>

በአማራ የኅልውና ተጋድሎ ላይ እያጎነቆለ የሚገኘው የጎጠኛነት አደጋ !!! (አቻምየለህ ታምሩ)

በአማራ የኅልውና ተጋድሎ ላይ እያጎነቆለ የሚገኘው የጎጠኛነት አደጋ !!!

 

 

አቻምየለህ ታምሩ
የአማራ የኅልውና አደጋ ስንል በዋናነት አማራ ክልል ከሚባለው ውጭ በመላው ኢትዮጵያ ባባቶቹ ርስት፣ ባያቶቹ ባድማ  እንደ ክዋክብት ተሰራጭቶ በሚኖረው አማራ ወይም ብአዴን በ1986 ዓ.ም. ባወጣው ፕሮግራሙ  መግቢያ ላይ «በአማራ ብሔር ስም የሚነግድ ትምክህተኛ»  እና «የሌሎችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለመጨቆን ከአማራ ክልል የሄዱ ነፍጠኞች » ሲል በፈረጀው አማራ ላይ የተጋረጠውን በሕይወት የመኖር ያለመኖር የኅልውና አደጋ ማለታችን ነው።
የዚህ የኅልውና አደጋ ዋነኛ ማሳያዎቹ አርባጉጉ፣ ወተር፣ ጅግጅጋ፣ ሐረር፣ ወለጋ፣ አርሲ፣ ጅማ፣ ጉራፈረዳ፣ ወልቃይት፣ ራያ፣ ወዘተ ይኖሩ የነበሩ አማሮች  ቤታቸው እየተቃጠለ፣ ንብረታቸው እየተወረሰ፣ ያለፍርድ እየተገደሉ፣ እጃቸውና አንገታቸው እየተቆረጠና ቤት ተዘግቶባቸው እየተቃጠሉ በግፍ እንዲሞቱና ከዚህ ሁሉ የተረፉት ደግሞ እንዲፈናቀሉ የተደረጉበት የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጽዳትና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው። አማራ ክልል በሚባለው ከሚኖረው የአማራ ሕዝብ ቁጥር ያልተናነሰ ቁጥር ያለው አማራ ክልል ከሚባለው ውጭ የሚኖረው አማራ ዛሬ ላይ አስከፊ የኅልውና አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል።
የአማራ የኅልውና አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስከፊ ደረጃ ላይ በደረሰበት ሁኔታ ነው እንግዲህ እነ በረከት ሰምዖን ብአዴን የሚባለውን  የአጋሰሶች ስብስብ ፈጥረው አማራ ክልል በሚባለው አካባቢ የሚኖረውን አማራ በእንደራሴነት ሲገዘግዝ ግፍና በደል መሮት በአንድ እንዳይነሳ፣  እንዳይተማመንና አንድ ልብ እንዳይሆን አድርገው የዘረጉት የቢሮክራሲና የቁጥጥር ስርዓት የወለዳቸው ትርኪምርኪዎች የተጫነባቸውን ቆሻሻ ሳያራግፉ ወደ አማራው ትግል ስለገቡ ዛሬ ላይ አማራውን በጎጥ ወስነው ገመት ጉተታ ውስጥ በመክተት ትኩረቱን  እንደ አማራ በተጋረጠበት የኅልውና አደጋ ላይ እንዳያደርግ እንቅፋት ሆነውበት የሚገኙት። እነዚህ ጎጠኞች አማራው በጣምራ ሊያደርገው የሚገባውን የኅልውና ተጋድሎ አቅጣጫ አስተው አማራ ርስበርሱ እንዲከሳከስና ሞትን እንዲያነግስ፤ ጠላት ያደረጉት ሰርግና ምላሽ  እንዲሆንላቸው እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ይገኛሉ።
ሰማዩንም ምድሩንም «የኛ ነው» የሚል እጅግ ነውረኛ የሆነ የአፓርታይድ አገዛዝ በሕዝባችን ላይ ተጭኖ፣ የሕዝባችን የኅልውና አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ፣ ሰብዓዊ መብቱ ተገፎ፣ ሐሳቡን እንዳይገልጽ ታፍኖና ተለጉሞ፤ የኩራት በርኖሱ ተቀዶ፣ በየሄደበት እየታገተና የአፓርታይድ አገዛዙ ባበጀለት የቁም መቃብር ውስጥ እየተሰቃየ ባለበት በዚህ ወቅት የአፓርታይዱ አገዛዝ ግብረበላ ሆነው የኖሩትን የብአዴን ኮልኮሌዎች በአንድ አካባቢ ተወላጅነት ወስነው ለነሱ ጭፍራ የሆኑ የብአዴን ነውረኞችን [[በሕይወት የሌሉትም ይሁኑ በቁም የሞቱት] ሲያወድሱና ሲያወግዙ የሚውሉ የተንኮል ውርስ የተጠናወታቸው ጎጠኞችና የአማራ ሕዝብ አላማ የሌላቸው ከንቱዎች ከዋነኞቹ የፋሽስት ወያኔና የናዚ ኦነግ አህዮች ከሆኑት ከነውረኛ ብአዴኖች ባልተናነሰ በጋራ ልንፋለባቸው የሚገባ  የአማራ ሕዝብ የኅልውና አደጋዎች ናቸው።
Filed in: Amharic