>

ተነሱ. . . . እናንት የባቢሎን ምርኮኞች ! (አሰፋ ሃይሉ)

ተነሱ. . . . እናንት የባቢሎን ምርኮኞች !

 

አሰፋ ሃይሉ
* በዛሬ ዘመን – ዘረኝነት አገንግኖብናል፣ አጠላልቶናል፣ አናክሶናል፣ ወደፊትም ያጠፋፋናል፣ ዜጋ በቋንቋ አይሸንሸን፣ በዘር፣ በደም፣ በጋብቻ፣ በትውልድ፣ በጎጥ፣ በብሔር፣ በነገድ አይከፋፈል፣ ዜግነት እና የዜግነት መብት ለሁሉም እና ለያንዳንዱ ዜጋ ከነሙሉ ጥቅሙና ክብሩ ይሰጥ – ለጋራ ሀገር የምንሠራ የአንድ ሀገር ዜጎች እንሁን – ብሎ ማለት … ይህም ‹‹ደርግ›› ከሚባለው መንፈስ ጋር በምርኮ ተይዟል!
—–
በቅዱስ መጽሐፍ የምናገኛቸው የጥንት እስራኤላውያን አንድ ከሁሉም የፈጣሪ ቁጣዎች እጅግ የሚጠሉት ቁጣ አለ፡፡ ምርኮ፡፡ ለሌሎች ተላልፎ መሰጠት፡፡ ለአሶራውያን ተላልፎ መሰጠት፡፡ ለባቢሎናውያን ምርኮ መሰጠት፡፡ ለሮማውያን ምርኮ መሰጠት፡፡ ለግብጻውያን ምርኮ መሰጠት፡፡ ለፋርስ ምርኮ መሰጠት፡፡ ለእስራኤላውያን የፈጣሪያቸው የእግዚአብሔር የመጨረሻው ትልቁ ቅጣት ሕዝበ እስራኤልን ለአረመኔዎች ምርኮ አሳልፎ መሰጠት ነው፡፡ የበዙ የአይሁዳውያን ፀሎቶች ፈጣሪያቸውን በአሕዛብ እጅ አሳልፎ እንዳይሰጣቸው የሚለምኑባቸው፣ አሊያም አሳልፎ ስላልሰጣቸው የሚያመሰግኑባቸው ናቸው፡፡
ብዙዎቹ የእስራኤል ነቢያት ንጉሦቻቸውንና ሕዝባቸውን ከጎደፈ የኃጥያት አኗኗር ለመመለስ የሚጠቀሙበት ውጤታማ ማስፈራሪያ እስራኤል በአረመኔዎች (ወይም በኢ-አማኞች) እጅ ተላልፋ ልትሰጥ እንደሆነ ትንቢትን በመናገር እንደነበረ እንገነዘባለን፡፡ ነብዩ ኤርምያስ እስራኤላውያን ለ70 ዓመት ለባርነት ተላልፈው የሚሰጡበት የባቢሎን ምርኮ እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ ሆሴዕ፣ እዝራ፣ ኢሳያስ፣ ሣሙኤል፣ አሞፅ፣ ዳንኤል፣ እየሱስ ክርስቶስ ራሱ፣ እና ሌሎችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኛቸው የበዙ የእስራኤል ቅዱሳን በሕዝበ እስራኤል ላይ ሊመጣባቸው ያለውን ምርኮ አስቀድመው የሚያስጠነቅቁ ነበሩ፡፡
ለዚህ ነው – እስራኤላውያን 70 ዓመታት ከቆየው የባቢሎን ምርኮ ነፃ ወጥተው ወደ ቅድስቲቱ እየሩሳሌም በመመለስ ታላቁን የሠሎሞንን ቤተመቅደስ ዳግም ለማነፅ የበቁበትን ዘመን ከዘመኖቻቸው ሁሉ ታላቁን ፍስሃ እንዳገኙበት ስኬታቸው አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ምክንያቱም በምርኮ ተላልፎ እንደተሰጡ የመቅረትንም የባሰ መቅሰፍት ስላዩት፡፡ በአሶራውያን እጅ በምርኮ ተላልፈው የተሰጡ አስር የእስራኤል ነገዶች እየሩሳሌምን ለዘመናት እንደናፈቁ በመካከለኛም ምስራቅ በየተበተኑበት የምርኮ ምድር እንደጨው ቀልጠው ቀርተዋል፡፡ ምርኮ አስከፊ ነው፡፡ ግን ለእስራኤላውያን ብቻ አይደለም፡፡ ለሰው ልጅ ሁሉ፡፡
