>

የዓባይ ድርድርን ፍሬምወርክ መንግስት ለህዝብ ይፋ ያድርግ!  (ቅዱስ ማህሉ)

የዓባይ ድርድርን ፍሬምወርክ መንግስት ለህዝብ ይፋ ያድርግ! 

ቅዱስ ማህሉ
 
»»ሴራ ከጫና አያድነም! 
 
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተመሳሳይ ቀን አንዴ ቫቲካን ጉብኝት ላይ መሆናቸውን በሌላ ደግሞ የሚንስትሮች ም/ቤት ስብሰባ ላይ መገኘታቸውን የሚገልጹ ዘገባቸዎች እያየን ነው። ይህ ጉዳይ እንዲሁ የተደረገ አይደለም። ይሁን እንጅ የዓባይን ግድብ ድርድር የሚመሩት ሰው በአንድ ጊዜ በተመሳሳይ ቀን ሁለት ሃገራት ላይ ስብሰባ መገኘት አይችሉም።
እኛ ስለ አባይ ሃገራዊነት እና የትውልድ ጥቅም ጉዳይ ብናወራም መንግስት ግን አሁንም ሌላ ሴራ እየተበተበ ነው። ምናልባትም ቀጣዩ የአብይ አህመድ መንግስት የሴራ ፖለቲካ ሰለባ የሚሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው። የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሴራ ሰለባ ከመሆናቸው በፊት መንግስት መጀመሪያ የትልቅ ቅጥፈት እና ከተቻለም በተለይም ደካማዎቹን የወንጀል ተባባሪ ያደርጋቸዋል። አሁን ጥያቄው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የት ናቸው ነው? ቫቲካን ወይስ አዲስ አበባ?
አሜሪካ በአባይ ግድብ ላይ ባወጣችው መግለጫ ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ እንዳትሞላ ያለችው ውሳኔ ምናልባትም ድርድሩ ውስጥ ሲገቡ መንግስት የተስማማው ቅድመ ሁኔታ ይሆናል። መንግስት እስከዚች ደቂቃ ድረስ ድርድሩን በተመለከተ ስላለው ወይም ቀድሞ ስለተስማማበት ማዕቀፍ/ፍሬምወርክ ሁሉንም ነገር በድብቅ ይዞታል። ሁሉንም ነገር በድብቅ መያዙ እየጎዳው ያለው ኢትዮጵያን ነው። መንግስት ይህን ማድረጉ የሚያውቁ ሰዎች እንዳይናገሩ አድርጓል። ምክንያቱም በዝርዝር ስለጉዳዩ አይታወቅም። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ታረቁ ተብሎ በተግባር ግን ከኢሳያስ አፈወርቂ እና ከአብይ አህመድ ውጭ ስለ እርቁ ሂደት እና ምንነት የሚያውቅም አንድም ሰው እንደሌለው ማለት ነው።ይሄ የሃገራት እርቅ አይደለም። የአባይም ጉዳይ ልዩነቱ ሌላኛዋ ተደራዳሪ እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ ለሾው አለመመቸቷ እና ጫናም መፍጠር መቻሏ ላይ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የድርድሩን ዝርዝር ፍሬምወርክ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ ያድርግ። አለዚያ ከውጭ የሚመጣውን ጫና ብቻ ሳይሆን ከውስጥም የሚነሳበትን ተቃውሞ ለማስተናገድ ይገደዳል። ይህን የሚችል አቅም አለው ብየ አላምንም።
የዓባይ ነገር እያነጋገረ ይቀጥላል….
እውነቱን ለመናገር በዓባይ ጉዳይ ሱዳን ከኢትዮጵያ መንግስት የበለጠ ግልጽ እና ጠንካራ አቋም አላት። ያውም በግብጽ እሽሩሩ እየተባለች! ለዓባይ ግድብ እና የድርድር ሂደት ትክክለኛ መፍትሄው ከድርድር መውጣት ነው። እስካሁን የኢትዮጵያ መንግስት ይህን አላደረገም። የኢትዮጵያ መንግስት መግባት ባልነበረበት ድርድር ውስጥ ከመግባትም ባለፈ እስካሁን ከሚያወራው በቀር ተጨባጭ ዝርዝር ዶክመንት ለህዝብ ይፋ አላደረገም። የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም ትኩረቱ ዓባይ እና ዘላቂ ሃገራዊ ጥቅሙ ሳይሆኑ በዚያ ምክንያት የተፈጠረውን የህዝብ ተነሳሽነት ለፖለቲካ ጥቅም ማዋሉ ላይ ነው። በሚያሳዝን መልኩ መንግስት ባለው ደካማ የዲፕሎማሲ ብቃት ቀድሞ መግባት ባልነበረበት እና ከገባም በኋላ በሰበብ ማቋረጥ ይጠበቅበት የነበረውን ድርድር ውጤት ላይ ደርሶ የፊርማ ቀን ሲቀር ነው የተረዳው። ከፊርማ የቀረውም ስብሰባ ላይ ነኝ በሚል አይረቤ ምክንያት ነው።
አሜሪካም ስብሰባውን ስትጨርሱ መጥታችሁ ፈርሙ፤እስከዚያው ግድቡን ውሃ አትሙሉ አለች። መንግስት መውጣቱን በይፋ ካልተናገረ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዓባይ ግድብ ድርድር ጉዳይ በግብጽ አሸናፊነት መጠናቀቁ አይቀሬ ነው። ይህ እንዳይሆን መንግስት እውነተኛ ፍላጎት ካለውእንደ ሱዳን ግልጽ እና ጠንካራ አቋም ማንጸባረቅ ይጠበቅበታል። ከዚያ ውጭ የገባበትን የዲፕሎማሲ አረንቋ ከማወሳሰብ በቀር ትርፍ የለውም። መንግስት በድርድሩ ላይ የነበረውን ደካማነት አደብዝዞና አንሻፎ በማቅረብ ለዳግም ገንዘብ መዋጮ እና ለፖለቲካ ድጋፍ ስሜት መቀስቀሻ ለማዋል እየሞከረ ነው። ይህ አይጠቅምም! ለዘላቂ መፍትሄ አሁንም ሰከን ብሎ ያልተነኩ የዲፕሎማሲ አማራጮችን መጠቀም እንጅ እናንተ በምትሰሩት ስህተት ህዝቡን የገንዘብ ጥም ማርኪያ እና የፖለቲካ ፍላጎታችሁ መጠቀሚያ ለማድረግ አትድከሙ። መጀመሪያ ከእናንተ ጋር እንተማማን እንጅ!
Filed in: Amharic