>
5:18 pm - Friday June 16, 6722

የወሳኝ ጊዜ  ሰው ! (ሙክታሮቪች) 

ወሳኝ ጊዜ  ሰው !

(ሙክታሮቪች) 
አንዳንዴ ስናጣው ብቻ መልካምነቱን የምናስበው ሰው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሞልቶኣል። እኔ የቅርብ የኢትዮጵያ ታሪክን አንብቤ እንደተረዳሁት ኢትዮጵያ የአክሊሉ ሀብተወልድ ውለታን የረሳች ሀገር ናት። ነገ የሙስጠፋንም ውለታ ትረሳለች ብዬ እሰጋለሁ። ሙስጠፋ በአለማቀፍ ድርጅቶች ከየተባበሩት መንግስታት ጀምሮ በርካታ ተመሳሳይ ድርጅቶች ውስጥ ለቤተሰቡና ለዘመዶቹ የሚሆን በቂ ክፍያ አግኝቶ እየኖረ የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ ነው። ሀገሩ ስትፈልገው የመጣ ሀገር ወዳድ ነው።

ተወልዶ ባደገበት ሀገሩ፣ በተለይ በኢህአዴግ የተዘረጋው ሶማሌን እንደሁለተኛ ዜጋ የበይ ተመልካች፣ ግዴለሽ፣ ሙሰኛ፣ ለሀገር የማያስብ ተገንጣይ አድርጎ  መሳሉ   ሚያንገበግበው ሰው ነው። ይህ ስሜቱን Abtigis በሚል የብዕር ስም በ somalionline ፎረም ላይ አክቲቪስት እየነበረ በቁጭት እየተንገበገበ ይናገር በነበረበት ወቅት አውቀዋለሁ። ለሀገር የሚያስብ ሶማሌ የሀገር ልጅ እድል መነፈጉ ያናደው ነበር። ይህ ስሜቱን እኔም እረዳለሁ። በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ ከምስረታ ጀምሮ 12 አመት ቆይቻለሁ። ቀላል ጊዜ አይደለም።

