>

የኢትዮጵያ መንግስት እና ኮሮና ቫይረስ !!! (ቅዱስ ማህሉ)

የኢትዮጵያ መንግስት እና ኮሮና ቫይረስ !!!

ቅዱስ ማህሉ
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሲኒማ ቤቶች እና ቲያትር ቤቶች ላይ መንግስት ምን ለማድረግ ወሰነ? የዚህ ወረርሽኝ ስርጭት ኢትዮጵያ ውስጥ አንዴ ከተስፋፋ ብዙዎች ሲጻፍ ሟርት እና ክፉ ነገር መመኘት የሚመስላቸው ሁሉ ደርሶ ማየታቸው አይቀርም። ስለዚህ መንግስት ጠንካራ እና ተፈጻሚ የሚሆኑ ውሳኔዎችን ማሳለፍ አለበት። ለምሳሌ ስብሰባ ተከለከለ ተብሎ በየቀኑ ከማንም በላይ ሰዎችን እየሰበሰበ ያለው መንግስት ራሱ ነው። ጉዳዩን በቀናት እና በሳምንታት ዘመቻ የሚቀለበስ የመሰላቸው ብዙዎች ናቸው። ጉዳዩ ከሚታሰበው በላይ አሳሳቢ እና አስፈሪ ስለሆነ መዘጋት ያለባቸውን ተቋማት በጊዚያዊነት በመዝጋት ወይም ለምሳሌ የግል ሲኒማ ቤቶች መንግስት ባይዘጋባቸውም 100ሰው የሚይዝን ሲኒማ ቤት 40ሰው ብቻ እንዲመለከት ቁጥሩ በመቀነስ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ የራሳቸውን አስተዋጾ ማበርከት ይኖርባቸዋል።መንግስት እንደዚህ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊጎዱ የሚችሉ ቢዝነሶችን(በረጅም ጊዜ የማይጎዳ ይኖራል ብየ አላስብም) ከከፍተኛ ግብር ቅነሳ እስከ አነስተኛ ብሎም ወረርሽኙ እስኪቆም ድረስ ለተወሰነ ጊዜ ከግብር ነጻ የእፎይታ ጊዜ በመስጠት ማበረታታት አለበት። የኮሮና ቫይረስ ከህዝብ ጤና እኩል ኢኮኖሚን ሊያናጋ የሚችል አደጋ ነው። የዘመቻው አጋር ማድረግ ይገባዋል። ይሄ የቫይረስ ወረርሽኝ በእንጭጩ ካልተገታ ኢትዮጵያ ትልቅ የሃዘን ድንኳን መሆኗ አይቀርም። ለመሆኑ መንግስት ብዙ ታማሚዎች(ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል) ባንዴ ሲመጡበት ማስተናገድ የሚችልበት አቅም አለው? በሆስፒታሎቿ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አልጋዎች ያሏት አሜሪካ ላይበቃ ይችላል በሚል ለወትሮው በሆስፒታል ክትትል የሚደረግላቸውን ታማሚዎች በቤታቸው ክትትል እንዲያደርጉ እያደረገች ነው። ይሄም ሆኖ በወረርሽኙ ምክንያት አልጋ ላይበቃ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የአሜሪካ ብሄራዊ አለርጅ እና ተዛማች በሽታዎች ቢሮ በትንሹ አንድ ሚሊዮን ያህል አሜሪካዊያን ሊሞቱ ይችላሉ ብሎ ሰግቷል። ይህ ቁጥር በአሜሪካ የርስ በርስ ጦርነት እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሞቱትን አሜሪካዊያን አንድ ተደምሮ እንኳ ይበልጣል። ዓለም ለምን እንደሰጋ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ብዙም ዓይናቸውን ገልጠው መመልከት የቻሉ አይመስለኝም። ለወትሮው ሆስፒታሎቹ ለበሽተኞች በቂ አልጋ የሌሏት ኢትዮጵያ በዚህ በሽታ ችላ ስትል ማየት በጣም ያሳዝናል። ወረርሽኝ እንደመሆኑ መጠን የተወሰነ ሰው መሞቱ እንደማይቀር ግልጽ ነው። የነዚያን ሰዎች ቁጥር ቅድመ ግምት ወስዶ መንግስት የአስከሬን መጠቅለያ ፕላስቲኮችን በስፋት በመላው ሃገሪቱ ማሰራጨት በተለይም በሽታው በስፋት የሚታይባቸውን ቦታዎች ለይቶ ማሳወቅ እና እነዚያን ቦታወች ሰዓት እላፊ በማውጣት እንቅስቃሴ መገደብ እንዲሁም ሌሎች ወደዚያ እንዳይሄዱ የትራንስፖርት አገልግሎት ማቋረጥ እና በሚዲያ መንገር 24/7 ሊሰራበት የሚገባ ለነገ የማይባል ስራ ነው! ከታች ያለው ቪዲዮ 200ሰው በሚኖርበት አንድ ዝግ መንደር ውስጥ ያለ አንድ ታማሚ በሆነ መንገድ ከታጠረው መንደር ቢወጣ ወይም ሲወጣ የተቀረውን ሃገር እንዴት ሊያዳርስ እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ/ሲሙሌሽን ነው። ቡኒው ከለር ኮሮና ያለባቸው ሰዎችን ይወክላል። ግራጫው ደግሞ ጤነኛው ህብረተሰብን ይወክላል። እንዴት እንደሚሰራጭ ተመልከቱ በዚህ ውስጥ የሚሞተው እየሞተ የሚድነው አብዛኛው ደግሞ እንደምታዩት እየበዛ ይሄዳል።በፒንክ ቀለም የተወከለው ኮሮና ይዞት የሚተርፈው ነው። ብዙዎችን ለማትረፍ ግን ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። አሁን ግንዜቤ ለመስጠት እየተባለ ህዝብ እየሰበሰቡ እጅ ማስታጠብ የበሽታውን ስርጭት ማባባስ ነው። ሌላው በድጋሚ ለመንግስት ማሳሰብ የምፈልገው ጉዳይ እስር ቤቶች በአስቸኳይ ከህዝብ ጥየቃ ለጊዜ ካልተከለከሉ በቀር ሁሉም ላይ ሞት እንደተፈረደባቸው ይሰማኛል። መፍጠን፣መወሰን እና መተግበር ብዙ አደጋን ይቀንሳል!!!
Filed in: Amharic