>

ኮሮናና ብልጽግና ፓርቲ ምንና ምን ናቸው? (ግርማ በላይ)

ኮሮናና ብልጽግና ፓርቲ ምንና ምን ናቸው?

 

ግርማ በላይ

 

ብልጽግና ፓርቲን “ብልግና ፓርቲ” የሚሉ ጨዋነት የሚጎድላቸው ግልፍተኞች አሉ፡፡ እኔ ግን አንድ አካል መጠራት የሚፈልግበትን ስም – ስሙ እንደማይመጥነው ብረዳም እንኳን መጠራት ከሚፈልግበት ስም ውጭ የመጥራት ድፍረትና ፍላጎት የለኝም፡፡ እንደሱ ከሆነ ምጥምጥ የመሰለች አረማሞ ባርያ “አልማዝ” ተብላ ስትጠራ፣ በጠባይዋ መክፋት ሳቢያ “አንች ጊንጥ!” የምንላት ከፈሷ የተጣላች ሴት ወይወዘሮም “ዐመለ ወርቅ” ስትባል ጣልቃ እየገባን ስም ስናስቀይር ወይም ከስማቸው ፊደል ስንቀንስ መዋላችን ነው ማለት ነው፡፡ መቼስ ስም አይገዛ! ይጠሩበት ግዴለም፡፡

ለማንኛውም ብልጽግና ፓርቲ በአሁኑ ወቅት “አልሸሹም ዘወር አሉ” እንዲሉ ከሕወሓት መራሹ ኢሕአዲግም ሆነ ከደርግ ኢሠፖ ባልተናነሰ ሁኔታ ተክለ ሰውነቱን በመገንባትና ህጋዊነትና አግባብነት በሌለው የገቢ ምንጭ ኪሱን በማጠብደል ላይ ይገኛል – ‹ከወፈሩ ሰው አይፈሩ› አይደል ነገሩ? ሌሎች እንደዚያ የማድረግ መብት እንዳላቸውና እንደሌላቸው፣ ቢያደርጉ ደግሞ እጀ ረጂሙ ብልግና ማነው እቴ ብልጽግና ምን እርምጃ ሊወስድባቸው እንደሚችል ከግምት ባለፈ እምብዝም አላውቅም፤ የሀገራችንን ዕድለቢስነት ግን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ከድጥ ወደ ማጥ የሚሰነቅር ዋልጌና ሥልጣን ወዳድ እንጂ ከራሱ ባለፈ ለሀገርና ለወገን ከእውነት የሚጨነቅ መልካም ሰው ሊወጣላት አልቻለም፡፡ አገር ምድሩ በኮሮና ቫይረስ ሥጋት ተጨንቆና ተጠብቦ በሚገኝበት ሀገራዊ ድባብ “የገበያ ግርግር ለቀጣፊ ያመቻል” እንዲሉ ሆኖ ይህ ፓርቲ ቆሜለታለሁ ለሚለው ሕዝብ ቅንጣት ሳይገደው በገቢ አሰባሰቡ ላይ ብቻ መጠመዱ ያሳዝናል፡፡ የሚዲያ ወሬው ሁሉ ብልጽግናን የሚያገዝፍ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ሕዝብ ተረስቷል፡፡

ፓርቲው ከሀብታሞችና ከፋብሪካ ባለቤቶች ሚሌኒየም አዳራሽ ውስጥ የፓርቲው ሊ/ መንበር ቆመው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ በገሃድ ማግበስበሱ ሳያንስ ሰሞኑን ደግሞ በይሉኝታ ይመስለኛል ሥልቱን በመቀየር በ”ፕሌጅ” የሀብታሞችን መንደር እያተረማመሰው ይገኛል፡፡ ፕሌጅ ማለት ቃል ማስገባት ማለት ነው፡፡ ሕዝብ በኮሮና ቫይረስ እየተጨነቀ ለገንዘብ መሮጥና ለሕዝብ ጤንነት ደንታቢስ መሆን አሣፋሪ ነው፡፡ አገርና ሕዝብ ሰላም ሲሆኑ ይደረስበት ነበር፡፡ አሁን ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ፡፡ በድብቅ ስብሰባ ማድረግም ሆነ ለገቢ ስብሰባ አቅልን ስቶ እንዲሀ መሯሯጥ ሳይውል ሳያድር ትልቅ ዋጋ ያስከፍላልና ቆም ብለው ቢያስቡበት ጥሩ ነው፡፡ ጸጸት ያለፈ ስህተትን አያርምም፡፡

በየቀበሌውና በየከፍተኛው የሚገኙ የፓርቲው አባላትና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሙስና ደረጃቸውን ከፍ አድርገው ዛሬ ዛሬ የሚጠይቁት ጉቦ በሚሊዮን ቤት እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ በተለይ በመሬት አስተዳደር፣ በንግድ ዘርፍ ፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት የተሠማሩ ባለሙያዎች ፋይልን በማጥፋትና መብራት የለም በማስባል የሚዘርፉት ገንዘብ ሀገርና መንግሥት ስለመኖሩ ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ ሁሉም በምሬት የሚናገረው ጉዳይ ነው፡፡

ስለዚህ ከአሁኑ እንዲህ ከሆነ ምርጫው ሲቃረብና ሲደርስ ይህ ብልጽግና የሚባል ፓርቲ ሌሎች ፓርቲዎችን እንዴት አድርጎ ቀረጣጥፎ እንደጅብ እንደሚሰለቅጣቸው ኮሮና ቀድሞ ካልጨረሰን የምናየው ይሆናል፡፡ ከደርግና ከወያኔ አለመማር ምን ዓይነት ነፈዝነት እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ የሥልጣንና የገንዘብ ፍቅር ለካንስ እንደዚህ ያሳብዳል? ለማንኛውም ለኮረና ብቻ ሣይሆን በፍቅረ-ንዋይ ታውሮ ከኮረና በባሰ ሁኔታ አገርን እያመሰና ሁሉንም ለራሱ እያግበሰበሰ የሚገኘው ብልጽግና አደብ እንዲገዛና መሪዎቹም ወደ ኅሊናቸው እንዲመለሱ ወደ ፈጣሪ እንጸልይ፡፡

Filed in: Amharic