>
5:13 pm - Saturday April 18, 5029

ዓለማችን ከስሕተቷ ካልተማረች ወረርሽኝ መደጋገሙ አይቀርም (መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ)

ዓለማችን ከስሕተቷ ካልተማረች ወረርሽኝ መደጋገሙ አይቀርም!

ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

• “ነገርን ከሥሩ ውሃን ከጥሩ” እንዲሉ አበው አንድ ችግር ሲከሠት የችግርም መንሥኤንም ማወቅ ለችግሩ መልስ የምናገኝበት ትልቁ ቊልፍ ነውና ኮሮና ወይም ኮቪድ 19ን (Covid-19) አስመልክቶ CNN መጋቢት 11/ 2012 ዓ.ም. ይዞት በወጣው ዘገባ “Bats are not to blame for corona virus. Humans are.” (የሌሊት ወፎች ለኮሮኖ ቫይረስ ሊወቀሱ አይገባም፤ ሰዎች እንጂ) በሚል ርዕስ ወረርሽኙ በተቀሰቀሰበት በህዋን ገበያ የነበረውን የእንስሳት፣ የአዕዋፍና ያልተፈቀዱ የዓሣ ዓይነቶች ሽያጭ በተለይ የሌሊት ወፍን ለወረርሽኙ መቀስቀስ ታላቁ ምክንያት እንደሆነች የዘርፉ ምሁራን ገልጸዋል፡፡ https://edition.cnn.com/…/coronavirus-human-act…/index.html…

ነገሩ ያሰጋቸውና ችግሩን የተረዱ ብዙዎች ተመራማሪዎች ግን አስቀድመው “please Chinese, do not eat everything that moves” (እባካችሁ ቻይናውያን የሚንቀሳቀሰውን ሁሉ አትብሉ) በማለት በዘመናችን ሰዎች ከልክ ያለፈ የእንስሳት ጋር ያላቸውን ቀረቤታና አበላል እንዲያስተካክሉ መፈክር ይዘው ቢወጡም “ልትጠፋ የቀረበች ከተማ ነጋሪት ቢጎስሙባት አትሰማ” ሆኖ ነገሩ፤ ጆሮ ዳባ ልበስ ተብለው ቆይተዋል፡፡

• “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንደሚባለው የሀገራችን አባባል አብዛኛውን ጊዜ ለወረርሽኝ መቀስቀስ መነሾቹ እንስሳት ናቸውና ከ17 ዓመት በፊት ለሳርስ በሽታ መነሾ የነበሩትን ድመትና ውሻ የሌሊት ወፎች እና ሌሎች አደገኛ እንስሳት እንዳይበሉ የኮሮና ሥርጭትን ለመግታት የቻይና የሺንዜን ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በሕግ በመደንገግ የመጀመሪያዋ ሆናለች፡፡ https://www.bangkokpost.com/…/chinese-city-of-shenzhen-to-b…

• ከ7 ዓመት በፊት “መጽሐፍ ቅዱስና የሕክምና ሳይንስ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት መጽሐፍ ላይ የዓለማችን ሕዝቦች ለመብልነት ከተከለከሉት ከእንስሶችና አዕዋፍ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማራቅ ካልቻሉ ብዙ ወረርሽኝ በዓለም ላይ ሊከሠቱ እንደሚችሉ ጽፌ ነበር፡፡

ለምሳሌ በዓለም ላይ ከተከሠቱት 10 ታላላቅ ወረርሽኝ ውስጥ እጅግ ዘግናኙ ከ1346-1353 የተነሣው ጥቁር ሞት (ብላክ ዴዝ) ሲሆን ከ75-200 ሚሊየን ሰዎችን ገድሏል፡፡ ይህ በሽታ በእስያ ሲሆን የጀመረው ወደ ተለያዩ አህጉሮች በነጋዴ መርከቦች ውስጥ ባሉ የዛሬ 3500 ዓመት ለመብልነት ከተከለከሉት አይጦች እና በነርሱ ውስጥ በሚኖሩ ተባዮች ነበር ተዛምቶ ሚሊየኖችን የቀጠፈው፡፡ https://www.livescience.com/12951-10-infectious-diseases-eb…

• በ1918 ዓ.ም የተከሰተው በመላው ዓለም የተስፋፋው የኢንፍልዌንዛ ወረርሽኝ ከ20-50 ሚሊየን ሰዎችን ገድሏል፡፡ በመጀመሪያው 25 ሳምንታት ብቻ 25 ሚሊየን ሰዎችን ገድሏል፡፡ የዚህ በሽታ መነሾም ለመብልነት የተከለከለው አሣማ ነበረ፡፡

እንደሚታወቀው ወደ መቶ የሚጠጉ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰዎች የሚተላለፉ ሲሆኑ በሽታውም Zoonotic Disease በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከእነዚህ አደገኞች የእንስሳት፣ የአራዊት፣ የአዕዋፍ ዓይነቶች መራቅ እንዳለብን እግዚአብሔር ለሙሴ ገልጾለት ለምግብነት እንዲውሉ የተፈቀዱ ንጹሓን እንስሳት፣ አራዊትንና አዕዋፍን በተጨማሪም ለምግብነት የተከለከሉትን በዘሌ 11 እና በዘዳ 14 ላይ በዝርዝር አስፍሯቸዋል፡፡

ከጤንነት አንጻር ሲታዩም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ እንስሳት እንዳይበሉና እንዳይነኩ መከልከሉ ካላቸው ታላቅ መንፈሳዊ አስተምህሮ በተጨማሪ የሰው ልጆች በእነዚህ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይጠቁ ለመጠበቅም ጭምር የሚጠቅሙ እንደሆነ ያጠኑ ተመራማሪዎች አሉ፡፡

• ለምሳሌ ያህል የቀዶ ሕክምና ባለሙያው ዶ/ር ኤ. ሬንድል እና ዴቪድ አይ ማችት ለ30 ዓመታት ያህል በዘሌ 11 ላይ የተደነገገውን የምግብ ሕግ ጥበብ በጥልቀት በማጥናት ከዛሬ 3500 ዓመት በፊት የተሠሩት እነዚህ የምግብ ሕገጋት አኹን ካለው በሳይንስ የተደገፈ የሥጋ አበላል ሥርዐት ጋር ያላቸውን ጥብቅ ግንኙነትን ሲያስረዱ በጥናታቸውም ከተከለከሉ ምግቦች መኻከል የዓሣማና የጥንቸል ሥጋ ምን ያኽል ለበሽታ የተጋለጠ መኾኑን ተንትነው በስፋት አስቀምጠዋል (Coder 1969 p.49, A.Rendle Short 1942 p.85) ፡፡

•ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከኾነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲበሉ የተፈቀዱና በትክክለኛው መንገድ የታረዱ የእንስሳትን ሥጋ መብላት እንስሳቱ በበሽታ ቢጠቁ እንኳን በሽታው ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድሉ አናሳ ነው፡፡ የተፈቀዱ የእንስሳትን ሥጋ በመብላት የሚመጣ መኾኑ የሚታወቀው የኮሶ ትል ሲኾን ይኽም በሽታ ጐልቶ ሊወጣ ያልቻለው በንጽሕና ጒድለት የሚመጣ ስለኾነ ነው፡፡

ካልተፈቀዱ እንስሳት መካከል ለምሳሌ “trichinosis” (ትራኪኖሲስ) የተባለው በሽታ ወደ ሰው የሚተላለፈው እንዲበላ ያልተፈቀደውን በበቂ ኹኔታ ሥጋው ያልበሰለን የዓሣማንና የድብን ሥጋ በመብላት ነበር፡፡ በዶ/ር ቫንዴለን እ.ኤ.አ በ1969 ዓ.ም ተጽፎ በነበረው ጥናት በጊዜው ዐሥር በመቶ የሚኾነው የአሜሪካ ሕዝብ በዚኹ በሽታ እየተጠቃ እንደነበረ ጽፏል።

• ዶ/ር ሩሴል በጥናቱ እንደገለጸው ፈረሶችና ጥንቸሎች ሸኰናቸው ስንጥቅ ስላልኾነ ለምግብነት ተከልክለው ነበር፤ የፈረስ ሥጋ ሲመረመርም በአብዛኛው ቫይረሶችንና ጥገኛ ተሐዋስያንን ይዟል፡፡

ጥንቸሎችም በዐይን ስናያቸው የዋሆች ቢመስሉም “ቱላሬሚያ” ለሚባለው ተላላፊ በሽታ መከሠት መንሥኤ ናቸው ብሏል፡፡

• የሜዲካል ዶክተር የኾነው ተመራማሪው ዶን ኮልበርት በዚህ ላይ የሚጨምረው ዓሣማዎች ስግብግብ ከመኾናቸው በተጨማሪ አግበስባሾች እንስሳት ናቸውና ቆሻሻ፣ ዐይነ ምድር እና ብስባሽ ሥጋ ጭምር ይበላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በአሜሪካ ታላቁ የኮሌራ ወረርሽኝ የመጣው በላውዚያና ውስጥ እ.ኤ.አ ከነሐሴ-ጥቅምት 1978 ዓ.ም ሲኾን የኮሌራው ምልክቶችም አፋጣኝ ተቅማጥ ወደ አፋጣኝ ድርቀት፣ ራስን መሳት፣ ከመጠን በላይ ውጥረትና ሞት ነበሩ፡፡ በኋላም በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ምን ተመግበው ነበር ተብሎ ሲመረመር የዓሣማ ሥጋ፣ mussel soup (የሙሴል ሾርባ)፣ የዓሣማ ደም ከኈምጣጤ ጋር ተለውሶና ጨዋማ በውሃ ውስጥ የሚኖረው “brine shrimp” (ብራይን ሺርምፕ) ከተደባለቁ አትክልት ጋር ተጨምሮ እንደነበር በጊዜው በምርመራ ተረጋግጦ ነበር፡፡

• በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው በዚህ የምግብ ሕገጋት ውስጥ የተከለከሉትን እንስሳትን በድናቸውን እንኳ መነካት እንደሌለበት ሲከለክል ምናልባት ግን የእነርሱን በድናቸውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ንጹሕ እንደማይሆንና በድናቸውን የሚያነሣ ልብሱን ማጠብ እንዳለበት ከ3500 ዓመታት በፊት፡
✍️ በዘሌ 11፥24-25 ላይ፡- “የእነርሱን በድን የሚነካ ኹሉ እስከ ማታ ርኩስ (ቆሻሻ) ነው፤ ከእነርሱም በድን የሚያነሣ ኹሉ ልብሱን ይጠብ እስከ ማታም ርኩስ (ቆሻሻ) ይኾናል፤ በድኑንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ” በማለት ለሙሴ ገልጾለት ነበር፡፡

• ይህ ለሙሴ የተነገረው አምላካዊ ትእዛዝ ከጤንነት አኳያ ከታየ እጅግ የሚጠቅም ሕግ ነበረው፤ ምክንያቱም ብዙ በሽታዎች ሥጋቸውን ከመብላት ይልቅ በበሽታ የተጠቁትን እንስሳት በመንካት ወይም በድናቸውን በመሸከም የሚተላለፉ መኾናቸውን ሰዎች ባለማወቅ ብዙ ጒዳት ላይ ሳይወድቁ በፊት የሚጠብቁ ዐጥሮችም ጭምር በመኾናቸው ነው፡፡

ለምሳሌ “Tularemia” (ቱላሬምያ) የተባለው ገዳይ በሽታ ዐምስት በመቶ የኾነው የበሽታው መተላለፊያ መንገድ በበሽታው የተጠቁ የጥንቸሎችን በድን በመንካትና በደንብ ያልበሰለ የጥንቸልን ሥጋ በመመገብ ነው፡፡

ሌላው “anthrax” (አንትራክስ) በመባል የሚታወቀው በሰዎች ቆዳ ላይ የሚታይ በሽታ የሚተላለፈው በበሽታው የተጠቁ እንስሳትን ጸጒርና ቆዳ በመንካትና የተበከለው ሥጋቸውን በመመገብ ጭምር ነው፡፡

በእነዚኽ በመጽሐፍ ቅዱስ ባልተፈቀዱ እንስሳት የሚመጡትን በሽታዎች የመቀነሻው የመጀመሪያው መንገድ በመጽሐፍ ቅዱሱ ሕግ እንደተጻፈው በድናቸውን የነኩበትን እጅ በደንብ መታጠብ ነው፤ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በደንብ አድርጎ መታጠብ የበሽታ አስተላላፊ የኾኑ በዐይን የማይታዩ ጥቃቅን ተሐዋስያን (micro organisms) ከቆዳ ላይ በማስወገድ የበሽታውን ወደ ሰውነት መግባት ይከለክላል፡፡

ንክኪው ረዘም ላሉ ሰዓታት ከኾነ ማለት በድናቸውን በመሸከም ቢኾን ረቂቃኑ ተሐዋስያን ወደ ልብሶች ጭምር ስለ ሚሰራጩ ሰውነትን ብቻ ሳይኾን ልብስንም ጭምር ማጠብ ያስፈልጋል፤ ኾኖም ግን ሰውዬው ይኽነን ሳያደርግ ቢቆይ እነዚኽ ተሐዋስያን ቆይተው በድንገት ወደ ሌላ ሰው በመዛመት ሌሎች ሰዎችን ጭምር የበሽታው ተጠቂዎች ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

እነዚኽ በዐይን በማይታዩ በረቂቃን ተሐዋስያን የሚመጡ በሽታዎችን አስቀድሞ የመከላከል ትእዛዝ ከ3500 ዓመታት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸ ቢኾንም ብዙ ሰዎች ባለመረዳታቸው የሞቱ እንስሳትን በድን በመሸከምና በመብላት ለበርካቶች ሕማማት ተጋልጠው ኑረዋል፡፡

በአጉሊ መነጽር ካልኾነ በቀር በዐይን ሊታዩ የማይችሉትን ለጤና ጠንቅ የኾኑትን እነዚኽ ረቂቃን ባሲሊ፣ ማይክሮብስ፣ ባክቴሪያና ሌሎች ተውሳኮች መኖራቸውን ጌታ ለሙሴ ገልጾለት በማወቁ ሙሴ የመጀመሪያው ጥቃቅኖች የኾኑ ተውሳኮችን (micro organisms) ነገር የሚያውቅ ሰው ያስብለዋል፡፡

ከ3 ሺሕ ዓመታት በኋላ ታላቁ የሕክምና ሊቅ ሉይስ ፓስተር በዘመኑ የነበሩት ምሁራን ባለማወቅ እጅጉን ቢቃወሙትም በማስረጃ መኖራቸውን እስካስረዳበት ድረስ እነዚኽን ጥቃቅኖች የኾኑ ተውሳኮችን ማንም ሳያውቃቸው ኑሯል፡፡

በመኾኑም እነዚኽ ጥቃቅን ተውሳኮች ከሚያስተላልፉት በሽታ አንጻር አስቀድሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳመለከተው የሞቱ ከብቶችን በድን መንካት መከልከል ከነኩም በኋላ እጅን፣ ሰውነትን መታጠብና ልብስን በአግባቡ ማጽዳት ትኩረት የሚሰጥበት ጉዳይ ነበር፡፡

በራሳቸው የሞቱ ከብቶችን በደናቸውን መንካትም ሆነ ሥጋቸው እንዳይበሉ በዘዳ 14፥21 ላይ “አንተ ለአምላክኽ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ነኽና የበከተውን ኹሉ አትብላ” ይላል፡፡

በሐዲስ ኪዳንም በሐዋ 15፥29 ላይ “ከደምም (ደም ከመብላት)፣ ከታነቀም (የሞተ ከብት ከመብላት)፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚኽ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችኊ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚኽም ኹሉ ራሳችኹን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችኊ ጤና ይስጣችኊ” በማለት ሥጋቸውን ከሚጐዳና ሥጋዊ በሽታን ከሚያስከትልባቸው ከነዚህ ነገሮች እንዲርቁ አስተምረዋል፡፡

የሞተ ከብት ሥጋ እየበሉ ሰዎች ለብዙ ሺ ዘመናት ከቆዩ በኋላ አሁን ግን በራሳቸው የሞቱ እንስሳት ሥጋ መመገብ በጤንነት ላይ የሚያመጡት ታላቅ ጒዳት በዘመናችን በመረጋገጡ አኹን ባለንበት በ፳፩ (21) ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የምግብ ሕግ ላይ በበሽታ የሞቱ ማናቸውም የእንስሳት ሥጋ እንዳይሸጥ ተከልክሏል፡፡

ዶ/ር ዊሊያም በጥናታቸው ላይ ይኽነን ሲጠቁሙ “በራሳቸው በሞቱ የእንስሳት በድን ውስጥ የተደበቁ ቁንጫዎች፣ መዥገሮች፣ ተባዮች “bubonic plague (ቡቦኒክ ፕሌግ), spotted fever (ስፖትድ ፊቨር- ነጠብጣባማ የቆዳ ቊስለት የሚያመጣ የትኩሳት በሽታ ዐይነት), typhus fever” (ታይፈስ ፊቨር- የተስቦ ትኩሳት)” የሚባሉ ገዳዮች በሽታዎችን የተሸከሙ መኾናቸውን አኹን ባለንበት ዘመን አውቀናል” ብለዋል፤ በመኾኑም ሰው አስቀድሞ ይኽነን ሕያው የኾነ የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድሞ ቢያውቅና ቢረዳ ኖሮ ብዙ ችግርና ጉዳት ሳይደርስ በፊት አስቀድሞ መቈጣጣር በቻለ ነበር ብለዋል (Coder p.49, Modern Science and the Christian Faith, 1948 p.191)፡፡

በተከታይ በምጽፍላችሁ ጽሑፌ እጅግ መመረዝን ስለሚያስከትሉት በብዙ ዓለማት ለኮሌራ መቀስቀስና ለሚሊየኖች ሞት ምክንያት የሆኑት ከዛሬ 3500 ዓመት በፊት ስለተከለከሉት የባሕር ዓሣዎች አቀርብላችኋለሁ፡፡ በፌስ ቡክ የምጽፈው በጣም ትንሹን ነውና የምትችሉ ግን “መጽሐፍ ቅዱስና የሕክምና ሳይንስ” የሚለው መጽሐፉን ብታነቡ ዕውቀታችሁ በእጅጉ ይሰፋል፡፡

“መጽሐፍ ቅዱስና የሕክምና ሳይንስ” ከሚለው መጽሐፌ ከገጽ 31-37 በጥቂቱ የተወሰደ)
✍️ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

ይቀጥላል፡

መጽሐፉን በሁሉም የመጻሕፍት መሸጫዎች ወይም 0913422447 ይገኛል።

Filed in: Amharic