>

በዓለም-ዓቀፍ ሚዲያዎች ከተነበቡ ኮቪድ-19 ነክ ዜናዎች (ሳምሶም ጌታቸው)

በዓለም-ዓቀፍ ሚዲያዎች ከተነበቡ ኮቪድ-19 ነክ ዜናዎች

ሳምሶም ጌታቸው
 
ኮቪድ-19 እና ፍራቻ
በግብፅ ሀገር በኮሮናቫይረስ ተጠቅተው የሞቱ አንዲት የህክምና ዶክተር ሴት፣ የቀብር ሥርዓታቸው በሚፈፅምበት አካባቢ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው። ነዋሪዎቹ ድርጊቱን የፈፀሙት ሀኪሟ የሞቱት በኮቪድ-19 በሽታ ስለሆነ በእኛ ሠፈር መቀበራቸው እኛንም በብሽታ ያስፈጀናል በሚል ሥጋት ተነሳስተው መሆኑ ተነግሯል። ነገሩን ሰምተው በብሽጭት የጋዩት የሀገሪቱ ጠ/ሚ ሙስጠፋ ማድቡሊ ድርጊቱን የፈፀሙትን ሰዎች “ማፈሪያዎች” ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን፤ የሟች ባል ጋር ደውለው በሆነው ሁሉ ማዘናቸውን በመግለፅ በግብፅ ሕዝብ ስም ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል። የሟችን አስክሬን ይዞ ወደቀብር ሥፍራው የደረሰውን አምቡላንስ አናሳልፍም ብለው የከለከሉትን ሰዎች ለመበተን ፖሊስ ደርሶ አስለቃሽ ጭስ የተጠቀመ ሲሆን፤ በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ 23 ሰዎች ተይዘዋል ተብሏል። የሀገሪቱ የሙስሊሞች ታላቅ አባት ድርጊቱን ከግብረገብም፣ ከሰብአዊነትም ሆነ ከሐይማኖት የራቀ ክፉ ተግባር ነው ያሉት ሲሆን፤ የሀገሪቱ ዋና አቃቤ ሕግም የሽብር ድርጊት ሲሉ ኮንነውታል።
ኮቪድ-19 እና መፍትሔ
የዓለም የጤና ድርጅት በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የምርምር ተቋማት ከ70 በላይ ለኮቪድ-19 የሚሆኑ ክትባቶች ተስፋ ሰጪ በሆነ መልኩ ምርምራቸው እየተካኼደ መሆኑን ገልጿል። በተለይ በልምድም ሆነ በብቃታቸው የበለጠ አቅም ያላቸውና ፈጣን ውጤት እያሳዩ ያሉ ሶስት የምርምር ተቋማት ተመርጠው በጤና ድርጅቱ ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነ ታውቋል። አንዱ የቻይና-ሆንግኮንግ የምርምር ተቋም ሲሆን፣ ሁለቱ ደግሞ የአሜሪካ ድርጅቶች ናቸው ተብሏል። በተለይ የቻይና-ሆንግኮንግ ተመራማሪዎች ቡድን በእንስሳት ላይ የሚያካሂዱትን የመጀመሪያ ደረጃ ምርምርም ሆነ ፈቃደኛ በሆኑ ጤነኛ ሰዎች ላይ የሚያደርጉትን ደረጃ 2 ምርምር ጨርሰው፤ በህሙማን ላይ መሞከር ወደሚችሉበትና ወሳኝ ወደሆነው ደረጃ 3 ለመሻገር እየተዘጋጁ ነው ተብሏል። ሁለቱ የአሜሪካኖቹ የመድኃኒት ምርምር ተቋማትም በቻይናዎቹ በአንድ ደረጃ ተቀድመው፤ በፔንሲልቬኒያ የሚገኘው “ኢኖቪዮ” የተባለው የምርምር ተቋም መድኃኒቱን ባለፈው ሳምንት በፈቃደኛ ሰዎች ላይ መሞከር የጀመረ ሲሆን፤ ሌላኛው ማሳሹሴትስ የሚገኘው “ሞደርና” የተባለው የምርምር ተቋም ደግሞ በፈቃደኛ ሰዎች ላይ ሙከራውን መጀመር የሚያስችለውን ፈቃድ ከተቆጣጣሪው መ/ቤት አግኝቶ ለመጀመር እየተዘጋጀ ነው። ከእነዚህ 3ቱ ውጭ ያሉት 67 ያህል የምርምር ተቋማት ለምሳሌ እንደ የጃፓኑ ኦሳካ ዩኒቨርሲቲ፣ የአውስትራሊያው ኩዊንስ ላንድ ዩኒቨርሲቲ፣ የእንግሊዞቹ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እና ኢምፔሪያል ኮሌጅ ሎንዶን አገኘን ያሏቸውን ክትባቶች የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራዎቻቸውን በእንስሳት ላይ እያካኼዱ ነው ተብሏል። የመድኃኒት ኢንደስትሪ አንድን አዲስ ክትባት በጥቅም ላይ ለማዋል ከ10-15 ዓመታት ይፈጅ የነበረውን ጊዜ ከ1 ዓመት በታች ለማውረድ እየጣረ ነው ተብሏል።
ኮቪድ-19 እና እንስሳት
በመካከለኛው ምስራቅ ሰዎች የቤት እንስሳቶቻቸውን የኮሮናቫይረስ በሽታ ያስተላልፉብናል በሚል ፍራቻ እያወጡ እየጣሏቸው በመሆኑ እንስሳቱ እጅግ ለሚያሳዝን ችግር እየተጋለጡ እንደሆነ ተነግሯል። የዓለም ጤና ድርጅት “ኮቪድ-19 ከእንስሳ ወደ ሰው ስለመተላለፉ የታወቀ ነገር የለም። ባይሆን ጥቂት እንስሳት በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች ወደእነሱ እንደተላለፈባቸው ታውቋል” በማለት ቫይረሱ አሁን ባለው ተጨባጭ መረጃ የሚተላለፈው ከሰው ወደ ሰው በመሆኑ ተገቢው ጥንቃቄ በዚያ በኩል እንዲደረግ ያሳስባል። የወረርሽኙ ጣጣ የዓለምን ኢኮኖሚ በማናጋቱ ችግሩ ከሰው ልጆች አልፎ እንስሳቱን ሁሉ በየሀገሩ ለስቃይ ዳርጓል። በጀርመን ሀገር የሚገኝ አንድ የእንስሳት ማኖሪያ ሥፍራ በኮቪድ-19 ምክንያት የሀገሪቱ እንቅስቃሴ በመዘጋቱ እንስሶቹን አስጎብኝቶ የሚያገኘው ገቢ ተቋርጦበታል። በዚህም የተነሳ ድርጅቱ የተወሰኑትን እንስሳት ብቻ መርጦ ለማቆየት የጨከኑ ርምጃዎችን ለመውሰድ እያሰበ መሆኑን አስታውቋል። እናም በበጀት ችግር ቀለብ ሊሰፍርላቸው ያልቻላውን ጥቂት እንስሳት መርጦ በማረድ ቀሪዎቹን ለመቀለብ አስቧል። “የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ቀድመው መሰዋት ያለባቸውን እንስሳት ዝርዝር ሁሉ አዘጋጅተናል” ሲሉ የኒዉሚኒስታ የእንስሳት ማኖሪያ ኃላፊ ተናግረዋል። ኃላፊዋ ስለውሳኔያቸው ሲያስረዱ “ነገሩ ቢያሳዝንም ዓይኔ እያየ እንስሳቱ በረሃብ ሲሰቃዩ ከማይ በሰላም እንዲያሸልቡ ማድረግን እመርጣለሁ” ብለዋል። አንዳንድ የእንሳት ማኖሪ ሥፍራው ሠራተኞች በበኩላቸው ስለተፈጠረው ችግር ሲያስረዱ “እንስሳቱ ከምግብ ዕጥረቱ ባልተናነሰ ሌላ የመንፈስ ስብራት ተጋርጦባቸዋል። ያም የሆነው እንስሳዎቹ በሰዎች መጎብኘትን ለምደውት ስለነበር አሁን ጎብኚ ሲጠፋ በጣም በድብርት እየተቸገሩ ነው። በተለይ ጦጣዎቻችን ሰዎችን ማየት ነፍሳቸው ነበር” ብለዋል የችግሩን ስፋት ሲያስረዱ።
ኮቪድ-19 እና ውዥንብር
የናይሮቢ ከተማ “ገዢ” ማይክ ሶንኮ በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት ሕይወታቸው ይበልጥ ለተመሳቀለባቸው ደሃ የከተማዋ ነዋሪዎች፤ መንግስት የመደበላቸውን የምግብ ድጋፍ ሲያከፋፍል እሳቸውም ሄነሲ የተባለ የአልኮል መጠጥ ጨምረው እንደሚያከፋፍሉ መግለጫ ሰጥተዋል። “ለሕዝባችን ያዘጋጀነው ጥቂት ጠርሙስ የሄነሲ ምርቶች በእጄ ይገኛሉ። እሱን እናከፋፍላችኋለን። ምክንያቱም የዓለም ጤና ድርጅትና ሌሎች የጤና ተቋማት ባደረጉት ጥናት አልኮል ኮሮናቫይረስንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ዓይነት ቫይረስ ለመግደል እጅግ የማይተካ ሚና እንዳለው አረጋግጠዋል” ሲሉ ተናግረዋል። የሚገርመው የዓለም ጤና ድርጅት አልኮል በመጠጣት ኮቪድ-ን መከላከል አይቻልምና ተጠንቀቁ ብሏል። ብቻ ነገሩን የሰሙ ኬንያውያን ሰውዬውን እያብጠለጠሏቸው ነው። ሆኖም ግን ሰውዬው በተደጋጋሚ በፈፀሟቸው ቅሌቶች መዘለፍም ሆነ መወቀስ ብርቃቸው አይደለምና ምንም አይመስላቸውም ይላል ዘገባው። ከዚህ በፊትም አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወርና በገንዘብ ዝውውር መከሰሳቸውን በማስታወስ የካበተ የቅሌት ልምዳቸውን ዘርዝሮላቸዋል። በተጨማሪም ሰውዬው ከጥቂት ወራት በፊት ፈፅመውታል በተባለ ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ብክነት በሀገሪቱ ፍ/ቤት ከቢሯቸው መታገዳቸውን አስታውሷል። ድርጊቱን ቢሸመጥጡም።
Filed in: Amharic