>

ኢትዮጵያዊቷ በጎ አድራጊ ለጣሊያን 27ሺ ዶላር ረዳች!!! (አድማስ ራድዮ)

ኢትዮጵያዊቷ በጎ አድራጊ ለጣሊያን 27ሺ ዶላር ረዳች!!!

አድማስ ራድዮ
 
ጣሊያን ከኮሮና ቫይረስ ጋር እያደረገች ላለችው የሞት የሽረት ትግል ያግዝ ዘንድ ኢትዮጵያዊቷ በጎ አድራጊ ዶክተር መንበረ አክሊሉ የ26ሺ ዶላር ዕርዳታ አደረገች።
ዶክተር መንበረ ለአድማስ ሬዲዮ እንደገለጸችው ፣ በመጣው መቅሰፍት ልቧ ተነክቷል። በተለይም ጣሊያን ለረዥም ጊዜ የኖረችበትና ጣሊያናውያንም ከወደቀችበት የጎዳና ህይወት ያወጧት በመሆኑ ጣሊያን ላይ የወረደው መቅስፍት ልቧን እንደነካትና እንዳስለቀሳት ተናግራለች። 
 
“ጣሊያን ኖርያለሁ፣ አራስ ሆኜ የልጄ አባት በተወኝ ጊዜ፣ መንገድ ላይ ወድቄ፣ ጎዳና ተዳዳሪ ሆኜ ነበር፣ ያን ጊዜ ከመንገድ ላይ አንስተው፣ ከነህጻን ልጄ አጥበው ነፍስ እንዲኖረን ፣ ህይወታችን እንዲቀጥል ያደረጉት ጣሊያኖች ናቸው። ከዚያም ልጄ ሴንት ፒተር ካቴድራል ክርስትና ተነስቶ፣ ቆርበን ፣ እነሱም ተንከባክበውን ኖረናል፣ በቅርብ ጣሊያን ስሄድ ያ ካቴድራል ባዶ ሆኖ ሳይ፣ እነዚያ በፈገግታ ያስተናገዱን በፍቅር ያኖሩን ጣሊያኖች ቅስማቸው ተሰብሮ ሳይ፣ ባዶ ሆነው ሳይ አልቻልኩም፣ ምንስ ቢኖረኝ እና ብስጣቸው ነው ያልኩት” ስትል ለአድማስ ሬዲዮ ገልጻለች።
 
አያይዛም “እናም ከባለቤቴ ጋር ተማክሬ ፣ የጣሊያን በጎ አድራጎት ድርጅት ዕርዳታ ያሰባስብ ስለነበረ፣ 25ሺ ዩሮ / 27ሺ ዶላር አካባቢ ረድተናል።” ብላለች።
 
በዚህ ዕርዳታ ጣሊያኖች እጅግ መደነቃቸውንና ፣ በዚህ ክፉ ወቅት አንድ ኢትዮጵያዊት ይህን ማድረጓ ለኢትዮጵያ ያለንን ስሜት የሚጨምር ፣ ለኢትዮጵያውያን ያለንን ፍቅር የሚጨምር ትልቅ ነገር ነው ልባችን ተነክቷል ማለታቸውን ገልጻልናለች። ዶክተር መንበረ አያይዛ ፣ “ከዚህ በፊት ለተለያዩ አገራት፣ የራሷን አገር ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ ለአሜሪካውያን በ9/11 ጊዜ እና ለሌሎችም ያቅሟን ማድረጓን ገልጻ፣ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መተሳሰብ፣ ኢትዮጵያውያንም በአካል እንኳን ባይገናኙ እየተደዋወሉ እንዲጠያየቁ፣ በተለይም ዕድሜያቸው የገፉትን እንዳንረሳቸው አደራ ብላለች። 
 
በርካታ የጣሊያን ጋዜጦችም እየደወሉ እንዳነጋገሯትና የሷ የአንዲት ኢትዮጵያዊት ርዳታ ሁሉም ስለኢትዮጵያ እንዲጽፉ፣ የኢትዮጵያውያን ውለታ ልባችን ገብቷል ብለው እንዲጽፉ እንዳደረጋቸው ገልጻለች።  
Filed in: Amharic