>

ኮሮና ሆይ ቅዳሴ አስታጉለኻል እና እግዚአብሔር ያስታጉልኸ!!   ( ዳንኤል ክብረት )

ኮሮና ሆይ ቅዳሴ አስታጉለኻል እና እግዚአብሔር ያስታጉልኸ!!

ዳንኤል ክብረት
ሊቀ ሊቃውንት ሥሙር አላምረው እንዲህ አሉ፦
…ነሐሴን እግዚአብሔር ይቅሠፈው!
ወሩ ከላይ ዝናም ከታች ምንጭ እየገነፈለ ምድራችን በውኀ የምትሸፈንበት ወርኀ ነሐሴ ነው። ተረኛው ቀዳሽ ካህን ከቤቱ ወደቤተ ክርስቲያን ለመኼድ አንድ ትንሽ ወንዝ ተሻግሮ ነበር የሚኼድ፤ ከዕለታት በአንድ ቀን በነሐሴ ወር ግን ካህኑ ቀን ጎደለበት ወንዙ ሞላበት፤
ወንዙን ለመሻገር የቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሞገስ
ወይም የክሪስ ኤንጅል plexiglass ያስፈልጋል
ግን ኹለቱም አልነበረውምና ወደቤቱ ተመለሰ። ቅዳሴው ታጎለ።
ይኽን ነገር የሰማ የቅኔ ተማሪ እንዲኽ ሲል ቅኔ ቆጠረበት።
“እግዚአብሔር ይቅሥፎ ለዘኀለፈ ነሐሴ፤
እንተ ዘነሐሴ ክረምት እስመ አኅጎለ ቅዳሴ፤
ያለፈው ነሐሴን እግዚአብሔር ይቅሠፈው
የነሐሴ ክረምት ቅዳሴ አስታጉሏልና”
አይ የካህኑ አበሳ!
ቅዳሴ አላስታጉልም እንደምንም ልሻገር ብሎ ሰጥሞ ቢሞት፣ ተዳድፎ ሊቀድስ አስቦ ይኾናል የተቀሰፈ የሚለው ይኖራል፤
(( ዳንኤልን ያከበረ አንበሳ አግናጥዮስን መብላቱ፣ አግናጥዮስ ሀይማኖት ስላልነበረው ነው እንዴ? አግናጥዮስን ሳትኾን ‘አንበሳውን’ አትዳፈር!))
ወንዙን ፈርቶ ሲቀር ይኸ ፈሪ ቄስ ፈጣሪውን አምኖ ዋኝቶ መሻገር ሲገባው ቅዳሴያችንን አስታጎለ ተብሎ አምኖ ባለመሻገሩ ይወቀሳል።
እንደ ተሜ ያሉት ባለቅኔዎች ደግሞ የቀረውን ካህን ያይደለ ያስቀረውን ክረምት ይወቅሳሉ።
ይኽ የኛ ጊዜም በሽታ እንደ ሰርዶ በየምድሩ የበቀለበት በመኾኑ ቅዳሴያችን እንደ ሱራፌል ኾኗል፤ ቀዳሹም አስቀዳሹም ካህን። አልተለመደምና ይጨንቃል ለኛ፤ ቢኾንም ማዕበሉ ጸጥ እስኪል ወንዙ እስኪጎድል በቤት መቆየት በጎ ነው፤ ከፍጹምነት ላልደረስን ወጣንያን ክርስቲያኖች። የአንዳድ መምህራን ወንድሞቻችን ሐሳብም ቢኾን ወንዙ እስኪ ጎድል ሕዝብ በቤት አይቆይ የሚል አይደለም፤
የሐሳቡ ልዩነት ያለ በግቡ ሳይኾን በሂደቱ ላይ ነው፤ በሂደቱ እኔም ችግር ብየ የማስበው ጉዳይ ነበረ፤ ኾኖም እርስ በእርስ እንደ ድንጋይ ከሚወራወሩት ሮኬት ለመዳን Iron Dome( የብረት ጣርያ) ውስጥ ሀገራቸውን አስጠልለው የሚኖሩት እስራኤልና ፍልስጥኤም እንኳ በጋራ ገዳያቸው ኮሮና ምክንያት በጋራ መሥራት ሲጀምሩ እኛ መድረሻችን አንድ ኾኖ መንገዳችን የተለያየ ሰዎች አንድ ኾነን፥
ኮቪድ ያኅጉልከ እግዚአብሔር ሥላሴ፤
ኮሮና ሕማም እስመ አኅጎልከ ቅዳሴ፤
ቅዳሴ አስታጉለኻልና ኮሮና ኾይ እግዚአብሔር ያስታጉልኽ። እንበል።
አስታጉለኻል ማለታችንም ምእመናንን ስላሰቀረ ብቻ ነው።
Filed in: Amharic