ይህን እንድል ያስቻለኝ ይህ ፎቶ ስለተማረከው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ እና ስለ ምርኮ ዘመናችን የጫረብኝ ምስል ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው፡፡ ወቅቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ የሥርዓቱ ጠባቂዎች ብዙ ዜጎችን ለሞትና ለእስር የዳረጉበት ወቅት ነበር፡፡ በዚሁ በፌስቡክ ላይ አንዱ ፀሐፊ፡- ‹‹ወያኔዎች የት የተዋጉትን ነው፣ በሻዕቢያ ታዝለው አይደል ወይ አዲሳባ የገቡት፣ አብዮታዊ ሠራዊታችን ቢፈልግ ኖሮ ድባቅ ይመታቸው ነበር፣ ምናምን… ›› እያለ የኩነኔና የስድብ ውርጅብኙን ‹‹ወያኔዎች›› ባላቸው የሥርዓቱ ጌቶች ላይ ያወርዳል፡፡ ይህን ያነበበ አንዱ የወያኔ ደጋፊ ደግሞ የሰጠው መልስ ባሰብኩት ቁጥር ሁሌ ያስገርመኛል፡፡
መላሹ ይሄን የሻዕቢያ ታጋይ የኢትዮጵያን ወታደር የሚማርክበትን ትንሽ መጠን ያለው ፎቶ ከጸሐፊው ፖስት ሥር ካስገባ በኋላ እንዲህ የሚል ምላሽ አስፍሮለታል፡- ‹‹ጀግናው የወያኔ ታጋይ፣ ያንተን ደርግ እንደዚህ አስቀዝኖ ነበር የማረከው፣ ጠይቃቸው ደርግ አባቶችህን..!››፡፡ ቃለ ምልልሱ ይኸው ነበር፡፡ (የሚገርመው በፎቶግራፉ የሚታየው ማራኪ የወያኔ ሳይሆን የሻዕቢያ ‹‹ታጋይ›› (ጀሌ) ነበር፡፡ ፎቶውን ያነሳውም ሻዕቢያዎቹ እይልን ድላችንን ብለው ከአውሮፓ ያስጠሩት ማርቲን ፕሎት የተባለ ጋዜጠኛ ነበር፡፡)
ገረመኝ በወቅቱ፡፡ አሁንም ይገርመኛል ሳስበው፡፡ በዚህች ሀገር እኮ – እስካሁንም – እኩል መብት ያለው – እኩል አሸናፊ – እኩል ተሸናፊ የሆነ – የጋራ ውርደትና የጋራ ሥኬት ያለው ዜጋ የለም፡፡ ሥርዓት የለም፡፡ መንግሥት የለም፡፡ በዚህች ሀገር አንዱን የሚያመውና የሚያንገበግበው የቁጭቱና የሀዘኑ ምንጭ የሆነ ክስተት – ለሌላው ደግሞ የሚያስፈነጥዘውና የሚያኮራው የድሉ፣ የጭፈራው ምንጭ ነው፡፡
በዚህች ሀገር ሁለት ዓይነት ሕዝብ ነው ያለው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ‹‹ደርግ›› በሚል የወል (የጋራ) መጠሪያ ስም የማረከው ወያኔና – ‹‹ደርግ›› በሚል የወል (የጋራ) መጠሪያ የተማረከው ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ፡፡ ማራኪና ተማራኪ ተዳብሎ የሚኖርባት ሀገር ነች ያለችን፡፡ የጥንት እስራኤላውያን በምርኮ ተይዘው ወደ ማረኳቸው ሕዝቦች ምድር ነበር የተጋዙት፡፡ ለዚያም ነው ከምርኮ ምድራቸው ወደ ነፃነጽ ሀገራቸው ለመመለስ ኁሌም ይናፍቁ የነበሩት፡፡ የእኛ ሕዝብ ግን የተማረከው በገዛ ሀገሩ ላይ ነው፡፡ በምርኮ እየተገዛ ያለውም በራሱ የነፃነት ምድር ላይ ነው፡፡
