>
5:13 pm - Friday April 19, 2622

በጋምቤላ  የኢ/ካ/ቤን የሐይማኖት አባት የነበሩት አረፉ!!! (ታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)

በጋምቤላ  የኢ/ካ/ቤን የሐይማኖት አባት የነበሩት አረፉ!!!

ታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ
 በኢትዮጵያ ፣የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት  የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ን ሚሽነሪ   ጳጳስ የነበሩት አንጄሎ ሞርሳቺ  በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ  ህይወታቸው ማለፉን ቤ/ክቱ በሀዘኔታ  ገለጸች።
የካቶሊክ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው በትላንትናው እለት መጋቢት /ማርች 25,2020እኤአ   በአውሮፓ የወረርሽኙ ዋንኛ የሞት አውድማ  የሆነችው ጣሊያን ፣ሎምባርዴ ግዛት ውስጥ  ከዚህ አለም በሞት የተለዩት  የስድሳ ስባት አመቱ አባ አንጄሎ   ቤተክርስቲያኒቱ በወረርሽኙ ካጣታቸው የመጀመሪያው ታላላቅ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች መካከል አንዱ ናቸው ተብሏል።
እኤአ ከ1991 ጀምሮ  ለሀዋሪያዊ ተልእኮ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከሃያ እምስት ሺህ በላይ ተከታዮች በሚገኙባት ጋምቤላ ክልል ውስጥ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ  በማገልገል  እስከ ጳጳስነት  ደረጃ የደረሱት አባ አንጄሎ እኤአ 2010  የጳጳስነት(Bishop)  ማእረግን የተቀቡ ሲሆን  ዜና እረፍታቸውም ቤተክርስቲያኒቱን እና አጠቃላይ  የእምነት ልጆቿን በተለይ በጋምቤላ ውስጥ በአካል የሚያውቋቸው ልጆቻቸውን  በእጅጉ እንዳሳዘነ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የወጣው የሐዘን መግለጫ ያትታል።
ወደ ጋምቤላ መንደሮች  የሚወስዱት  የመኪና መንገዶች  በዝናብ እና በጎርፍ ሲጥለቀለቅ  ባባሮ ወንዝ ላይ በታንኳ በማቆራረጥ ወጣቶችን፣ ችግረኞችን ያስተምሩ እና አልሚ ምግቦችን በመስጠት ይረዱ እንደ ነበር ያወሳው ዝክረ አባ አንጄሎ በክህነት አገልግሎታቸው ሰላሳ ስምንት አመት በጳጳስነታቸውም አስር አመታት በጎቻቸውን በእረኝነት  ማገልገላቸውን ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ከሀያ እንድ ሺህ በላይ ሰዋች ህይወትን በአለማችን ላይ የቀጠፈው፣ከአራት መቶ ሺህ በላይ ያጠቃው የኮሮና ቫይረስ   ወረርሽኝ ከስድሳ በላይ የካቶሊካዊት ቤ/ን ቄሶችን መግደሉን  ዜና ዘገባው አክሎ ጠቁሟል።
Filed in: Amharic