>
5:18 pm - Thursday June 14, 4801

በአፄ ዮሐንስ ስህተትና ጦስ - አጼ ምኒልክ ለምን ይውቀሱ ??? (ዘመድኩን በቀለ)

በአፄ ዮሐንስ ስህተትና ጦስ – አጼ ምኒልክ ለምን ይውቀሱ ???

ዘመድኩን በቀለ
ጥያቄዬን እደግመዋለሁ ኤርትራን የሸጣት ፤
ለጣልያንም አሳልፎ የሰጣት ማነው ? አጼ ዮሀንስ አይደሉምን???
 
• ቀዝቀዝ ያለ ውኃ እየጠጣህ ጭር፣ ፀጥ፣ ረጭ ያለ ቦታ ተቀምጠህ ተረጋግተህ አንብበው። ትፈወስበታለህ። አመለካከትህም ይቀየራል። ትረጋጋለህም።
• ይሄን ታሪክ ውሸት/ሀሰት ነው የምትል ባንዳና የባንዳ የልጅ ልጅ ካለህ መረጃህን ይዘህ አምጥተህ መሞገት ነው።
•••
የቀድሞዋ ወዳጄ Veronica Melaku በአንድ ወቅት ኤርትሪያን ለኢጣሊያ ማን አስረከባት? በማለት ትጠይቅና መልሱን በዝርዝር እንደሚከተለው ትተነትነዋለች።
•••
ለዝርዝሩ ከዚህ በታች የማስቀምጣቸውን ንጥር ያሉ የታሪክ እውነቶች ልብ ብለው ይከታተሉ ትልና በመቀጠልም ይሄን የታሪክ እውነታ ለመጻፍ ያነሳሳኝ አንዱን ንጉሥ አጥላልቼ ሌላውን የኢትዮጵያ ንጉሥ ለማሞገስ ሳይሆን ታሪክን የፖለቲካ መሣሪያ ለማድረግ የማይተኙ የታሪክ ደላላዎች አፄ
ሚኒልክን ባልዋሉበት እና ባልተገኙበት “ኤርትራን የሸጡ ንጉሥ ” እያሉ ብዙ ሰዎችን በሐሰት እያሳሳቱ ስለሆነ ሰዎች በተወናበደ ታሪክ እንዳይሳሳቱ ትክክለኛውን ታሪክ ለማስረዳትና ለማስገንዘብ ብዬ ነው ብላ ብላ ትቀጥላለች።
•••
የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት አፍሪካን የፖለቲካና የኢኮኖሚ መሣሪያቸው ለማድረግ መቀራመት ከጀመሩ ብዙ መቶ ዓመታትን ማስቆጠራቸው ይታወቃል። በተለይም በበርሊኑ ኮንፈረንስ የአፍሪካን ካርታ ጠረጴዛ ላይ በመዘርጋት ሲከፋፈሉ
ኢትዮጵያ ለኢጣሊያ በቅኝ ግዛትነት ተሰጣት። በዚህም መሠረት በበርሊኑ ኮንፈረንስ ቀድማ ምፅዋና አሰብ ላይ የከተመችው ጣሊያን ከምፅዋና ከአሰብ እየተንደረደረች ግዛቶችን መቆጣጠር ጀመረች። እስኪ ከዚህ በታች ኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ህልሟን ደረጃ በደረጃ እንዴት ለማስፋፋት እንደሞከረችና በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ኤርትሪያን ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠረች እንመልከት።
•••
የመጀመሪያው መጀመሪያ
•••
1~ በ 1862 ጁሴፔ ሳፔቶ ከአፋሩ ሱልጣን መሐመድ ሀሰን በ8100 ብር የገዛውን የአሰብ መሬት በ 1874 በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ለኢጣሊያ መንግሥት በማስረከቡ 28 ጊዜ
መድፍ ተተኩሶ አሰብ ላይ የኢጣሊያ ባንድራ ተውለበለበ።
[ እዚህ ጋር ምኒልክ የሉም ]
•••
2~ በ 1875 በኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ አደገኛ እና መዘዝ ያለው “የሂወት ውል” በአፄ ዮሐንስና በእንግሊዝ መካከል ተፈረመ። ይሄ ውል ኢትዮጵያ በአንድ ደካማ ጠላት ሁለት እጅግ አደገኛ ጠላት የገዛችበት አደገኛ ውል ሆኖ ተመዘገበ።
በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት እመለሳለሁ።
•••
3~ በጥር 28 /1877 ዓም በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የእንግሊዝ መንግሥትና ኢጣሊያ በተስማሙት መሰረት በኮሎኔል ሳሌታ የሚመራ የኢጣሊያ ጦር ምፅዋን ተቆጣጠሮ ምፅዋ ላይ የኢጣሊያ ባንድራ ተውለበለበ።
 [ ልብ በሉ እዚህ ጋርም ምኒልክ የሉም ]
•••
4~ በ ሰኔ 17/ 1877 ዓም በኮሎኔል ሳሌታ የሚመራው የኢጣሊያ ጦር ከምፅዋ ተነስቶ አርፋሌንና ሕርጊጎን አልፎ ሰሀጢን ተቆጣጠረ።
•••
5~ በ ጥር 1880 ዓም ራስ አሉላ በጀኔራል ጀኔ የሚመራውን የኢጣሊያ ሰራዊት 500 ገድለው ታላቅ ድል አስመዘገቡ።
የሚያሳዝነው ነገር ምፅዋ ከዶጋሊ የሚርቀው ሃያ ኪሜ ሆኖ እያለ ራስ አሉላ ተንደርድረው ለምን ኢጣሊያኖችን ከምፅዋ አላስወጡም? ለምን ምፅዋ እንዲከማቹና እንዲስፋፉ ፈቀዱላቸው?
[ ይሄም ሌላው ጥያቄ ነው ? ጥያቄው ግን ምኒልክ አይመለከትም አልነበሩማ!]
 
