>

የወልቃይት ጉዳይ - ብዙ ውሸቶች በተፈተጉ የታሪክ ማስረጃዎች ተንጓልለው የቀረቡበት የታሪክ ማጣቀሻ!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

የወልቃይት ጉዳይ – ብዙ ውሸቶች በተፈተጉ የታሪክ ማስረጃዎች ተንጓልለው የቀረቡበት የታሪክ ማጣቀሻ!!!

አቻምየለህ ታምሩ
 
* አገር ቤት ገበያ ላይ ውሏል!
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በትኩረት ካጠናኋቸው የኢትዮጵያ ታሪክ አምዶች መካከል የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ የወሰን፣ የመልክዓ ምድርና ማኅበራዊ ታሪክ አንዱ ነው። እነሆ ከአክሱም ዘመን ጀምሮ ሕወሓት ወደ ሥልጣን እስከመጣበት ድረስ ባሉት 1660 ዓመታት ውስጥ የነበረውን የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ የወሰን፣ የመልክዓ ምድርና ማኅበራዊ ታሪክ አንድ በአንድ አጥንቼ በመጽሐፍ መልክ ያዘጋጀሁት የታሪክ ሰነድ ኢትዮጵያ ውስጥ ገበያ ላይ ውሏል።
የወልቃይት ጉዳይ   አገር ቤት  ለገበያ ከመቅረቡ በፊት አሜሪካን አገር መታተሙ ይታወቃል። አገር ቤት የታተመው የወልቃይት ጉዳይ መጽሐፍ አሜሪካን አገር በታተመው መጽሐፍ ውስጥ ገጹ በመብዛቱ ያልተካተቱ በርካታ ዶሴዎችን ጨምሮ የያዘ ነው።
መጽሐፉ በአክሱም ዘመን የነበረውን የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ የወሰን፣ የመልክዓ ምድርና ማኅበራዊ ታሪክ ከሚያረጋግጡት የዐፄ ኢዛና የዐፄ ካሌብ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ጀምሮ በኋለኛው ዘመን የትግራይ ተወላጅና ገዢዎች የነበሩት እነ ዐፄ ዮስጦስ፣ የዘመነ መሳፍንቱ ራስ ሚካኤል ስሑል፣ ራስ ወልደ ሥላሴ ክፍለየሱስ፣ ዐፄ ዮሐንስ፣ በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የኖሩ የትግራይ አለቆችና በዚህ ዘመን የኖሩት የትግሬው የታሪክ ጸሐፊ ደብተራ ፍሥሓጊዮርጊስ ዓቢየዝጊ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የምዕራብ ትግራይ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ገብረ ሥላሴ ባርያ ጋብርና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የትግራይ አበጋዝ የነበሩት ደጃዝማች በላይ አባይ በየዘመናቸው ስለወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ የወሰን፣ የመልክዓ ምድርና ማኅበራዊ ታሪክ የሰጡትን ምስክርነት ይዟል።
በመጽሐፉ  ከተካተቱ ዶሴዎቹ መካከል የትግሬ ተወላጁና ኢትዮጵያን ከ1703 ዓ.ም. – 1707 ዓ.ም. የገዙት የዐፄ ዮስጦስ ታሪከ ነገሥት፤ ትግራይን ከ1780 ዓ.ም. – 1808 ዓ.ም. የገዙት ራስ ወልደ ሥላሴ ክፍለየሱስ  የትግራይን ወሰን አስመልክቶ ለራስ ጉግሣ የላኩት መልዕክት፤  በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የምዕራብ ትግሬ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ገብረ ሥላሴና በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የኖሩት የትግሬው ደብተራ ፍዐፄ ዮሐንስ  ሁለት ጊዜ የጻፉት ደብዳቤና አንድ ጊዜ ያስነገሩት አዋጅ፤  ሥሓጊዮርጊስ ዓቢየዝጊ በትግርኛ ቋንቋ በጻፉት «ታሪኸ ኢትዮጵያ» መጽሐፋቸው ውስጥ ስለ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ የወሰን፣ የመልክዓ ምድርና ማኅበራዊ ታሪክ የሰጧቸው ምስክርነቶች ዋናዋናዎቹ ናቸው።
