪው የካቲት 23 መላ ኢትዮጵያን የጀግኖች አባቶቻችንን የአድዋን ድል የምንዘክርበት ቀን ነው፡፡ የካቲት 23/1888 ዓመተ ምህረት ሀገራችንን አናስነካም ያሉ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በዘመናዊ አውሮፓዊ ጦርሠራዊት ፊት ራሳቸውን ስለ ሀገራቸውና ስለ ትውልዶቻቸው አሳልፈው ለመስጠት በፅናት የቆሙበት ዕለት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሌላውን ሊያጠቁ አይወጡም፡፡ ራሳቸውን ከሌላው ሊከላከሉ ግን በፅናት ይቆማሉ፡፡ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ምልክታችን ጋሻ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ በፍቅር የመጣብንን እናስተናግዳለን፣ በፀብ የመጣብንን ደግሞ – እቴጌ ጣይቱ የጣልያኑን ወኪል ካውንት አንቶኔሊን ‹‹የፈለግክበት ሂድ፣ ከፈለግክም ተመልሰህ አትምጣ፣ ተመልሰህ ስትመጣ፣ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን!›› እንዳሉት – በፀብ የሚመጣብንን ደግሞ ጋሻችንን ከፊት አድርገን በፅናት ለማይቀረው ሞት ተሰናድተን እንጠብቀዋለን፡፡
ከጦርነቱ አስቀድሞ አፄ ምኒልክ ለዓለም መንግሥታት በላኩት መልዕክት ‹‹ኢትዮጵያ የማንም እርዳታ አያስፈልጋትም፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› (“Ethiopia has need of no one; Ethiopia shall stretch forth its hands unto God!”)የሚል መልዕክት ነበር ያሰፈሩት፡፡ እውነትም ለኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያንና ከአምላካቸው በቀር ማንም አልደረሰም፡፡ ለኢትዮጵያ ልጆቿ ደረሱላት፡፡ አምላኳ ደረሰላት፡፡ እና በዓለም ታሪክ ሲዘከር የሚኖርን ታላቅ ድልን ተቀዳጀች፡፡ ፍትህና ሃቅ፣ ግፍንና ማንአህሎኝነትን ያሸነፉበት ድል ነው የአባቶቻችን የአድዋ ድል፡፡
ሰሞኑ የአድዋ ድል ሰሞን ነው፡፡ ኢጣልያ የኢትዮጵያውያን አባቶቻችንን ብርቱ ክንድ ስትቀምስ ግን አድዋ የመጀመሪያዋ አልነበረም፡፡ ኢጣልያኖች የኢትዮጵያውያንን መሪር ክንድ የቀመሱት – ከአድዋ ድል ዘጠኝ አመታት አስቀድሞ – እንደ አድዋ ባለ ማንአህሎኝነት – እና በእንግሊዞች የመሠሪነትና የመገፋፋት ሥራ – ተደፋፍረው የሀገራችንን ምድር በረገጡበት – በዶጋሊ ላይ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ያኔ ለብዙ ዘመን በእርስ በርስ ጦርነትና የእኔ እነግሳለሁ ፉክክር ተበጣጥሰው የቆዩት የኢጣልያ ግዛቶች ለአንድነት በተነሱት ባለራዕይ መሪዎቻቸው በእነ ጁሴፔ ማዚኒና ጋሪባልዲ ሀገራዊ አንድነታቸውን ተቀዳጅተው ብሔራዊ ጉልበታቸውን ማፈርጠም ሲጀምሩ – 30 ዓመት እንኳ አልሞላቸውም፡፡ በዚያች በ30 የአድንድነት ዘመናቸው እንደ ጥንታውያን ቅድመ አያቶቻቸው – ዓለምን እንዳስገበሩት እንደ ታላቋ ሮማ የጥንት ኃያላን ነገሥታት – እንደ ሌሎቹ ጎረቤቶቻቸው አውሮፓውያን – እንደ እንግሊዝና ፈረንሣይ ጀርመን ፖርቹጋል – እነርሱም ሌሎች ሕዝቦችን ወግቶ በቅኝ ግዛት ማስገበር አማራቸው፡፡ እና ግን – እግዚአብሔር ሊያስተምራቸው (የእጃቸውን ሊሰጣቸው) ሲፈልግ – ካላጡት ሀገር – ከጥንት ዘመን ጀምሮ በጀግንነታቸውና ለሀቅ ሲሉ አንገታቸውን በመስጠት ወደሚታወቁት ወደ ኢትዮጵያውያን ምድር አንቀዥቅዦ አመጣቸው፡፡
ወቅቱ በፈረንጆች 1887፣ በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር 1879 ጥር ወር ነበረ፡፡ በቀይ ባህር ላይ ወዲህ ወዲያ የሚሉ የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ወታደሮች አይዟችሁ እኛ አለንላችሁ ብለዋቸዋል የጣልያኖቹን ጀማሪ ቅኝ ገዢዎች፡፡ የግብፁ ፓሻ ሐሰን መሀመድም ከአምስት ሺኅ የሚበልጥ መድፈኞች በብዛት የተካተቱበት ጦሩን በምፅዋ ላይ አስፍሮ ከእንግሊዞች በተነገረው መሠረት ኢጣልያኖቹን ሽር ጉድ ብሎ ተቀብሎ መርቆ፣ ሰንቆ፣ ጥቁር አስካሪ ምንደኞችን ጨማምሮ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ዘልቀው የመጡበትን የማስገበር ተልዕኮ እንዲወጡ  አሳለፋቸው፡፡
የኢትዮጵያው ጀግና፡፡ የሐማሴኑ አንበሣ፡፡ የበዝብዝ አሽከር፡፡ ራስ አሉላ እንግዳ፡፡ ሰሙ የጥልያንን መሬት ታክኮ መምጣት፡፡ (ከዘጠኝ ዓመታት በኋላም መጣሁም አልመጣሁምም ሳይሉ፣ ጦርነት ሳያውጁ፣ ውስጥ ውስጡን አፈር እየማሱ ያገራችንን መሬት እየዘለቁ የሚገቡበትን አካሄድ አፄ ምኒልክ “እንደ ፍልፈል መሬት እየማሱ ወዳገራችን መጥተዋል” በማለት ነበር የገለጿቸው፡፡ ያኔም በአሉላ ዘመን እውነትም እንደ ፍልፈል ነበር የገቡት፡፡ መሬት እየቆፈሩ፡፡ መሬት እየታከኩ፡፡ በቁጥቋጦ መሐል እንጣጥ እያሉ፡፡
ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው ኢጣልያኖቹ ወደ 550 ጦር ሠራዊት ነበረ ወደ ኢትዮጵያ ያዘለቁት፡፡ ከምፅዋ የመለመሏቸውን ‹‹አስካሪ›› እየተባሉ የሚጠሩ ከኗሪዎቹ ሀበሾች በደሞዝ ቆርጠው አብረው ስንቅ እንዲሸከሙ፣ ጠብመንጃ እንዲወለውሉ፣ አጋሰሶቻቸውን እንዲጎትቱ፣ ሲከፋም ጠብመንጃ እንዲተኩሱ የሚቀጥሯቸውን መናጆዎችን አስከትለው ነበረ፡፡ የኢጣልያኑ ወራሪ ሠራዊት የጦር አለቃ ኮሎኔል ቶማስ ዲ ክርስቶፎሪ ይባላል፡፡ (ክርስቶስን ‹‹ካላየሁ አላምንም›› ያለውን ሃዋርያ – የቶማስን – ስም ከክርስቶስ ስም ጋር አጣምሮ የያዘ የጦር አዝማች ነበር የመጣብን!)፡፡ ቶማስ ዲ ክርስቶፎሪ የመጣበት ዓላማ – ይዞ የመጣውን ሠራዊት – ኢጣልያኖች በሰሃጢ ላይ ወደ ገነቡት ትልቅ ምሽግ ማድረስና – ሰሃጢ ላይ ያለውን ጦር አጠናክሮ – ወደ ኢትዮጵያ እስከቻሉት የረገጡትን መሬት እያስገበሩ ለመዝለቅ ነበረ፡፡
‹‹ንጉሥ ማራኪ፣ የቱርክ መድኃኒት፣ የደርቡሽ ጠላ፣ የተባለው አሉላ – ይህን ሰማ፡፡ እና ምንም አላወላወለም፡፡ የክርስቶፊ  አንዳንዶች ቅቤ አንጓቾች… አሉላ ለአፄ ዮሐንስም አላማከረም፣ አፄ ዮሐንስ ቢያውቁ ኖሮ ይከለክሉት ነበር… በማለት ፅፈዋል፡፡ ዋናው ነጥብ ግን አሉላ ጊዜ አላባከነም፡፡ ማቄን ጨርቄን አላለም፡፡ ወትሮም በአካባቢው ቱርኮች እያለ የሚጠራቸው ግብፆች ካሁን አሁን ይመጡብናል ብሎ ሃያ ሺህ ሠራዊቱን ይዞ ከቦታ ቦታ እየተሽከረከረ ሲያንዣብብ ነበር አሉላ እንግዳ – የሐማሴኑ ገዢ፡፡ የታሪክ ፀሐፊውና ደራሲው ማሞ ውድነህ – ለዶጋሊ መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል – በ1979 ዓመተ ምህረት ባሳተመው መጽሐፍ – በጉራዕ የነበሩ የራስ አሉላ ባለሟሎች ዘወትር ‹‹ምፅዋን ከቱርኮች እጅ አስለቅቄ፣ ፈረሴን ቀይ ባህር ላይ ሳላጠጣ አልመለስም›› ከሚለው የዘወትር የአሉላ ፉከራ ተነስተው እንዲህ  ብለው ገጥመውለት ነበረ ይለናል፡-
“ምፅዋን ከግብጾች ነጻ ሊያወጣት
ወደ እናት አገሩዋ እንዲመልሳት
አዞታል ዮሐንስ በጥብቅ አስጠንቅቆ
የኢትዮጵያን ወኔ ጀግንነት አስታጥቆ
ከቀይ ባሕር ውሃ ፈረሱ ሳይጠጣ
አይቀርም አሉላ የመጣው ቢመጣ”
እንግዲህ ጣልያኖችን እዝጌሩ የጣላቸው እንዲህ በመሠለ ኢትዮጵያዊ ጀግና እጅ ነበረ፡፡
እና አሉላ ያደረገው ነገር – የዘመኑ የወያኔ ታጋዮች ‹‹ቆረጣ›› የሚሉትን ነገር ነበረ፡፡ (የቆረጣው ምክንያት ግን ይለያያል፡- ልዩነቱ አሉላ የኢትዮጵያን ዳርድንበር ከወራሪ ለመከላከል ነበር ቆረጣን የተጠቀመው፣ ወያኔዎች ደግሞ አባቶቻቸው የተጋደሉለትን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ቆርሰው ለማስገንጠል ነበር! ይሄን ልዩነት ምንግዜም መዘንጋት አያስፈልግም!) የኢጣልያኖቹ ጦር ያሰበበት ሰሃጢ ላይ ከመድረሱ በፊት – አሉላ በቆረጣ ገስግሶ ሄዶ ዶጋሊ ላይ ጠበቀው፡፡
22 የጦር መኮንኖች ያሉበት የኢጣልያኖቹ 550 ሠራዊት (ከነአስካሪሶቹ) ልክ ዶጋሊ ላይ ሲደርስ – የአሉላ እንግዳ ሠራዊት – እንደ መብረቅ በላዩ ላይ ወረደበት!! ኢጣልያኖቹ የያዟቸውን መድፎች እራሱ ለመተኮስ ፋታውን አላገኙም ነበረ፡፡ በጠብመንጃና በጨበጣ ነበር ከጀግኖቻችን ጋር የተሞሻለቁት፡፡ በዚያ ሁኔታ የወገን ጦርና የወራሪዎቹ ጦር ለድፍን አራት ሠዓታት ያህል በነፍስ በሥጋ፣ ለሞትና ለህይወት፣ ለወረራና ለነፃነት ተፋለሙ፡፡
ከአራት ሰዓታት ቆይታ በኋላ በሐማሴኗ የኢትዮጵያችን የድል ምድር – በታላቋ ዶጋሊ ላይ የተገኘው ነገር – በመቶዎች የሚቆጠሩ ሀገራቸውን ብለው አንድያ ነፍሳቸውን የሰጡ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን አስከሬን ብቻ አልነበረም፡፡ ከሸሹትና ቆስለው በእንፉቅቅ ካመለጡት ወደ 80 የሚጠጉ ኢጣልያኖች በቀር – የቶማስ ክሪስቶፎሪ ወራሪ የኢጣልያ ሠራዊት – ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፍ – በዶጋሊ መሬት ግብዓተ መሬቱ ተፈፀመ፡፡
January 26, 1887፡፡ ጥር 19/1879 ዓመተ ምህረት፡፡ ያች ዕለት ኢትዮጵያኖች – ራሳቸውን ከኢጣልያኖች ወራሪ ጦር ለመከላከል – በጀግናው ራስ አሉላ እንግዳ ሠይፍ – ታላቅ ተዓምርን ያደረጉበት – ታላቅ የነፃነትን ፋና ያበሩበት – የአድዋን የማይቀር ድላቸውን ለሚያስተውል አስተዋይ ሁሉ በሩቅ ያመላከቱበት – ታላቅ የድላቸው ቀን ነበረ፡፡
ዶጋሊ በኋላ ኢጣልያኖቹ በዋና ከተማቸው በሮም እስከዛሬም ድረስ በክብር ቆሞ የሚገኝ መታሰቢያ ኃውልት አቁመዋል፡፡ ለማን? በኢትዮጵያው ጀግና በራስ አሉላ አባነጋ እጅ በዶጋሊ ላይ ለተሰዉባቸው ‹‹ጀግና›› ሠራዊቶቻቸው መታሰቢያነት፡፡ በእርግጥ ሁሉም የየራሱ ጀግና አለው፡፡ ለግፍ ዓላማ ሀገራቸው በሩቅ ምድር ባህር አሻግራ ብትልካቸው – ለእናት ሀገራቸው ሲሊ ተዋግተዋልና – ለወረራ ለላከቻቸው ሀገራቸው ሲሉ በሩቅ ምድር እየተፋለሙ የወደቁ እውነትም ጀግኖቻቸው ናቸው፡፡ ለእነዚያ ቢሸነፉም ግን ሞተው ለቀሩ ጀግኖቻቸው ጣልያኖቹ ኃውልት ሲያቆሙ – እኛስ ምን አደረግን?
እኛ ኢጣልያኖቹ በዋና ከተማቸው እንዳደረጉት እዚህ አዲስ አበባ ላይ ለአሉላ ድልና ለተሰዉት ኢትዮጵያውያን ኃውልት አቆምን? …እንዴት ተደርጎ!!!?? በየት በኩል?!! ያ ከሆነማ – ባጠገባቸው የአሉላን ኃውልት ቢያቆሙማ – የኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ ያላት አገር ናት ብለው – ኢትዮጵያ የኤርትራ ቅኝ ገዢ ናት ብለው – የኢትዮጵያን ሕዝብ አስገብረው አራት ኪሎ ቤተመንግሥትን በጠመንጃቸው፣ መላውን ኢትዮጵያ ደግሞ በተገንጣይነት ስነልቦናቸው የተቆጣጠሩት ወያኔ-ኢህአዴጎች – እንዴት እንቅልፍ ይወስዳቸዋል??
እኛ ያደረግነው ነገር ግልፅ ነው፡- እኛ ያደረግነው – የኢትዮጵያ ታሪክ የ100 ዓመት ታሪክ ነው ብሎ – የጀግኖቹን ኢትዮጵያውያን የእነ ራስ አሉላን የጀግንነት ፍልሚያ፣ እና ድል፣ እና የነጻ ሕዝቦች ብሥራት፣ እና ታሪክ ሙልጭ አድርጎ የካደው ወያኔ የሚባል የኢትዮጵያ ባንዳ – ስለ አሉላ ጀግንነትም ሆነ ስለኢትዮጵያውያኑ መስዋዕትነት ላያነሳ እርም ብሎ ምሎ – ሐማሴንን፣ ዶጋሊን፣ ሰሃጢን፣ ሀገሩን ሁሉ – ለሻዕቢያ መርቆ ሰጥቶ ከእናት ሀገሩ ከኢትዮጵያ አስገነጠለው!!!!! በዚህች በኢትዮጵያችን የቅርብም ሆነ የሩቅ ዘመን ብዙ ታሪኮች ተከናውነዋል፡፡ እንደ ወያኔ ያለ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ታላቅ እፍርት የተጫወተ እፍርታም ፍጡር ግን ይህች ምድር አፍርታ አታውቅም!! ለወደፊትም የምታፈራ አይመስለኝም!!