• የዶጋሊውን ድል የሰሙት አፄ ዮሐንስ በዚህ ትልቅ ድል እንደ መደሰት እና ጀኔራሉን አሉላን እንደ መሸለም አሉላን ከመረብ ምላሽ ግዛቱን በመሻር የቁም እስረኛ አደረጉት።
[ ልብ በሉልኝ እዚህ ጋርም ምኒልክ የለም ]
•••
6 ~ በ 1880 ዓም የአሉላን ከስልጣኑ መሻርና በቁም እስር መሆን የሰማውና በዚህም የተበረታታው የኢጣሊያ መንግሥት የጦር ሠራዊቱን እንደገና በማደራጀት የኢጣሊያ ፓርላማ በወሰነው መሰረት በጀኔራል ሳን ማርዛኖ የሚመራው የኢጣሊያ ጦር ከምፅዋ ተነስቶ ወደ መሀል ኤርትሪያ መንቀሳቀስ ጀመሮ ብዙ የኤርትሪያ ግዛቶችን ዶጋሊን ጨምሮ
ተቆጣጠረ።
 [ ልብ እንበል ንጉሡ አሁንም አፄ ዮሐንስ ናቸው ]
•••
7~ ይሄን የሰሙት አፄ ዮሐንስ ክተት ዐውጀው 159,000 ሠራዊት ወታደር ይዘው ዘመቱ። በመካከል  ይሄን ሠራዊት ኤርትራን ለተቆጣጠሩት ለኢጣሊያኖች ሲያስጎበኙ እና ሲያንገራብዱ ከርመው አንድም ጥይት ሳይተኩሱ ኤርትሪያን ለቀው ወጡ።
 [ ልብ አላችሁልኝ እዚህ ጋርም ምኒልክ
የለም ]
•••
8 ~ የአፄ ዮሐንስን ወደ ኋላ አፈግፍጎ መመለስ
የተመለከተው ጀኔራል ባልዴሴራ በ1881 ዓም የኢጣሊያ መንግሥት ወሰኑን መረብ ወንዝን አድርጎ የመጀመሪያ ቅኝ ግዛቱን #ኤርትሪያ ብሎ ሰየመ። ሙሉ የኤርትራ ግዛት በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት በኢጣሊያ ቁጥጥር ስር ወደቀች።
[ ጻፍልኝ ይሄንን “ባህረ ነጋሽ”  “ኤርትሪያ” የሚል አዲስ ስም የተሰጣት በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ነው ]
•••
★ አፄ ዮሐንስ 159, 000 ሠራዊት ካሰለፉ በኋላ ለምን ኤርትሪያን ለቀው ወደ ኋላ ወጡ?
ሦስት ታሪካዊ መላ ምቶች አሉ:
1ኛ ~ በጀኔራል ሰር ማሪጅኖ የሚመራውን የኢጣሊያ ጦር ማሸነፍ ከባድ እንደሆነ በመገንዘባቸው።
2ኛ ~ የሸዋው ምኒልክና የጎጃሙ ተክለሃይማኖት ውስጥ ውስጡን በመስማማት አገዛዛቸውን እየተገዳደሩ ስለመጡ እነሱን ለመቅጣት።
3ኛ ~ በሂወት ዉል የተበሳጨው በመሃድ የሚመራው የመሃንዲስት ጦር በጎንደር በኩል ገብቶ ወረራ በመፈፀሙ የማሃዲስትን ጦር ለመውጋት።
•••
በመጨረሻ በመንታ ሃሳብ የተከፋፈሉት የአፄ ዮሐንስ ልባቸው ወደ መተማ በማዘንበሉ መጋቢት 1 ቀን 1881 ከደርቡሾች ጋር በተደረገ ጦርነት ሕይወታቸው አለፈ።
አፄ ዮሐንስ ከመሞታቸው ከወራት በፊት ኢጣሊያ ድንበሩን መረብ ወንዝ ላይ አድርጎ ግዛቱን #ኤርትሪያ በሚል ስም ከሰየመ በኋላ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ቅኝ ግዛቱን ጀመረ።
•••
ጥቅምት 25 1882 አዲስ አበባ እንጦጦ ማርያም
ቤተክርስቲያን የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ” ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ዘ ኢትዮጵያ ” በሚል ከመንገሣቸው ከዓመት በፊት ኤርትሪያ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ሆና ነበር።
በዚህም መሰረት ምኒልክ በሰሜን በኩል ከአፄ ዮሐንስ የተረከቡት ግዛት ኤርትራ የሌለችባትን ኢትዮጵያ ነበር። ይሄ ታሪካዊ ሃቅ ተመዝግቦ እያለ ታሪክን የፖለቲካ መሳሪያ ማድረግ ተገቢ አይደለም። በማለት ቬሮ ጦማሯን ትፈጽማለች።
