>

ለመሆኑ አሳዳጃችን ኮሮና ማነው? ... ምንድር ነው? (መኮንን ከበደ)

ለመሆኑ አሳዳጃችን ኮሮና ማነው? ምንድር ነው?

መኮንን ከበደ
የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ለመጀመርያ ግዜ በሰው ልጅ የታወቀው እንደጎርጎርሳውያኑ በ1960 ዎቹ ነበር።ሆኖም ግን በሳይንሱ አከባቢ ትኩረትን የሳበው የዛሬው COVID-19 /SARS-cov-2 ታላቅ ወንድም  SARS (severe Acute Respiratory Syndrome) በ 2002 አ.ም ተከስቶ የ 800 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈ በኃላ ነው።እስከዚህ ግዜ ድረስ ኮሮና ሰው ላይ የከፍ ጉዳት ያደርሳል ብሎ ያሰበ አልነበረም።እስካሁን 40 ገደማ የቫይረሱ ዝርያዎች መኖራቸው ታውቋል።
በ 2002 የተከሰተው SARS-Cov-1 መነሻው ከለሊት ወፍ ነበር።የለሊት ወፍ immunity  ለቫይረሱ ምላሽ ስለማይሰጥ ቫይረሱ ለረጅም ግዜ ተረጋግቶ መቀመጥ እና የዘረመል ሽግግር ማድረግ ይችላል።የሰው ልጅ immunity ግን ያለ የሌለ ሀይሉን ቫይረሱን ለመዋጋት ስለሚያውል ሌሎች በሽታዎች እኛን በቀላሉ በማጥቃት እሰከ ሞት ማድረስ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በሚገርም ሁኔታ በ2002 አከባቢ የተደረጉ ጥናቶች ቫይረሱ ከተወሰነ ግዜ በኃላ የዘረመል ለውጥ (evolution)አካሂዶ በአዲስ መልክ ሊከሰት ይችላል ብለው ነበር።ነገር ግን ማንም ቅድመ ዝግጅት ሳያደርግ ከወራት በፊት የተወሰነ የዘረመል ለውጥ አድርጎ ከተፍ አለ።እንሆ ኮሮና ዘበናዩ የሰው ልጅን መግቢያ መውጫ አሳጥቶ በሩን አዘግቶ ቤቱ ቁጭ አደረገው።
ይሄ መግቢያ መውጫ ያሳጣን ቫይረስ 90 ናኖ ሜትር ብቻ ነው።የተዋቀረው ከ 4 የተለያዩ ፖሮቲኖች እና ከ አንድ ዘለላ ዘረመል(single Stranded RNA )ነው።RNA  neucleotide ከተባሉ 4 ኬሚካሎች ቅንብር የተዘጋጀ ኮድ እና የጀነቲክ መረጃ ነው።መረጃው ቫይረሱ እራሱን ለማራባት የሚረዱትን ፖሮቲኖች እንዴት ማምረት እንዳለበት ጭምር የያዘ ነው።
የቫይረሱ የተለበጠበት envelope የተሰራው ከ lipid ነው።”እጃችሁን በሳሙና እና በውሀ ታጠቡ “የሚባለው ይሄ አካል ከሳሙና እና ከውሀ ጋ ሲዋሀድ ስለሚፈርስ እና ቫይረሱ ስለሚበተን ነው።ሌላኛው የቫይረሱ የውጨኛ አካል ላይ እሾክ መስሎ የሚታየው ሹል ነገር spike የተባለ ፕሮቲን ነው።
የሰው ሴሎች የጀነቲክ መረጃዎችን የሚያስቀምጡት እንደ ቫይረስ በRNA ሳይሆን በDNA ነው።ነገር ግን RNA ን ለተለያዩ ጉዳዮች ይጠቀማሉ።ለምሳሌ ከጄኖሞች መመርያ በመቀበል ፕሮቲን ወደ ሚመረትበት አካል ሄደው ፕሮቲን ያስመርታሉ።ቫይረስ በራሱ መራባት ስለማይችል እቺን የኛን ሂደት ነው ለራሱ ጥቅም ጠልፎ የሚጠቀማት።ኮሮና ወደ ሰውነታችን እንደገባ ራሱን ከኛ መልእክት አመላላሽ RNA ዎች ጋ አመሳስሎ ወደ ሴሎች እምብርት ይገባል።ከገባ በኃላ ፕሮቲን አምራች አካላት የእኛ  ሜሴንጀር RNA ስለሚመስላቸው የቫይረሱን ኮድ እያነበቡ እሱ የሚፈልገውን ፕሮቲን ማምረት ምጀምራሉ።
የኛ ሰውነት በቫይረሱ hijack ተደርጎ የሱን ስራ እየሰራ መሆኑን የሚያውቅበት ዘዴ የለውም። በዚህ ሂደት ነው እንግዲ ቫይረሱ ለመራባት ግብአት የሚሆኑትን ፕሮቲኖች አዞ እያሰራ በነፃ የሚራባው።
ቫይረሱ መጀመርያ ወደ ሰውነታችን እንደገባ ከእኛ ሴሎች ጋ የሚያገናኘው ፕሮቲን spike (እሾክ የምትመስለዋ ነገር) ናት።እቺ ፕሮቲን እኛ ሳምባ ውስጥ ከሚገኘው ACE2 ከተባለ ሌላ ፕሮቲን ጋ እጅና ጓንት በመሆን ነው ወደ ሴሉ የውሰጠኛ ክፍል የሚገባው።በትንፍሽ የሚተላለፈውም እቺ ፕሮቲን የምትገኘው ሳምባ ውስጥ ስለሆነ ነው።ACE2 በተለይ የደም ግፊትን የመቆጣጠር ሚና ያለው ፕሮቲን ነው።
ምናልባትም የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ላይ ቫይረሱ የከፍ ጉዳት እያደረሰ ያለው በዚህ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ሳይንቲስቶች እየገለፁ ነው።
ለመኑ መፍትሄውስ ምን ላይ ደርሧል የሚለውን ደሞ በቀጣይ ክፍል እናያለን።
Filed in: Amharic