ሆሣዕና…
መጋቤ ሐዲስ ሄኖክ ፈንቴ
ሆሣዕና ማለት መድኀኒት ማለት ነው። ሆሣዕና የጌታችን የአምላካችን በዓል ነው። ከጌታችን ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው። ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኢየሩሳሌም ወደ ቤተ መቅደስ ለመግባት በፈለገ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ፊታችው ባለው ሀገር ሂዱና አህያ ከውርጭላዋ ጋራ ታስራ ታገኛላችው ፈታችው እምጡልኝ ምን ታደርጋላችው? የሚላቸው ሰው ካለ ጌታቸው ይፈልጋቸዋል በሉ ብሎ ላካቸው።
ከዚህ በሇላ ደቀ መዛሙርቱ እንዳዘዛቸው ሂደው ፈተው አመጡለት። በዚያም የተሰበሰቡት ሁሉ በአህዮች ላይ ልብሳቸውን ጎዘጎዙለት ጌታችንም በሁለቱ አህዮች ላይ ተቀመጠ። ከሌሎቹ እንስሳት አህዮችን መርጦ በአህዮች ተቀምጧል። አህዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ታሪክ አላቸውና :-
የበልአም አህያ የመልአኩን ክብር ለመግለጥ አፍ አውጥታ ተናግራለች ዘሁል22+28
ጌታችን በተወለደ ጊዜ አህዮች ከከብቶች ጋር በበረት እስትፋሳቸውን አሟሙቀውታል።
ቅዳሴ ማርያም የሆሣዕና እህዮች ከሁሉ ተመርጠው አምላካችን ተቀምጦባቸዋል። ለምን የተዋረዱት አህያዮች መረጠ ?ቢባል :-
1. ትሕትናን ለማስተማር
የትሕትና ጌታ መሆኑን ለመግለጽ ነው እንጂ ደመና አዞ ነፋስ ጠቅሶ በእሳት መንኮራኩር ላይ የሚረማመድ አምላክ ነው ነገር ግን የመጣው ለሰው ልጅ ትህትናን ሊያስተምር ነውና በአህያ ተቀመጠ።
2. ትንቢቱን ለመፈጸም
ትንቢት- አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሁትም ሁኖ በእህያም በውርንጭላቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ሰረገላውንም ከኤፍሬም ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም ያጠፋል ብሎ ዘካርያስ ትንቢት ተናግሮ ነበርና ለመፈጸም ነው ዘካ 9+1
3 ምሳሌውን ለመግለጽ
ምሳሌ- ቀድሞ ነቢያት ዘመነ ጸብእ ከሆነ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታያሉ ዘመነ ሰላም ከሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታዩ ነበርና ጌታችንም ዘመነ ሰላም ነው ሲል በአህያ ተቀምጦ መጥቷል።
4 ምሥጢሩን ለመግለጽ
ምሥጢር- በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም እሱም ካልፈለጋችሁኝ አልገኝም ከፈለጋችሁኝ አልታጣም ሲል በአህያ ተቀምጦ መጥቷል።
ህድግት የእስራኤል ምሳሌ ህድግት ቀንበር መሸከም የለመደች ናት እስራኤልም ህግ መጠበቅ ለምደዋልና። እዋል የአህዛብ ምሳሌ እዋል ቀንበር መሸከም አለመደችም
አህዛብም ህግ መጠበቅ አለመዱምና (አንድም) ህድግት የኦሪት ምሳሌ ህድግት ቀንበር መሸከም እንደለመደች ኦሪትም የተለመደች ህግናትና እዋል የወንጌል ምሳሌ
እዋል ቀንበር መሸከም አለመደችም ወንጌልም ያልተለመደች አዲስ ህግ ናትና በሁለቱም ላይ መቀመጡ ኦሪትንም ወንጌልንም የሰራሁ እኔ ነኝ ሲል ነው።
ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ 16 ምእራፍ ነው 14ቱን ምእራፍ በእግሩ ሂዶ ሁለቱን ምእራፍ በአህያይቱ ሂዷል በውርጭላይቱ ሁኖ 3 ጊዜ ቤተ መቅደሱን ዙሯል
14 ምእራፍ የአስርቱ ትእዛዛትና የአራቱ ኪዳናት ምሳሌ አስሩ ምእራፍ የአስርቱ ትአዛዛት አራቱ ምእራፍ የአራቱ ኪዳናት ምሳሌ ነው።
አራቱ ኪዳናት የሚባሉት እነዚህ ናቸው ኪዳነ ኖህ : ክህነተ መልከ ጼዴቅ :ግዝረተ አብርሀም እና ጥምቀተ ዮንሐስ ናቸው።
በአህያይቱ ላይ ልብሳቸውን አንጥፈውለታል:: ልብስ በአካል ያለውን ነውር ይሸፍናል። አንተም ከባቴ አበሳ ነህ ሲሉ በአህያዋ ላይ ኳርቻ ሳያደርጉ ልብስ አንጥፈውለታል ኳርቻ ይቆረቁራል ልብስ አይቆረቁርም የማትቆረቁር ህግ ሰራህልን ሲሉ ነው።
ስለምን ልብሳቸውን አነጸፉለት ቢባል ? በእዩ ልማድ ነው እዩ የተባለው ሰው በእስራኤል ላይ ሲነግሥ እስራኤል ልብሳቸውን አንጥፈውለት ነበረና በዚያ ልማድ አንጥፈውለታል።
እኩሌቶቱ ደግሞ ዘንባባ አንጥፈውለታል ።
ስለምን ዘንባባ አነጠፉለት ቢባል? ዘንባባ የድል ምልክት የደስታ መግለጫ የምስጋና መስጫ ነው አብርሃም ይሥሐቅን በወለደ ጊዜ አምላኩን በዘንባባ አመስግናኗል
ይስሐቅም ያእቆብን በወለደ ጊዜ አምላኩን በዘንባባ አመስግኗል። እስራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ በዘንባባ ንሴብሆ እያሉ እህተ ሙሴ ማርያም ከበሮ እየመታች አምላካቸውን አመስግነዋል።
ዮዲት እስራኤልን እየገደለ ያስቸገረው ሆለፎርኒስን አንገቱን ቆርጣ በገደለችው ጊዜ እስራኤል ዮዲት መዋኢት ዮዲት ኀያሊት ብለው በዘንባባ አመስግነዋታልና በዚያ ልማድ ዘንባባ አያነጠፉ አመስግናውታል። ዘንባባ እሾህ አለው ትምእርተ ኀይል ትምርተ መዊዕ አለህ ሲሉ ዘንባባ እሳት አይበለውም ለብልቦ ይተወዋል ባህርይህ አይመረመርም ሲሉ ነው።
የዘይት ቅጠል ነው ያሉ እንደሆነ ዘይት ጽኑ ነው ጽኑዐ ባህርይ ነህ ሲሉ ዛይት ብሩህ ነው ብሩሀ ባህርይ ነህ ሲሉ ዛይት መሥዋእት ነው መሥዋእት ትሆናለህ ሲሉ በዘይትም ቅጠል አመስግነውታል። ከፊት ከሇላ ያሉት ሆሣዕና በዓርያም ለዳዊት ልጅ መድኀኒት መባል ይገባዋል እያሉ አመስግነውታል። የምስጋና ጌታም በአህዮች ተቀምጦ ወደ መቅደስ ገብቷል።
በጋጥ መታሰር የሚገባቸው አህዮች ሲፈቱ በኀጢአት የታሰረ ሰው መቸ ይሆን የሚፈታው? ህሊናው የታሰረ ሰው መቸ ይሆን የሚፈተው? የሚታሰሩ አይዮች ሲፈቱ ሰዎች ለምን ይታሰራሉ? ሆሣዕና የታሰሩት ሁሉ የተፈቱበት ቀን ነው። የታሰሩ አኅዮች የኀጢአት እስረኛች የህሊና እስረኛች የኦሪት እስረኞች ሁሉ የተፈቱበት ነው።
ጌታችን በምህረት ሲመጣ ሁሉ ይፈታል። በአምሳሉ የፈጠራቸው እንኳን ሰዎቹ ግእዛን የሌላቸው አኅዮቹ ሳይቀር ተፈዋል።
የምህረት ጌታ ማራናታ ማቴ 21+1