ደግነቱ ‹‹ኤርትራ›› ተባልንም ‹‹ኢትዮጵያ›› አንድ ቀን የሀበሻ ሕዝቦች ሁሉ ከአንድ እናት ማህፀን የፈለቁ፣ ለዘመናት በጋራ አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ በመከራም በደስታም ዘመናትን የዘለቁ ሕዝቦች መሆናቸውን የሚያይ ባለራዕይ ትውልድ፣ ያን በወያኔና ሻዕቢያ ሸፍጥ የተዳፈነ እውነተኛ ዝምድናና አንድነታችንን የሚያይና የሚረዳ ነቄ ትውልድ በሚፈጠርበት በአንዱ ቀን ላይ – የወያኔ ክህደት እየተወገዘ – እየተኮነነ – የአንድ እናት ወንድማማች፣ እህትማማች ሕዝቦች በአንድ ባንዲራ ሥር ለጋራ ብልፅግና በጋራ የሚሠለፉበት ቀን መምጣቱ አለመቅረቱ ነው!! እርግጠኛ ነኝ አይቀርም ያ ታሪካችን ከከሃዲያን ታሪክ ተላቆ የጀግንነት የጋራ ታሪካችን የሚታወስበት፣ ደማችን የሚታደስበት ቀን!! ያ ቀን አይቀርም!!! እስከዚያው – ይሁን ብለን – ዝምምምምም አልን፡፡
‹‹ይህች ዓለም የሠላም መድረክ ሆናለች፣ በጦር የተጋደሉ ጀግኖች ተዋናዮቿ ከመድረክ ወርደዋል፣ ቃለመነባንባችንን የምናሰማው ከዳተኛ ተዋናዮቿ ነን፣ በመድረክ የቀሩት ጀግኖች ዝም ያሉት ዛፎች ብቻ ናቸው!››   (— ስሙ ያልታወቀ የጥንት ፈላስፋ)
“አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ
ጎበናን ከሸዋ፣ አሉላን ተትግሬ
ስመኝ አድሬአለሁ፣ ትናንትና ዛሬ
አሉላን ለጥይት ጎበናን ለጭሬ
ተሰባሰቡና ተማማሉ ማላ
አሉላ ተትግሬ ጎበና ተጋላ፡፡
“ጎበና ሴት ልጁን ሲያስተምር ፈረስ
አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሲያስተኩስ
አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ
ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ፣ የእምቧይ ካብ፡፡”
ይህ ግጥም ብላቴን ጌታ መርስኤ ኀዘን ወ/ቂርቆስ፣ ‹‹የአማርኛ ሰዋስው›› በሚል ርዕስ፣ በ1919 ዓም ካሳተሙት መጽሐፍ፣ ‹‹ወርቃ ወርቅ የአማርኛ ቅኔ›› ከሚለው ክፍል የተገኘ- ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የገጠሙት ነው፡፡ (ግጥሙ የተጠቀሰው፡- በደራሲ ማሞ ውድነህ፣ ለዶጋሊ ድል መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ከተዘጋጀው ‹‹አሉላ አባ ነጋ›› ከተሰኘው፣ በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት፣ በ1979 ዓም፣ በአዲስ አበባ ከታተመው ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሐፍ፣ ገጽ 15 ላይ፡፡)
ሀገራቸውን ለሚወዱ፣ እና ቤዛ ሆነው ሀገራቸውን ሕዝባቸውን ከወራሪዎች ባርነት ላዳኑ፣ ደማቸውን በምድራችን እንደ ውሃ ላርከፈከፉ፣ ክቡር፣ ደግ፣ ሩህሩህ፣ ጀግና ሀበሻ አባቶቻችን፣ አያቶቻችን፣ ቅድመአያቶቻችን – ነፍሳቸው ባረፈችበት የሠማያት ቅፅር – የበዛ ሠላም፣ የበዛ ክብር፣ የበዛ እረፍትና ምስጋና ይሁንላቸው!!
ክብር ለሀበሻ ጀግኖች!
ክብር ለጀግኖች አባቶቻችን!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!! 
______________
ምስሉ ኢጣልያኖች – በሮማ ከተማ – ከአድዋ ድል አስቀድሞ – በJanuary 26, 1887 (በጥር 19/1879 ዓ.ም.) – በበዶጋሊ ለሞቱባቸው 500 ሠራዊቶቻቸው ያቆሙት የመታሰቢያ ኃውልት (dogali-obelisk-in-baths-of-diocletian-rome)!
Filed in: Amharic