>
5:18 pm - Tuesday June 15, 4241

እኛ እና የቫይረስ ጦርነት፤ በመንግስት ሊወሰዱ የሚገባቸው አፋጣኝ እርምጃዎች፤ (ያሬድ ሀይለማርያም)

እኛ እና የቫይረስ ጦርነት፤ በመንግስት ሊወሰዱ የሚገባቸው አፋጣኝ እርምጃዎች፤

ያሬድ ሀይለማርያም
 
ወገኔ ሆይ ክፉ ቀን ከፊታችን ተደንቅሯል። የሰሞኑ ሁኔታ ጦርነት በጥይት ብቻ ሳይሆን በቫይረስም ሊካሄድ እንደሚችል የሚያሳይ ነው። ችግሩ ስንቶቻችን ነገሩን እንደ ጦርነት ወስደነዋል? ጥይት ካልጮኸ፣ መድፍ ካልተንጎደጎደ፣ ቦንብ ካልዘነበ ጦርነት የተካሄደ የማይመስለው ያገሬ ሰው አለም ከቫይረስ ጋር የገጠወ ፍልሚያ እንዴት ሊያስተናግደው ይሆን? አዎ ከቫይረስም ጋር ጦርነት ይካሄዳ፤ ወይም በጥይት ፋንታ በቫይረስም ጦርነት ይካሄዳል።
 
በሳይንስ እና በሥልጣኔው ይታበይ የነበረው አለም ሊቋቋመው ያልቻለው የኮሮና ቫይረስ ከአንድ የአለም ጫፍ እስከ ሌላኛው ሁሉንም ስጋት ውስጥ ከቷል። በሕክምናው ሳይንስ እጅግ የረቀቁት ምዕራባዊያን የሚይዙት፣ የሚጨብጡት ጠፍቷቸዋል። ሕዝባቸውን በየጉሮኖው እንዲሰትር፣ ቀለቡን በጊዜ እንዲገዛ፣ እራሱን ከማናቸውም ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዲያቅብ፣ ቡናም እንዳይጣጣ አዋጅ አስነግረውም የወረርሽኙን መስፋፋት ግን ለማስቆም ተስኗቸዋል። ሥልጡኑ ሕዝባቸው በሕክምና ባለሙያዎች እና በመንግስታቱ የታዘዘውን ቀጭን ትዕዛዝ ውልፍት ሳይል ቢተገብርም በየቀኑ በአውሮፓ ውስጥ ብቻ ከአንድ ሺ በላይ ሰው እየሞተ ይገኛል። 
 
የምዕራቡን አለም ዝግጅት፣ የሕዝቡን ተባባሪነት እና በሽታውን ለመቋቋም ያላቸውን አቅም እያሰብኩ አገሬን እና የደቦ ኑሮ የሚኖረውን ወገኔን ሳስብ እነሱን እንዲህ ያንገዳገደ ቫይረስ እኛን ምን ያደርገን ይሆን? እያልኩ እጨነቃለሁ። አዎ የምዕራቡ አለም ሕዝብ ኑሮው ለየቅል ነው። ማንም በማንም ላይ ተዛዝሎ አይኖርም። ማህበራዊ ሕይወታቸውም እጅግ የሳሳ ከመሆኑም የተነሳ በደህናውም ጊዜ ሰዎች ከሚገናኙበት ይልቅ የማይገናኙበት ጊዜ ይበዛል። ጎረቤትህን ወይም ከጎንህ የሚኖር ዘመድህን ሳታየው ሳምንታት ወይም ወራት ሊቆጠሩ ይችላሉ። ዛሬ ደግሞ በአዋጅ ከማህበራዊ ቅርርብ እራቅ ስለተባለ ሁሉም የሚሸምተውን ሸማምቶ በየቤቱ ከትሞ ጊዜው ያመጣብንን ጣጣ በዜና ይከታተላል።
 
በተቃራኒው ኑሮው በደቦ የሆነው የአገሬ ሰው የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ከጠዋት እስከ ማታ እንዲሁ በየመንገዱ ሲዋትት፣ ሲጋፋ እና ሲሰለፍ ይውላል። እኛ ዘንድ የሚያሰልፉን እና እርስ በርስ ሲያጋፉን የሚውሉ ነገሮች ብዙ ናቸው። ለታክሲ ሲሰለፍ፣ ለዳቦ ሲሰለፍ፣ ለመገበያየት ሲሰለፍ፣ ለጸሎት ሲሰለፍ፣ ለህክምና ሲሰለፍ፣ ለትምህርት ሲሰለፍ፣ እጅ ለመታጠብ ሲሰለፍ፣ መዳኒት ለመግሳት ሲሰለፍ፣ ለመመጽወት ሲሰለፍ፣ ለድጋፍና ተቃውሞ ሲሰለፍ ይውላል። ኑሯችን የሰልፈኛ ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል። ተሰልፈን በወረፋ ነው ኑሮን የምናጣጥማት። በዚህ ኑሮዋችን ላይ የኮሮና አይነት ወረርሽ፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው የሚሆነው።     
 
ይህ አለም አቀፍ ወረርሽኝ በአገራችን ምልክት ካሳየበት ጊዜ ጀምሮ በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የሚመሰገኑትን ያህል አንዳንዱም ግራ የሚያጋባ ነው። መንግስት ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ቀድሞ መከልከሉ እጅግ የሚያስመሰግነው ቢሆንም በራሱ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የሚካሄዱ ስብሰባዎች እና የኃይማኖት ተቋማት ላይ ጥብቅ እርምጃ አለመወሰዱ በሌሎች መንገዶች እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ሁሉ ገደል ይጨምራቸዋል።
 
መንግስት ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሳይወጡ በፊት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ እና ማናቸውንም ስብሰባዎች የሚከለክል አዋጅ ሊያውጅ ይገባል። በበርካታ የአውሮፓ አገራት ያለ በቂ ምክንያት መንገድ ላይ መውጣት እና ከሁለት ሰው በላ ሆኖ መሰባሰብ መከልከል ብቻ ሳይሆን በገንዘብ እና በእስርም የሚያስቀጣ ተግባር ተደርጎ ታውጇል። ይህንንም እንዲያስፈጽሙ ቁጥራቸው በርከት ያለ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ፖሊሶች እና የመከላከያ ሰራዊትም ተሰማርቷል። 
 
ኢትዮጵያም ሳይዘገይ በፊት የሚከተሉትን እርምጃዎች ብትወስድ፤
 
+   ለተወሰኑ ሳምንታት ወይም ለአንድ ወር የሚቆይ ማናቸውንም አይነት ስብሰባዎች እና የአደባባይ ዝግጅቶችን ማገድ፤
 
+ ሁሉም የኃይማኖት ተቋማት መደበኛ የሆኑ የጸሎት እና የትምህርት ፕሮግራሞቻቸውን እንዲሰርዙ እና ይህን ተላልፈው በሚገኙ ተቋማት ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ፤ 
 
+ ምዕመናን በየቤታቸው ሆነው ጸሎት እንዲያደርሱ እና ወደ እነዚህ ሥፍራዎች ለጊዜው እንዳይሄዱ ጥብቅ ማሳሰቢያ መስጠት፤
 
+ የባህል ህክምና እና የኃይማኖት ፍወሳ የሚካሔድባቸው ቦታዎችም እንዲሁ ለተወሰነ ጊዜ ተዘግተው እንዲቆይ ማድረግ፤ ለዚህም ዋናው ምክንያት ሰዎች ቫይረሱ ይዟቸው ቢታመሙ እንኳን ነገሩን ለመንግስት አሳውቀው ወደ መደበኛ ጤና ጣቢያዎች ከመሄድ ይልቅ ወደ ጸበል እና የባህል ህክምናዎች ወይም መንፈሳዊ ህክምና ወደሚሰጥባቸው ሥፍራዎች በመሄድ እራሳቸውን ሊደብቁ እና ቫይረሱም በስፋት እንዲሰራጭ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉበት እድል ሰፊ ስለሆነ እና ያለውም ተመክሮ ይህን ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳይ፤
 
+ የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ ለማህበረሰቡ የሚያሰራጩ፣ እኛ በልዩ ጥበብ ወይም በባህል መዳኒት በሽታውን እናድናለን ወይም መዳኒቱ ከእኛ ዘንድ አለ ወይም ቫይረሱን በመንፈሳዊ ኃይሎ እናስወግዳለን የሚሉ ማደናገሪያዎችን እያሰራጩ ሕዝቡ የወረርሽኙን ባህሪ በሚገባ ተረድቶ እና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ በቂ የሆነ ጥንቃቄ እንዳያደርግ በሚያዘናጉ እና በሚያሳስቱ ሰዎች ላይ ጥብቅ የሆነ ሕጋዊ እርምጃዎችን የሚወሰድ መሆኑን ቀድሞ ማሳወቅ እና ይህ በተላለፉ ሰዎችም ላይ እርምጃ መውሰድ፤
 
እነዚህ እና ሌሎች ጥብቅ የቁጥጥር እርምጃዎችን በማከል ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባይቻል እንኳ በሰፊው እንዳይሰራጭ እና አገሪቱንም ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ እንዳይከታት ለማድረግ ይቻላል። 
 
እጃችሁን ቶሎ ቶሎ በሳሙና ታጠቡ፤
እጅግ የግድ ካልሆነ በቀር ከቤት አትውጡ፤
ከማናቸውም ማህበራዊ መስተጋብሮች ታቀቡ፤
እቤታችው ሆናችው ጸልዩ፤ የምታመልኩት አምላክ ሁሉም ስፍራ ላይ አለና፤
ሕመማችውን ሳትደብቁ ለዶክተሮች እና ለጤና ባለሙያዎች አሳውቁ፤
ቫይረሱ በባህላዊ ህክምና የሚድን ስላልሆነ በየመንደሩ የሚታዘዙላችሁን የመላምት ቅመማዎች ከመውሰድ ታቀቡ፤
 
በጤና ያቆያችሁ!!!!
Filed in: Amharic