>

የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገባ!!! (አማራ ሚዲያ)

የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገባ!!!

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በኩል የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጥሶ መግባቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአማራ ሚዲያ ማዕከል ገልፀዋል።
የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ትናንት መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ. ም ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በኩል በመግባት ስናር በተባለ የኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች እርሻ ልማት ካምፕ ዙሪያ መስፈሩን ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የተናገሩት።
ዳር ድንበርን ጥሶ የገባው የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ከኮር ሁመር ከተማ በተወሰነ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ስናር በርሀ በሚያለሙት በአቶ ሰለሞን በየነ እና በአቶ ስመኘው ብርሀኔ የእርሻ ካምፕ ዙሪያ መስፈሩ ነው የተገለፀው።
ወደ ኢትዮጵያ የገባው የሱዳን መከላከያ ሰራዊትም ትናንት መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ያለማንም ከልካይነት ድንበር ጥሶ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ በሰው ላይ በቀጥታ ጉዳት አላደረሰም ቢባልም ስናር አካባቢ ምሽግ ሲቆፍር፣ በርሀውን በእሳት ሲያቃጥልና ወታደራዊ ካምፕ እየሰራ መሆኑን የዐይን እማኞች ነግረውናል።
የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ እና የአካባቢው የፀጥታ አካላት የሱዳን መከላከያን ሰራዊትን ከስናር ለማስለቀቅ በሚል ለመግባት ያደረጉት ሙከራም በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ከልካይነት አለመሳካቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊትም ወደ ኮርሁመር ስናር አቅጣጫ በማቅናት ስፍራው በሱዳን የመከላከያ ሰራዊት አባላት የተያዘ መሆኑን ተመልክቶ መፍትሄ እያፈላለገ መሆኑን ገልጾልናል ሲሉ ነዋሪዎች አስታውቀዋል።
የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት በተለያዩ ጊዜያት ድንበር ጥሶ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በባለሀብቶችና በእርሻ ካምፓቸው ላይ ጥቃት እያደረሰ እንደሚመለስ የሚታወቅ ቢሆንም በወርሀ ሰኔ 2010 ዓ.ም በስናር በኩል ያደረገው ጥቃት በአካባቢው አርሶ አደሮችና ሚሊሻዎች አማካኝነት በተሰጠው ራስን የመከላከል የመልስ ምት የህይወትና የአካል ጉዳት ደርሶበት በርካታ ከባድ መሳሪያዎችን ሳይቀር ተማርኮ መመለሱ ይታወሳል።
ሱዳን ከሉአላዊነት ጋር በተያያዘ ለምትፈፅመው ጥቃት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በኩል የሚሰጠው ምላሽ እጅግ የዘገዬና ከፍተኛ መለሳለስ እየታዬበት ነው ሲሉ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርባሉ።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት መንግስት የሰጠውን የፋኖ አመራሮችና አባላትን በማሳደድ፣ በማሰርና በማጥቃት መዋቅሩን የማፍረስ ተልዕኮ በጎንደር መሀል ከተማ፣ በገንዳ ውሀ፣ በዳባት እና በሌሎች አካባቢዎችም እየፈፀመ ባለበት ሁኔታ ነው ሉአላዊነት መደፈሩ የተነገረው።
መከላከያ የሀገር ሉአላዊነት ማስከበር ሲገባው በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በአማራ ሰሜን ጎንደር ዙሪያ ሉአላዊነት በማስከበር ረገድ ተሞክሮ አላቸው የተባሉ ፋኖ አርበኛ ብርሀኑ ነጋ፣ ንጉስ በላይና ሌሎችንም በማሰር የአካባቢው የመስተዳድር አካላትን ሚና ተክቶ እስከመስራት እየደረሰነው የሚሉ ቅሬታዎች ይነሱበታል።
የአማራ ሚዲያ ማዕከል በጎንደር አዘዞ የ33ኛ ክፍለ ጦር የመከላከያ አዛዥ የሆኑትን ኮሎኔል ደስታው ተመስገንን በስልክ ለማነጋገር ሞክሯል።
ስለሁኔታው መረጃ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ኮሎኔል ደስታው በበኩላቸው “…ሆኗል አልሆነም የሚለውን ማረጋገጫ ስለሚያስፈልግ እዛ ደግሞ የተላከ ቡድን ስላለ ያን ቼክ አድርገን የምንነጋገረው እንጅ አሁን ይሄ ነው የሚባል የለም።” ካሉ በኋላ ጥያቄ ስናነሳ ስልካቸውን ዘግተዋል።
ምንም እንኳ ኮሎኔል ደስታው ገና እንዳልተረጋገጠ ቢናገሩም በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የኮር ሁመርና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም አንዳንድ የመስተዳድር አካላት የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት ድንበር ጥሶ መግባቱን አረጋግጠውልናል።
Filed in: Amharic