>

የዳግማዊ አጼ ምኒልክ እናት ማን ናቸው? ክፍል ፪  (አቻምየለህ ታምሩ)

የዳግማዊ አጼ ምኒልክ እናት ማን ናቸው?

 [ክፍል ፪]  
አቻምየለህ ታምሩ
ታዬ ቦጋለ የሚባለው ሰውዬ ስለ ዐፄ ምኒልክ እናት ማንነት  በአደባባይ ያለማስረጃ ስላቀረበው የተሳሳተ ሀተታ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተመዘገበን  የዘመን ማስረጃ ጠቅሼ  ሰነድ በማያያዝ  እናታቸው ማን እንደሆኑ  የሚያሳይ ጽሑፍ በትናንትናው እለት አትሜ ነበር። ለዚህ ስርዓት የተላበሰና ማስረጃ አቅርቦ ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ  ታዬ የሰጠው ግብረ መልስ ግን ሳይቆነጠጥ አግድም ያደገ ስድ ልጅ ለስድብ ከሚናገረው የብልግና ቃል ይባስ የወረደ ዘለፋ፣  የብልግና ቃልና  ስድብ ማዥጎድጎድ ነበር።
ታዬ ከሰደበኝ ስድብ ሁሉ ያሳቀኝ የወያኔ ተላላኪ በሚል ያቀረበው ነው። «እኔ ምኔ የወያኔ ተላላኪ ይመስላል?» ወደሚል ተራ መከላከል ውስጥ አልገባም። «የወልቃይት ጉዳይ» የሚለውን ዳጎስ ያለ መጽሐፌን ያነበበና የሚያውቀኝ  አንድ ወዳጄ ደውሎ ታዬ ቦጋለ <«የወያኔ ተላላኪ፣ የዩቱብ ገንዘብ ለቃሚ፣ እየጠጣ  የሚጽፍ፣ ወዘተ. . .የሚለው  አንተን ነው ወይም ሌላ አቻምየለህ አለ?» ፤ «በዚህ አያያዙ  “መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ”  ብሎ የጻፈውን መጽሐፍ ልክ አንተን ዋሽስቶና ፈጥሮ ለማጠልሸት እንደሞከረው ሁሉ በውሸትና በፈጠራ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ ለታሪክ ቀርቶ ለሰፈር ወሬ የማይመጥን አለመሆኑን  እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል»>  ወይ ብሎ ጠይቆኝ ነበር።
ለማንኛውም እኔ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ እያስተማርሁ ተመስገን ደሳለኝ ያዘጋጀው በነበረው ፋክት መጽሔት ላይ በቋሚ አምደኛነት በምጽፍበት ወቅት «ወያኔ ልማታዊ መንግሥት ሳይሆን ዘራፊ አገዛዝ “ roving bandit” ወይም “Kleptocracy”  ነው» እያልሁ በምጽፍበት ወቅት  እኔን ዛሬ በወያኔ ተላላኪነት የሚከሰኝ ታዬ ቦጋለ  ቦሌ ክፍለ ከተማ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ይሰራ የነበረውና የወያኔን ልማታዊ መንግሥትነት [ በትግርኛ ወያናይ ዲሞክራሲ ይሉታል] ለወያኔ ካድሬዎች ይሰብክ የነበር ሰው ነው። ለዚህ ማስረጃው ኤርምያስ ቶኩማ የተባለ ሰው ጅላይ 23 ቀን 2019 ቀን «ገራፊዬ ተንታኝ ሲሆን» በሚል የሰጠው ስምክርነት ነው። ይህ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሰራተኛ የነበረውና ስለ ወያናይ ዲሞክራሲ ስልጠና ይሰጥ የነበረው ሰውዬ ነው እንግዲህ ከወያኔ ግድያ በመርፌ ቀዳዳ አምልጦ ከአገሩ የተሰደደን «የወልቃይት ጉዳይ» መጽሐፍ ጸሐፊ በወያኔ ተላላኪነት የሚከሰው።
የሆነው ሆኖ ‹የታሪክ ተመራማሪ› እየተባለ ሳይቆነጠጥ አግድም ያደገ ልጅ ለስድብ ከሚናገረው የብልግና ቃል ይባስ በወረደ ዘለፋ ለሚሳደብ ሰው በዚያ ደረጃ ወርጄ መልስ መስጠት አልፈልግም። ይህን የማላደርገው አንደኛ ኅሊናዬ ስለማይፈቅድልኝ ነው፤ ሁለትም ለማማር ብለው የሚያነቡኝንና የሚያደምጡኝን ወገኖቼን ስለማከበር ለነሱም ስል የወረደ ዘለፋ ውስጥ አልገባም፤ መትፋት ያስነውራልና!
