>
5:13 pm - Saturday April 19, 7794

እንጠንቀቅ እንጂ አንፍራ !!  (ዘመድኩን በቀለ)

እንጠንቀቅ እንጂ አንፍራ !!

     ዘመድኩን በቀለ
መጠንቀቅ መልካም ነው። መጨነቅና መፍራት ግን ራሱ ኢቦላ ከኢቦላም የከፋ ነው። ይልቅ እንደ ክርስቲያን “በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ” 
ሮሜ 12፥12
 
“ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ፥ ኃጢአትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በልባችሁ ይሆን ዘንድ መጥቶአልና አትፍሩ።” ዘጸ 20፥20።
•••
መጀመሪያ አለመፍራት። ፍርሃት ከኮሮና የበለጠ ገዳይ እንደሆነ ማወቅ ይገባል። ጭንቀት በራሱ ከኮሮና የበለጠ ገዳይ ነው። ሰው ይፈራል። መፍራት ተፈጥሮአዊም ነው። ሥጋ ለባሽ ይፈራል። ይሄም ተገቢ ነው። ከመጠን ያለፈ ፍርሃት ግን ገዳይ ነው። ለክርስቲያን ጥንቃቄ እንጂ ፍርሃት አይመከረም። ፍርሃት ከእግዚአብሔር የመለየት፣ የመራቅ ምልክት ነው። እግዚአብሔር እንደተለየህ የምታውቀው የፍርሃት መንፈስ ሲያጥለቀልቅህ ነው። ሰምተሃል።
•••
ለምሳሌ አንተ የውኃ አገልግሎት እንደልብ በሌለበት ሃገርና ከተማ የምትኖር ሰው፣ እስከዛሬ ከአህያና ከከብት ጋር እየተጋፋህ የምትኖር ሰው፣ ገዳይ የሚባሉት ውኃ ወለድ በሽታዎች ምንም ያላደረጉህ ሰው። አሁን እጅህን ታጠብ፣ እግርህን ታጠብ፣ ያለዚያ ትሞታለህ ስትባል ምኑ ነው የሚያስፈራህ? ይሄንን ውኃ የናፈቀው ህዝብ እንዲያ ብትለውስ ምን ዋጋ አለው?
• ቀላል ጥያቄ እኮ ነው? ከዚህ በታች ያሉትን ጥያቄዎች ለራስህ መልስና ፍርሃትህን አስወግድ
• እስቲ አሁን በሰፈራችሁ ውኃ አለች?
• በምትሠሩበት ሆስፒታል ውኃ አለች?
• በምትጠቀሙበት ምግቤት ውኃ አለች?
• የሆስፒታል፣ የምግቤት መጸዳጃ ቤቶች ውኃ አላቸው?
• ውኃ በሰፈራችሁ ከመጣች ስንት ጊዜዋ ነው? መልሱን ለእናንተው።
• ምግብቤት ገብታችሁ ከታሸገ ውኃ በቀር ይቀርብላችኋል?
•••
ደግሞስ እስከ ዛሬ እሱ ሸራተንና ሂልተን ውስኪ እየጠጣ፣ በውስኪ እየታጠበ ተንደላቆ ይኖር የነበረው “ የኢትዮጵያ መንግሥታችን” ለእኛ ለሰፊው ኢትዮጵያ ህዝብ በገዛ ገንዘባችን ገዝተን እንጠጣ፣ እንታጠብበትም ዘንድ ይሄን የጉሽ ጠላ የመሰለ መረሬ ጭቃ የተሞላበት ቆሻሻ ውኃ አልነበረም ወይ ከቤታች ድረስ በቧንቧ እየላከ ስንጠቀምበት የኖርነው ?
•••
ስለዚህ ለኢትዮጵያ ህዝብ የምመክረው ውኃ ካለ ታጠብ፣ በተረፈ በሌለ ነገር አብዝተህ አትጨነቅ። እኔ በበኩሌ እጃችሁን በሳሙና ለ20 ሰከንድ መታጠብ የሚለውን የጤና ባለሙያዎችን ምክር አከብራለሁ። ለኮረና ብቻ ሳይሆን ሌላም ጊዜ ቢሆን መታጠብ ግድ ነው። መታጠብ ብቻውን ግን ያድንሃል ብዬ እጅህ እስኪላጥ ስትፈተግ እንድትውል አልመክርህም። በእጅ መታጠብ ቢሆን ኖሮ 24 ሰዓት ያለማቋረጥ ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት የሚያገኙት አውሮጳውያኑ ባልታመሙ ነበር። አሜሪካና ካናዳ ባልተጨነቁም ነበር። መታጠቡ ሸጋ ነገር ሆኖ ነገር ግን በሽታው በየሰከንዱ የሚታጠቡትንም ሀገራት አልማረም።
•••
ቆይ ግን አሁን አንተ እጅህን በየሰዓቱ ልታጠብስ ብትል ውኃዋን በምትፈልጋት ሰዓት ታገኛታለህ ወይ? ይሄን ጽሑፍ እያነበብክ እንኳ በቤትህ፣ በሰፈርህ፣ በመንደርህ ውኃዋ ከመጣችስ ስንት ቀኗ ነው? ስትመጣስ ምን መስላ ነው የምትመጣው? የደፈረሰ ጠላ መስላ አይደለም ወይ የምትመጣው? ያው ውኃ ተጠትቶ፣ በእሱው ታጥበህ አይደል እንዴ እስከዛሬ በሰላም የኖርከው? መታጠቡ እንዳለ ሆኖ ችግሩ ከመታጠቡ ብቻ አይመስለኝም። [ መቅሰፍት ይሰመርበት ]
•••
“ ኮሮናን ከፍተኛ ሙቀት ይገድለዋል። እንደ ሻይና ሾርባ የመሰሉ ትኩስ ነገሮች ይገድሉታል። ስፖርት መሥራት ፍቱን መድኃኒት ነው በሚለውም የአንዳንድ ሰዎች ምክር ላይ ተቃውሞ የለኝም። ሙቀትን ማን ይጠላል። ትኩስ ነገር መጠጣት፣ ትኩስ ነገር መብላት ስፖርት መሥራትም ሸጋ ነገር እኮ ነው። ለኮሮናም ባይሆን ከኮረናም ዉጪ ቢያደርጉት መልካም ነው። ነገርግን ኮረናውን ይሄ የሚያቆመው ቢሆን ኖሮ ኮሮና ሳውዲ ዐረቢያ ባልገባ ነበር። በሙቀቱ ምክንያት ግብጽና ኢራን ባልገባ ነበረ? ዱባይስ ምን ሊሠራ ይገኝ ነበረ? ሙቀቱም መፍትሄ አይመስለኝም። [ ንስሐ ]
•••
ትኩስ ነገርስ በመጠቀም እንደ አረብ ሻይ የሚጠጣ አለ እንዴ? ሩቅ ምሥራቆች ሾርባ ቀለባቸው ነው። ነገር ግን ኮሮና እነሱንም ከመድፈር ወደ ኋላ አላለም። የአሜሪካን የቅርጫት ኳስ ተጫዋች፣ የአውሮጳ ኳስ ተጫዋቾችን ስፖርተኞችን ከቤት ያዋላቸው ስፖርት ስለማይሠሩ አይደለም እኮ። ለኮረና ተብሎም ባይሆን ዘወትር ስፖርት መሥራት ሸጋ ነው። ነገር ግን ስፖርት ብቻውን ከኮረና አያስመልጥም። [ ይሄንንም እያነበብክ ንስሐ አይታይህም አይደል ]
•••
በአውቶቡስ፣ በባቡር፣ በከፍተኛ ህዝብ በሚበዛባቸው ሥፍራዎች አለመገኘት። ሲያስነጥሱ እጅዎን በመዳፍዎ መሸፈን። የበር እጀታዎችን አለመንካት። የአውቶቡስና የባቡር እጀታዎችን አለመደገፍ። የባንክ ኤቲኤም ማሽኖችን በእጅ ያለመንካት። የሊፍት ቁጥሮችን አለመጫን። አለመጨባበጥ ወዘተ ከኮሮና ያድናል ተብሏል። ወዳጄ አይፍረድብህ፣ አይታዘዝብህ። የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር፣ የስፔይን ባለ ሥልጣናት፣ ቤተ መንግሥት እኮ ነው የነበሩት። ወፍ ዝር በማይልበት ቤተ መንግሥት። እናም ህዝብ በበዛበት ሥፍራ መገኘቱ ብቻም አይደለም ወዳጄ? አይጣልብህ። ዋናው ነገር ከእግዚአብሔር ጋር መጣበቅ።
•••
እኛ ኢትዮጵያውያን ካለን የቆየ ልምድ አንጻር መፍትሄው ጸሎት ነው። ምህላ፣ ስግደት፣ ምጽዋት፣ ዝማሬ፣ ጠበል፣ እምነት፣ መፋቀር፣ መዋደድ፣ ይቅር መባባል፣ ራስንና አካባቢን ማጽዳት። በደንብ ማጽዳት። አለመተኛት፣ ኃጢአትን መተው። ንስሐ መግባት፣ ሥጋወደሙ መቀበል።
•••
በአውሮጳ ሞተ ተያዘ ሲባል እንጂ የሞተው፣ የታመመውን እስከአሁን ሲያሳዩ አላየሁም። የኢራንና የቻይናን የህዝብ ሞት በድብቅ በተቀረጹ ቪድዮዎች ደርሰውኝ አይቻለሁ። እናም መፍራቱ በልክ ቢሆን ይመከራል። በአውሮጳ በደንብ የተሸጠው ሳሙናና ሶፍት ነው። ሳሙናና ሶፍት ከበሽታው ጋር ምን እንደሚያገናኛቸው መድኃኔዓለም ነው የሚያውቀው። ሱፐር ማርኬቶች የወረቀትና የሳሙና፣ የእጅ ማጽጃ እንደ አልኮል ያሉ አቅርቦቶች ናቸው ድራሻቸው የጠፋው። አይ አውሮጳ ?
•••
ብዙ ኩንታል እህል ያከማቻችሁ፣ ዘይት ዱቄት የከዘናችሁ። መድኃኒት ያጠራቀማችሁ መቼ ልትበሉት ነው? እናንተ እየበላችሁ ጎረቤታችሁ በረሃብ ሲረግፍ አይታችኋል? እናንተ ቤት የሚቁላላው ወጥ አካባቢያችሁን ሲያውደው በሚፈጥረው መዓዛ ድኃው የሚዝናና ይመስላችኋልን? ውድድርም ቢሆን በደህና ጊዜ እንጂ በመከራ ጊዜ የሚያስፈልገው እንደ እውቁ እግር ኳስ ተጫዋች እንደ ክርስቲያኖ ሮናልዶ መሆን ነው። ታዋቂ ሆቴሉን በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎች ህክምና ይውል ዘንድ በነፃ ሰጠ። ለህክምና ባለሙያዎቹም ደምወዝ እከፍላለሁ አለ። ይሄ ነው ሰው ማለት። አንስገብገብ፣ እኔ ብቻ፣ ለእኔ ብቻም አንበል። እንረዳዳና ይህን ክፉ ቀን እንለፈው።
•••
“አቤቱ፥ ኃጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኃጢአት ሠርተናልና ኃጢአታችን ይመሰክርብናል ነገር ግን ስለ ስምህ ብለህ አድርግ።”  ኤር 14፥7።
•••
ሻሎም  !  ሰላም  !  
መጋቢት 7/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic