>
5:18 pm - Thursday June 16, 0749

ዶክተር ጭቁኑና የከንቲባው ፀሃፊ ! (አሌክስ አብርሃም)

ዶክተር ጭቁኑና የከንቲባው ፀሃፊ !

(አሌክስ አብርሃም)
‹‹ዶክተር›› ጭቁኑ እባላለሁ ! በእንግጭላ ወረዳ በሚገኘው ጭገር መንጫ ጤና ጣቢያ ብቸኛ የጤና ባለሙያ ነኝ ! የመጀመሪያ ቀን የጤና ጣቢያውን ስም ስሰማ እንደመሳቅም እንደማፈርም  ቃጥቶኝ ነበር …ይሁንና የተመደብኩበት ቦታ  ከእንግጭላ ከተማ የሰባት ሰዓት የእግር መንገድ እንደሚርቅ ሲነገረኝ ስሙን ረስቸ ራሴን ይዠ ኡኡኡኡ ብየ ለእድሌ አለቀስኩ !
በኋላ ‹‹ጭገር መንጫ›› ስያሜው ከየት እንደመጣ ስጠይቅ በደርግ ጊዜ አንድ እጩ መምህር ነው አሉ… እንደኔው እዛ እንደተመደበ ይነገረውና ‹‹እባካችሁ ቀረብ አርጉኝ ቤተሰብ አለኝ …ካገባሁ ገና አመቴ ነው…አራስ ሚስት አለችኝ ህፃን ልጅ አለኝ እባካችሁ ….› እያለ ፀጉሩን እየነጨ ኡኡ ሲል …ትእቢተኛው የወረዳ ሃላፊ
‹‹ጓድ ! አትወራጭ!!… ሳይማር ላስተማረህ ህዝብ እንኳን ፀጉርህን ጭገርህን ብትነጭ መቅረት የለም አቢዮት ላይ ነን !…አሁን ትሄዳለህ አትሄድም ?›› ብሎ እጁን የታጠቀው ሽጉጥ ላይ ጣል ሲያደርግ ….ያ ሚስኪን አስተማሪ ሰባት ሰዓት የሚፈጀውን መንገድ በአራት ሰዓት ፉት ብሎት የተመደበበት ደረሰ አሉ !እስካሁን ያንን ሪከርድ የሰበረ የለም ! በቃ አካባቢው በዚቹ ሰበብ ‹‹ጭገር መንጫ›› ተብሎ ቀረ !የሰውን መከራ ስም የምታደርግ አገር !
   የሆነ ሁኖ ‹‹ዶክተር›› ጭቁኑ እባላለሁ !በርግጥ ዶክተር አይደለሁም … ያው የምኖርባት ትንሽ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ጤና ጣቢያው ላይ ተመድቤ ከመጣሁበት እለት ጀምሮ ‹‹ዶክተር›› ስለሚሉኝ ‹‹ተው ዶክተር አይደለሁም›› ብል ‹‹ኧረረ በእንግጭላው መድሃኒያለም ! ሃዲያሳ ምንድነሁ ዶፍተር ? ›› አሉኝ ተገርመው !
‹‹ከዶክተር ዝቅ ይላል ›› አልኩ እንዲገባቸው ብየ
‹‹አሃ! ዝቅ ከፍ ምንድነው? …እርጎ የመሰለ ካቦርታ ለብሰዋል፣ አገሬውን ሁሉ በማዳመጫ አንጀቱ ውስጥ ያለውን በሽታ እያዳመጡ በመርፌ እየጨረቆሱት ነው… ሃዲያሳ ምንድነኝ ሊሉ ነው? …አይ አጉልም መተናነስ ደግ አደለም ዶፍተር ›› ብለው እንደውም ራሱን ከፍ ከፍ የማያደርግ ትሁት ዶክተር መጣ ተብሎ ወሬው ተዳረሰ !! ዱክትርናውን በዚህ ሁኔታ ተቀበልኩ !!ሰው መቸስ በአንድም በሌላም መንገድ ዱክትርናውን የሚቀበልባት አገር ናት !
ቤተሰቦቸ ለሞላ ስም ለምን ጭቁኑ እንዳሉኝ ባላውቅም ዶክተር የሚለው ስም ለስሜ ግርማ ሞገስ ስለሰጠው እየቆየ ሲሄድ ወደድኩት ! በዚህ የገጠር ጤና ጣቢያ ላለፉት ሶስት አመታት እንደዶክተር ሳይሆን እንደወታደር ፍዳየን እየበላሁ ቆይቻለሁ !! ምሽግ መቆፈር እና ሰላምታ የምሰጠው አዛዥ ሲቀር ያው የወታደር ኑሮ ነበር ኑሩየ !ከተማ ጉዳይ ሲኖረኝ (ብዙ ጊዜ ለእናቴ ብር ለመላክ ባንክ ፍለጋ) ሰባት ሰዓት በእግሬ መጓዝ አለብኝ !! በሽተኛ መጣ ከተባለ በደረቅ ሌሊት ይሁን በጠራራ ፀሃይ ተነስቶ በተጠንቀቅ ዝግጁ መሆን ስራየ ነው!
በዚች ጤና ጣቢያ ላለፉት ሶስት አመታት ከእኔና ከጤና ጣቢያው ዘበኛ ገሞራው በስተቀር ሌላ ሰራተኛ ኑሮ አያውቅም ! ገሞራው ማታ ማታ ክላሽንኮቩን ታጥቆ ጤና ጣቢያውን ሲጠብቅ ያድራል (ባይጠብቀውም ምኑ እንደሚሰረቅ እንጃ… ባዶ ህንፃ ነው ) ቀን በሽተኛ ካልመጣ ‹‹የሽንብራው ጥርጥር ›› የተባለውን የድሮ ዘፈን አንጀት በሚበላ አሮጌ ዋሽንቱ ያንቆረቁረዋል ! አካባቢው ጭር ሲልና ብቻችን ስንሆን ደግሞ ክላሽንኮቭ ጠመንጃውን መፈታታትና መገጣጠም ያስተምረኛል !!እንደውም መፈታታቱን ጨርሸ የሙከራ ተኩስ ላይ ደርሻለሁ ‹‹ አንድ ቀን ወደጫካ ሂደን እናኖገዋለን›› ብሎኛል !
ታዲያ አንዳንዴ የዚች አገር ነገር ስልችት ሲለኝ …ወጣትነቴ እዚህ ገጠር እንደሻማ ቀልጦ ማለቁ ሲያሰጋኝ …የሃላፊዎችና ባለስልጣት የገገረ ግዴለሽነት ሲያስመርረኝ …ያገለገለ  ጠመንጃም ቢሆን ገዝተህ  ከሩቅ የሚታየው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ  ሸፍት ሸፍት ይለኛል!
አንድ ቀን ዘበኛውን ‹‹ያ እዛጋ የሚታየው ጫካ ማን  ይባላል ›› አልኩት
‹‹ቅንድብ መንጫ ›› አለኝ ! እዚህ አገር ከመንጨት ሌላ ስራ የላቸውም እንዴ ?! አልኩ ለራሴ
‹‹ምናልከኝ? ››
‹‹አይ ወዲህ ነው ! ›› ደግሞ አገሬን ሰደብክ ብሎ በጥይት ቢነጨኝ!
ጤና ጣቢያው አሁን ባለው የተራቆተ አቋም ‹‹ጤና›› የሚለውን ስም አንስተው ‹‹ፖሊስ›› ቢተኩበት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥሩ ፖሊስ ጣቢያ ይወጣው ነበር ! የህክምና ቁሳቁስ ከባድ እጥረት አለ …ሶስት ዓመት ሙሉ ከወረዳው ጤና ፅህፈት ቤት እስከክልሉ ጤና ቢሮ ደብዳቤ ብፅፍ በአካል እየሄድኩ ብለምን መልስ የለም ! በእርግጥ ያን ያህል ታካሚ አልነበረም ! ብዙ ጊዜ ስራ የሚበዛብኝ ወይ ክትባት ሲኖር አልያም ሃሙስ ሃሙስ ነበር …በአካባቢው ሃሙስ የሚውል ገበያ ስላለ ጠጅና አረቄ ሲግፉ የሚውሉ ገበያተኞች ተፈነካክተው ይመጣሉ …
አንዳንዴ ከመፈነካከት ከፍ ይላል…ለምሳሌ በመፍለጫ አናቱ ተተርክኮ ደሙን እያዛራ በቀረችው አቅሙ እየፎከረ የሚመጣ ‹‹ጀግና›› ያጋጥማል! በሳምነቱ የፈነከተውን ፈንክቶት ሌላኛው በተራው ይመጣል ! ከልምድ ስለማውቀው ‹‹አንተ ባለፈው እከሌን የፈነከትከው ነህ ›› ስለው ዝናው በመሰማቱ ደስ ብሎት ‹‹እንዴታ ! እርሰዎም ሰምተዋል ዶፍተር …ይሄ ሴታሴት ይሄው ዛሬ ተደብቆ በፈሪ ብትር እንዲህ ጫር አረገኝ ይላል …›› ጫር የሚለው ከስጋው አልፎ የራስ ቅሉን ጠርምሶትኮ ነው!
በአካባቢው ራቅ ራቅ ብለው ከተሰሩ የሳር ቤቶችና አንድ የቆርቆሮ ቤት (የቀበሌው ሊወመንበር ቤት ነው) በስተቀር ደህና ቤት እንኳን የለም …እዛ መሃል የምሰራባት ጤና ጣቢያ ከብሎኬት ተሰርታና ነጭ ቀለም ተቀብታ ስትታይ የደሃ አገር ቤተመንግስት ትመስላለች ! ‹‹ሽፈራው እድሜው ይርዘም ወስቢታሉን አምጥቶ አንጣለለው ይላሉ›› አርሶ አደሮቹ ! እውር ቤት አንድ አይና ብርቅ ነው !! ሽፈራው የወረዳው አስተዳዳሪ የነበረ ሰው ነው አሁን የወረዳው ከተማ ከንቲባ ሁኗል!! …ጤና ጣቢያውን እሱ ከኪሱ ያሰራው ነው የሚመስላቸው ! እሱም በየሰብሰባው እንደዛ እያለ ነው ጉራውነ የሚነፋው !! ‹‹ሳይማር ያስተማረን ህዝብ በበሽታ እንዳያልቅ አንገት ላንገት ተናንቄ …›› እያለ !
ታዲያ አንዳንዴ ጠንከር ያለ ህመም ሲገጥማቸውና ወደከተማ ሂደው እንዲታከሙ ስነግራቸው እፊቴ ባይሉትም ዞር ብለው ‹‹አሁን ለግሞ ነው እንጅ ይሄን የመሰለ ወስፒታል ቃያችን ተንጣሎ ለምን ከተማ ድረስ እንከራተታለን ››እያሉ ያሙኛል ! እንዲሁ ህንፃውን ከቤታቸው ጋር እያወዳደሩ ተሳልመውት ቢሄዱ የሚፈውስ ተዓምር አድርገው ያስቡታል! ኧረ አንዳንዴም ግልፍ ይላቸዋል..
መቸም ዘበኛው ገሞራው ከነክላሽንኮቩ ባይኖር አንድ ቀን እንደእባብ በሽመል ቀጥቅጠው በገደሉኝ ነበር!! የሆነ ሁኖ ጤና ጣቢያው ከሚሰጠው ህክምና ይልቅ ያች ትንሽ ባለሶስት ክፍል ህንፃ ለመንደሩ የስልጣኔ መጨረሻ የመንደሩም መኩሪያ እና ምልክት ነበረች ! ‹‹ግንቡ ቤት›› ይሉታል ! የዛች ቀበሌ አክሱም… የዛች አመዳም ገጠር ላሊበላ ነበር!
አንድ ቀን የመንደሩ ህፃናት አፈር አፈር መስለው ከጤና ጣቢያው አጥር ስር ከብት ሲያግዱ አግኝቻቸው …
‹‹ስታድጉ ምን መሆን ነው የምትፈልጉት?›› ብላቸው የተመካከሩ ይመስል ባንድ አፍ ‹‹ዶፍተር ›› አሉኝ …
‹‹ለምን ?››
‹‹እኛም ኸብቶቻችንም ግንብ ቤት እንድንኖር››
ይቀጥላል !
Filed in: Amharic