>

በኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነዉ፤ ርዳታ ያስፈልጋል!!! (ዶችቬሌ)

በኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነዉ፤ ርዳታ ያስፈልጋል!!!

ዶችቬሌ
የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት «FAO» በኢትዮጵያ በሶማሊና በኦሮምያ ክልል የአስቸኳይ የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልግ አስታወቀ። ድርጅቱ ይህን የገለፀዉ አካባቢዉ ላይ እጅግ ከፍተኛ የአንበጣ መንጋ የምግብ ሰብልን እና የግጦሽ ሳርን ማዉደሙን ተከትሎ ነዉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ እንዳደረገዉ በኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ ወደ 200 ሺህ ሄክታር መሪት ላይ የሚገኝ ሰብልን ማዉደሙን አስታዉቋል። ድርጅቱ ይፋ ባደረገዉ መግለጫ የአንበጣ መንጋ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪቃ በሚገኙ ሃገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የርዳታ ምግብ ጥገኛ እንዲሆኑ ዳርጎአል።
የመንግሥታቱ የምግብ እና የርሻ ድርጅት «FAO» እንዳስታወቀዉ በኢትዮጵያ  የአንበጣ መንጋ የገብስ፤ የስንዴ፤ የበቆሎ፤ ሰብልን አዉድሞአል የግጦሽ መሪትንም ከጥቅም ዉጭ አድርጎአል። የአንበጣ መንጋ ባደረሰዉ ጉዳት ምክንያት በተለይ በኦሮምያ እና በሶማሌ ክል የሚኖረዉ ሦስት አራተኛዉ ነዋሪ የርዳታ እህልን ይሻል ሲል ድርጅቱ ጥሪ አቅርቦአል። የአንበጣ መንጋው በበረታባቸው ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ደቡብ ሱዳን፣ዩጋንዳና ታንዛኒያ 20 ሚሊዮን ሰዎች እንዲሁም  በየመን 15 ሚሊዮን ሰዎች ብርቱ የምግብ ዋስትና እጦት እንደገጠማቸው ገልጿል። በመጋቢት ወር የሚጠበቀው ዝናብ በመጪዎቹ ወራት በምሥራቅ አፍሪቃ ከፍተኛ የአንበጣ መንጋ እንደሚከሰት የገለጸው ድርጅቱ ከኬንያ ወደ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ እንደሚዛመት አስጠንቅቋል። ከምሥራቅ አፍሪቃ በተጨማሪ አዳዲስ የአንበጣ መንጋ እየተፈለፈለ በሚገኝባቸው በኢራን እና በየመን አሳሳቢ እንደሚሆን የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት አስጠንቅቆአል።
Filed in: Amharic