>

ጎርፍና ግፍ!!! (ዳንኤል ክብረት)

ጎርፍና ግፍ!!!

ዳንኤል ክብረት
ሰሚ ካጡ የሶማሌ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል!?!
አንድ ሰው የጠፋች የአካባቢው ግመል ፍለጋ ጫካ ይገባል፡፡ ከብዙ መከራ በኋላ ያቺን ግመል አግኝቶ ከተማ ገባና ግመሏን ለባለቤቱ ሳይመልስ ሐሳቡን ቀይሮ ራሱ ያልባትና ይጋልባት ጀመር፡፡ ግመሏን ከአውሬ ለማዳን ጫካ ገብቶ የነበረው ሰውዬ እርሱ ራሱ ግመሏን መውሰዱ ብዙዎችን አስገረማቸው፡፡ ትንሽ ቆየና ከዚያች ከአንዷ ግመል ወተት እያለበ በግመሏ ላይ ተቀምጦ እየዞረ ለአካባቢው ሰው ወተት መሸጥ ጀመረ፡፡ ነገር ግን የግመሏ ወተት በአንድ ጊዜ ሀብታም ሊያደርገው አልቻለምና ሌላ ነገር አሰበ፡፡ በወተቱ ውስጥ ውኃ እየጨመረ ቀላቅሎ መሸጥ፡፡ ‹‹ሰውም ምነው የሰውየው አመሉም ወተቱም ተቀየረሳ›› እያለ ዝም ብሎ ይገዛ ጀመር፡፡ (ይገዛ የሚለው ቃል ጠብቆ እንዳይነበብ አሳስባለሁ)
ሰውዬውም በግመል ወተቱ ላይ ውኃን እያበዛው፤ የግመሉም ቁጥር እየጨመረ ሄደ፡፡ እየቆየም በግመልና በግመል ወተት ከሚታወቁት የሀገሩ ነጋዎች በላይ እኔ ነኝ ያለ፣ ቢጠሩት የማይሰማ ሀብታም ሆነ፡፡ የአካባቢው ሰዎችም ‹‹ይኼ ሰው ትናንት ምንም አልነበረውም፡፡ የጠፋ ግመል ሊፈልግ ጫካ ገባ፤ ተመልሶ መጣ፤ ከተማ ገባ፤ በአንድ ጊዜ ተመነደገ›› እያሉ ይገረሙ ነበር፡፡ ወተት ብቻ ተሽጦ እንዴት በሁለት ዓመት ሦስት መቶ ግመል ሊገዛ ቻለ፡፡ የሚለው የሕዝቡ ሁሉ ወሬ ሆነ፡፡
ሰውዬው ግን ምንም አልመሰለው፤ በወተቱ ውስጥ ውኃውን እየጨመረ ቀጠለ፤ እንዲያውም እበላ ባይ ቱልቱላዎችን ቀጠረና የእርሱ ወተት ሰው ጠጥቶት የማያውቅ መሆኑን እንዲለፍፉ አደረ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ወተቱን ለመልኩ ብቻ ይጨምርበትና የቀረው ውኃ ያደርገው ነበር፡፡ ‹‹ኧረ ሕዝቡ እያማረረ ነው፤ በአንድ በኩል በድንገት ተነሥህ፤ ከተማ ገብተህ ቢጠሩህ የማትሰማ ሀብታም ሆንክ፤ ይኼንን ስንታገሥህ ደግሞ ወተቱን ቀንሰህ ውኃውን እያበዛህ መሸጥ ጀመርክ፡፡›› ሲሉት ‹‹ተውት ባካችሁ፣ ለመሆኑ የእኔን ወተት ከመግዛት ውጭ ሕዝቡ ምን አማራጭ አለው፤›› ይል ነበር፡፡
በወተቱ ውስጥ የሚጨመረው ውኃም እየበዛ፣ ግመሎቹም እየበዙ ሄዱ፡፡ ግመሎቹም ሀገሩን ሞሉት፡፡ የሚያድሩበትና የሚግጡበት ልዩ የከተማ መሬት ተሰጣቸው፡፡ ወንዝ ዳር የሚገኝ ለም መሬት፡፡
አንድ ቀን ሸበሌ ወንዝ አጠገብ ግመሎቹን አሠማርቶ እርሱ አንድ ዛፍ ጥላ ሥር ሻሂ ከልጁ ጋር ይጠጣ ነበር፡፡ በዚህ መሐል ከደጋ የዘነበ ዝናብ ወንዙን ሞላውና በግራ በቀኝ ሲግጡ የነበሩትን ግመሎች ጠራርጎ ወሰዳቸው፡፡ የጎርፉን ድምጽ ሰምተው አባትና ልጅ ከጥሻው ሲወጡ ግመሎቻቸው ሁሉም ተወስደዋል፡፡ እሪታውን ሰምተው የተሰበሰቡ የሀገሩ ሰዎችም በአግራሞት የሆነውን ነገር ይመለከቱ ነበር፡፡
‹‹አየህ›› አሉት አንድ አዛውንት ‹‹ያ በወተቱ ላይ እየጨመርክ የሸጥከው ውኃ ተጠራቅሞ፣ ተጠራቅሞ ጎርፍ ሆኖ ግመሎቹን ወሰዳቸው፡፡ ግፍ እንደዚህ ነው፡፡ ሲሠራ ቀላል ይመስላል የተጠራቀመ ዕለት ግን ጎርፍ ሆኖ ይወስዳል፡፡ ተው ብንልህ አልሰማ ብለህ ነበር፤ አንተ በግፍ ግመል ስትሰበስብ የግፉ ውኃ ሌላ ቦታ እየተሰበሰበ መሆኑን ረስተህዋል፡፡ ቀን ጠብቆ ግን ይሄው ጎርፍ ሆኖ መጣ›› አሉት፡፡
Filed in: Amharic