>

በሀገራችን ሰዎች እየተራቡ ነው!!! (ቅዱስ ማህሉ)

በሀገራችን ሰዎች እየተራቡ ነው!!!

 

ቅዱስ ማህሉ
 
መንግስት የመብራት እና የውሃ ክፍያ ለሶስት ወራት ያህል በሙሉ ባይሰርዝ እንኳ ሩብ ዋጋው ብቻ እንዲከፈል ውሳኔ ያሳልፍ። የኢንተርኔት ዋጋም ቅናሽ ቢደረግበት በሳንባ ቆልፍ ላይ ሰዎች በቤታቸው ሆነው እንደልብ መረጃ እንዲለዋወጡ ከማስቻሉም በላይ እንዳይሰላቹ እና በጭንቀት ብቻ ቀኑን እንዳያሳልፉ ይረዳል።  በርግጥ ስራ ፈቶ በቤቱ ቁጭ ብሎ የሚያሳልፍ ሰው የሚጨነቀው እና የሚፈራው መራብን ብቻ አይደለም። ኪራይ የሚያስጨንቀው አለ። ነገ መንግስት የሚያመጣውም ጣጣ የሚያስጨንቀው አለ። ስለዚህ መንግስት በቴሌቪዥን በዚህ አከራይ እና ተከራይን በሚያስጨንቅ ጉዳይ እንኳ እንዴት የእፎይታ ጊዜ መስጠቱን አያውጅም? መንግስት ይሄን የመብራትና የውሃ ክፍያን ከተወ እና ከቤት አከራዮች ላይ የሚሰበስበውን ግብር ቢያንስ ይሄ የወረርሽኝ ስጋት እስኪያበቃ ቢያንስ ለሶስት ወራት ከተወው የመኖሪያ እና የንግድ ቤት አከራዮች ቢያንስ በግማሽ  ዋጋ ምናልባትም ከዚያም በላይ ለተከራዮቻቸው መቀነስ ያስችላቸዋል። ይሄ የተወሰነ እፎይታ ሊፈጥር ይችላል። ለዘለቄታው ግን መፍትሄው የሚሰሩ ሰዎች አፍና አፍንጫን መሸፈን አስገዳጅ አድርጎ ወደ ስራቸው እንዲመልሱ ማድረግ ነው። ይህን ማድረግ የሳንባ ቆልፍ ሊፈጥረው ከሚችለው በላይ ያንዣበበውን የርሃብ አደጋ እና የማህበራዊ ምስቅልቅል ለማስቀረት ይረዳል። እስከዚያው ድረስ ሁሉም በየጎረቤቱ ያሉትን ብቻ በማሰብ ለመርዳት ይሞክር። ሁሉም በየጎረቤቱ ያሉትን አቅመ ደካሞች እና ድሆች ከረዳ በየአካባቢው ያ ችግር ይቃለላል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ሌላ ወረርሽኝ በየአካባቢያችን መከሰቱ አይቀሬ ነው። በባህር ዳር እና በናዝሬት(አዳማ ) ሰዎች ከልጆቻችን ጋር ተራብን እያሉ ነው። በአዲስ አበባ የባሰ እንደሚሆን አያጠራጥርም። በሁለቱ ከተሞች እና በሌሎችም ጭምር መንግስት ለተቸገሩ እና ለተራቡ ሰዎች “ምግብ እዚህ ቦታ መጥታችሁ ውሰዱ” ብሎ በየቀበሌውም ቢሆን ሬሽን በአስቸኳይ መጀመር አለበት። ካልሆነ ከሳንባ ቆልፍ ወረርሽኝ የበለጠ ኢትዮጵያ ልትቀለብሰው የማትችለው ርሃብ እና ማህበራዊ ምስቅልቅል ከፊታችን አድፍጧል።
ሳምባ ቆልፍ እና  ረሀብ በአፍሪካ …
 
ሳምባ ቆልፍ  በአፍሪካ ከሚያደርሰው ጉዳት በላይ መንግስታቱ ባልተሰላ ስሌት በሚወስዱት እና ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ ኮፒ ፔስት በሚያደርጉት አሰራር ምክንያት የሚፈጠረው ምስቅልቅ፣ ረሃብ እና ስርዓት አልበኝነት ብዙ የአፍሪካ ሃገራትን ወደ ርስበርስ ጦርነት ሊከት ይችላል። ኢትዮጵያ ከዚህ ስጋት የነጻች አይደለችም። ትንሽ እየረፈደ እንደሆነ ቢሰማኝም አካሄዳችንን በፍጥነት ማረም እና ማስተካከል ካልቻልን ከላይ ያልኩትን ውሎ አድሮ በዓይናችን ስለምናየው ለማብራራት መድከም የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ይህች የምታዩዋት ባሏ ሙቶባት ብቻዋን ልጆች የምታሳድግ የቡላምቡሊ ወረዳ(Bulambuli District) ነዋሪ የነበረች ኡጋንዳዊ ናት። መንግስት ሳምባ ቆልፍ/ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚል ሁሉም በየቤቱ እንዲገባ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ቤቷን ዘግታ ተቀመጠች። የሷን ርሃብ ታግሳ የልጆቿን ጠኔ እና ዋይታ ግን መስማት ከአቅሟ በላይ ሆነባት። እናም ራሷን እንደምታዩት ሰቀለች። ይህ አፍሪካ ውስጥ የአንድ ሰው ዜና አይደለም። ኡጋንዳዊያን በአመታዊ አማካይ ገቢ ሲታይ  ከኢትዮጵያ  ይሻላሉ። ከህዝብ ቁጥር አንጻር ቢታይ እንኳ በኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች ያለው ህዝብ ቁጥር ከጠቅላላው 43 ሚሊዮኑ የኡጋንዳ ህዝብ ቁጥር ይበለጣል።
የሳምባ ቆልፍ/ኮሮና ቫይረስ/ ቀውስ በትክከለኛ መንገድ ተሰልቶ ካልተሄደበት በአፍሪካ ሳምባ ቆልፍ/ኮሮና ቫይረስ/ በሁሉም ቀስቶቹ ከማንም በላይ የሚወጋት ሃገር ኢትዮጵያ መሆኗ አይቀርም። ይሄን ከሃያ ቀን በፊት ጽፌው ነበር። ከሶስት ቀናት በፊት ዓለማቀፍ ድርጅቶችም የኢትዮጵያ መንግስት አሰራር፣ የመረጃ አያያዝ እና ኢ ዝግጁነት እንዲሁም የጥድፊያ ውሳኔዎች ወዘተ አሳስቧቸው ስጋታቸውን ይፋ አውጥተውታል። ስለዚህ በደንባራው ፖለቲካ ደንበር ደንበር ማለቱን ትተን ሰዋዊ እና ተፈጻሚ ውሳኔዎችን ከራሳችን ሃገር እና ህዝብ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር መፍቴዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባናል። ይህ ካልሆነ የከረምነበት ኮሮና ከጥቂት ቀናት በኋላ የአለመረጋጋት፣ የስርዓት አልበኝነት እና የነውጥ ዜናን ሊወልድ ይችላል። በተረፈ የምትችሉ ሰዎች ይህ ምስቅልቅል ሳይመጣ ቢያንስ ሌላ ሩቅ ቦታ መሄድ ሳያስፈልግ ችግር ውስጥ ይገባሉ ወይም የሚያግዛቸው የሌላቸውን የምታውቋቸውን አቅመ ደካማ ወይም ደሃ ጎረቤቶቻችሁን ለመርዳት ሞክሩ። ሁሉም በየጎረቤቱ ትንሽ ትንሽ ካደረገ ለጊዜውም ቢሆን አደጋው ቶሎ እንዳይመጣ የበኩላችንን በማድረግ ማራቅ እንችላለን።
Filed in: Amharic