በእኛ ሀገር – ሁሉም በአንድ ምድር ላይ ያለ ሕዝብ – በሁለት ተከፍሎ ነው የሚገኘው፡፡ የአንድ ሀገር ዜጎች ሁለት ቦታ በተከፈለ ቤት ውስጥ የደባል ኑሮ ነው የምንኖረው፡፡ ልክ እንደ ጥንት ሮማውያን አስገባሪዎችና አይሁዳውያን ተገዢዎች በአንድ ምድር በጌታና ሎሌነት ተከባብረው እንደሚኖሩት ባለ ግንኙነት – ገሚሱ ምርኮኛ – ገሚሱ ማራኪ ሆኖ ይኖራል በእኛም ሀገር፡፡
በሕይወቴ አጋጣሚ በአብዛኛው እግር ጥሎኝ ካወቅኳቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ውሰጥ – የወያኔ ‹‹ታጋዮች›› እና የሥርዓቱ ደጋፊዎች ድል አደረግንበት የሚሉትን ‹‹ግንቦት ሃያ ቀንን›› የድላችን ቀን ነው ብለው በደስታ የሚያከብሩት አስር ፐርሰንት እንኳ አይሞሉም፡፡ ይሄ እንግዲህ – በራሴ ሕይወት እንኳ ሳምፕል ወስጄ ስመዝነው – አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከነአስተሳሰቡ ‹‹ደርግ›› በሚለው ከረጢት ውስጥ ተከትቶ በማራኪዎቹ መዳፍ ውስጥ በገዛ ሀገሩ ላይ በግዞት የሚመላለስ የምርኮ ኗሪ መሆኑን ያረጋግጥልኛል፡፡
ሌላ ቀርቶ ‹‹ሕዝቡና ፓርቲው የአንድ ሳንቲም ሁለት ግልባጭ ማለት ነው›› እየተባለ በወያኔዎች በሚፎከርበት ሰሜናዊ ምድር ላይም ሄደህ ከእኩዮችህ ጋር በፅሞና ተቀምጠህ ሳለ … በጨዋታችሁ መሐል ‹‹ግንቦት ሃያ፣ ገለመሌ…›› ብለህ ወሬ ብትጀምርባቸው… በእርግጠኝነት ብዙዎቹ አኩርፈውህ በዚያው ተቀይመው ይቀራሉ፡፡ ተመልሰው ወደ አንተ ከመጡ ግን ‹‹ፋራ ነው! ጌጃ ነው! አዝግ ነው! ምን ይደረግ?!›› ብለው ደምድመው መሆኑን እርግጠኛ ሁን፡፡ የምናገረው እውነቱን ነው፡፡
ይሄ እውነት – ጨቋኙና ዘራፊው የወያኔ-ኢህአዴግ ሥርዓት – ከአሁኑ ትውልድ መንፈስ – ምን ያህል እንደተነጠለና ኋላ እንደቀረ የሚያመላክት ነው፡፡ በሌት ተቀን ሊያጠፉን ነው ፕሮፓጋንዳና፣ በድረሱልኝ ጥሪ እየተመራ.. በየጎሳውና በየብሔሩ በነቂስ ሲወጣ የምናየው ወጣት… እውነተኛ መንፈሱ ከዚህ የማራኪና ተማራኪ መንፈስ የተነጠለና የራቀ ነው፡፡ እናም ያ በአንድ ዘመን አላዋቂ ሰዎችን ለመጫረስ ዘመቻ ያነሳሳ የደርግ እና የፀረ-ደርግ ኩሸት በአሁን ዘመን ትውልድ ልብ ውስጥ አንዳችም ቦታ የለውም፡፡ ያለፈ ታሪክ ሆኗል፡፡ ያውም በውሸት የታለፈ ታሪክ፡፡ እውነታው ይሄ ነው፡፡
ሳስበው – ያ ከአመታት በፊት ‹‹ጠይቃቸው የተማረኩትን ደርግ አባቶችህን.. ብሎ በፌስቡክ ምላሹን የሰጠው የወያኔ ደጋፊ በትክክል አና በእውነት የሥርዓቱን የማይታበል አስተሳሰብ ገሃድ ያወጣ ይመስለኛል፡፡ አንደኛ ነገር – ወያኔዎቹ (ከብአዴኖችና ከሌሎችም መናጆዎቻቸው ጋር ሆነው) እስካሁንም ድረስ – ተዋግተው፣ አድምተው፣ አቁስለው፣ ማርከው፣ ቀብረው ያስቀሩትን ኢትዮጵያዊ – ‹‹ደርግ›› ነው ብለው የደመደሙ፣ በውሸት ኖረው፣ በውሸት ያፈጠጡ ማራኪዎች ናቸው፡፡
ለእነዚህ ብዙሃኑን ሕዝብ እንደ ምርኮኛቸው ለሚመለከቱ ገዢዎች – ‹‹ደርግን ማረክንበት›› በሚሉት ግዳያቸው – የገዛ ሀገሩን ከእነርሱ አስከፊ የዘረኝነት ጋኔን፣ ከእነሱ ሀገርን የመገነጣጠል ጋኔን፣ ከእነርሱ ኋላ ቀር የጋርዮሽ ዘመን አገዛዝ ሊከላከል የወጣን ብዙሃኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደተዋጉ ለአፍታ አይከሰትላቸውም፡፡ ማረክነው የሚሉት ሕዝብ ከእነርሱ ይበልጥ አስተዋይነት ያለውንና በተሻለ የአስተሳሰብ ሥልጣኔ ላይ ያለውን ሕዝባቸውን እንደሆነ አይከሰትላቸውም፡፡ ምክንያቱም እውነቱ ፈፅሞ እንዳይከሰትላቸው ምለዋል፡፡ ቢከሰትላቸውም እውነቱ ስለሚጎረብጣቸው በውሸታቸው ላይ የሙጥኝ ብለው መቅረትን መርጠዋል ማለት ነው፡፡
ሁለተኛ ነገር አሁን እየገዙትን ያለውን ሕዝብ በምርኮ እንደያዙት ሕዝብ ነው የሚያስቡት፡፡ የትግል አጋርነትና አብሮነት የሚሰማቸው ማርከው በቁጥጥራቸው ሥር አውለው ከሚገዙት ሕዝብ ጋር ሳይሆን – አዝሎም አንጠልጥሎም እዚህ ሕዝብ ጀርባ ላይ ካፈናጠጣቸው ከሻዕቢያ ጋር ነው፡፡ አሊያም ሀገሩን ክዶ እነርሱ በሚጠሩት ቃል ‹‹ታጋይነትን›› ከተጋራቸው ዜጋ ጋር ብቻ ነው፡፡ ሌላው ይህን የሚቃረን አስተሳሰብ የተሸነፈው የደርግ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሌላው ሕዝብ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ሕዝብ ነው፡፡ ሌላው ከወያኔ የዘረኝነት አስተሳሰብ ውጭ ሆኖ መኖርን የመረጠ ሕዝብ ‹‹የደርግ ርዝራዥ›› ነው፡፡
ይገርማል የኛ ነገር!! ከእርሱ አስተሳስብ ውጪ ያለን የአንድን ትልቅ ሀገር ሕዝብ አሁን እንዳለና ከእርሱ እኩል የዜግነት መብት የሚገባው ዜጋ ሳይሆን – እንደ አንድ መብት እንደሌለው ግዑዝ አካል – እንደ አንድ የተሸነፈ እርኩስ መንፈስ ‹‹የደርግ ርዝራዥ›› አድርጎ እየቆጠረ – ከ1983 ዓመተ ምህረት ጀምሮ እስከ ዛሬ ብቻውን (እና ከመሰሎቹ ጋር) ሕዝብና ሀገርን በምርኮ ይዞ እየገዛ የኖረ በኢ-አማኞች (አረመኔዎች) የተሞላ ገዢ አለ፡፡ በዚያ አረመኔ ገዥ እጅ ውስጥ ወድቀን እንኖር ዘንድ እስከዛሬም ድረስ የተፈረደብን – በገዛ ሀገራችን በነፃነት መራመድ የማንችለው፣ የራሳችንን ቤተመቅደስ ማነፅ የማይፈቀድልን፣  በባቢሎን ምርኮ ተላልፈን የተሰጠን ደግሞ ብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን አለን በሌላ በኩል፡፡
