>
5:13 pm - Tuesday April 19, 7644

ጥቂት በቃላት ኃይል ስለመቀሰፍና ስለመዳን!!!  (አሰፋ ሀይሉ)

ጥቂት በቃላት ኃይል ስለመቀሰፍና ስለመዳን!!!

አሰፋ ሀይሉ
 
“የቃል እሣት ነበልባሉ
የህብረቀለማት ኃይሉ
አልባከነምና ውሉ
ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ”
   — ሎሬት ጸጋዬ ገብረ-መድህን (1949 አም)
ሐይፐካንድሪያ እና አኖሳግኖዥያ (Hypochondria & Anosognosia)
ቃል እጅግ ታላቁ ኃይል ነው፡፡ ኃይለ ቃል ትልቁ መሣሪያ ነው፡፡ በአግባቡና በጥንቃቄ ከተጠቀምንበት ያለመልመናል፡፡ ያለ ኃላፊነት ስንጠቀምበት ደግሞ ያፀፋናል፡፡ ቃል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍን ስንገልጥ ፈጣሪ ምድርና ሠማያትን ያፀናው በቃሉ ነው፡፡ ይህችን ዓለምና ፍጡራኗን ሁሉ የፈጠረው በቃሉ ኃይል ነው፡፡ “ይሁን!” “እንፍጠር!” እያለ፡፡ ፈጣሪ ራሱ በመጀመሪያ ቃል ነበረ፡፡ ቃል ነው ሥጋ የሆነው፡፡ ቃል ተዓምራትን ይከስታል፡፡ ቃል የሕይወት ምንጭ ነው፡፡ ቃል ሞትንም ይጠራል፡፡ ቃል ታላቅ ኃይል አለው፡፡
ጠቢቡ ሠሎሞን በመጽሐፈ ምሣሌ 18፡4 ላይ “ቃል በብልህ ሰው ልብ ውስጥ የጠለቀ ውሃ ነው፣ የሚፈልቅ የሕይወት ምንጭና ፈሳሽ ወንዝ ነው” በማለት ይናገርና፣ “የአላዋቂና የችኩል ከንፈሮች የሚያመነጩት ቃል ግን ሞትን ይጠራል፣ ለራሱ ጥፋት ነው” በማለት ይነግረናል፡፡ በዚያው ምዕራፍ በቁጥር 21 ላይ ደግሞ ጠቢቡ ሠሎሞን ከአንደበታችን የሚወጣ ቃል ስላለው ኃይል ሲናገር፡- “ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው” ይለናል፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚያሳየን ጥንት ስንፈጠር ጀምሮ ቃል ያለውን ኃይል ነው፡፡ ቃል ያጠፋናልም፡፡ ያድነናልም፡፡
ዛሬ ላካፍላችሁ የፈለግኩት በሰዎች ወደ ሰዎች የሚሰራጭ ቃል እንዴት ጤነኛን ሰው ለበሽታ እንደሚዳርግ የሚያስረዳንን አንድ የህክምና ክስተት ወይም ሕመም ነው፡፡ የሕመሙ ዓይነት “ሐይፐካንድሪያ” ይባላል፡፡ ሐይፐካንድሪያ የሚለው ቃል ትርጉሙ ስለ በሽታ ሲወራ በመስማት ብቻ፣ በሽታው ውስጣችን ሳይኖር፣ ግን ልክ በሽታው እንዳለብን የሚሰማንና ለተለያዩ አካላዊ ህመሞች የሚዳርገንን – በቃል የሚመጣ በሽታ ነው፡፡
ይህን ሐይፐካንድሪያ የተባለ ሕመም ምልክት ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙት የእንግሊዝ የህክምና ሳይንቲስቶች ናቸው፡፡ በወቅቱ በእንግሊዝ ኮሌራን የሚመስል ተዛማች በሽታ (ወይም ‹‹አ.ተ.ት.›› የምንለውን ዓይነት አጣዳፊ በሽታ) በለንደን ውስጥ ስለ መከሰቱና መሰራጨቱ በሰፊው ተወራ፡፡ እና አካላዊ ምልክቶቹም ተዘርዝረው ተወሩ፡፡ ያን ተከትሎ ብዙ የእንግሊዝ ነዋሪ ወደ ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች – የሕመሙ ምልክቶች ታይተውብኛልና የህክምና እርዳታ እፈልጋለሁ እያለ ተንጋጋ፡፡
ሐኪሞቹን ግራ የገባቸው ነገር – እነዚያን ሰዎች ሲመረምሩ – ከኮሌራውም ሆነ ከሌላ ዓይነት በሽታ ነፃ ሆነው መገኘታቸው ነበረ፡፡ ነገር ግን አንድ እጅግ ያስደነቃቸው ግን – እነዚያ ሰዎች – የተዛማች በሽታ መከሰትን ወሬ ሰምተው – ራሳቸውን በራሳቸው ዳያግኖስ አድርገው እነዚያን በሽታዎች በራሳቸው ላይ ያገኙ ሲመስላቸው ግን – የሆነ የሚታመሙት ነገር ግን ነበራቸው! የእውነተኛውን በሽታ ምልክት የሚመስሉ ምልክቶችን ሰውነታቸው ያሳያል፡፡ ነገር ግን እውነተኛው በሽታ የለባቸውም፡፡  እና ግራ ገባቸው የእንግሊዝ ሃኪሞች፡፡ ሕመሙ ሳይኖርብህ – ነገር ግን ሕመሙን የሚመስል ምልክት በሰውነትህ ላይ እንዴት ሊገኝ ቻለ?
ይህን አስገራሚ ክስተት ለመተንተን ብዙ ወራት ፈጅቶባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ምክንያቱን አገኙት፡፡ የህመሙ ምክንያት ኮሌራው ወይም አተቱ አልነበረም፡፡ የሰዉ ህመም ምክንያቱ የኮሌራው መዛመት ወሬ ነው!! ያ ወሬ በሰዎቹ ጆሮ ገብቶ፣ አዕምሯቸው ደግሞ አናላይዝ ሲያደርገው፣ የአዕምሮ ማዕከላችን በቃ በሽታው አለብህ የሚሉ ሴንሰሪ ኒውሮኖችን መልዕክት ወደ ሰውነታችን ሴሎች ሁሉ ያሰራጫል፡፡ የዚያን ጊዜ ሰውነታችን አላስፈላጊ የሆኑ በሠላም ቀን ሊመነጩ የማይገባቸውን እንግዳ የሆርሞኖች እንቅስቃሴ ማድረግ ይጀምራል፡፡ ያ ደግሞ ጤነኛውን ሰው ሕመምተኛ አድርጎት ቁጭ ይላል፡፡ ደግሞ የሚገርመው ሰውየው የሚታመመው ነገር የሚያሳየው ምልክት ያንኑ ሰውየው የሰማውን ዓይነት ተዛማች ህመም የሚያሳያቸውን ምልክቶች ዓይነት ነው፡፡ በወሬ መታመም ይሉሃል ይሄ ነው፡፡
በእርግጥ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የ3ኛው ቫይማር የናዚ ሜዲካል ሳይንቲስቶች በኮንሰንትሬሽን ካምፕ በታጎሩ እስረኞቻቸው ላይ አደረጉት ከሚባሉ አሰቃቂ ሙከራዎች አንዱ እውነተኛ ገዳይ መርዝ እና ንፁህ ውሃን ለተለያዩ ሰዎች ‹‹መርዝ ነው፣ አሁኑኑ ይገላግላችኋል! ጠጡት!›› ብለው እንዲጠጡት ማስገደድ ይገኝበታል፡፡ እና እንደሚባለው ከሆነ – መርዙን የጠጡትም፣ ንፁሁን ውሃ የጠጡትም ሞተው የሚገኙበት አጋጣሚ ብዙ እንደሆነ ነው፡፡ ሰውነትህ ንፁህ ውሃ ጠጥቶ ለምን መርዝ እንደጠጣ ይቀሰፋል? – ምርምሩ ምን ያህል እንደሆነ ከተጣራ ምንጭ አላረጋገጥኩም፡፡ ግን እውነት ከሆነ – በቃ ሰውነትህ እንቅስቃሴውን የሚያቆመው – መርዝ ነው ተብሎ ስለተነገረህ ነው – አዕምሮህ ያንን ቃል አምኖ ስለተቀበለው – የሕይወት ዋና ሞተር የሆኑትን የካርዲዮ ቫስኩላር እንቅስቃሴዎች በቅፅበት ይዘጋጋቸዋል – ማለት ነው እንግዲህ!
የሆነ ሆኖ ግን – እነሆ ቃል – ከበሽታ አማፅያን ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች እኩል ቀሳፊ ኃይል ኖሮት – ሰውን ለበሽታና ለሞት መቅሰፍቶች እንደሚያጋልጥ እሙን ነው፡፡ እነዚያ የእንግሊዝ ሳይንቲስቶች – ያንን የኮሌራ ወረርሽኝ ገባ ሲባሉ – በአጣዳፊ ሸርተቴ፣ ራስ ምታት፣ የሆድ ቁርጠትና ማስመለስ የተቀሰፉት የለንደን ነዋሪዎች በሽታ – የኮሌራው በሽታ እንዳልሆነ በምርመራቸው አረጋግጠዋል፡፡ እና ለበሽታው የሰጡት ስም ‹‹ሐይፐካንድሪያ›› የሚል ነው፡፡ ሐይፐካንድሪያ – በወሬ ኃይል የምትታመመው ህመም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዚህ በሐይፐካንድሪያ ዙሪያ የህክምና ሳይንሱ አድጎ ‹‹አይ ኤ ዲ›› (ኢልነስ ኤንዛየቲ ዲስኦርደር) የሚል መጠሪያ ሁሉ ተሰጥቶት የሕመሙ ምንጮች ከበሽታ ወሬም ባለፈ ምን እንደሆኑ ብዙ ትንተናዎች የቀረበበትና በመላው ዓለም የህክምና ሳይንስ ተቀባይነት አግኝቶ የተካተተ የህመም ዓይነት ሆኗል፡፡
እና ይሄ ሐይፐካንድሪያ ሰሞኑን በምን ትዝ አለኝ? መቼም የሰሞነኛው የተዛማች በሽታ መቅሰፍት – የኮሮና-19 ምልክቶች ሁሉ ከየሚዲያው በቀላሉ በየሰዎች ሁሉ እንዲታወቁ ተደርገዋል፡፡ የአተነፋፈስ ችግር፣ ትኩሳት፣ ደረቅ ሳል፣ ከፍተኛ ድካም፣ ወዘተ እያለ ማንኛውም ሰው በቃሉ ይደረድርልሃል፡፡ እና እነዚህን ምልክቶች ከመስማት ብዛት ማታ ተኝተህ ብርድልብስ ሸፍኖህ አየር ካጠረህም – በኮሮና የተያዝክ ይመስልሃል፡፡ መስኮትና በሩን ጥርቅም አድርገህ – ላብ ካሰጠመህም – ኮሮና የያዘህ ይመስልሃል፡፡ ዕረፍት በማጣትህ ወይም በተለያየ ምክንያት ከፍተኛ የድካም ስሜት ሰውነትህን ከተጫጫነውም – ኮሮና ይዞኝ ይሆን እንዴ? ብለህ ትጨነቃለህ፡፡ ትንሽ ደገምገም አድርጎ ካሳለህም – በኮሮና ተያዝኩ ብለህ ልትደነግጥ ትችላለህ፡፡
እና አንዳንዴ – ጦር ከፈታው፣ ወሬ የፈታው – እንዲል ያገራችን ሰው – አንዳንዴ ምንም እንኳ ዳታው በእጄ ባይኖረኝ – የበሽታዎችን ወሬ ከመስማት የተነሳ ብቻ – የበሽታውን ምልክቶች በራሱ ላይ ያየ የሚመስለው – ወይም በትንሽ በትንሹ የሚከሰትበት – እና ሄዶ ሲመረመር ግን ‹‹ነፃ ነህ!›› ተብሎ ወደቤቱ የሚመለስ – በሐይፐካንድሪያ ተጠቂ የሚሆነው ሰው – ቁጥሩ ቀላል እንደማይሆን አስባለሁ!!! እና አንዳንዴ – በተዛማች በሽታዎች ስለመቀሰፍ አስከፊነትና አይቀሬነት – ከአፍ እየወጡ ከሚዛመቱ ቀሳፊ የችኩል ወሬዎች – ራስን መጠበቅና መከላከልም አስፈላጊ እንደሆነ አለመርሳቱ ይበጃል! ከቃላት አስከፊ ኃይል ራሳችንን እንጠብቅ – የዕለቱ መልዕክቴ ነው!
በእርግጥ በወሬ የተዛመተውን የሆነ ወረርሽኝ በሽታ ምልክቶች በእኔ ላይ ታይተዋል ብሎ ማመን ብቻ ሳይሆን፣ በትክክል እነዚያኑ በሚመስሉ የህመም ምልክቶች የሚጠቃውን የሐይፐካንድሪያ ህመምተኛ ተቃራኒ የሆኑ ሰዎች ደግሞ አሉልህ!! እነዚህ ደግሞ በ“አኖሳግኖዥያ” ሲንድሮም የተጠቁ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሄ “አኖሳግኖዥያ” ደግሞ ምንድነው? የአኖሳግኖዥያ ምልክቱ ደግሞ – በትክክል የአንድ በሽታ ምልክቶች በእርሱ ወይም በእርሷ ላይ እየታዩ መሆናቸውን እያወቀም – የለም! እነዚህ የዚያ በሽታ ምልክቶች አይደሉም! የሉብኝም! ደህና ነኝ! ምንም አልሆንኩም! ብሎ – ድርቅ ማለት ነው፡፡
እነዚህ በአኖሳግኖዥያ የተጠቁ ግለሰቦች በግልፅ የሚታይ የበሽታው ሁነኛ ምልክት እያጣደፋቸውም – ‹‹እኔ ደህና ነኝ! ምንም የተለየ ነገር አላጋጠመኝም!›› ብለው ድርቅ የሚሉ ሰዎች ናቸው!! አንዳንዴም እነዚህ አኖሳግኖዥያቲክ ፔሸንቶች – በምርመራ ጭምር የተረጋገጠላቸውን በሽታ ራሱ – የምርመራውን ውጤት አላምንም! ይሄ የኔ ውጤት አይደለም! ብለው መዓት ጊዜ የተለያየ ዓይነት ምርመራ ያሰራሉ፡፡ አኖሳግኖዥያ ባስ ካለ መታመምንና ጤነኛ ሁኔታ ላይ መገኘትን መለየት እንዲሳነን የሚያደርግ የአዕምሮ ሕመም ዓይነት እስከመሆን የሚያሻቅብበት ጊዜ አለ፡፡
ስለ አኖሳግኖዥያ ሳወራ – በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ የማውቀው አንድ የጓደኛዬ ጓደኛ ትዝ አለኝ፡፡ ሁሌ ከባድ ሳል ያስለው ነበረ፡፡ ግን ሁሌም ስትነግረው – ደህና ነኝ እኮ! ምንም አልሆንኩም! ከልጅነቴ ነው! እያሳልኩ ሁሉ የተወለድኩ ነው የሚመስለኝ! ሆቢዬ ነው! እያለ ያስቀን ነበር! አንድ ቀን አንድ ሃኪም ጓደኛዬ በአጋጣሚ መጥቶ ሲያስል ተመለከተውና – ሄደህ ሆስፒታል መመርመር አለብህ የሚል ምክር ሰጠው፡፡ ለእርሱም ያንኑ ለእኛ የሚመልሰውን መልስ እየመለሰ ይከራከረው ጀመር፡፡ ዶክተሩ ጓደኛዬ እሺ ሆስፒታል መሄድ ካልፈለግክ አርሾ ወይ ሌላ ክሊኒክ ሂድና ላብራቶሪ ምርመራ አሠራ አለው፡፡ እንዲያም ብሎት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡
ኋላ ከልጁ ስንለይ – ሃኪሙ የልጁ ህመም አኪዩት ስለሆነ ወደ እኛም እንዳይተላለፍብን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ለእኔና ለሌላ አንዱ ጓደኛዬ መከረን፡፡ ያ ስሙን የማልጠቅሰው ልጅ – እንዲያ እያሳለ ኖሮ – በመጨረሻ በ29 ዓመት የለጋ ዕድሜው – ከነሳሉ ሞተ፡፡ እርሱ እየሳልኩ ሁሉ ሳይሆን አይቀርም የተወለድኩት ነበረ የሚለው ለጠየቀው ሁሉ፡፡ የቀልዱን ነው፡፡ እያሳለ መሞቱ ግን ቀልድ አልነበረም፡፡ እውን ነው፡፡ አሁን ሳስበው – ምናልባት – ያ የጓደኛዬ ጓደኛ – ምናልባት እኛም እሱም ሁላችንም ሳናውቀው – የአኖሳግኖዥያ ሰለባ ሆኖ ይሆን? እያልኩ አስባለሁ በትካዜ፡፡
ከዚያ ልጅ የማይረሳኝ ነገሩ – ማታ አብሮን ጠጥቶ ከእኛ ጋር ካደረ – ጠዋት ተነስቶ ወደ ደጁ ይወጣና በቧንቧው ውሃ ፊቱንና ፀጉሩን እየተለቀለቀ ማንጎራጎር የሚጀምረው ነገሩ ነው፡፡ አንድም ቀን እንጉርጉሮውን ጨርሶት አያውቅም – በመሐል ዘፈኑን አቋርጦ ያስልና – ደግሞ ይቀጥላል፡፡ ሁሌ ከቤት ውስጥ ጋደም ባልኩበት እየሰማሁት ዘፈኑን በሳል ሲያቋርጥ ፈገግ እል ነበር፡፡ እንደቀልድ እየሳለ አለፈ፡፡
“የቃል እሣት ነበልባሉ
የህብረቀለማት ኃይሉ
አልባከነምና ውሉ
ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ”
   — ሎሬት ጸጋዬ ገብረ-መድህን (1949 አም)
አኖሳግኖዥያ እንግዲህ ባጭሩ ይህንን ነው፡፡ የህመሙ ምልክት እያለብህ – ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብለህ እስኪገልህ ድርቅ!!! ከበሽታ መሐል መቼም በሽታን አይመርጡትም! ግን እንዲያው ከትልቁ ሰይጣን፣ ትንሹ ሰይጣን ይሻል እንደሆን ግን… ከዚህስ የበሽታው ምልክት የለብኝም ብለህ ድርቅ ከምትልበት ከአኖሳግኖዥያስ- በሽታው ሳይኖርብህ አለብኝ ብለህ ድርቅ የምትልበት ሐይፐካንድሪያ ሳይሻል አይቀርም መሠለኝ!! ቢያንስ በጊዜ ምርመራና ህክምና ወደምታገኝበት ሥፍራ ሄደህ መፍትሄ ታገኝለታለሃ! ያኛው እኮ እንደ ውሃ እያሳሳቀ፣ አንድም ቀን ሳታምን፣ ወደማትመለስበት ይዞህ ጭልጥ ነው! በመሐል ለሌላውም ጠንቅ ትሆንም ይሆናል! ብቻ አንድዬ ይጠብቀን ከሁሉም!
ፈጣሪ – ከሐይፐካንድሪያም፣ ከአኖሳግኖዥያም፣ ከኮሮናም፣ ከሰው አጥፊና አስፈራሪ ወሬም፣ ከችኩሎችና አሸባሪዎች ቃልም – አንድዬ ሁላችንንም ይጠብቀን አቦ!!
ከአነጋገርህ የተነሳ ትፀድቃለህ፣ ከአነጋገርህም የተነሣ ይፈረድብሃልና፣ መልካምን ቃል ተናገር!”
Filed in: Amharic