ኾኖም ግን ዓላማዬ የመረመርኩትን ታሪክ ማስረጃ፣ ምንጭ እና መገኛ መጠቆም ስለኾነ ‹የታሪክ ተመራማሪው› የዳግማዊ ምኒልክ እናት ኦሮሞ መኾናቸውን ለማስረገጥ ወደጠቀሳቸው የታሪክ ምንጮች ልውሰዳችሁ።
‹የታሪክ ተመራማሪው› የዳግማዊ ምኒልክ እናት ኦሮሞ ናቸው ለማለት ያቀረበው ቀዳሚ የታሪክ ምንጭ ጳውሎስ ኞኞን ነው፡፡ «ጳውሎስ ኞኞ የዳግማዊ ምኒልክ እናት ኦሮሞ መኾናቸው አሳይተዋል» ብሏል። ይህ ፍጹም ፈጠራ ነው።
የጳውሎስ ኞኞ «አጤ ምኒልክ» የተባለው መጽሐፍ 509 ገጾች ያሉት ሲኾን በየትኛውም የመጽሐፉ ገጽ ላይ የዐፄ ምኒልክ እናት ኦሮሞ ናቸው የሚል ገለጻ የለውም። እንደውም ጳውሎስ ኞኞ «አጤ ምኒልክ» በሚለው መጽሐፉ በገጽ 13 ስለ ዐፄ ምኒልክ እናት ማንነት እንዲህ ነው የሚለው፡-
«ብዙ ታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት ወይዘሮ እጅጋየሁ ውብና ከደኅና ቤተሰብ መወለዳቸውን ይገልጻሉ። የአባታቸውን ስም ግን የሚገልጽ የለም። ለማ አድያሞ ይባላሉ። ይህን ሲተነትኑም አንዳንዶች ከጉራጌ አገር የተማረኩ ባሪያ ናቸው ይሏቸዋል።»
እንግዲህ! ጳውሎስ ኞኞ ስለ ዐፄ ምኒልክ እናት ማንነት የጻፈው «አንዳንዶች ከጉራጌ አገር የተማረኩ ባሪያ ናቸው ይሏቸዋል» የሚለውን ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ መጽሐፉን ከጥግ እስከ ጥግ ብትገልጡ ‹የታሪክ ተመራማሪው› እንዳለው ጳውሎስ ኞኞ የዳግማዊ ምኒልክ እናት ኦሮሞ መኾናቸው ያሳየበት አንዳች ገጽና ዐረፍተ ነገር አታገኙም።
ባጭሩ ‹የታሪክ ተመራማሪው› «ጳውሎስ ኞኞ የዳግማዊ ምኒልክ እናት ኦሮሞ መኾናቸው አሳይተዋል» ሲል የሰጠው መልስ መጽሐፉ ውስጥ የሌለ ነገር ነው።
‹የታሪክ ተመራማሪው› የዳግማዊ ምኒልክ እናት ኦሮሞ ናቸው ለማለት ያቀረበው ሌላው የታሪክ ምንጭ የአለቃ ለማን መጽሐፈ ትዝታ ነው። «መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ ፤ መንግሥቱ ለማ እንደጻፈው» በሚል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ2003 ዓ.ም. ያሳተመው መጽሐፍ 274 ገጾች አሉት። 274 ገጹን የአለቃ ለማ ኃይሉ ትዝታ ስትገልጡ ብትውሉ አለቃ ለማ የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት ኦሮሞ ስለመሆናቸው የተናገሩትን ተጽፎ አታገኙትም።
አለቃ ለማ ኃይሉ በመጽሐፈ ትዝታ ስለ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት የተናገሩት ከገጽ 7 እስከ 8 ሰፍሮ ይገኛል። እንዲህም ይላል፡-
«ያጤ ምኒልክ እናት አባት የላስታ የመቄት ተወላጅ ናቸው አድያሞ ይባላሉ፤ ደጃች አድያሞ።. . . ከዚያ ሸዋ መጣ። እዚህ ሎሌነት ገባ ለሣህለ ሥላሴ አያት። ሲኖር አድያሞ ለማ ከመንዝ ሴት ወልዷት ያጤ ምኒልክን እናት፤. . . እንግዲህ የምኒልክ እናት ባባቷ መቄት ናት።»
አለቃ ለማ ስለ ዐፄ ምኒልክ እናት ማንነት የተናገሩት በአባት መቄት በእናት መንዜ መኾናቸውን ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ‹የታሪክ ተመራማሪው› እንዳለው አለቃ ለማ የዐፄ ምኒልክ እናት ኦሮሞ ናቸው ብለው የነገሩት ታሪክ የለም!
