>

ይድረስ ለቤልጂግ አሊ - ባለህበት! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ይድረስ ለቤልጂግ አሊ – ባለህበት!

 

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ 

 

በዚህን መላው ዓለም በኮሮና ቫይረስ፣ ኢትዮጵያችን ደግሞ ለዬት ባለ ሁኔታ በዘረኝነት ጭምር ተወጥራ ኤሎሄ በበዛበት ወቅት ለግለሰብና ስለግለሰብ መጻፍ ሥራ ፈትነት መሆኑን እረዳለሁ – ለዚሁም ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ይሁንና ግለሰብ የማኅበረሰብ አባል እንደመሆኑና በመገንባትም ሆነ በማፍረሱ ረገድ ያለው አወንታዊም ይሁን አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ አንዳንዴ ሳይበዛ ስለግለሰቦች መናገር ወይ መጻፍ ብዙም ክፋት የለውም – ቢቻል ደግሞ ስለመጥፎም ሆነ ደግ ተግባራቸውና አስተሳሰባቸው ቢሆን ይመረጣል፡፡ የቤልጂግ ወዳጅ መንግሥቱም ሆነ ሂትለርና ሙሶሊኒ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ መለስም ግለሰብ ነበር፡፡ ጃዋርም ግለሰብ ነው፡፡ የነዚህን ግለሰቦች ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሁሉም የሚያውቀው ነውና ዝርዝር ውስጥ አልገባም፡፡

ሰሞኑን ወደ ድረገፆች የላክኋት አንዲት ጽሑፍ ነበረች፡፡ “ ‹ሰው ካልሄደ ወይ ካልሞተ አይመሰገንም› መባሉ እውነት ነው” – ትላለች ርዕሷ፡፡ ፈልጋችሁ ብታነቧት “ውብ” ናት አትጎዱም፡፡ ችግሩ በዚህች የአሁኒቷ ኢትዮጵያ ሰውን ማመስገንም ሆነ መውቀስ አይቻልም ወይም ከሆነ አካል ፈቃድ መጠየቅ ሳይኖርብህ አይቀርም፡፡ በዚህች መጣጥፍ ለመንግሥቱ ታቦት ይቀረጽ አላልኩም፤ ለኦህዲዱ መሪ ለፓስተር ዮናታን ማነው ለዶክተር አቢይ በስሙ “ቸርች ይቋቋምለት” የሚል ቃል አልወጣኝም፡፡ የመሰለኝን እውነት በግልጽነት ተናገርኩ፡፡ የምልከው ደግሞ ሆሄያትን ስነካ ለሚመጡልኝ አድራሻዎች እንጂ እገሌን ከእገሌ አልመርጥም፡፡ የምልክለት ሰው ከፈለገ ያነባል ካልፈለገም “delete” ያደርጋል እንጂ አንጃ ግራንጃ ስድብና ብሽሽቅ ውስጥ አይገባም ወይንም እንዲገባ አይጠበቅም፡፡ ከገባ ግን ያ ሰው የሆነ ሥነ ልቦናዊም ይሁን ሌላ ችግር አለበት፤ ዕድገቱም እንደተጓተተ መገመት አይከብድም፡፡ ንቆ መተው እያለ የኢሜል ሣጥንህ ውስጥ በገባ ነገር ሁሉ ግሥላ አትሆንም፡፡ እኔ ለምሣሌ ከ10 ሽህ በላይ ያልከፈትኳቸው የኢሜል መልእክቶች አሉኝ፡፡ ከነዚህ ለአንዱ ስድብ ብልክ ግን ተናድጃለሁ ማለት ነውና ስብዕናየን ያወርዳል፡፡ መልስ የምሰጥ ከሆነም በጨዋ ደምብ መሆን አለበት፡፡ ቃላትን እንዴት መጠቀም እንዳለብኝ ካላወቅሁ ይበልጥ የምጎዳው እኔ ራሴው ነኝ፡፡

ለዚህ ሰውዬ – ለቤልጂግ አሊ – መጻፍ የፈለግሁት ግን ብዙዎችን በርሱ ውስጥ ማግኘት ስለፈለግሁ ነው – ደግሞም ወደፊት እንዲህ ያለ ቅሌት አይለምደኝም፡፡ (I’m gonna tell him up to his bead tying throat! እንግሊዝኛው ጠፋህ እንዴ ወንድማለም? “እስከዶቃ ማሰሪያ እነግረዋለሁ!” እያለኩህ እኮ ነው በአራዳ እንግሊዝኛ፡፡)