•••
ህወሓት ግን ይሄን ታሪክ ፈጽሞ አታነሳውም። ዓለም
የሚያውቀው ፀሐይ የሞቀው ታሪክ ሆኖ ሳለ ትንፍሽ
አትለውም። እሷ አናሳ ስለሆነች ብዙሃኑን ጨፍልቃ ለመግዛት ስትል የግድ የፈጠራ ታሪክ መፈብረክና የፈጠራ ጠላት መሸመት ነበረባት። ለዚህ ደግሞ እንቅፋት ይሆነኛል ብላ የምታስበውን ዐማራውን ጠላት አድርጋ ተከሰተች።
ኦሮሞውም፣ ሱማሌውም፣ ቤኒሻንጉሉም፣ ደቡቡም
ዐማራውን እንዲጠላው የቻለችውን ሁሉ ጣረች። በአፍም በመጽሐፍም በብዙ ደከመች።
•••
ህወሓት ለጊዜው የሥልጣን ጥቅሟን እንጂ ኋላ ላይ
የሚያመጣባትን ክፉ መዘዝ አልተረዳችውም ነበር።
ለኦሮሞው በተስፋዬ ገብረ አብ በኩል የፈጠራ ድርሰት አስደርሳ በመሰቦ ሲሚንቶ የተገነባ የተቆረጠ የሴት ልጅ ጡት – በአኖሌ አቆመች።
•••
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ወዳጅ ለማድረግ ስትልም አፄ ሚኒሊክን የኢስላም ጠላት አድርጋ እንደነ አህመዲን ጀበል ያሉ ደቀመዛሙርትን አፈራች። ሸዋንና ዐማራን የጎዳች መስሏት አፄ ሚኒልክን ከናዚው ሂትለር በላይ ጨፍጫፊ
አድርጋ ሳለች። የሚገርመው ነገር ግን ህወሓት ተሳስታ እንኳን አፄ ዮሐንስ በቦሩ ሜዳ ላይ በእስላሞች ላይ ስላደረሱት ጭፍጨፋ ትንፍሽ ለማለት እንኳን አትሞክርም። ብቻ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምኒልክ፣ ምኒልክ፣ ምኒልክ
እያለች አየሩን ሁሉ ተቆጣጠረች።
•••
የሚገርመው ነገር ደግሞ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከትግራይ መጥተው ምኒሊክ ቤተመንግሥት ከገቡት የህወሓት ባለ ሥልጣናት መካካል ሟቹን መለስ ዜናዊን ጨምሮ በአብዛኛው የባንዳ ልጆችና የባንዳ የልጅ ልጆች መሆናቸው ነው።
በምኒሊካውያን የተሸነፉት የባንዳ የልጅ ልጆች የትግራይን ህዝብ ጨፍጭፈው፣ የተንቤንን መኳንንትና የነገሥታት ዘር እየለቀሙ በየተራ አርደው አጋጣሚው ሰምሮላቸው ምኒሊክ ቤተ መንግሥት ከገቡ በኋላ ብዙ ምኒሊክ ጠል ትውልድ ፈለፈሉ። ልክ እንደ ኢንኪዩቤተር ነው የፈለፈሉዋቸው። እናም
ምደረ ጫጩት ሁላ ዛሬ ተነስቶ እምዬ ምኒልክ ላይ አፉን ያላቅቃል።
•••
መሪዎቻችን እንደ ድንገት ከሰማይ የወረዱ፣ ሀገሪቷም ድንገት ከባህር የወጣች ደሴት አይደለችም። ብዙ ሺህ ዘመን የተለፋባት ዓለም በሙሉ በሚያኮራ ታሪኳ የሚያውቋቃት፣ በመጽሐፍ ቅዱስም በቁርአንም የተጻፈች ፣ ዛሬ ተቆርሳና
ተሸራርፋ እንዲህ ወደ ሚጢጢነት ለመቀየር ሳትጣደፍ በፊት ብዙ ዜጎች አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ድንበሯንም የዛሬን አያድርገውና “ከነባሕር በሯ ” አስከብረው
ያቆዩልን ሐገር ናት ኢትዮጵያችን።
••• እናስ አፄ ምኒልክ በምን
 ነው በኤርትራ ጉዳይ ተጠያቂ የሚሆኑት? እንዲያውም በአዲስ አበባ ውል መሠረት ኤርትሪያ የኢትዮጵያ ግዛት ሆና እንድትቀጥል ነው እምዬ ጣልያንን ጆሮውን ቆንጥጠው ያስፈረሙት።
•••
ሻሎም ! ሰላም !
የካቲት 24/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic