>

የአየር መንገዱ ውሳኔ እና የዓባይ ድርድር ጉዳይ!!! (ቅዱስ ማህሉ)

የአየር መንገዱ ውሳኔ እና የዓባይ ድርድር ጉዳይ!!!

ቅዱስ ማህሉ
 

* ፈተናዎች እና መፍትሄዎች!

 
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ4ቢሊዮን ዶላር በላይ እዳ አለበት።ከዚያ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከቻይና የተገኘ ነው። አየር መንገዱ ሲሽጥ የባለቤትነት ትልቅ ድርሻ ከሚኖራቸው ውስጥ ናት። በተጨማሪም በቻይና ብድር በግንባታ ላይ ያለ የማስፋፊያ ፕሮጀክትም በስራ ላይ ነው። ስለዚህ ከአየር መንገዱ እና ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት   በተጨማሪ ቻይና በአየር መንገዱ ውሳኔዎች ላይ በቀጥታ ተጽእኖ አትፈጥርም ማለት አይቻልም።
አየር መንገዱ ካለበት እዳ አንጻር ከስሙ በቀር ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ነው ማለትም ይከብዳል። ውሳኔውን ቢቀለብስ ከቻይና የሚደርስበት ጫና ቀላል አይደለም። የኬንያ አየር መንገድ እንደዚያ ዓይነት የእዳ ቁልል ሳይኖርበት እንኳ ቻይና በመንግስት ላይ ጫና እያሳረፈች ነው። ሆኖም ያ ከእኛ ብቻ ሳይሆን ከብዙ የአፍሪካ ሃገራት አንጻር የህግ በአንጻራዊነት የህግ የበላይነት የሰፈነበት ሃገር ስለሆነ ህዝብና ሃገርን ለአደጋ የሚያጋልጥን የፖለቲከኞች ውሳኔ መቀልበስ የሚችል የፍትህ ስርዓት አላቸው።
ከትናንቱ የኬንያ ፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ የቻይና መንግስት በኬንያ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ብዙም የሚቀይረው ነገር ስለማይኖር ባለስልጣናቱ አሁን ተረጋግተው ጊዜ ወስደው ለሃገሪቱ የሚበጀውን መምከር ይችላሉ። የህግ የበላይነት መከበር ለባለስልጣናትም እንዲህ ከለላ የሚሆንበት ጊዜ አለ። የኬንያ መንግስት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መቀልበስ አይችልም።
ከላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጉዳይ እና የገባበትን አጣብቂኝ ለማንሳት ሞከርኩ እንጅ ለወትሮው የህግ የበላይነት እንዲከበር የሚሰራ መንግስት ቢኖረን ዜጎች በፍትህ ተቋማቱ ላይ እምነት ስለሚያድርባቸው ወደ ፍርድ ቤት ሂደው የአየር መንገዱን እና የፖለቲከኞቹን ውሳኔ ከህዝብ ጥቅም አንጻር መሞገት ይችሉ ነበር።
በጠራራ ጸሃይ ለሚፈጸም ወንጀል እና ስርዓት አልበኝነት ከለላ የሚሰጥ መንግስት ባለበት ሃገር ግን ዜጎች የዚያ ዓይነት ተነሳሽነት ፈጽሞ ሊኖራቸው አይችልም። እናም የአየር መንገዱ ሃላፊዎች እና ፖለቲከኞች በገቡበት አጣብቂኝ ምክንያት አንድ የፍርድ ቤት ዳኛ በህግ ሊያግደው የሚችለውን በህዝብ ላይ የተደቀነ አደጋ ማስቀረት አልተቻለም። የአባይንም ግድብ ዛሬ ከረፈደ የምንጮኸው ከጅምሩ የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ህግም ውሳኔ ሰጭም ሆነው በመስራታቸው እና የህዝቡን ድምጽ ባለማክበራቸው ምክንያት ነው።
ነጻ የፍትህ ስርዓት ቢኖር ዜጎች የመንግስትን ድርድር በፍርድ ቤት ማስቆም ይችሉ ነበር። ምክንያቱም ድርድሩ ሳይጀመር ሂደቱ እና አገባቡን ብቻ ተረድተው ውጤቱን አርቀው ማየት የሚችሉ እና ኢትዮጵያን እንደማይጠቅም የሚረዱ ዜጎች ብዙ ነበሩና ነው። መንግስት እና ባለስልጣናቱ ይህን የተረዱት ድርድሩ አልቆ የፊርማ ቀን ሲቀር ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በትልቅ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ ያሰለፋቸው ሰዎች የዲፕሎማሲያዊ ብቃት ሲታይ ሃገሪቱ ያለችበትን ደረጃ ያሳያል። ሌሎቹ ተደራዳሪ ሃገራት ደግሞ በድርድሩ ኢትዮጵያ እርቃኗን ትታያቸዋለች። ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ነገር ይመዝኑበታል።መንግስት እኛ በየቀበሌው በለመድነው ቢሮክራሲያ “በሌላ ስብሰባ ላይ ነን። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ሌላ ሃገር ሂደዋል” ወዘተ በሚል ምክንያት ለፊርማ አልሄድም ማለት በዲፕሎማሲ ትክክልም፣አዋጭም ሆነ ዘላቂ መፍትሄ አይደለም። አሁንም የሆነ ቡድን እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስትን ከሶ በፍርድ ቤት የአባይ ድርድር እንዲቋረጥ የሚያዝ ትዕዛዝ እንዲተላለፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። ፍርድ ቤት መንግስትን ከድርድር የሚያግድ ብቻ ሳይሆን ድርድሩን እንዲያቆም ትእዛዝ ይስጥ። መንግስት የፍርድ ቤትን ውሳኔ አከብራለሁ ይበል። የኢትዮጵያ አየር መንገድንም በትገመሳሳይ መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ እንዲያቆም ይደረግ።ከአሜሪካም ሆነ ከቻይና የሚመጣበትን ጫና በፍርድ ቤት ታግጃለሁ በማለት የፍርድ ሂደቱን ይግባኝ እያለ ፍርድ ቤቱም እንደተለመደው በቀጠሮ በማራዘም ጊዜ መግዛት ይችላል። ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ቢሆንም ንጹሃንን ያለስራቸው ለመወንጀል የሚጠቅሱትን ህግ አንዳንዴ ለሃገር ሲባል መጠቀም ቢለምዱ ጥሩ ነበር። አሁንም ይህን ለማድረግ አልረደፈም።
Filed in: Amharic