ማጠቃለያ
ጳውሎስ ኞኞም ይኹን አለቃ ለማ ኃይሉ በመጽሐፋቸው የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ እናት ኦሮሞ ናቸው ብለው የሰጡት የታሪክ ምስክርነት የለም። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ሁለት ሰዎች ስለ ዐፄ ምኒልክ እናት ትውልድ ማንነት ሲያቀርቡ የታሪክ ማስረጃ አላቀረቡም።
የዐይን ምስክር ወይም ቀዳሚ ምንጭ ባለመኾናቸው ስለ ዳግማዊ ምኒልክ እናት ማንነት የሰጡት ምስክርነት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን፤ ዳግማዊ ምኒልክ በሕይዎት እያሉ  ከተጻፈ የታሪክ ምንጭ በላይ አሳማኝ ማስረጃ ሊኾን አይችልም። የጳውሎስ ኞኞ «ዐጤ ምኒልክ» ከመታተሙ ከ95 ዓመታት በፊት፣ አለቃ ለማ ምስክርነታቸው ከመስጠታቸው ከ70 ዓመታት በፊት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በሕይዎት እያሉ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ «የጎጃም ትውልድ ከአባይ እስከ አባይ» በሚል የመስክ ጥናት አካሂደው ባዘጋጁት መዝገብ የዐፄ ምኒልክ እናትና አያት የጎጃም ጎዛምን ሴት ወይዘሮዎች እንደኾኑ ነግረውናል። በሌላ አነጋገር ዐፄ ምኒልክ በሕይዎት እያሉ የተጻፈው የአለቃ ተክሌ መጽሐፍ ዳግማዊ ምኒልክ ከሞቱ ከ95 እና ከ70 ዓመታት በኋላ ምንም ማስረጃ ሳይጠቅሱ በጻፉት ሰዎች አስተያየት ሊሻር አይችልም።
ባጭሩ የአለቃ ተክሌ መዝገብ  ዳግማዊ ምኒልክ በሕይዎት እያሉ የተጻፈው የዘመን የታሪክ ምስክርነት ነው። ከቀዳሚው ዘመን የታሪክ ማስረጃ በኋላ የሚጻፍ ማንኛውም የታሪክ ምንጭ ቅቡል እንዲኾን ወይ በዘመኑ በነበረ የዐይን ምስክር የተጻፈ መኾን ይኖርበታል፤ አለበዚያም አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል። ስለ ዐፄ ምኒልክ እናት ማንነት የጻፉት ጳውሎስ ኞኞም ይኹኑ አለቃ ለማ ኃይሉ፣ እንደ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ የዘመን የዐይን ምስክሮች ስላልኾኑና ሁለቱም አሳማኝ ማስረጃ ስላላቀረቡ የዐፄ ምኒልክን እናት ማንነት በሚመለከት በዘመኑ ከተመዘገበው ከአለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ በላይ የታሪክ ማስረጃ ኾነው ሊቀርቡ አይችሉም!
Filed in: Amharic