ቤልጂግን  ፌስቡክን ጨምሮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አውቀዋለሁ፡፡ ይህ ስም ግን የብዕር ይሁን የእውነት አሁን ማስታወስ አልችልም፡፡ በዚህ ስም የሚጠራ ሰውዬ ግና ኃያል ሥነ ልቦናዊ በሽታ እንዳለበት ከተረዳሁ ቆይቻለሁ፡፡ እንደዚህ ያለ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ደግሞ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ዕድል ካገኙ ለሀገርና ለሕዝብ ትልቅ ነቀርሣ ናቸው፡፡ እናም ከተቻለና ዘመድ ካላቸው እምነታቸውም የሚፈቅድ ከሆነ ኮከባቸው ወይም ክፍላቸው ተቆጥሮ ወደ ጠበል ነው መሄድ ያለባቸው፡፡ ምንም ዓይነት የህክምና ጥበብ የተጣባቸውን አእምሯዊ ደዌ ሊፈውስ አይችልም፡፡ ቀድሞ አለመለከፍ ነው፡፡ መነሻቸው ትክክል ሊሆን ቢችልም ነገሩን እየለጠጡ ከሰውነት ተራ ይወጣሉ፡፡

በሥነ ልቦናው መስክ የተለያዩ የአእምሮ ህመሞች አሉ፡፡ ከነዚህ ዋናውና ይህ ሰው የተለከፈበት የአእምሮ በሽታ ዲሊውዥን (Delusion) ይሰኛል፡፡ እርግጥ ነው የአእምሮ በሽታዎች ተያያዥ ናቸው – አንዱን ከሌላው ለመለየት ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የአእምሮ በሽታ ማለት በጥቅሉ ከእውነት ጋር መጣላት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ፓራኖይድም አልከው ሜጋሎማኒያ፣ ሳይኮሲስም አልከው እስኪዞፍሬኒያ … ያው አእምሯዊ  ኢ-ሥርዓታዊነት ወይም disorder ነው፡፡ ይህ ሰውዬኣችን መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አሁንም እያሳደደው የሚገኝ ምሥኪን ዜጋ ነው፡፡ መንግሥቱ ራሱ ጉድጓዱ ተምሶና ልጡ ተርሶ አንድ እግሩ መቃብር ውስጥ ባለበት ሁኔታ ሥራ ፈትቶ ቤልጂግን እስካንዴኔቪያን አገሮች ድረስ ሄዶ ዕረፍት ሲነሳው ይታያችሁ፤ አለመታደል ነው በውነቱ፡፡ ቆሞ ቀር አስተሳሰብና አመለካከት ለብዙ ችግር ይዳርጋል፡፡ የዚህ ሰውዬ ዕድሜ ቢሰላ ከሦስት ቢበዛ ከአራት አይበልጥም፡፡ ቤልጂግ የኖረውና የሞተው ከ1968 እስከ 1972 ነው፡፡ የአራት ዓመት ዕድሜ ልጅ ነው እንግዲህ የኔን ጽሑፍ አንብቦ ከሥር ያስቀመጥኩትን ግልፍተኛ አስተያየት የሰጠው፡፡ የአራት ዓመት ልጅ ምንም ሊረዳ አይችልም፡፡ የኔን ጽሑፍ ለመረዳት ቢያንስ ከ18 ዓመት መብለጥ አለበት፡፡ የተቃወምኩት መቃወሙን ሳይሆን የተቃወመበትን መንገድ መሆኑ ደግሞ ልብ ይባልልኝ፡፡

ጅምሬን ከማጠናቀቄ በፊት ለማንኛችንም የሚሆን አንዳንድ ነጥቦችን ላስቀምጥ፡፡ ከለውጥ በስተቀር የማይለወጥ እንደሌለ ይነገራል፡፡ አንድ ሰው ሊበድለን ይችላል – አውቆም ሆነ ሳያውቅ፡፡ ግን ያን በደል ዕድሜ ልካችንን እያሞሰካን ከኖርን ሌላ ሥራ የለንም ማለት ነው፡፡ የዛሬ 40 ዓመት የተሠራብን ግፍና በደል ቀንም ሌትም እየመጣ የሚያስጨንቀን ከሆነ የዕድገታንን በሮች ሁሉ ጥርቅም አድርገን ዘግተናል ማለት ነው፡፡ ይቅርታርና ምሕረትን ከሚያስተምሩን ከፈጣሪም፣ ከባህልና ወግም ተራርቀናል ማለት ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥቱን ሥርዓት በዕጥፍ ድርብ የሚያስከነዳ ስንትና ስንት ጉድ እየተሠራ እንዳለ ቤልጂግ አያውቅም – እዚያው 69ኙ ላይ ተቸክሎ ቀርቷል፡፡ በአማሮች ላይ ሦዶም ወገሞራዊ ውርጅብኝ እንደደረሰባቸውና በኢሕአፓ አባላት ላይ የደረሰውን ስቃይ እንደጽድቅ የሚያስቆጥር ግፍና በደል በኢትዮጵያውያን ላይ ባለፉት 30 ዓመታት እንደወረደ ቤልጂግ በሕጻንነቱ ስለሞተ አንዳችም ነገር አያውቅም – ከዚያ ወዲህ ላለው ነገር በአምኔዥያ ኅሊናው ታውሯል፡፡ በምኒልክ የደነቆረ “ምኒልክ ይሙት!” እያለ ሲምል ይኖራል እንደተባለው ነው፡፡ ቤልጂግ አሁንም ያለው 69 እና 70 ዓመተ ምሕረት ነው፡፡ “መንግሥቱ ለፍርድ ይቅረብ!” እያለ እንደዶን ኪሾት ከተራራና ከንፋስ ጋር እየተፋለመ ይገኛል – ይህ ምሥኪን ዜጋችን፡፡ ዘመድ ካለው ምከሩት – (ኦ! ይቅርታ – ለካንስ ይህን መሰሉ በሽታ በምክር አይመለስም)፡፡ እኛን ሊያፈራርሰን የደረሰው የዘመኑ ኮረና ቫይረስ ማለቴ በቀለ ገረባና ጃዋር መሀመድ ከአባታቸው ከዶፍተር ገመቹ መገርሣ ጋር የሸረቡት ዐረባዊ በተለይም ግብፃዊ ሤራ እንጂ መንግሥቱ አሁን ፈረድንበት አልፈረድንበት የራሱን ሒሳብ ሊያወራርድ የቀረው ግፋ ቢል አንድ ሐሙስ ነው፡፡ ቤልጂግ ግን አንደኛው መነኩሴ በርህራሄ ሴትዮን በትከሻው ተሸክሞ ወንዙን ካሻገራት ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኋላ “ህጋችንን ጥሰህ ለምን ሴት ተሸከምህ?” ብሎ ለጠየቀው ጓደኛ መነኩሴ ሴትዮዋን በጭንቅላቱ ውስጥ እስከዚያን ጊዜ ድረስ እንደተሸከማት በምፀት እንደተናገረለት ልክ እንደዚያ የዳላይ ላማዎቹ ነገር አመንዣኪ መነኩሴ ሆነና መንግሥቱንና ጭካኔውን በአእምሮው እንደተሸከመ ሊያረጅ ነው – አረጀ እንጂ የምን ሊያረጅ ነው፤ ቤልጂግ ቢያንስ ከአሁን በኋላ እንኳን ሰው ሆኖ የሰውነትን ፀጋዎች በመላበስ እንደሰው እንዲመላለስባቸው እባካችሁን እንጸልይለት፡፡ (ከተናግሮ አናጋሪ ይሰውራችሁ!)

ይህን ነው የላከልኝ – ለራሴም እንደማልራራ ከዚህ ተረዱ! እንጂ ምን ቅብጥ አድርጎኝ ስድቤን ለሰዳቢ አሳልፌ እሰጣለሁ?

 

Beljig Ali
Fri, Mar 20, 3:59 PM (18 hours ago)
to me

Please dont send me your garbage any more.

 

Thanks 

 

EMAIL: ma74085@gmail.com

Filed in: Amharic