ከሰነድ የታሪክ ማስረጃዎች በተጨማሪ መጽሐፉ ሳይንሳዊ የታሪክ ማስረጃዎችንም አካቷል። በዚህ መጽሐፍ ከተካተቱት ሳይንሳዊ የታሪክ ማስረጃዎች መካከል ዋናው በጎንደር ዘመን የተገነባውና ወልቃይት ውስጥ የሚገኘው የቤተሙሎ ቤተመንግሥት የአርኪዎሎጂ ምርምር ውጤት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በመጽሐፉ ከሕወሓት ዘመን በፊት ባሉት አራት መቶ አመታት ውስጥ ማለትም ከ1591 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራን የገዙ አስተዳዳሪዎች በሙሉ ስም ዝርዝራቸውና የገዙበት ዘመን ከነ ትውልድ ሐረጋቸው አንድ በአንድ ከነማስረጃው ቀርቧል።
ከደጃዝማች ውቤ ኃይለ ማርያም ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መጨረሻው ድረስ የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ አስተዳዳሪ የነበሩትና ታሪካቸው ያልተነገረላቸው የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ አርበኞች ማንነትና የፈጸሙት ጀብዱ ታይተው ከማይታወቁ ልዩ ፎቶግራፎቻቸውጋር በመጽሐፌ ውስጥ ተካቶ ይገኛል።
ሕወሓትና የሕወሓት ፕሮግራም አቀንቃኞች [ፈረንጆችን ይጨምራል] በመጽሐፍ መልክና በድረ ገጽ ባሰራጯቸው አርቲክሎቻቸው የጻፏቸው የፈጠራ ታሪኮችና በሽምግልና እድሜ የሚገኙ ታዋቂ የትግራይ ሰዎች ጭምር በድምጸ ወያኔ ቴሌቭዥን እየቀረቡ ስለ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ የወሰን፣ የአስተዳደርና የመልክዓ ምድር ታሪክ የሰጧቸው የውሸት ምስክርነቶች በሙሉ በተፈተጉ የታሪክ ማስረጃዎች ተንጓልለው የቀረበበት የታሪክ እውነት ከዶሴ በተጨማሪ በተለያዩ ዘመናት በኖሩ የትግራይ ሰዎች ጭምር በተዘጋጁ ታሪካዊ ካርታዎችና ታሪካዊ ፎቶግራፎች ተደግፎ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀርቧል።
ባጭሩ ከ700 በላይ  በሆኑ የታሪክ ምንጮች የዋጀው የወልቃይት ጉዳይ  መጽሐፍ፤   456 ገጾች፣ ዘጠኝ ክፍሎችና 23 ምዕራፎች ያሉት  ሲሆን  የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ የወሰን፣ የማኅበራዊ፣ የአስተዳደርና የመልክዓ ምድር ታሪክን በሚመለከት  የ1660 ዓመታት legal document ተደርጎ ሊቀርብ የሚችል ነው። በዚህ ወቅት  እውነት፣ ታሪክና ማስረጃ የያዘ መጽሐፍ ማንበብ የምትሹ ሁሉ መጽሐፉን ብታነቡ እንደልብ የማታገኟቸውን ውድ ሰነዶች፣ በቀላሉ የማይገኙ ዶሴዎችን፣  የስሜን አውራጃ ዝነኛ አስተዳዳሪዎችን ታሪካዊ ፎቶግራፎችና ታሪክ እንዲሁም በስነቃል የቀረውን  ማኅበራዊ ታሪካችንን በመገብየት አብዝታችሁ  ታተርፉበታላችሁ!  መጽሐፉ በአዲስ አበባና በሁሉም የአገራችን ክፍሎች በሚገኙ መደብሮች ይገኛል።
መልካም ንባብ!
Filed in: Amharic