>
5:13 pm - Saturday April 18, 2792

የሞራል ምሰሶ ሆነዉ ከፊት የሚቆሙለትን ሚዲያዎችን የማይደግፍ ህዝብ ነጻነትን ይመኛታል እንጅ ከቶም አያገኛትም!!! (ሸንቁጥ አየለ)

የሞራል ምሰሶ ሆነዉ ከፊት የሚቆሙለትን ሚዲያዎችን የማይደግፍ ህዝብ ነጻነትን ይመኛታል እንጅ ከቶም አያገኛትም!!!

 

ሸንቁጥ አየለ
* ” የተመስገን ደሳለኝ ሚዲያ/መጽሄት የገንዘብ እጥረት ገጠመዉ ከገበያም ሊወጣ ነው” የሚለው ዜና ለብዙሀኑ ሙሾ የመሆኑን ያህል ለእነ እንቶኔ ሰርግና ምላሽ ነው… ጎበዝ ይህ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም!!!
ተሜ ከወያኔ ጋር ብዙ ትግል ያደረገ ነዉ። ከኦህዴዳዉያን/ኦነጋዉያን ጋርም ብዙ እየታገለ ያለ ነዉ። ተመስገን ደሳለኝ የአሜሪካ ኢንባሲ እራሱ ከሀገር ቤት እንዲወጣ ብዙ ጉትጎታ ቢያደርግበትም ለህዝቤ ድምጽ ሆኜ እዚሁ ሀገር ቤት እሞታለሁ ያለ ጀግና ነዉ።
ሌላዉ ቀርቶ ከስምንት አመት በፊት  “ዜጎችን ከኢትዮጵያ ወደ ኢትዮጵያ የማባረር ሂደት ህገመንግስታዊ አንደምታ እና ትዉፊታዊ እሴቱ ”  የሚል ጽሁፍ ለማሳተም በርካታ የግል ጋዜጦችን ባነጋግር ሁሉም ፈቃደኛ አልሆኑም ነበር።
 ምክንያታቸዉም ወያኔ በጠላትነት የፈረጀዉ የአማራ ብሄር ህገመንግስታዊ መብቱ ይከበር የሚል ጥያቄ የያዘ ጽሁፍ ስለሆነ ነበር። ሆኖም ሳይፈራ ይሄን ጽሁፍ ለማተም ፈቃደኛ ሆኖ የተገኘዉ የተመስገን ደሳለኝ መጽሄት ብቻ ነበር።
 ተመስገን ደሳለኝ ስለ ሁሉም ኢትዮጵያዉ መብት የታገለ ጀግና ነዉ። ስለ ሙስሊሙ፡ ስለ ክርስቲያኑ፡ ስለ አማራዉ ፡ ስለ ኦሮሞዉ፡ ስለ አፋሩ ፡ ስለ ሶማሌዉ እንዲሁም ስለ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ድምጽ ለመሆን ታግሏል። ዋትቷል። ብዙ መከራ ተቀብሏል። ታስሯል። ተገርፏል። ተገፍቷል። ብዙ የስነልቦና ሰበራ ለማድረግም በተመስገን ደሳለኝ ላይ ተሞክሯል።
አንድ ጊዜ ስለ ተመስገን ደሳለኝ ገጠመኝ የሰማሁት ነገር ደግሞ ሁሌም ለተመስገን ደሳለኝ አክብሮቴ ከፍ ያለ እንዲሆን አድርጎታል።
 የወያኔ ባለስልጣናት ተመስገንን ለማስፈራራት እቢሯቸዉ ይጠሩታል። ተሜን በአማራነቱ ብዙ ቢሰድቡትም ስድባቸዉን ከቁብ አልቆጠረላቸዉም። እነዚህ የህዉሃት ባለስልጣናት ወዲያዉ አንድ የብአዴን ባለስልጣን ጠርተዉ ቢሮ ያስመጡታል።
ወዲያዉም ይሄን የብአዼን ባለስልጣን በአማራነቱ እያበሻቀጡ ይሰድቡት ይጀምራሉ። የብአዴን ባለስልጣኑንንም ብዙ ከሰደቡት እና ካሽቆጠቆጡት ብኋላ ወደ ተመስገን እየተመለከቱ የአማራን ህዝብ መሳደብ ይጀምራሉ። በማስከተልም ተመስገንን ” አንተንም ልክ እንደዚህ የብአዴን ባለስልጣን እንደ አህያ እንጭንሃለን። አማራ አህያ ነዉ” ብለዉ ያስፈራሩታል።