በዛሬ ዘመን – ኢትዮጵያውያንን በአንድ ብሔራዊ ሀገራዊ ስሜት ሥር አሰባስበን – ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ ጫፍ እስከ ምሥራቅ – በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያለውን ሕዝባችንን እና አንጡረ ሃብታችንን አስተባብረን – በየትኛውም ዓለም ያለውን ዜጋችንን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር አሰባስበን፣ ሀገራችንን እና ሕዝባችንን አንድም ሳናስቀር እንዲያልፍለት፣ ለሁላችንም የምትመቸን በዕውቀትና በሀብት የበለፀገች – ከዘረኝነት የፀዳች – ታላቅ የሆነች ኢትዮጵያን ለመመሥረት እገሌ ከእገሌ ሳንባባል አብረን በጋራ እንቁም – ብሎ ማለት – ደርግነት ነው፡፡ ይህ የሀገራዊ አንድነት አስተሳሰብ፣ ይህ ሀገራዊ ብሔራዊ የጋራ ዓላማን የመፍጠር አጀንዳ… ይህም ‹‹ደርግ›› ከሚባለው መንፈስ ጋር በምርኮ ተይዟል፡፡
በዛሬ ዘመን – ዘረኝነት አገንግኖብናል፣ አጠላልቶናል፣ አናክሶናል፣ ወደፊትም ያጠፋፋናል፣ ዜጋ በቋንቋ አይሸንሸን፣ በዘር፣ በደም፣ በጋብቻ፣ በትውልድ፣ በጎጥ፣ በብሔር፣ በነገድ አይከፋፈል፣ ዜግነት እና የዜግነት መብት ለሁሉም እና ለያንዳንዱ ዜጋ ከነሙሉ ጥቅሙና ክብሩ ይሰጥ – ለጋራ ሀገር የምንሠራ የአንድ ሀገር ዜጎች እንሁን – ብሎ ማለት … ይህም ‹‹ደርግ›› ከሚባለው መንፈስ ጋር በምርኮ ተይዟል፡፡
የፖለቲካ ነፃነት ይኑረን – ሰዎች ያመኑበትን ሃሳብ ያራምዱ – ዲሞክራሲ ይስፈን – በሕዝብ የተመረጡ እውነተኛ ሰዎች ይምሩ – መንግሥት በዳኝነት ሥራ ጣልቃ አይግባ፣ መንግሥት በሐይማኖት ሥራ ጣልቃ አይግባ፣ መንግሥት አንድን አስተሳሰብ ቅዱስ አድርጎ በሕገ መንግሥት ቀርጾ ሌላውን እርኩስ አድርጎና ‹‹ደርግ›› ‹‹ንጉሣዊ›› ‹‹ትምክህታዊ›› ‹‹ጠባባዊ›› ‹‹ፋሺስታዊ›› ወዘተ የሚል ቅፅል እየለጠፈ በአድልዎ ላይ መሠረቱን አይገንባ፣ ለሁሉም ዜጋ የሚሆን ሀገር ይፍጠር፣ አንዱ አሸናፊና ማራኪ፣ ሌላው ተሸናፊና በምርኮ የተያዘ የሆነችው ኢትዮጵያ ትብቃን ብሎ ማለት በአሁን ጊዜ … ይህም ‹‹ደርግ›› ከሚባለው መንፈስ ጋር በምርኮ ተይዟል፡፡
ከሌብነትና ከሙስና ከዝርፊያ የፀዳ የሀገር አስተዳደር እናቋቁም፣ ሕዝብ በነፃ ይምረጥ – የፀረ ሙስና ሕዝብ ለመረጣቸው ተወካዮቹ ተጠሪ ይደረግ – ሀብት ግልፅ ይሁን – የሀብት ማግኛ መንገዶች ግልፅ ይሁኑ – ሕዝብ ሁሉ፣ ዜጋ ሁሉ፣ ግለሰብ ሁሉ – ሁሉም ጥሮ ግሮ በእኩል ተወዳድሮ የሚያልፍለት ሀገር እንመስርት – ሥልጣንን የዝርፊያና የጥቅሞች ሁሉ ምንጭ ማድረግ ይብቃ ብሎ ማለት – ይህም ‹‹ደርግ›› ከሚባለው መንፈስ ጋር በምርኮ ተይዟል፡፡