 አንድ ሰው በማወቁ መሸለም ሲገባው ለማህበረሰቡ አጥብቆ ስለሚቆረቆር ብቻ በኢህአዴግ ጥርስ ውስጥ ይገባ ነበር። እኛ ሀገርና ህዝባችንን የምንወድ የሶማሌ ልጆች የኢህዴግ ትዝታችን ይህ ነው።
ለውጥ ከመምጣቱ በፊት እኔም ከፍራቻ ጋር እየታገልኩ ስለኢትዮጵያ አንድነት እፅፍ ነበር። በመጠኑም ቢሆን ኢህአዴግን እቃወም ነበር። የሶማሌ ክልልን በተመለከተ አልፅፍም። አብዲሌ ይቆረጭመኛል ብዬ እፈራለሁ። ደግሞም ይቆረጭመኝ ነበረ። ብታሰር #ፍሪ #ሙክታሮቪች ብርቅ ነው!
ሙስጠፋ ግን ከአብዲኢሌ የጭካኔ አገዛዝ ጋር ይፋለም ነበረ። ለአብዲ የእግር እሳት ሆኖበት ነበር። ሙስጠፋ ኢንግሊዘኛን አቀላጥፎ ስለሚናገርበት የአብዲን ወንጀል ለአለማቀፍ ታዛቢ ያሳጣበት ነበር። አብዲሌ ሙስጠፋን ለማስፈራራት ኢንጂነር ወንድሙን በአሳቃቂ ሁኔታ ገድሎ አባቱን አስፈራርቶ እና ቶርቸር አድርጎ ከመቃወም እንዲታቀብ ሊያደርገው ቢሞክርም ሙስጠፋ እሺ አላለም። (ታሪክ ያስታውሰዋል ያለፈበትን፣ እኔ ለ UN እና ለአለማቀፍ የመብት ታጋዮች ስለቤተሰቡ ደህንነት የተማፀነበትን ፅሁፍ አንብቤ ከልቤ አዝኛለሁ)
ሙስጠፋ እንግዲህ እኔ የማውቀው አክቲቪስት በነበረበት የጭቆና ዘመን ነው። ሁል ጊዜ ለሶማሌ ህዝብ መብት ሲጨቃጨቅ ሲነታረክ አውቀዋለሁ። አንድ የእሱን አቋም የሚያስረግጥልኝ ነገር አለ። የኢትዮጵያ ጠንካራ አንድነት  በኢትዮጵያ ለሚገኝም ሶማሌ በሌላ ጎሮቤት ሀገር ለሚገኝም የሶማሌ ማህበረሰብ ይጠቅማል ባይ ነው። እንዲሁም፣
በሶማሌ ክልል ውስጥ የሶማሌ ህዝብ አንድነት ለኢትዮጵያ አንድነት በጣም ይጠቅማል ባይ ነው።
ከተለያዩ ክርክሮቹ፣ ቃለመጠየቆቹ እና ከሽማግሌዎች ጋር በሚያደርገው ውይይት የሶማሌን ህዝብ ጅምላ አንድነት ወደ ኢትዮጵያ ማዕከላዊ ፖለቲካ በማምጣት፣ የሶማሌ ህዝብ ከኢትዮጵያ ሀብት የድርሻውን በፍትሀዊነት የሚጠይቅበት፣ በስልጣን ክፍፍል የሚገባውን የሚያገኝበትን የፖለቲካ አካሄድ የሚመርጥ ብልህ ፖለቲከኛ ነው። (ሙገሳ አይደለም፣ እውነት ነው)
ሙስጠፋ አክቲቪስት ነበረ። ለኢትዮጵያ የሚያዋጣውን የፖለቲካ አካሄድ ይናገር ነበረ። ፖለቲካ እንጀራው አልነበረም። የሚፈልገውን አይነት ሀገር እና አስተዳደር ሲሰብክ ስለነበረ፣ የለውጥ እድል ሲያገኝ ወደ ሀገሩ ለመምጣት ምንም ወደ ኋላ አላለም።
(ስንቶች አሁንም ተቺ ብቻ ሆነው እንደቀሩ ኢንተርኔቱ ይቁጠረው።)
ይህን ሁሉ ለምን አወራለሁ? እውነት ለመናገር ሙስጠፋ ስለሚያሳዝነኝ ነው። በጣም ሀገሩን የሚወድ፣ በጣም የሶማሌ ማህበረሰቡን የሚወድ፣ የተማረ፣ መማሩን በሀሳቡ ስፋትና ጥልቀት ያሳየ ነው። በእኩልነት የሚያምን ነው። ሀገራችን መልካም አሳቢዎቿን ሁሌ ትበላለች። ይህ ያስፈራኛል።
ኢትዮጵያውያን ከሙስጠፌ ጋር እንዲሆኑ እኔ እመኛለሁ። የዶክተር አብይ አስተዳደር ከሙስጠፌ ጋር እንዲሆን በጣም እፈልጋለሁ።
በተለይ በዚህ በሽታ ወቅት ስለ አርብቶአደሩ የሶማሌ ህዝብ በጣም ያሳስበናል። የኛ ህዝብ በአርብቶ አደርነት የኑሮ ጣጣ ምክንያት የሚንቀሳቀስ ነው። ይህ በሽታ መንቀሳቀስ አይፈልግም። እና ምን ተሻለ? ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል። ለዚህም የፌዴራል መንግስት ድጋፍ ማድረግ አለበት። ኢትዮጵያውያንም የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፣ እርስበርስ እንደገጋፍ።
በዚህ የበሽታ ዘመን አንዳችን ላንዳችን መሆን አለብን።
ሙስጠፋ የተፈጠረውን አነስተኛ ችግር በአመራር ብልህነቱ ተሻግሮታል። መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በህግ የበላይነት የግድ መታመን አለበት።
ሀገራችንን ፈጣሪ ይጠብቅልን።
ኢትዮጵያን የሚጠብቋት ልጆችዋን አምላክ ይጠብቅልን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
Filed in: Amharic