ተመስገን ቆራጡም ” ብአዴኖች አማራ አይደሉም።አማራ አንበሳ እንጂ አህያ አይደለም። ይሄ የብአዴን ባለስልጣን. አማራ ቢሆን ኖሮ እንኳን ልትሰድቡት ቀና ብላችሁ አታዪትም ነበር።እንዲህ ቁጭ ብሎ ከሚሰደብም ገሎ ይሞት ነበር ::” ብሎ ይመልስላቸዋል።
እዚያ ተቀምጦ የነበረዉ የብአዴን ባለስልጣንም  በሀፍረት ፊቱ ቲማቲም ይመስላል። እናም ተመስገን ላይ የስነልቦና ሰበራ ለማድረግ የሞከሩት ወያኔዎች እራሳቸዉ ላይ ብአዴኑን  እንዳነሳሳባቸዉ ሲገባቸዉ ተመስገንን ቶሎ ከቢሮ አስወጥተዉ ያባርሩታል።
እናም እንደ ተመስገን ደሳለኝ አይነት ጀግና የህዝብ ልጅ የህዝብ ድምጽ ስለ ህዝብ የሚታገለዉ ሰዉ ለህዝብ ድምጽነት ያቋቋመዉ ሚዲያ እንዴት የገንዘብ ችግር ይገጥመዋል?
የአዲስ አበባ ህዝብ ብቻ በርካታ ሚዲያዎችን ለመርዳት በቂ ነዉ። ምክንያቱም ዛሬ እነ አቢይ/ለማ/ጀዋር የአዲስ አበባን ህዝብ መጤ ነህ ፡ መሃል ሸዋ ሀገርህ አይደለም ብለዉ ቤቱን አፍርሰዉ ንብረቱን ነጥቀዉ የጎዳና ተዳዳሪ እያደረጉት ነዉ። ወደፊትም ይሄንኑ ስራቸዉን አጠናክረዉ ይቀጥላሉ።
እናም  የአዲስ አበባ ህዝብ.  የምትኖርበት ሀገርህ አይደለም  እየተባለ ባለበት በዚህ ወቅት ድምጽ ሊሆኑት የሚችሉ ሚዲያዎችን በልዩ ልዩ መልክ እንዲጠነክሩ እንዴት ማድረግ ያቅተዋል? ነዉ ወይስ ህዝቡ ድምጽ የሚሆኑት ግለሰቦች እና ሚዲያዎች አይፈልግም? ወይስ እኛ ችግር እያልን የምንለዉ ነገር እዉነት አይደለም? ነዉ ወይስ ህዝብ የህዝብን ችግር ግለሰቦች ብቻቸዉን እንዲፈቱለት እየጠበቀ ነዉ?
ድምጽ የሚሆኑለትን፡ የሞራል ምሰሶ ሆነዉ ከፊት የሚቆሙለትን እና ስለሱ የሚጋደሉለትን ግለሰቦች፡ ሚዲያዎች፡ እና ልዩ ልዩ ሀይሎች የማይደግፍ ህዝብ ነጻነትን ይመኛታል እንጅ ከቶም አያገኛትም።
አንድ እንደ ተመስገን ደሳለኝ አይነት ጀግና ለማዉጣት እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም። የኛ ህዝብ ደግሞ የጀግና ዋጋ አልገባ እያለዉ ሚሊዮን ጀግኖቹን ሳይረዳቸዉ፡ ሚሊዮን ባለ አዕምሮዎቹን ሳያግዛቸዉ እየዘገዬ ሚሊዮን ባንዶች እና ከሃዲያን እጫንቃዉ ላይ ሲጨፍሩበት ይኖራሉ።
 ምስጉን ህዝብ. ግን  እንድ ተመስገን ደሳለኝ አይነት ጀግኖቹን ሳይዘናጋ ይጠብቃል፡ ይረዳል፡ ያጀግናልም።  አንዱን ጀግና የሚንከባከብ ህዝብም በርካታ ጀግኖች. እና ባለ አእምሮዎች እንደ ማይደርቅ ምንጭ ይፈልቁለታል።
Filed in: Amharic