ከግል ጥቅም በላይ ለሀገር ጥቅም ማሰብ – ይህም ‹‹ደርግ›› ከሚባለው መንፈስ ጋር በምርኮ ተይዟል፡፡ ከአንድ ብሔርና ጎሳ በላይ ለአጠቃላይ ለሀገርና ሕዝብ እናስብ ማለት – ይህም ‹‹ደርግ›› ከሚባለው መንፈስ ጋር በምርኮ ተይዟል፡፡ የዘርና የዘረኝነትን አስተሳሰብ ከመንግሥት ሥርዓት ውስጥ እናውጣ ማለት – ይህም ‹‹ደርግ›› ከሚባለው መንፈስ ጋር በምርኮ ተይዟል፡፡ አጠቃላዩን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ዳር ድንበር የሚያስከብረው የጦር ሠራዊታችን ከብሔርና ከጎሳ ሽንሸናና አስተሳሰብ ይውጣ፣ ሁሉም ለኢትዮጵያዊነት ዘብ ይቁም ብሎ ማለት – ይህም ‹‹ደርግ›› ከሚባለው መንፈስ ጋር በምርኮ ተይዟል፡፡
እንግዲህ በዚህ ዓይነት – ሁሉም መልካም ሀገራዊ ነገሮቻችን ሁሉ ‹‹ደርግ›› በተባለ ሁሉንም ዓይነት በሰማይ በምድር የማይገናኙ ነገሮችን ሁሉ አነባብሮ በሚይዝ ትልቅ የፈጠራ ኮሮጆ ውስጥ ገብተው – በምርኮ ተይዘዋል ማለት ነው፡፡ መልካም ነገሮቻችን ሁሉ – ያውም በገዛ ምድራችን ላይ – በአካሉም በመንፈሱም እራሱን እንደ ሕዝቡ አካል አድርጎ ለማያይ አረመኔ ዘረኛ የባቢሎን ገዢ በምርኮ ተላልፈው ተሰጥተውብናል፡፡ ለእስራኤላውያን የባቢሎን የምርኮ ዘመናቸው በ70 ዓመቱ አብቅቶላቸዋል፡፡ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ባቢሎናዊው የምርኮ ዘመናችን መቼ እንደሚያበቃ አንድዬ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡
ባቢሎን የትግል ጥሪ ምልክት ነው፡፡ ባቢሎን – የሰው ልጅ ሰብዓዊ የአዕምሮና የመንፈስ ኃይሉን ለተሻለ የሰውን ልጅ ጥቅምና ክብር ከፍ በሚያደርግ ተግባር ላይ እንዳያውለው – በላዩ ላይ የተጫነበትን ኋላቀርና አረመኔ የጭቆና መዳፍ – ከላዩ ላይ ለመበጣጠስ፣ እና ራሱን እንደ ሰው፣ እንደ ዜጋ፣ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ነፃ ለመውጣት – ማድረግ ያለበትን ታላቅ ትግል የሚያመለክት የትግል ጥሪ ቃል ነው፡፡ Babylon symbolizes an oppressor against which righteous believers must struggle!  ….. Babylon is calling, Ethiopia is falling! በባቢሎን ምርኮ ያላችሁ ያገሬ ልጆች ሆይ – ተነሱ ለነፃነታችሁ!
“ተነሱ እናንት የርሃብ እስረኞች
ተነሱ የምድር ጎስቋሎች
ፍትሕ በሚገባ ይበየናል
ሻል ያለ ዓለምም ይታያል፡፡
“ከእንግዲህ ባለፈው ይብቃን እስር
ተነሱ ባሮች ጣሉ ቀንበር
የዓለም መሠረት አዲስ ይሁን
ኢምንት ነን እልፍ እንሁን፡፡
“የፍጻሜው ጦርነት ነው
ሁሉም ዘብ ይቁም በቦታው
የሰው ዘሮች በሙሉ
ወዝ አደር ይሆናሉ!
“የፍጻሜው ጦርነት ነው
ሁሉም ዘብ ይቁም በቦታው
ኢንተርናሲዮናል
የሰው ዘር ይሆናል!”
  (— የኢንተርናሲዮናል መዝሙር)
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic