>
5:18 pm - Monday June 14, 6556

ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ እና የሕይወት ትውስታዎቹ!!! (አሰፋ ሃይሉ)

ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ እና የሕይወት ትውስታዎቹ!!!

አሰፋ ሃይሉ
በ1983 አካባቢ ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ ሩህ የሚባል መጽሔት ማዘጋጀት ጀምሮ ነበረ፡፡ ምናልባትም ከድህረ-ደርግ (ወይም ቅድመ-ኢህአዴግ) የመጀመሪያው የግል መጽሔት ሣትሆንስ ትቀራለች ‹‹ሩህ››? እና በዚያ ላይ አንዳንድ የቆዩ ትዝታዎቹን እያነሳ ፈገግ ያሰኘን ነበረ፡፡ እስቲ በጥቂቱ የማስታውሰውን ያህል፡-
፩ . ጥያቄ፡- ጋሼ ጳውሎስ፤ አንድ ጊዜ በጋዜጣ ላይ ለሰጠኸው ምላሽ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ፊት ተከሰህ ቀርበህ በነጻ የተለቀቅክበት ጊዜ ነበረ ይባላል.. እስቲ ስለዚያ ባጭሩ አስታውሰን?
መልስ፡- ‹‹አዎ ነበረ፡፡ ምን መሠለሽ? ያኔ የአብዮት ዘመን ነው፡፡ አስጊ ጊዜ ነበረ፡፡ እና በጋዜጣ እየጻፍኩ አንዱ አሳባቂ አንባቢ.. እንዲህ የሚል ጥያቄ ጽፎ ለዝግጅት ክፍላችን ላከ፡- ‹‹የማከብርህ ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ፤ አንድ ጥያቄ ብቻ ላቅርብልህ፤ እውነቱን ንገረኝ እስቲ፡- ለመሆኑ አሁን እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ አብዮት ትወደዋለህ??›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ይታይሽ እንግዲህ… ‹‹አልወደውም›› ብል ጉድ ሊፈላ ነው፤ ያልወደድኩትን ‹‹እወደዋለሁ›› ማለቱ ደግሞ ከህሊናዬ ጋር ፀብ መግጠም ሆነብኝ፡፡ ስለዚህ እንዲህ የሚል መልስ ሰጠሁት፡-
‹‹ውድ አንባቢያችን፤ ለተሳትፎህ እናመሰግናለን፡፡ እኔን በግሌ ለጠየቅከኝ ጥያቄህ ግን በምሣሌ መልስ ብሰጥህ እመርጣለሁ፡፡ እንዲህ እንዳንተ.. ያኔ ክርስቶስ በምድር ተዓምራትን እየሠራ በሚመላለስበት ዘመን ነበር… አንዱ ለፈተና ያለው ሰው… ሌላውን ምስኪን ምዕመን ጠጋ ይልና፡- ‹‹ለመሆኑ ማርያምን ትወዳታለህ?›› ብሎ ቢጠይቀው… ነገሩ ያላማረው ምዕመን እንዲህ ብሎ መለሰለት ይባላል፡- ‹‹ምነው አልወዳት? ከግንድ የሚያላጋ ልጅ አላት!!››፡፡ እና ወንድሜ እኔም አብዮቷን የምወዳት እንደዚያው ነው፡፡››
ይህን መልስ አትሜ አወጣሁ፡፡ ብዙዎች ጮኹ፡፡ ለኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያምም ክስ አቀረቡብኝ፡፡ አስጠራኝ፡፡ እኔም እንደርሳቸው ያለ ልጅ እያላት አብዮቱን እንዴት ልጠላ እችላለሁ? ይህን ማለቴስ ምንድነው ክፋቱ? ብዬ ተማጥኖዬን አቀረብኩ፡፡ ኮ/ሉም ከት-ከት ብሎ ከሣቀ በኋላ ‹‹ነገሩስ እውነት ብለሃል፤ ችግር የለውም፤ ግን እንዲያው ይቺን የምትተነኩሳትን ነገርህን ግን ተው፤ ለራስህው ነው፤›› ብለው እየሳቁ መከሩኝ፡፡ እኔም አልደገምኳትም፡፡››
፪ , ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ ስለልጅነት ጊዜው በሩህ መጽሔት ላይ ሲጽፍ፡-
‹‹በልጅነቴ ስዕል በጣም እወድ ነበረ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሲደርስ የሰፈሬ ልጆች ሁሉ እኔጋ እያመጡ ነበረ የሚያስሉት፡፡ እና አምስት አምስት ሳንቲም እየተቀበልኩ የፈለጉትን እሰራላቸው ነበረ፡፡ ግን አንዳንዴ.. ሳንቲም በጣም ያስፈለገኝ ቀን.. አለ አይደለ.. ሰው በጣም የሚወዳቸው.. እና ቶሎ የሚወስድልህ መላዕክታት አሉ አይደል? እና የሰፈሬ ልጆች እኔ በአለላ ቀለም ለእንቁጣጣሽ ለዘመድ/ቤተሰብ የሚሰጡት መልዓክታት እንድስልላቸው ሲመጡ፡- ‹‹የትኛውን መልዓክ ነው የምትፈልገው?›› ብዬ እጠይቅና… ‹‹ቅዱስ ገብርዔልን›› ወይ ደግሞ ‹‹ቅዱስ ሚካኤልን›› ወይ ‹‹ፈረሠኛውን ጊዮርጊስን›› ካሉ.. የለም ለገብርኤል፤ ለሚካኤልና ለጊዮርጊስ ዋጋ ያስጨምራችኋል በአስር-አስር ሣንቲም ነው የምስልላችሁ.. ከፈለጋችሁ.. ሌላ መልዓክ በአምስት-ሣንቲም ልሳልላችሁ..›› እላቸዋለሁ፡፡
ልጅ ደግሞ የከለከልከውም ነገር ደስም ይለዋል፤ እንደገናም ሰዉም ስዕል ልትሰጠው ስትል ‹‹የገብርዔል አለህ?›› እያለ ታዋቂዎቹን መላዕክታት ቶሎ ስለሚገዛህ ልጆቹም ‹‹እሺ›› ብለው በአስር ሳንቲም ተስማምተን ያስሉኛል፡፡ እኔ ደግሞ ራሴም ለቅዱስ ዮሐንስ በብዛት የሚፈለጉትን መላዕክታት እስልና ለአላፊ አግዳሚው የበዓል መላዕክታት ግዙኝ እያልኩ ሳዞር እውላለሁ፡፡ ብዙው ስዕሌ ይሸጥልኝ ነበረ፡፡ ሆኖም አንዳንዴ እጥረት ያጋጥመኛል፡፡ ለምሳሌ ከያንዳንዱ መልዓክ አስር አስር ሥዕል ይዤ እወጣና.. የሚገዙኝ የቅዱስ ገብርኤልን ብቻ ይሆንና.. የሌሎቹ መላዕክታት ሥዕል እያለኝ.. ሌላው ይመጣና.. የገብርኤል አለህ? ይለኛል፡፡ አይ የሚካኤል ነው ያለኝ ብትለው አይገዛህም፡፡ ስለዚህ መላ አመጣሁ፡፡
ምን መሰለህ መላዬ… ? መላዕክታቱ በአንዳንድ ነገሮቻቸው ካልሆነ.. በብዛት ይመሳሰላሉ፡፡ ባይመሳሰሉም የያኔ ሰው ሽማግሌው አሮጊቱ ሁሉ ብዙ ጊዜ ባፉ ይጥራቸው እንጂ አይለያቸውም፡፡ ስለዚህ የመላዕክቱን ስም በሥዕሎቼ ላይ ሳልፅፍባቸው ይዤ መንገድ እወጣና፡- ‹‹ጋሼ/እትዬ ሁሉም ዓይነት አለኝ፤ እርስዎ የማንን ይፈልጋሉ?›› ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ‹‹የገብርኤል›› ካሉኝ.. እላዩ ላይ ‹‹ቅዱስ ገብርኤል›› ብዬ በያዝኩት አለላ መንከሪያ እጥፍና እሸጥላቸዋለሁ፡፡ ‹‹ራጉኤል›› ላለኝም ስዕሉ ያው ሆኖ ‹‹ቅዱስ ራጉኤል›› ለሌላውም በቃ እንደዚያ አደርግ ነበር፡፡ እና ሁሉንም ስዕሎቼን ሸጬ የምገባ እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ታዲያ ሁሌ አይምሰልሽ ይሄ፡፡ ባመት አንዴ እኮ ነው የሚያጋጥምሽ፡፡ ልጅነት ደስ ይላል መቼስ፡፡ አንዳንዱ እኮ እያወቀም ቢሆን – ያንቺ ነገር አስገርሞት ይሆናልም እኮ ‹‹ይሁንለት!›› ብሎ የሚገዛሽ!!! (ረዥም ሣቅ)››
፫ . አንዴ በሩኅ መጽሔት ላይ ስለድሮው የጋዜጣ ህይወት ሲናገር፡-
እንደ ሙሻዘር በመሰለ የጥያቄና መልስ አምዴ ላይ… ያኔ ይኸውልሽ.. ይሄ ሞዝቮልድ አልጋ.. የስፖንጅ ፍራሽ.. የመሣሠለውን ሰዉ ገና በደንብ አልለመደውም ነበረ፡፡ እና ብዙም ነገር ያመጣል እየተባለ ይወራም ነበረ፡፡ ታዲያ አንዱ ብልጥ አንድ ጊዜ እኔ ያንን እንድናገርለት ብሎ ምን የሚል ጥያቄ አመጣብኝ መሠለሽ?
‹‹ጋሼ ጳውሎስ፤ ይሄ የስፖንጅ ፍራሽ አጓጉል ሙቀትና ቅዝቃዜ የመያዝ ነገር ስላለው.. በሒደት የተኙበትን ለካንሰር በሽታ ሊዳርግ ይችላል የሚባለውን ነገር አንተ እንዴት ታየዋለህ?›› አለኝ፡፡
ከዚያ ምን ብዬ መለስኩለት መሰለሽ፡- ‹‹ወዳጄ፤ ጥያቄህ ጥሩ ነው፡፡ የስፖንጅ ፍራሽ ላይ መተኛት ለካንሰር በሽታ ይዳርጋል መባሉንም ሰምተህ ይሆናል፡፡ እኔም ሰምቼያለሁ፡፡ ግን ወሬውን አትመን ወዳጄ፡፡ ይህ የሣር ፍራሽ ነጋዴዎች ገበያቸው እንዳይቀንስ ያናፈሱት ወሬ ነውና ፈፅሞ አትመናቸው፡፡ ልዩነቱ ምን መሠለህ? የሣሩ ፍራሽ ርካሽ ነው፡፡ የስፖንጁ ደግሞ ትንሽ ወደድ ይላል፡፡ አንተ ግን ያለስጋት ኪስህ ኑሮህ በፈቀደልህ ተኛ፡፡ እንቅልፍን የሚሠጥ ፈጣሪ ነው፡፡ ባሻህና በቻልኸው ላይ ብትተኛ ምንም በሽታ አይነካህም፡፡›› ስል መለስኩለት፡፡
እሱም በሌላ ጊዜ፡- ‹‹እኔ ገንዘብ የሌለኝ በወዜ የማድር ደሃ ሰው ነኝ፡፡ ሚስቴ ነጋ ጠባ የስፖንጅ ፍራሽ ካልገዛኅ እያለች ብትነዘንዘኝ መፍትሄ ብታመጣልኝ ብዬ ነበር የጣፍኩልህ፡፡ አንተም ‹‹እግዚአብሔር ይስጥልኝ በመልስህ ደህና አድርገህ ገላገልከኝ፡፡ አሁን ግን የስፖንጅ ፍራሽ ገዝቼያለሁ፤ ይመስገነው እኔም ሚስቴም ደህና እንቅልፍ እየተኛን ነው፡፡ ባይሆን ለመነሳት ችግር ሆኖብናል፡፡›› የሚል መልስ ላከልኝ፡፡ ሁሌ አልጋዬ ላይ ጋደም ባልሁ ቁጥር አልረሳውም ያንን ባለ ፍራሽ፡፡
፬ .ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ አንድ ጊዜ በቃ ስለምንም ነገር ‹‹ውድ አንባቢ ሆይ…›› ብሎ ሊጽፍ በሞከረ ቁጥር ክልከላው በረታበት፡፡ ደግሞ ይህንኑም በተመለከተ ስሞታውን ‹‹ይድረስ ለክቡር ጓድ እከሌ…›› ብሎ ቢጽፍም ፀሐፊዎቹ ከፍተው እያዩ ለባለስልጣን ሳያደርሱ እያስቀሩበት ተቸገረ፡፡ ከዚያም አውጥቶ አውርዶ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ጽፎ በጋዜጣ አሳተመው፡- ‹‹ለእግዚአብሔር የተጻፈ ደብዳቤ›› ብሎ፡፡ በእርግጥ የወቅቱ ባለጊዜዎች አልገባቸው ሆኖ እንጂ.. የመልዕክቱ ሽሙጥ ለእነርሱ ነበረ፡፡
በዚያ ደብዳቤው በመጀመሪያዎቹ መስመሮች አካባቢ እንዲህ ይላል ጋሼ ጳውሎስ፡- ‹‹ይድረስ ለተከበርከው ቸሩ ፈጣሪ እግዚአብሔር ሆይ፡፡ ‹ለጤናህ እንደምን ከርመሃል?› ብዬ እንዳልጀምርልህ.. አንተ ለሁሉ ጤናን የምትሰጥ.. እንዴት ጤንነት አይኖርህ? እንዴትስ ብደፍር አንተን ስለጤንነትህ እጠይቅሃለሁ? ብዬ ተውኩት፡፡ ‹የት ነህ?›ም ብዬ እንዳልጠይቅህ.. አንተ ባንድጊዜ በሁሉም ስፍራ የምትገኝ.. እንዴት ተብሎ አድራሻህ ይጠየቃል? ብቻ ይህን ሁሉ አስቤ ሠላምታውን ተውኩት፡፡ ቅር እንደማትሰኝብኝ ተስፋ አደርጋለሁ?…›› እያለ ብሶቱን ሁሉ ለፈጣሪ እየደረደረ.. እያሳቀም፤ አንጀትን እየበላም ይዘልቃል፡፡ አይ ጋሼ ጳውሎስ!!! ጉዱ የማያልቅ ሰው ነበር፡፡
፭ ፠ ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ ራሱ በቤቱ ያሳደጋቸው ወንድና ሴት አንበሶች ነበሩ፡፡ እርሱን ለምደውታል፡፡ ጋሼ ጳውሎስ ስለሱ ሲናገር፡-
‹‹ከጊዜ በኋላ ወንዱ አንበሳ ቁጣው እየጨመረ መጣ፡፡ ጭራሽ የቤቱን ሰው ሁሉ – ከጳውሎስ ኞኞ በስተቀር – አላስጠጋም አለ፡፡ ሰፈሩን ሁሉ ያሸብረው ነበር፡፡ በተለይ አንዴ እጅግ ተቆጥቶ ሚስቱን (ሴቷን አንበሣ) በክርኑ ደቁሶ ገደላት፡፡ እየቆየ ሲሄድ ቀለቡም ችግር ሆነ፡፡ በዚያ ላይ ሰፈሩ ሁሉ ስሞታ በስሞታ ተጥቀለቀለቀብኝ፡፡ ያኛው ልታስጨርሰን ነው ይላል፡፡ ይሄኛው ጎረቤት ልጆቻችንን ልታስበላ ነው ወይ? ይላል፡፡ በቃ ሁሉም አንበሣውን ተመቀኘው፡፡ ሰው ለካ በሰው ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ኧረ ቆይ.. ሰው በአንበሣ ላይ እንዴት እንደሚቀና ብታዪ ጉድ ነው የምትዪው፡፡ ለካ ሰውን ቅናት ውስጥ የሚከትተው ፍርሃት ነው፡፡ …
‹‹ፈርተውት እኮ ነው፡፡ እና በቃ ሁሉም ከሠፈራችን ይውጣልን አሉ፡፡ እርሱም አመሉ አስቸገረ፡፡ አንዴ ተቆጥቶ ላበላው ስል ክንዴን ይዞ በፈጣሪ ተዓምር ነው የለቀቀኝ፡፡ እኔም ምንም እንኳ እንደ ልጄ ባየው.. በቃ ከሰዉም ከኔም ከምኑም አልሆነ ብዬ እያዘንኩ እንደምንም ጨከንኩና መንግስት እንዲረከበኝ ጠየቅኩ፡፡ መንግስትም ተረከበኝ፡፡ ያ ነው ስለ አንበሳው ያለው ትክክለኛው ታሪክ፡፡ እጅግ ለማዳ ነበረ ብታዪ፡፡ አቤት ጠባይ፤ አቤት ግርማ ሞገስ፤ አቤት ጨዋታ ወዳድነቱ፤ ምን ዋጋ አለው? መጨረሻው አላምር አለ እንጂ፡፡
‹‹አየሽ ሁሉም ፍጥረት በሰላም ለመኖር መጀመሪያ ከራሱ ጋር መስማማት አለበት፡፡ ከራሱ የተጣላን ፍጡር ምን ልታደርጊው ትቺያለሽ? አዎ፡፡ ከሌላ ሳይሆን ፈጣሪ በመጀመሪያ ከራሳችን ጋር እርቅ ያውርድልን ማለት ነው፡፡ ከራሱ ያልተስማማ፤ ከሌላውም ስምም ሆኖ መኖር ያዳግተዋል፡፡ እኔም በአንበሣዬ የተገነዘብኩት ያንን እውነት ነው፡፡ ይሄ በተለይ ለእኛ ለሰዎችም ይሠራል ባይ ነኝ እንግዲህ እኔ፡፡ የሚቀበለው ይቀበለኝ፡፡ እኔ ይህን እውነት ያወቅኩት ከአንበሣ ጋር መከራዬን በልቼ ነው፡፡ የማይቀበለው ሰው ቢኖር ግን ከራሱ ሕይወት መከራውን በልቶ ሲደርስበት ይረዳዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ፈጣሪ ከራሳችን ጋር ያስማማን፡፡ ከዚያ ከሌሎች ጋር፡፡››
/በነገራችን ላይ አንጋፋው የሐገር ፍቅር አርቲስት አብራር አብዶ የጋሼ ጳውሎስ ኞኞን ‹‹ለእግዚአብሔር የተጻፈ ደብዳቤ›› የሚል ጽሑፍ በቃለ-መነባንብ መልክ በመድረክ ወርቅ አድርጎ ይጫወተዋል፡፡ ድሮ ድሮ ላይ አብራር የተቀረጸውን ይህን ትዕይንት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይቀርብ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አሁን አየሁት የሚልም ገጥሞኝ አያውቅም፡፡/
በመጨረሻ የዛሬ ሶስት ዓመት ይህን ጽሑፍ ሳወጣ፣ አንድ ‹‹ዜና ኤላ›› የተባለ አስተያየት ሰጪ ስለ ጋሼ ጳውሎስ የሰጠውን ኮመንት አቅርቤ ልሰናበት፡፡ እንዲህ ነበር ያለው፡-
‹‹ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም። ዘዴኛ፣ ደፋርናአዋቂ ነው። የህዝብ ጉዳይ ለጳውለስ ከሁሉ የበለጠ ነው።በ3000 ሺ ብር በጨረታ ሲትሮን መኪና ከአራተኛ ክፍለ ጦር ገዝቶ በመንቀባረር ኖራል።ቤቱ ውስጥ አምሳ ማሳደግ ጀምሮ ሆዱን አልቻልኩትም” ድረሱልኝ” በማለት ይታወቃል። ሚስቱን ያገኛት ለቅሶ ላይ ደረቷን ስትመታ እንደሆነ ተናግራል።የሚኒሊክን መጽሐፍ ለመፃፍ ሲነሳ ብዙ ወዳጆች ሊያሳጣው እንደሚችል ብዙ ሰው ገምቷል። ወጣቱ ትውልድ የጳውሎስን ታሪክ ለመማር ተግቶ መስራት ይኖርበታል። ሁለገብ ሰው ወያኔን አቅምሳል።ወያኔን አትፈራቸውም ተብሎ ተጠይቆ: አልፈራቸውም በማለት መልሳል።ምክንያቱም መገነዣዬን ገዝቼ ስለተቀመጥኩ ነው በማለት ተናግራል።የ1966 ድርቅ እንደ ጳውሎሰ የሰራ የለም።ምንአልባት ኮሚሽነር ሽመልስ አዱኛ የእውነት እየአለቀሰ ዕርዳታው በወቅቱ ለተረጁዎች አድርሰዋል። ስንቱን መዘርዘር ይቻላል? …።››
ለጋሼ ጳውሎስ ኞኞን ነፍስ የበዛ ሠላምን ተመኘሁ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic