>

ኮሮናን እየተዋጋን ፍትሕ እንጠይቃለን፤ መንግስት ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስን በአፋጣኝ ሊፈታው ይገባል!!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ኮሮናን እየተዋጋን ፍትሕ እንጠይቃለን፤ መንግስት ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስን በአፋጣኝ ሊፈታው ይገባል!!!!

ያሬድ ሀይለማርያም
ጋዜጠኛ ያየሰው “ከኮሮና ቫይረስ መዛመት ጋር አያይዞ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ ሊሞት ስለሚችል (በቁጥር የተገለጸ ) ያስከሬን ሥፍራ እንዲዘጋጅ መንግስት አዟል” የሚል ዘገባ ሰርተህ እኛንም፣ ሕዝቡንም አስደንብረሃል ተብሎ ነው የታሰረው። ጋዜጠኛው ዘገባውን ከሰራ በኋላ ከመንግስት እና ከሕዝብ የተከተከለውን ወቀሳና ወርጅብኝ ተከትሎም በይፋ ይቅርታ ጠይቆ ያስተላለፈውን መረጃ አንስቷል። ታዲያ አልገባህ ያለኝ፤
+ ግለሰቡን በሕግ የሚያስጠይቀው ነገር እንኳ ቢኖር ፖሊስ ጋዜጠኛውን አስሮ ማቆየት ለምን አስፈለገው?
+ ጋዜጠኛውን አስሮ ቃሉን ከተቀበለስ በኋላ በምን የሕግ መሰረት ነው ዋስትና ከልክሎ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ አካሂዳለው በሚል ጋዜጠኛውን በእስር የሚያቆየው?
+ ጋዜጠኛው የተናገረው ነገር ግልጽ እና እሱም እራሱ አምኖ ይቅርታ የጠየቀበት ሆኖ ሳለ ፖሊስ በምኑ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ሊያካሂድ ነው የተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀው? ምንስ ማስረጃ ቀርቶት ነው?
+ የፖሊሶቹ አሳፋሪ እና ሕግን ያልተከተለ እርምጃ አልበቃ ብሎ የአራዳ ፍርድ ቤት ፖሊስ ለጠየቀው ምክንያት የለሽ ጥያቄ ድጋፍ በመስጠት የተጨማሪ ስድስት ቀን የምርመራ ጊዜ ለምን ይሆን የሰጠው? ይህ አይነቱ ድርጊት በዘመነ ወ/ሮ መአዛ መፈጸሙ ደግሞ የበለጠ ያሳቅቃል።
+ መንግስትስ ቢሆን አንዳንዱ ሚዲያ እና ታዋቂ ግለሰቦች ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ፤ ከዛም አልፎ ለብዙ ሰዎች መሞት ምክንያት የሆኑ ዘገባዎችን በቲቪ ጭምር ሲያሰራጩ ለነበሩ ሚዲያዎች ሰላሳ የምክር እና የተግሳጽ ደብዳቤ እየጻፈ፤ አንዳንዴም እርምጃ እወስዳለሁ እያለ ቢፎክር ይቅርታ እንኳ ሳይጠይቁት እና ከአድራጎታቸውም ሳይታቀቡ እነሱ ላይ ያሳየውን ሰፊ ትዕግስት ለጋዜጠኛ ያየሰው፤ ሊያውም ለተፈጸመው ድርጊት ይቅርታን የጠየቀን ሰው እስር ቤት ወስዶ ማጎር ምን ይሉታል?
የአብይ አስተዳደር የሕግ የበላይነትን በአግባቡ አለማስከበር ብቻ ሳይሆን ሚዛናዊነትን የሳተ እና ወጥነት የሌለው የሕግ አፈጻጸም ትግበራው ከወዲሁ አንድ ሊባል ይገባል።
አሜሪካ እና አውሮፓ ያሉ መገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞች የተለያዩ መረጃዎችን ወይም የግምት መነሻዎችን እየተንተራሱ በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ በሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ሊሞት እንደሚችል እና መንግስታት በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ጠባ ነጋ ያሳስባሉ፣ ይዘግባሉ አንዳንዴም የተሳሳቱ የቁጥር ግምቶችንም ያሰራጫሉ። እንግዲህ እንደ ኢትዮጵያ መንግስት አካሄድ ከሆነ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች እና ሚዲያዎች ላይ እርምጃ መወሰድ ነበረበት ማለት ነው።
ለእኔ የጋዜጠኛ ያየሰው እስር የፖለቲካ እንድምታው ነው ጎልቶ የሚታየኝ። ግለሰቡ መንግስትን ሊጎረብጡ የሚችሉ ዘገባዎችን ደጋግሞ በመስራቱ የሥርዓቱ አይን ውስጥ የገባ ይመስላል።
ፍትሕ ለጋዜጠኛ ያየሰው!
Filed in: Amharic